ቅድመ- ታሪክ
ልጅነቱን ያሳለፈው ውጣ ውረድ በሞላው ህይወት ነው። ዕድሜው ከፍ ሲል ወላጆቹ ትምህርት ቤት አልሰደዱትም። ከብት እየጠበቀ ግብርናን ብቻ እንዲያውቅ መንገዱን አሳዩት። በቀለ እንደ እኩዮቹ ከሜዳ እየዋለ ሲመሽ ቤቱ ይመለሳል። የእነሱ አካባቢ ዱርና ጫካ የሞላበት ነው። አንዳንዴ ገና በወጉ ሳይመሽ የአውሬዎች ድምጽ ይሰማል።
የነ በቀለ መኖሪያ በአዲስ አበባ ክልል ቢሆንም ከከተማ ወጣ ያለ ስፍራ ነው። በልጅነቱ ስለከተማው ድምቀትና ማማር ሲተረክለት አድጓል። ብዙ ባይልም እሱም ቢሆን በመጠኑ ያውቀዋል። ያም ሆኖ ከጫካማው ሰፈር ርቆ ከከተማ ለመኖር ዕድሉን አላገኘም።
በቀለ ዕድሜው ሲጨምር የወላጆቹን መሬት እያረሰ ቤተሰቡን ማገዝ ጀመረ። ጉርምስናው አግዞትም የበረታ ጉልበቱ መልካም ፍሬን ያስገኝለት ያዘ። ይህኔ ቤተሰቦች ትዳር ይዞ የልጅልጆችን እንዲያሳያቸው ተመኙለት። እሱም ቢሆን ዕቅዳቸውን አልተቃወመም። ጎጆ ቀልሶ ልጆች ሊያፈራ በሙሉ ልብ ተዘጋጀ።
አዲስ ህይወት
ከጊዚያት በኋላ የወላጆቹ ምኞት ሰመረ። በቀለ ሚስት አግብቶ ትዳር መመስረቱን ወዳጅ ዘመድ አወቀለት። እንዲህ ከሆነ ወራት በኋላ ቤቱ በመጀመሪያው ልጅ ተባረከ። ይህኔ ገበሬው በቀለ ልጁን ለማሳደግ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያሻው አሰበ።
የሚኖርበት የየካ ‹‹ቁልቲ›› ዙሪያ ገባ ቀበሌ ጫካማና ደን የለበስ ነው።ስፍራውን ከዛፎች ጭፍጨፋ ለመታደግ ጠዋት ማታ የሚጠብቁ ዘቦች ወርሀዊ ክፍያ አላቸው። እነዚህ ደን ጠባቂዎች ለማገዶ ለቀማና ለዛፍ ቆረጣ የሚመጡትን ለይተው ያውቃሉ።
አንዳንዶች ጨለማን ተተግነው ዛፎችን ይቆርጣሉ። ሌሎች ደግሞ የተተከሉ ችግኞችን ነቅለው ቦታውን ያራቁታሉ። ብዙዎች ወደዚህ ስፍራ ሲመጡ የራሳቸውን ዓላማ ይዘው ነው። ከእንዲህ መሰሎቹ ደኑን ለመጠበቅ ሌት ተቀን የሚተጉት ጠባቂዎች ሁሌም ኃላፊነት አለባቸው።
ጠባቂዎቹ ጠመንጃ በትከሻቸው አንግበው በንቁ ዓይኖቻቸው ስፍራውን ያማትራሉ። ኮሽታን የሚለዩት ጆሮቻቸው ድምጽ ባሰሟቸው ጊዜም ከቦታው ደርሰው ሁኔታውን ያጣራሉ። እንደገመቱት ሆኖ ዛፍ ጨፍጫፊዎች ከሆኑ በዋዛ አይለቋቸውም። እጅ ከፍንጅ ይዘው ለህግ ያቀርቧቸዋል።
እንጀራ ፍለጋ
በቀለ ተወልዶ ያደገበት አካባቢ በዚሁ ስራ የተቃኘ መሆኑን ያውቃል። ለእሱና ለአካባቢው ነዋሪዎች የ‹‹ቁልቲ›› ደን አስትንፋሰ እንደሆነ ዓመታትን ዘልቋል። ለስፍራው ለምነትና ለነፋሻው አየር መኖር ሰበብ የሆነው ይህ ጫካ ለብዘዎቹ የእንጀራ ማግኛ ጭምር ሆኗል።
በደን ልማቱ ጥበቃ ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላችው ብዙዎች ቤታቸውን ደጉመው ልጆች ያስተምራሉ። በቀለም በዚህ ስራ ለመቀጠር ዕድሉን ባገኘ ጊዜ ደስተኛ ሆነ። ካለው የግብርና ውሎ በተጨማሪ የወር ደመወዝተኛ መሆኑ አቅሙን ደገፈለት። እሱም እንደሌሎች ጠመንጃውን አንግቦ በደኑ እየዞረ ጥበቃውን ጀመረ።
