የተወለዱት በደቡብ ክልል ሸኔ ከተማ ነው። ከልጅነታቸው ጀምሮ ለትምህርት ባላቸው ፍቅር ከተወለዱበት ከተማ ርቀው በመጓዝ የትምህርት ጥማታቸውን ለማርካት ወጥተው ወርደዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት ሸኔ ከተማ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀድሞ አጠራር ናዝሬት (ዓዳማ) በሚገኘው አፄ- ገላውዲዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ውጤታቸውም አመርቂ በመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል አልተቸገሩም።
ፍላጎታቸው ወደ ሳይንሱ በማዘንበሉ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ በማጥናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአፄ ኃይለሥላሴ እጅ በ1965 ተቀበሉ። ውጤታቸውም ከፍተኛ ስለነበረ በጀማሪ መምህርነት በዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀጠሩ። በወቅቱ ያስተምሩ የነበሩትን የውጭ መምህራንን ለመተካት የአሜሪካ መንግሥት በሰጠው ዕድልም በመጠቀም አሜሪካን አገር ድረስ ተጉዘው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ የትምህርት መስክ አግኝተዋል። ወቅቱ በኢትዮጵያ የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ፍጅት የነበረበት ቢሆንም የብዙዎችን ዛቻና ማስፈራራት ወደ ጎን በመተው የሀገሬን ችግር አብሬ እካፈላለሁ በሚል ወገናዊ ስሜት ወደ ሀገራቸው በ1970 ተመለሱ። የወቅቱን ፈተናን በመጋፈጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ሙያቸውን ቀጠሉ።
በዚሁ በማስተማር ሙያቸው ላይ እያሉም የዓለም ጤና ድርጅት የሰጠውን ዕድል በመጠቀም ወደ አሜሪካን አገር አቅንተው በቆላ ቀመስ በሽታዎች ዙሪያ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመሥራት ቻለዋል። ከማስተማር ጎን ለጎንም በፖለቲካው ዘርፍ ሰፊ ተሳትፎ ያላቸው እኒሁ ምሁር ከተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ እስከ ዘመነኛው የኢህአዴግ ፖለቲካ ድረስ ባልተቋረጠ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አልፈዋል። ዛሬም የፖለቲካ መድረኩ ዋነኛ ተዋናይ ናቸው። እኒህ ጉምቱ ምሁርና የፖለቲካ ሰው ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው። አዲስ ዘመንም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከእኒሁ ምሁርና ፖለቲከኛ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን:- ቃለ መጠይቃችንን ወደ ፖለቲካው ዓለም እንዲገቡ ካደረገዎት አጋጣሚ ብንጀምርስ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ይቻላል፤ ፖለቲካ እኔ የምንተዋወቀው ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። እራሴን ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ነው ፖለቲካን መለማመድ የጀመርኩት። ባደግኩበት አካባቢ የመሬት ከበርቴዎች በገበሬው ላይ ከፍተኛ በደልና ጭቆና ይፈጽሙ ነበር። ከበርቴዎቹ ከመፋነናቸው የተነሳ በመሬታችሁ ላይ ቋሚ ተክል አትተክሉም፤ በዚህ መሬት ላይ አትቀብሩም የሚሉ ለማመን የሚያስቸግሩ ግፎች በገበሬው ይፈፀሙ ነበር። ይህንኑ ግፍና በደል በመቃወምም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ ነበር። ከዚህ ውስጥ የጃርሶ የገበሬዎች አመጽ ተጠቃሽ ነው። እኔ ይህንን እያየሁ ነው ያደግኩት። ወደ ትምህርቱ ዓለም ከተቀላቀልኩ በኋላም በተለይም በ1958 አካባቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ነበርኩ። ከጌታቸው ማሩ እና መሰል ስመጥር የወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች