በህይወታችን ውስጥ፣ የሚያጋጥመንን ፈተና ተው፤ ብንለው እንደማይሰማን እናውቃለን፤ ፈተና አግቢዎቹን እንዲሁ ተዉን ብንላቸውስ ይተዉን ይሆንን ?እንዲህ እያሰብኩ ያለሁት እም ኀበ-አልቦ አይደለም። በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ እየሆነ ያለውን ድርጊትም በሉት ክንውን ከማየት በመነሳት ነው።
በበርማ የሮሒንጋ ሙስሊሞች ሐገር አልቦ ህይወትና መፈናቀል ለዚህም የዓለሙ ድርጅትም ሆነ የክፍለ ዓለሙ የኢዥያ መንግስታት ማህበር እየወሰደ ያለውን ዘገምተኛ ሐሳብ ሳስብ ልቤ በሀዘን ይደማል። ለእነዚህ ሰዎች ከሁሉም የሚቀድመው የሰው ልጅነታቸው ነው፤ ከዚያ ቀጥሎ እምነታቸው። የሚያንማር ወይም የቀድሞዋ በርማ መንግስትም እነዚህን ሰዎች የእኔ ህዝብ አይደሉም ከማለት ሌላ አለመሆናቸው ለማስረገጥ ሰራዊቱን አሰማርቶ በኃይል እስከ ማፈናቀል የዘለቀ እርምጃ እየወሰደ ነው። እነርሱን በድንበርተኛነታቸው የተቀበሉት ሐገራትም ስደተኞች መጡብን እንጂ ህዝባችን ተመለሰ፤አላሉም።
ታዲያ ሮሂንጋዎች ከመሬት ውስጥ እንደ እንጉዳይ ፈሉ ? (እንጉዳይም ለመፍላቱ በቂ ዳራ አለው፤ ወይም ያስፈልገዋል) እኛ ይላሉ፤ ሮሒንጋዎቹ ከዚህ መኖሪያ ውጭ የምናውቀው ማደሪያም ሆነ መኖሪያ የለም። አንድ ቀን ግን ወደ ሐገራችሁ ወደ ባንግላዴሽም ይሁን ማሌዥያ ሂዱ እንጂ ሐገር አለን ብላችሁ እንዳትቀመጡ አሉን። በወሩም በተኛንበት ቤቶቻችንን ማቃጠልና ሴቶቻችንን መድፈር ጀመሩ፤ ጨርቄን ማቄን ሳንልም አካባቢው ለቅቀን እንድንሄድ ገፋፉን ነው፤ የሚሉት።
ሮሒንጋዎቹ መልካቸው ወደበርማ ሳይሆን ወደህንዳዊያኑ የሚያደላ ጠይምነት ያላቸው ግን የሚናገሩት ቋንቋ ከበርሚዝ ዘዬ ለየት ያለ ቢሆንም እምነታቸው እንዳስወገዛቸው ነው፤ የሚናገሩት። በዕድሜ የገፉ አዛውንት፣ እምቦቃቅላ ህጻናትና ጎልማሶች ሁሉ ናቸው የዚህ ሰቆቃ ሰለባ የሆኑት።
እንዲያውም አካባቢውን ያጠኑት ሰዎች ከዘመናት በፊትም በዚህ አካባቢ ላሉ ሰዎች ሆን ተብሎ የትምህርት የኢኮኖሚ ድጋፍና ማህበራዊ አገልግሎቶች ተነፍገው ምድሪቱን ነቅለው እንዲወጡ ይገፉ ነበረ። በሚያንማር ሁሉም ሰው እኩል መብት እንዳለው ቢነገርም የቀደሙት ሚያንማሮች የመስራችነት መብት እንዳላቸው ፊት ለፊት ነው የሚናገሩት።
ጠመንጃ ነካሾቹ ወታደሮች በስልጣን ላይ በቆዩባቸው ጊዜያትም ያልተነገረው ሰቆቃና ያልታበሰው እንባ የሮሒንጋዎቹ ነበረ። አሁንም ግን ሰቀቀናቸው ቀጥሏል። ወደ መሀሉ ሀገር ካለው ህዝብ ጋር የተቀላቀሉት ሮሒንጋዎች አንድም ሮሒንጋዊነታቸውን ትተዋል አለዚያም እምነታቸውን ለውጠዋል። የቡድሒስት መነኮሳቷ ሐገር በርማ የተተዉትን ሰዎቿን የያዘችበትን መንገድ ማቃናት አልቻሉበትም።