በቀለ ተረኛ በሆነ ጊዜ በደኑ መሀል ይዟዟራል። በአጋጣሚ ምሳር ያገኘባቸውን እየያዘም ለሚመለከተው ያሳልፋል። በደኑ ቅጠል ጠርገው፣ እንጨት ሰብረው የሚያድሩ ሴቶችም ቢሆኑ ከእሱ እይታ አያልፉም። ህጻናትን ጨምሮ ምስኪን እናቶች በእንጨት ለቀማ የሚውሉበት የ‹‹ቁልቲ›› ደን አንዳንዴ በውሰጡ የሚፈጸም ጥቃትን ሸፍኖ ያስተናግዳል።
ጫካውን ተተግነው ክፋት የሚያስቡ ወንዶች በስፍራው የደረሱ ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ። እነበቀለ ከጥበቃው ባሻገር እንዲህ አይነቶቹን አጋጣሚዎች ያውቋቸዋል። ብዙ ሴቶች ለእንጨት ለቀማ ወጥተው ላልፈለጉት እርግዝናና ለጥቃት ተጋልጠዋል።
የጫካው ትዕይንት በዚህ ብቻ አያበቃም። የነጋባቸው አውሬዎችም ድንገት ደርሰው በሰውና በእንስሳ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ከዋሻቸው የሚወጡ ጅቦች ሁሌም ቢሆን ለአካባቢው ስጋት ናቸው። ድንገት ያገኙትን ከመተናኮልና ባስ ሲልም ከመብላት ወደኋላ አይሉም።
በቀለ የግብርና ስራውን እንደያዘ የደን ጥበቃውን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከትዳር አጋሩ መደዳውን የወለዳቸው ስድስት ልጆቹ የእሱን እጅ ይናፍቃሉ። እሱ ሳይማር መቅረቱ ይቆጨዋልና ልጆቹ ባለፈበት መንገድ እንዲሄዱ አይፈቅዱም።
ለትምህርት የደረሱ የበቀለ ልጆች ደብተር ይዘው ትምህርት ቤት ይውላሉ። የቤት እመቤቷ እናታቸውና ደን ጠባቂው አባታቸው ከእነሱ ብዙ እንደሚሹ አይጠፋቸውም። ዛሬ ካሉበት ኑሮ ተላቀው ነገን በተሻለ ለማለፍ ከድህነት እየታገሉ መማርን አማራጭ አድርገዋል።
ተጠራጣሪው
ደን ጠባቂው ጎልማሳ ስራው ላይ ሲገኝ ጥርጣሬን ያበዛል። ማንም በአጠገቡ ባለፈ ጊዜ በበጎነት መመልከት አይቀናውም። ደኑን ረግጦ የሄደ ሁሉ ለጥፋት የመጣ ይመስለውና ፊቱን ይጨፈግጋል። መሳሪያውን ከትከሻው አውርዶ መነካካት የሚወደው በቀለ ይህን በማድረጉ ስሜቱ የተለየ ይሆናል። ለእሱ መሳሪያው መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን ማስፈራሪያው ጭምር ነው። በደኑ ውስጥ ሲውል አሻግሮ እያየ ከልቡ ይመካበታል። ወጣ ሲልም ከሰው ዓይን እንዲገባ ልዩ ትኩረትን ይስባል።
አንዳንዴ በቀለና ባልንጀሮቹ ከከተማ ይዘልቃሉ። ብዙ ጊዜ እንዲህ ሲያደርጉ ዋናው ምክንያታቸው መዝናናት ይሆናል። ‹‹ተዝናናን›› ሲሉ ደግሞ መጠጥ ያዘወትራሉ። መጠጡ ከእርካታ አልፎ ስካር ሲያመጣ አለመስማማት ይከተላል። መንደራቸው ሲመለሱ ሲሄዱ የነበራቸው ስሜት አብሯቸው አይዘልቅም።
በቀለ የወር ደመወዝ ሲቀበል ከተማ የመሄድ ልምድ አለው። ለቤት የሚያስፈልገውን ሰጥቶ የሚዝናናበትን በመያዝ ከሰፈሩ ይርቃል። በዚህ ቀን ከራሱ አልፎ ሌሎችን ለመጋበዝ አይሳቀቅም። ተመልሶ ስራ የሚሄድ ከሆነም ልበ ሙሉነት እየተሰማው ነው። መጠጥ ቀምሶ መሳሪያ ሲይዝ ውስጡ ትዕግስት አልባ እንደሚሆን ጠንቅቆ ያውቃል።
ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም
በቀለ በዚህ ቀን የቁልቲን ደን ሲጠብቅ ውሏል። ዕለቱ የደመወዝ ቀን በመሆኑም የተለመደውን ብር ቀንሶ ቀሪውን ለሚስቱ በመስጠት ከጓዶቹ ጋር ተቃጥሯል። ይህ ከመሆኑ በፊት አብሮት ከሚጠብቀው ጓደኛው የተረከበውን ጠመንጃ ከአንድ ጥይት ጋር ከቤቱ አኑሯል።
መጠጥ ቤት
ከቀትር በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ከተማ የዘለቀው በቀለ ከአንድ መጠጥ ቤት ተገኝቷል። በኪሱ ያለው ገንዘብ አላሳቀቀውም። አንዱን ጨልጦ ሌላው ሲቀዳለት ለቀጣዩ መጠጥ ራሱን ያዘጋጃል። አንድ ሁለት ማለት የጀመረው አባወራ የሰዓቱን መንጎድ አስተውሏል። አሁን ጨዋታው ደምቆ ሞቅታ እየመጣ ነው። ምሽቱ ከገፋ ግን እሱን ጨምሮ የሩቅ ተጓዦቹ ባልንጀሮች በጊዜ ለመድረስ ይቸግራቸዋል።
ከመንደራቸው ራቅ ያሉት ባልንጀሮቹ ምሽቱንና የመንገዱን ርቀት ገምተው ለመሄድ ተነሱ።በቀለም በእጁ የያዘውን በቁሙ ጨልጦ ከኋላቸው ደረሰ። ጓደኛሞቹ ከተማውን ለቀው ወደመንደራቸው ተጓዙ። ከስፍራው ሲደርሱ ምሽቱ ገፍቶ አንድ ሰዓት ተኩል ሆኖ ነበር።
በዚህ ሰዓት ትምህርት ቤት የሚውሉ ተማሪዎች ወደ ቤታቸው ይገባሉ።ጉዳይ ከከተማ ያዋላቸው አንዳንዶችም ጫካው በዝምታ ሳይዋጥ በእርምጃ ይጣደፋሉ። በቀለም ባልንጀሮቹን ተሰናብቶ ወደ ቤቱ አቅጣጫ ጉዞ ጀምሯል። በሰውነቱ የዘለቀው መጠጥ ሙቀቱን አክሎ ድካም ቢጤ እየተሰማው ነው። ቤቱ ደርሶ ማረፍ እንዳለበት ከራሱ ጋር መምከር ይዟል።
በቀለ ቤቱ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ኮሽታ ቢጤ ተሰማው። ይህኔ ልማደኛ ዓይኖቹ በጥርጣሬ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ጀመሩ። ጆሮዎቹን አቅንቶ ማዳመጡን ቀጠለ። በውል ያለየው አንዳች ድምጽ በዙሪያው እንዳለ አልጠረጠረም።
ከጥርጣሬው ሳይወጣ በጆሮ ግንዱ ፈጥኖ ያለፈ የድንጋይ እሩምታ ተሰማው። ድንጋዩን ዝቅ ብሎ ለማሳለፍ እየሞከረ ጥግ ይዞ ጠበቀ።አሁንም ተከታታይ ውርወራ በጆሮ ግንዱ አልፎት ሲሄድ አስተዋለ።በቀለ ካለበት ሆኖ ዓይኖቹን ወደ አንድ አቅጣጫ ላከ። ወዲያው ማንነታቸውን ያላወቃቸው ሁለት ሰዎች ሮጥ ብለው ሲያልፉ አያቸው።
እንደነደደው ወደ ቤቱ ሮጦ ገባና ወደ ጓዳው አመራ። ከሰዓታት በፊት ከባልንጀራው የተቀበለው መሳሪያ ከቤቱ እንዳለ ያውቃል። እልህና ቁጭት እያነቀው ጠመንጃውን ከተቀመጠበት አንስቶ እየሮጠ ወጣ።በእሱ ላይ ይህን ያደረጉ ሰዎች ርቀው ሳይሄዱ ሊይዛቸው ፈልጓል።የሰዎቹ ድርጊት ከጥቃት በላይ መሆኑ የገባው በቀለ ቀድሞ በነበረበት ቦታ ሊደርሰ መሳሪያውን ወድሮ ገሰገሰ።
ጥቂት ቆም ብሎ ኮቴ አዳመጠ። የጫካው ቅጠል በጫማ እየተረገጠ ነው። የሚሰማው እርምጃ የአንድ ሰው ብቻ አለመሆኑ ገባው።ከደቂቃዎች በፊት ድንጋይ የወረወሩበትን ሁለት ሰዎች አሰባቸው።ግምቱ እንዳልሳተ ሲረዳ ኮሽታውን ተከትሎ ወደፊት አመራ።አልተሳሳተም። ሁለት ሰዎች ከእሱ እምብዛም ሳይርቁ አጠገቡ ተገኝተዋል። ጨለማውን እየጣሰ ቀረባቸው።