ጋር አብሬ እሳተፍ ነበር። ኢህአዴግ ከገባም ጀምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋም በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ከ28 ዓመታት በላይ ቆይቻለሁ። በአጠቃላይ ከ40 ዓመት በላይ በፖለቲካው ዓለም ቆይቻለሁ ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን:-ኢህአዴግ 42 የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ሲያባርር አንዱ ነበሩ፤ እሰቲ ስለሁኔታው ቢያጫውቱን
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ኢህአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር እኔ አዲስ አበባ አልነበርኩም። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አማካኝነት ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሞስኮ ነበርኩ። ኢህአዴግ ግንቦት 20/1983 አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በቅድሚያ ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የሰላምና ዴሞክራሲ ኮንፈረንስ ማካሄድ አንዱ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የሚሳተፈው ደግሞ በኢሰፓ ውስጥ ያልነበረና በቀይሽብር ውስጥ ያልተሳተፈ ሰው መሆን አለበት የሚል መስፈርት ስለነበረ ከሁለቱም ነፃ መሆኔን የሚያውቁ የቅርብ ጓደኞቼ በዚህ ስብሰባ እንድሳተፍ ስሜን አስተላልፈው ጠበቁኝ። ስለዚህም ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስኩ እኔ ባልፈልገውም በጓደኞቼ ገፋፊነት በስብሰባው መሳተፍ ጀመርኩ። ይህ ስብሰባ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱ የምትመራበት ቻርተር የሚፀድቅበት በመሆኑ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነበር። ከቻርተሩም ውይይት በኋላ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተውጣጣ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም በመወሰኑ የፓርላማ አባልና የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆኜ ተመደብኩ። ትምህርት ሚኒስቴርን እንደገና ለማደራጀትና በጦርነት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችንም እንደገና ለማቋቋም በተደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነበረኝ። በአማራ፤ በትግራይ፤ በደቡብና ኦሮሚያ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲሠሩ አድርጌያለሁ። አሁን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ መቀሌ ዩኒቨርሲቲን የመሰሉ ተቋማትን መሠረት የጣልኩት እኔ ነኝ።
ሆኖም ግን ኢህአዴግ ከነበረው አቋም እየተንሸራተተና አምባገነን ባህሪ እየያዘ በመምጣቱ ከእኔ ጋር ልንስማማ አልቻልንም። በምሰነዝራቸው ሃሳቦችና ትችቶች የተነሳ‹‹ በየነን ተጠንቀቁት፤ እሱ አደገኛ ሰው ነው›› የሚል ማሸማቀቂያ ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ይሰነዘርብኝ ነበር። የተወሰኑ ጊዜያት በዚህ መልኩ ከቀጠልኩ በኋላ የ1984 ምርጫ መጣ። በዚህ ምርጫም የምርጫ ኮሚሽነሮች ተብለው ከተሰየሙት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበርኩ። ኢህአዴግ በወቅቱ ሰፊ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ ቢያስብም ህብረተሰቡ ግን ያሳየው ከድጋፍ ይልቅ ተቃውሞ ነበር። በዚህም በመደናገጥ የተለያዩ አምባገነናዊ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ። እኛ ምርጫ ኮሚሽነሮች