የሮሒንጋዎቹ ድምጽ ተቆርቋሪ የሆነው አካልም ለዚህ ነው፤ በዳዮቻችንን ተዉን ስላልን ይተዉን ይሆን ሲሉ የሚጠይቁት።
ወዲህ ወደ አፍሪካ ስንመጣም፤ በኮንጎ በማዕከላዊ አፍሪካ፣ በናይጄሪያ ቻድና ካሜሩን ተመሳሳይ በሆነ የሽብር ቀለበት ውስት ያሉ ሰላማውያን ወገኖች ጥያቄም ይኸው ነው።
በናይጄሪያ ሰሜን ምስራቅ ቦኮሐራም ያሰለጠናቸው (ያሰየጠናቸው ማለቱ ይቀላል) ወገኖች በገበያ ስፍራዎች በመናኸሪያዎችና ህዝብ ሰብሰብ ይልባቸዋል በሚልባቸው ስፍራዎች ቦንብ የታጠቁ መልእክተኞቹን እየላከ ህዝብን በደም አበላ መንከርና ማናወጥ ስራዬ ካለ፣ እነሆ፣ አንድ አሰርት ዓመት ባጀ። ለመሆኑ እነርሱ እንዲመጣ የሚፈልጉትን ሥርዓት ለማምጣት ጭዳ የሚሆኑት ሰላማውያን አላልቅ አላችሁ ወይስ የእናንተ መንግስተ ሰማይ ያለው በሲኦል በኩል ነው፤ ብዬ ማጠየቅ ግድ ይለኛል። ገድላችሁ ተቀደሱ እንደማለት ያለ ማንነት አላቸውና።
የኮንጎውም ሆነ የናይጄሪያው፤ የአፍጋኒስታኑም ሆነ የሶሪያው የሚጋሩት ተመሳሳይ ነገር ወደምንፈልገው ግብ ለመድረስ በማይፈለግም መንገድ ቢሆን መጓዝን ተገቢ ነው፤ ብለው ማመናቸው ነው።
እነዚህን ሰዎች ታዲያ ፣ ተዉን ስላሏቸው ይተዉ ይሆንን?
ይህን ሐሳብ እኛን ራሳችንን ወደሚያስጨንቀው ነገራችን እናምጣው። በሐገራችን በኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ነገር በማይፈለግ መንገድ ለማምጣት የወጠኑ፣ ውጥናቸውንም ወደ መሬት ያወረዱና ዱር ቤቴ ያሉ ከተሜዎች እዚህም እዚም እየታዩ ነው። አሁን ባለው የዓለሙ ተጨባጭ ሁኔታና እንዲሆንላቸው በሚመኙት ነገር መካካል ያለው የግብ መዳረሻ ታክቲክ አዋጭ ነው ብለው ያምናሉ? ንግድ እንኳን ሲጀመር የምናወጣው ወጭ ከአምራቹ ጥያቄና እኛ ካለን የአቅርቦት መጠን ጋር መጣጣሙን አስበን ነው ወደ ሜዳው የምንገባው።
አሁን ያለው የሐገራችን ሁኔታ ግን እነርሱን ወደሚፈልጉት ግብ ለማድረስ የሚመች ሜዳ ጠፍቶ ነው፣ ወይንስ የተከፈተው ሜዳ ሳሆን እኛ የምንከተለው መንገድ ነው ወደምንፈልገው ግብ የሚያደርሰን ብለው በመቁረጥ የቆረጡትን ቃጫና የፈተሉትን ጅራፍ ማጮህ ነው የመረጡት። እውን ይኼ ኩሩና ታጋሽ ህዝብ ጅራፍና አለንጋ ያስፈልገዋልን ? ካለ አለንጋ የሚፈልገውን ነገር በሚፈልገው መንገድ የመምረጥና የማጣጣም መብቱ ሊጠበቅ አይችልምን? አይገባውምን? ነው ወይስ የሚስፈልገው ነገር አሁንም የምናውቅልህ እኛ ነን ለማለት የተዶለተልን ሤራ አካል ነው?