በቀለ የድንጋይ ውርወራው ምንጭ ከእነሱ እንደሆነ አምኗል። ይህን ሲያደርጉ ምን አስበው እንደሆነ አልገባውም። ምላሹን ለማግኘት ጊዜ አልነበረውም። ለፈጸሙበት በደል ዋጋቸውን ሊሰጣቸው ወሰነ። ውስጡ በንዴት እየጨሰ ‹‹እናንተ እነማናችሁ? ››ሲል ጠየቀ። ሰዎቹ ስሙን ጠርተው ማንነታቸውን ሊነግሩት ሞከሩ። ሊሰማቸው አልፈቀደም።
ከትከሻው ያነገበውን መሳሪያ አውርዶ አነጣጥሮ ተኮሰ። በውስጡ የነበረችው አንዲት ጥይት ዒላማዋን አልሳተችም። በቀለ በአጭር ርቀት የነበረ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ሲወድቅ ተመለከተ። አብሮት የነበረው መንገደኛ እየሮጠ ሲሄድ የወደቀውን ሰው መለስ ብሎ ቃኘው። ልቡ ደጋግሞ መታበት። እጅና እግሩ እየተንቀጠቀጠ አጠገቡ ደረሰ።
ወጣቱ ተማሪ ደብተሩ ተበትኖ በደም ተነክሯል። ልጁንና ቤተሰቦቹን አሳምሮ የሚያውቀው በቀለ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ። ተማሪው ሁሌም በዚህ ሰዓት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እንደሚገባ ያውቃል።ሰላማዊና ጨዋ የሚባል ልጅ ነው። አሁን ድርጊቱን እሱ እንዳልፈጸመው ገባው። መሳሪያውን አንግቦ እጁን ለመስጠት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገሰገሰ።
የፖሊስ ምርመራ
ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ ከአካባቢው ነዋሪ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ የተሟላ ቡድን አደራጅቶ ከስፍራው ደረሰ። የሟችን አስከሬን አንስቶም አስፈላጊውን መረጃ ለመውስድ ምርመራውን ጀመረ። ሟችና ገዳይ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ናቸው። ከዚህ ቀድሞ ቤተሰባዊ ቅርበታቸው የጠበቀና ጠብና ቅራኔ ያልነበራቸው እንደሆኑ ፖሊስ አረጋገጠ። በቀለ በዕለቱ ከፖሊስ ጣቢያ ደርሶ በሰጠው ቃል ወንጀሉን በስሜታዊነት ተነሳስቶ መፈጸሙንና በድርጊቱም ክፉኛ መጸጸቱን ተናገረ።
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 605/06 በተከፈተው ዶሴ ቃሉን የተቀበለው መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ ወንጀሉ የተፈጸመበትንና የውግ ቁጥሩ 24233737 የሆነ ኤስኬኤስ ጠመንጃን በኤግዚቢት ተቀብሉ አስፈላጊውን ምርመራ እንዳጠናቀቀ የክስ ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ አሳለፈ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
መልካምስራ አፈወርቅ