ተብለን ብንሰየምም በጎን ኢህአዴግ ከእኛ ዕውቅና ውጭ የራሱን መንገድ እየቀየሰ ነበር። በተለይም ሥልጣኔን ይነጥቁኛል ብሎ ያሰባቸውን ኦነግን የመሳሰሉ ፓርቲዎች እያሳደደ ማሰርና መግደል ጀመረ። አምባገነናዊ ባህሪውም በግላጭ ጎልቶ ወጣ። እኛም ይህንን እና መሰል ኢፍትሃዊና አምባገነናዊ አካሄዶችን በመቃወማችን ከፓርላማ አባረሩን። የሽግግሩን መንግሥት ለማፍረስ አሲራችኋል ተብለን ጥርስ ተነከሰብን። ከትምህርት ሚስቴርም በአቶ ታምራት ላይኔ ሁለት መስመር ደብዳቤ ተሰናበትኩ። ወደ ዩኒቨርሲቲ ስሄድም በግቢው ጥበቃዎች እንዳልገባ ተከለከልኩ። እኔን ጨምሮ 42 ጉምቱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተባረርን።
አዲስ ዘመን:-የተባረራችሁበት ምክንያት ምንድን ነበር?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ይሄነው የሚባል ውሃ የሚቋጥር ምክንያት አልነበራቸውም። ብዙዎቹ መምህራን የተባረሩት ‹‹ሻይ ስትጠጡ ኢህአዴግን አምታችኋል›› በሚል ተልካሻ ምክንያቶች ጭምር ነው። በየቦታው በሰገሰጓቸው ካድሬዎቻቸው አማካኝነት በሚለቅሟቸው ወሬዎች ተነስተው ለዚች ሀገር የጀርባ አጥንት የነበሩ ሙህራንን ለማባረር ቻሉ። የእኛን ሃሳብ አይደግፍም የሚሉትን በሙሉ እስከ ወረዳ ድረስ በመውረድ በርካታ ባለሙያዎችን በባትሪ እየፈለጉ ጡረታችውን ጭምር በመንፈግ እንዲሰናበቱ አደረጉ። በዚህም ድርጊታቸው እስካሁን ድረስ እንደሚታየው በትምህርት ጥራቱ ላይ ጥቁር አሻራ ማሳረፍ ጀመሩ። በወቅቱ ኢህአዴግ የወሰደውን የማባረር እርምጃ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በመቃወም ለአቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር። አቶ መለስም እሳቸው በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያወቁት ነገር እንደሌለና ጉዳዩ የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን ዋሽተው ለዲፕሎማቶቹ ይነገሯቸዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ብቃት የሌላቸውን መምህራን የማሰናበት ሙያዊ መብት ስላለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገቡም ይናገራሉ። በዚህ መልስ ግራ የተጋቡትና በተለይም ‹‹ብቃት የሌላቸው መምህራን ናቸው የተሰናበቱት›› የሚለው የአቶ መለስ አባባል ያልተዋጠላቸው እነዚሁ ዲፕሎማቶች ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ተረዱ። ‹‹ብቃት የሌላቸው ምሁራን ናቸው የተባረሩት ላላችሁት ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ብቃት የለውም ወይ ?›› የሚል ጥያቄ ዲፕሎማቶቹ ለአቶ መለስ አነሱ። በዚህ የተደናገጡት አቶ መለስ አንዳንድ ስህተቶች መኖራቸውን በማመናቸው ስልክ ደውለው ወደ ዩኒቨርሲቲ መምህርነቴ እንድመለስ አደረጉ። ብዙዎች ግን እንደወጡ ቀርተዋል።
አዲስ ዘመን:- ፕሮፌሰር በየነ ለዘብተኛ ፖለቲካኛ ናቸው፤ ለኢህአዴግ የሚመች ፖለቲካ ስለሚያራምዱ ነው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሲታሰሩ እሳቸው የተረፉት የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ለዘብተኛ ፖለቲከኛ የሚለው ቃል እራሱ ከየት እንደመጣ አይገባኝም። ማን ይህንን ስም እንደሰጠኝም አላውቅም። ምናልባት ‹‹ተሳዳቢ አይደለም፤ ሥርዓት አልበኛ አይደለም›› የሚል ትርጉም ካለው እስማማለሁ፤ ይመቸኛል። እኔ አስተዳደጌ ሥርዓት የተሞላበትና ሃይማኖተኛ ከሆነ ቤተሰብ የተገኘሁ ነኝ። ሌላውን ማክበርና ሌላውን ማዳመጥ ያደግኩበት ሥርዓት ነው። በእኔ መርህ በሃሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም። በሃሳብ መለያየት ሐጢያት አይደለም። በሃሳብ ተለያይቶ መፋጨት፤ መጨቃ ጨቅና መታገል የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫ አድርጌ እወስደዋለሁ። ሰላማዊ ፖለቲካ ለማካሄድ ያገኘሁትን ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅሜአለሁ። ህዝቡ መብቱን አሳልፎ እንዳይሰጥና አምባገነኖችን ከመታዘዝ እንቢ እንዲል ማድረግ ከቻልኩ ለእኔ ትልቅ ዕድል አድርጌ እወስደዋለሁ። በዚህ ረገድም አምባገንን የነበረውን የኢህአዴግ ሥርዓት አልታዘዝም በማለት ህዝቡ ያሳየው እምቢተኝነት የዚህ ትግል አንዱ መገለጫ ይመስለኛል።