ይኼ ህዝብ፣ ለአስራ ሰባት ዓመታት “እግዚአብሔርን ማመን አያስፈልግህም፤ ልታምን የሚገባው በራስህና በእጆችህ ሥራ ብቻ ነው”፤ ተብሎ ተመርጦለት፣ እንዲያውም “ሰውን ሰው ያደረገው ሥራ ነው”፤ ይሉትን ብሒል በደረቁ አምጥተው ጭነውበት፣ የነፍስያ ቤቱን በጽሞናና በልቡ ሲያስስ ኖረ፤ ይህም አለፈ፤ ብሎ በዚያ እግር የተተኩት ደግሞ ሲመጡ፣ “እግዚአብሔርን እመን፤ እኛን ደግሞ የበለጠ እመነን” የሚሉና መንፈሳዊም ሆነ አካላዊ መስተዳድሩን ሁሉ በእጃቸውና በጉልበታቸው ጥርነፋ፣ የቆለመሙ ገዢዎች ሆኑ።
አንድ ጊዜ የዩጋንዳው የአንድ ወቅት ፕሬዚዳንት፣ ኢዲ አሚን በኡጋንዳ ሐሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ነጻነት ሲጠየቁ፣ “አዎ፣ በሐገራችን ውስጥ ሐሳብን እንደልብ መግለፅ ይቻላል፤ ከገለጹ በኋላ ግን ዋስትና መስጠት ያስቸግራል” ሲሉ መደመጣቸው ይታወሳል።
በአፍሪካ ውስጥ፣ ሥልጣንን የነብር ጅራትን ከመጨበጥ ጋር እያነጻጸሩ ራሳቸውን የዘላለም መሪ አድርገው በማሰብና አንቱ አስብለው፤ አቻ-የለሽ አድርገው ይቆዩና፣ ጊዜ ሞታቸው ደርሶ፣ ጉዞ ፍታት ሲደረግላቸው ሳጥን ሰብረው ለመውጣት ክፉኛ ሲፍገመገሙ እንታዘባለን። አሁንም ኢዲ አሚን ከአፌ አይጥፋና ከካምፓላው ቤተ መንግስቱ ወደ ሣውዲ አረቢያ በቻርተወር ፕሌኑ በርሮ ከጠፋ በኋላ፤ የእርሱን ሥፍራ በታንዛኒያ ጦር ድጋፍ አባርረው ሥልጣኑን የያዙትን ዶክተር ሚልተን ኦቦቴን፣ (በጄኔራል ኢዲ አሚን በመፈንቅለ መንግስት ከመባረራቸው በፊት፣ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ነበሩ) በቅርቡ ተመልሼ እመጣለሁ፤መድረሻ አሳጣችኋለሁ እያለ ሲያዝጋቸው ቆይቶ፣ ስልጣኑ ሳይሆን የዩጋንዳን መሬት እንደናፈቀ ቀርቷል። ግን ግን፣ ክፉዎችን፣ ተዉን ስንላቸው ሳይሆን መተው በሚገባቸው ሰዓት ግን ትተው መሄዳቸውን ይዘነጋሉ።
ተዉን ስላልናቸው የማይተዉን ብዙ ነገሮች በህይወታችን ውስጥ አሉ። ለአብነት ሳንጠቅስ የምንጠቅሳቸው ከመልካምነት ይልቅ ክፋቱና ጉዳቱ ያዘነበለባቸው ብዙ ነገሮች አሉን።
በሰው ልጅ ባህሪይ ውስጥ ቀድመው የተተከሉትና ሰው ከመሆን ዕጣ ጋር የሚያያዙት ነገሮቻችን ደጋግ ናቸው። በረቂቅ መንፈስነት በውስጣችን ያሉት እንደ መሳቅ፣ መደሰት ደስታን ማጋራት፣ መናፈቅ፣ ማፍቀር፣ ደግነት፣ የዋህነት፣ ይቅር ባይነት፣ መተውና ማንቀላፋትን የመሳሰሉ ነገሮች ባህሪያዊና ሰዋዊ ናቸው። ከማፍቀር ይልቅ መጥላትን ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከመቻቻል ይልቅ መገፋፋትን የምንማረው ከህይወት ነው።
አሁን አስቸጋሪ ሆነው ህይወታችንን እያመሳቀሉ ያሉት ነገሮች አብረው የተሰጡን መልካሞቹ ባህሪያታችን ሳይሆኑ የተማርናቸውና ያደግንበት ማህበረሰብ ያወረሰን የመለያየት ጠባዕያት ናቸው።