ሌላው ደግሞ ተሳድቤም፤ ድንጋይ ወርወሬም፤ ጦር ሰብቄም በተገኘው አጋጣሚ ሁላ ሥልጣን ላይ ልውጣ ከሚለው ፖለቲከኛ እለያለሁ። ይህንን ባለማድረጌ ለዘብተኛ ፖለቲከኛ የሚባል ከሆነ መቼስ ምን ይደረጋል። መቼም ቢሆን እኔ ይህንን የፖለቲካ ስልት አልደግፈውም። በሁከት፤ በብጥብጥና በመሣሪያ ኃይል ሥልጣን የሚይዙ አካላት ያለውን አምባገነን መንግሥት ከማውረድ የዘለለ ፋይዳ የላቸውም። በብዙ አገራት እንደታየው በጠመንጃ የመጣ መንግሥት ዴሞክራሲን ሲያረጋግጥ አልታየም። ስለዚህም ህዝቡ በምርጫ የሚጥለውና የሚሾመው የፖለቲካ ሥርዓት እስኪገነባ ድረስ በሰላማዊ ትግሌ መቀጠሌ የማይቀር ነው።
የታሰረ ፖለቲከኛ ብቻ ነው ሐቀኛ የሚለውን አልስማማበትም። መታሰር ጀግንነት አይደለም። አንዳንድ ፖለቲከኞች በሰበብ አስባቡ ከመንግሥት ጋር በመናቆርና ግጭት በመፍጠር ታስረው ጀግና መባል ይፈልጋሉ። ከእኔ በላይ ፖለቲከኛ የለም ለማስባልም መታሰር የሚፈልጉ በርካታ ፖለቲከኞች እንዳሉ አውቃለሁ። መንግሥት ይህንን ስለሚያውቅ ችላብሎ የተዋቸው እንዳሉ በተደጋጋሚ አይቻለሁ። ይህ በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችም ጋር ይታያል። አንድ ሰሞን እንደውም መታሰር የቁርጠኛ ፖለቲከኛ መለያ ባህሪ ተድርጎ ይወሰድ ነበር። በቀላሉ የህዝብ ድጋፍ ማግኛም ስልት ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ አካሄድ ደግሞ ምንም ለውጥ እንዳለመጣ ሁላችንም አይተናል። መታሰር ሳይሆን ህዝብን ማንቃት ነው ለውጥ የሚያመጣው።
አዲስ ዘመን:- በአሁኑ ወቅት እርስዎ በመድረክ ፓርቲ ውስጥ ያለዎት ኃላፊነት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ዶክተር መረራ ጉዲና የመድረክ ፓርቲ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ሲሆኑ እኔ ደግሞ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን በማገልገል ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን:- አሁን የመድረክ ፓርቲ አጠቃላይ ቁመና ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- መድረክ ፓርቲን ያቋቋሙት ስምንት ፓርቲዎች ናቸው። በተለያዩ ምክንያቶች መዝለቅ ያልቻሉ ፓርቲዎች ተቀንሰውና ታጥፈው አሁን አራት ፓርቲዎች ቀርተዋል። አሁን ኦፌኮ፤ ኢሶዴፓ፤ ሲአን እና አረና ቀርተዋል። በቅርብ ጊዜ ደግሞ የአፋር ህዝቦች ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ተቀላቅሏል። ሆኖም ግን በአንዳንድ አለመግባባቶች የመድረክ ፓርቲ ይኑር አይኑር በማይታወቅበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በተለይም የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ ምርጫው መራዘም አለበት፤ የለበትም በሚለው ሃሳብ ላይ ባለመግባባታችንና ይህንኑ ተከትሎ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይቋቋም በሚለው ላይ በመካከላችን ልዩነት በመፈጠሩ ፓርቲው ህልውናውን እያጣ ሄዷል።