አሁን በቅርቡ አንድ ነጭ ብሔረተኛ ነኝ የሚል አሜሪካዊ በኤንቢሲ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ፣ እንዴት ስለልነት ታወራለህ ሲሉት እኔ የማወራለት ልነት እኮ ረቂቅና የማይታይ ሳይሆን ግልፁን ልዩነት ነው። እኛ ነጮች ነን፤ የተለየን ነጭ ነን፤ ይህን ማንነት ከሌላ ጋር ደባልቆ ማሰብ ተገቢ አይደለም፤ ይህ ማንነትም በሌሎች መከበር አለበት፤ አላከብርም የሚለውን እንዲያከብር የማድረግ ነጫዊ ግዴታ አለብን ብዬ አምናለሁ፤ ደግሞ ሲል ነው የተደመጠው። ይህ ንግግር ከላይ ሲያዩት ርቱዕ በሆነ መንገድ ልክ የሚመስል ነጭ አንጋሽ የሆነ ራስ በልዩነት አስቀምጦ ሌላው ለራሱ ዕጣ ፈንታ የመተው ንቀትን ያዘለ ነው።
አንተን ጥቁር ወይም ሒስፓኒክ ወይ ሞንጎላዊ ዝርያ ካለው ኮሪያዊና ቻይናዊ በሥነ-ተፈጥሮ የሚለይ ነገር አለ እንዴ ብሎ ጋዜጠኛው ሲጠይቀው እንዲህ ዓይነቱ ብሒል ማንነታችን ለመጨፍለቅ ከሚታሰብ የጠቅላይነት አስተሳሰብ (hasty Generalization) የሚመነጭ፣ እይታ ነው፤ አለው። ጋዜጠኛው እንዲሁ አልተወውም፤ እንዳንተው እጅ፣ እግር፣ ማሰቢያ አእምሮ፣ ህልም፣ ራዕይ፣ ግብ፣ ፍላጎት፣ እምነትና ፍቅር አለኝ፤ በትውልዴ ከአንግሎ ሳክሰንና ከአፍሪካዊ ቤተሰብ የተዳቀልኩ፣ ነኝ፤ በአንድ ቋንቋ ብንነጋገርም ካንተ የተለየ አስተሳሰብ አለኝ፤ አሁን የምትለው ማንነት እንዲህ መሰሉን አካሄድ ይቀበላልን ? ልዩነትን በጸጋ የሚቀበልና በእኩል ስሜት የማስተዳደር ምኞት ብቻ ሳይሆን ምቾት አለህን ? ሲለው፣ በቅድሚያ የኔን የዘር ልዩነት መቀበል አለብህ፤ ከዚህ በስተቀር ለአኗኗሬ የምምርጠውን መንገድ መቀበል ይጠይቅሃል፤ ከዚያ እናስብበታለን ሲል ነው፤ የመለሰለት።
የዚህ ሰውዬ መልስ ያለጥርጥር፣ ዘረኝነትን የተላበሰ ነው፤ ከዚህ በፊት በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓተ አገዛዝ ከዚህ የተለየ ነገር አላሉም፤ “በልዩነት እኩልነት” (Separate but Equal) ነበረ፤ የሚሉት። ደቡብ አፍሪካውያን ታዲያ በጽኑ ነበር የታገሏቸው። ልዩነትን መቀበል ባይከፋም፣ በአገዛዝ ሥርዓታቸው ውስጥ ግን ገዢዎቹ ለነጮቹ የተስማማ፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ባቡር፣ ሆቴል፣ መዋኛ፣ወዘተ…ኖሯቸው ይንንም ለማስከበር ህግ አርቅቀው፣ በሐጉም መሰረት ማስፈጸሚያ የመከላከያና የፖሊስ ኃይል አደራጅተው ነበረ፤ ሃገሪቱን የሚመሩት። ሥልጣነ መንግስት ብቻ አይደለም ኢኮኖሚውንም ሆነ ማህበራዊ መገልገያው የሰማይና የምድር ያክል የተራራቀበት አገልግሎት የሚሰጠው ጥቁሮቹ ደቡብ አፍሪካውያን ይህንን አድሏዊ አስተዳደር ለማስወገድ የታገሉትንና መስዋዕትነት የከፈሉትን ያህል፤ ከእነርሱው መካከል የተመረጡና ጥቅማቸው የተረጋገጠላቸው ጥቂት ጥቁሮች (የዙሉው መሪ ጋሻ ቡቴሌዚ አንዱ ነበረ) ደግሞ ይህንን አገዛዝ በማንቆለጳጰስ የተገፉ ወገኖቻቸውን የመከራ ዕድሜ ያስረዝሙ ነበረ። በዕውን ነጮቹ ተዉን ስለተባሉ ይተዉ ነበርን ? ግን እውነት ነው ዕድሜ ይቀጥሉ ይሆናል እንጂ ነገር ሲበቃ ያበቃል። ታዲያ ጥቂት ነጮች ዛሬም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የቦር (የአፍሪካነር ቋንቋ ብቻ የሚነገርበት የነጮች ሪፐብሊክ) ለማቋቋም ሲታትሩ ነበረ። ሲወድቁ ሐገር ይዘው ሊወድቁ የሚያስቡ ክፉዎች ብቅ ብለው ነበረ፤ የቅኖች አምላክ አላሳካላቸውም እንጂ።
የሚያዋጣው በእኩልነት አንድነት እንጂ፣ በልዩነት ተብሎ የሚሰራ አንድነት የሚያዛልቅ አይደለም። ምክንያቱም የሚራገብ ልዩነት የሚጠቅመው የተለየሁ ነኝ ብሎ ለሚያስበው ለዚያ ቋንቋ ተናጋሪ “ጥቂት ብልጦች” እንጂ ለህዝቡ አይደለም። የሚገርማችሁ በቦር ግዛት ውስጥ ለማቋቋም አስበው በነበረው መንግስት ውስጥ ያጎነቆለው ልዩነት አስቂኝ ነበረ። ከ400 ዓመት በፊት በተደረገ ጦርነት ስፍራው ላይ አውሮፓውያን ሲገኙ የመጡት ከተለያየ ግዛት ነበረና፤ ስለ መንግስት ምስረታ ሲነገር፣ የሚቆመው መንግስት የደቾች ነው፣ የእንግሊዞች ነው የአይሪሾች ነው፤ ወይስ የጀርመኖች ነው ተብሎ ውዝግብ ተነስቶ ነበረ። ነጭነትም እኮ ልዩ ልዩ አለው፤ ልዩነትን አጥብቦ በጋራ ጉዳይ ላይ ለመስማማት መዘጋጀት ነው፤ የሚያዋጣው።
እስካሁን ባነሳሁት ክፍል ላይ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ልዩነትን የሚያባብሉ፣ እሽሩሩ የሚሉና ተንከባክበው ለማሳደግ ሌት ተቀን ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች አንድነት ሲሏቸው፣ ጋራተኛነት ሲባሉ፣ ህብረት ሲባሉ የማይዋጥላቸው ምክንያት፣ በልዩነቱ የሚያተርፉት የፖለቲካ ንግድ ትርፍ ለጊዜው አዋጭ ስለሆነላቸው ነው። “ላንተ ስንል ተጎዳን፣ ላንተ ስንል ተከበብን፣ ላንተ ስንል ተጠቃን” ብለው ማህበረሰቡ በሚሰማቸው ቋንቋ ስለሚያቃስቱ ህመምና ስቃይ ማጋባት ቀላል ስለሚሆንላቸው ነው፤ ለጊዜው።
ስፋት ያለውን፣ ሩቅ ግብን የሚያስቀምጥና ስራው ሁሉን አካታች የሆነ አጀንዳ ያላቸው ወገኖችን ማጣጣል፣ ስም ማጥፋትና ማኪያኬስንማ በፈጠሯቸው የመገናኛ ብዙሃን ቻናሎች ሁሉ “በደንብ” (አንዳንዶቹን ግን የቡቱ ቡቱቱ ተረት ይበልጣቸዋል)፤ ያውቁበታል። እንዲህም በማድረግ ለኪሳቸው የሚተርፍ ነገር ከሐገር ቤትም ከባህር ማዶም አጠረቃቅመው የራሳቸውን “የምድር ገነት መኖሪያ” ቤት ይገነባሉ። ያዋጣቸው እንደሆነ ጊዜ ራሱ ፈራጅ ነው። እንደ እኛ ደሃ ለሆነና ገና ብዙ ሥራ ለሚጠብቃት ሐገር ግን መተባበርን የመሠለ፣ ሐገራዊ አንድነትን የሚያህል መልካምነትም ጉልበትም የለም። ግን እነዚህን እኩልነትንና አንድነትን አፍራሽ ተነጣይ ወገኖች፣ “ተዉን ስላልናቸው ይተዉን ይሆን ?” ወይስ ጊዜው ሲፈቅድ ፍጻሜው ወዳልታወቀ አቅጣጫ የሚበርረውን ባቡራቸውን አቀዝቅዘው በጋራ ሐዲድ ላይ ወደሚፈስው ታላቅ ወንዝ በመቀላቀል በጋራ ኩራት ይጓዙ ይሆን?
ደቡብ አፍሪካን ከነችግሩ፣ ወደሚያስገርም የጋራ ቤትነት የለወጠው ስምምነት እኛ ቤትና ምድርም ሆኖ፣ እነጋሻ ቡቴሌዚን አብሮ ሰራተኛ ያደረገው ለውጥ የእኛንም ክፉዎች አለዝቦ ለአብሮነት ያብቃን እላለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