አዲስ ዘመን:- በመድረክ ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች ምርጫውን በተመለከተ ያሳዩትን አቋም ቢያብራሩልን ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ከመድረክ ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮ፤ ሲአንና አረና ምርጫ መካሄድ አለበት ካልሆነም ብሔራዊ አንድነት መንግሥት መቋቋም አለበት የሚል አቋም ሲያራምዱ በእኔ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ እና የአፋር ህዝቦች ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የምርጫውን መራዘም ደግፈን ቆመናል። በተለይም ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት ጠንካራ በመሆኑ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ማቋቋም አያስፈልግም ብለን አቋም ይዘናል። ከመቶ በላይ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው መንግሥት እናቋቁም የሚለው ሐሳብ ለእኔ ከጨዋታ የዘለለ ትርጉም የለውም። ወትሮም ቢሆን ምንም መግባባት የማይታይበት የፖለቲካ ባህላችን መቶ ምናምን ፓርቲዎች በሚያደርጉት ትርምስ ጭራሽ አገሪቱን ወደመበታተን ሊያመሯት ይችላሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት ከህዳሴ ግድብና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሀገራችን ሰላምና ደህንነት ሥጋት ውስጥ በገባበት ወቅት አገሪቱ የሚያስፈልጋት ጠንካራ መንግሥት እንጂ በአለመግባባት የሚታመስ የፓርቲዎች ስብስብ መሆን ስለሌለበት ብሔራዊ አንድነት መንግሥት የሚለው ሚዛን የሚደፋ ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን:- መድረክ የአምስት ፓርቲዎች ጥምረት ቢሆንም ኦፌኮ ፈላጭ ቆራጭ ሆኗል፤ ሌሎች ፓርቲዎች ሚናቸው የተድበሰበሰ ነው ሲባል ይደመጣል፤ እውነትነት አለው?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- በዚህ ደረጃ የተጋነነ እንኳን ባይሆን ችግሮች እንዳሉ ግን መደበቅ አልፈልግም። በተለይም በኦፌኮ በኩል መተዳደሪያ ደንቡን በጣሰ መልኩ የሚደረጉ ተግባራት ፓርቲውን ለውድቀት እየዳረገው ነው። የመድረክ መተዳደሪያ ደንብ የመድረክ አባላት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሐድ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ጥምረት መፍጠር አይችሉም በሚል የትኛውንም የጎንዮሽ ግንኙነት እንዳያደርጉ ይከለክላል። ኦፌኮ ግን ኦነግንና ሌሎች በኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት እንዲመቸው ይህ አንቀጽ እንዲሻሻል ሙግት ሲያርግ ቆይቷል። እኛም የዚህ አንቀጽ መሻሻል ክፍተት እንደሚፈጥር በማመን አንቀፁ መሻሻል እንደሌለበት ብዙ ብንከራከርም የሌሎቹን ፓርቲዎች እገዛ ባለማግኘታችን አንቀፁ ሊሻሻል ችሏል። አረናና ሲአን የራሳቸውን ቁመና ካጡና በኦፌኮ ተጽዕኖ ሥር ከወደቁ ስለቆዩ የኦፌኮ ሐሳብ ተፈፃሚ ሆኗል። ኦፌኮ ይህችን ቀዳዳ ተጠቅሞ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጥሬያለሁ ብሎ መድረክ የማያውቀውን መግለጫ መስጠት ከጀመረ ውሎ አድሯል። ከሌሎች ፓርቲዎች ጋርም ተጣምረናል ብለው መግለጫ ሲሰጡ እንሰማለን። በነዚህና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ በየጊዜው ልዩነት ሲፈጠር ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በምርጫው መራዘም ዙሪያ ለመመካከር አራቱን የመድረክ አባላት ማለትም ኦፌኮ፤ ኢሶዴፓ፤ አረናና ሲአንን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎችንም ጠርተው ነበር። በኮሮና ምክንያት ምርጫውን ማካሄድ ስለማንችል በቀጣይ እንዴት መሄድ እንዳለብን የሚያመላክቱ መንግሥት ያስጠናቸው አራት አማራጮች ቀርበውልን ውይይት አደረግን። እኔ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲን በመወከል አራቱም ሕገ መንግሥታዊ መሆናቸውን በመገንዘብና ሆኖም ግን ሦስቱ ለጊዜው እንደማያዋጡ በማመን የሕገ መንግሥት ትርጉም መስጠት የሚለው የተሻለ መሆኑን ሐሳቤን ሰነዘርኩ። በወቅቱ አረናና ሲአን ከእኔ ጋር ተመሳሳይ አቋም ሲያራምዱ ነበር። በኋላ ግን የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ እንዲሰበሰብ ተደርጎ መድረክ ሌላ አቋም እንዲይዝ ግፊት ሲደረግ ነበር። መድረክ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲቋቋም አቋም መያዝ አለበት የሚል አቅጣጫ ሲያዝ እኛ እንደማንስማማ ተናግረን ወጥተናል። እኛ ባልተገኘንበት የኦፌኮ፤ የአረናና የሲአን አመራሮች ተሰብስበው ብሔራዊ አንድነት መድረክ ይቋቋም የሚል አቋም መያዛቸውን ገልፀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መጻፋቸውን ሰምተናል። እኛም ልዩነቶች እየሰፉ በመምጣታቸው የመድረክን መጨረሻ ጊዜ ይፍታው ብለን ዝም ብለን ተቀምጠናል።
አዲስ ዘመን:- አቶ ጀዋር የኦፌኮ አባል ሲደረግ በመድረክ ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች ዜናውን የሰሙት ከህዝብ እኩል ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- እውነት ነው። እኛ የአቶ ጀዋርን ወደ ኦፌኮ መቀላቀል የሰማነው ዘግይተን ነው። በእርግጥ መድረክ ውስጥ አባል የሚሆኑት ፓርቲዎች ናቸው ግለሰቦች አይደሉም። አንድ ፓርቲ ግለሰብን አባል አድርጎ ሲቀበል የፓርቲው ውሳኔ ነው እንጂ ሌሎቹን የጥምረቱን ፓርቲ አባላት የማማከርም ሆነ የማሳወቅ ግዴታ የለበትም። መተዳደሪያ ደንቡም ይህንን ነው የሚፈቅደው። ስለዚህም ይህን ግለሰብ ተቀበሉ፤ አትቀበሉ የሚል መብት ማንኛውም ፓርቲ አይኖረውም።
አዲስ ዘመን:- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በበጎም ይሁን በመጥፎ ጉልህ ድርሻ ያለውን ግለሰብ አባል ሲደረግ በጥምረቱ ውስጥ ያሉ ሌሎቹ ፓርቲዎች የማወቅ መብት የላቸውም ወይ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- አሁን ዘወር ብዬ ሳየው መተዳደሪያ ደንቡ ክፍተት እንደላው ይሰማኛል። ዞሮ ዞሮ ግለሰቦች ለአንድ ፓርቲ ዕድገትም ሆነ ውድቀት የራሳቸው የሆነ ሚና ስለሚኖራቸው ፓርቲዎች አባል ስለሚያደርጉት ሰው ማንነት የማሳወቅ ግዴታ ሊኖርባቸው ይገባል ብዩ አምኛለሁ። ይህንን በቀጣይ የምናስብበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን:- እርስዎ በግልዎ የጃዋርን ጉዳይ ለማጣራት ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄደው ነበር፤ ለምንድን ነው የሄዱት?
ፕሮፌሰር በየነ:- የአቶ ጀዋር ጉዳይ እየጎላ ሲመጣና የዜግነቱ ጉዳይ እየተነሳ መከራከሪያ ሲሆን መድረክን ለማዳን ስል ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄጄ ነበር። በኤምባሲው የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊውን በአነጋገርኩበት ወቅትም ጀዋር የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው በግልጽ ነግሮኛል። ስለዚህም ጀዋር የውጭ ዜጋ ነው። አንድ የውጭ ዜግነት ያለው ሰው በሌላው አገር ፖለቲካ ውስጥ ግብቶ እንቅስቃሴ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ስለምረዳ የሚመለከተው አካል አንዳች ውሳኔ እንዲያሳልፍ በግልጽ ተናግሬ ነበር። መንግሥት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት የሰጠው አይመስለኝም፤ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።
አዲስ ዘመን:- ህውሓት ከምርጫ ቦርድ አቋም አፈንግጦ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ የሚተቹም ፤ የሚደግፉም ወገኖች ተስተውለዋል፤ እርስዎ ይህንን እንዴት ያዩታል?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- እኔ ሦስተኛ ዲግሪዬን የሠራሁት በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ነው። እንደባለሙያ ስመለከተው የኮሮና ቫይረስ እጅግ አደገኛ የሆነ ቫይረስ ነው። በዓለም ላይ እንደታየውም ለበርካታ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል። ይህንንም በአግባቡ ስለምረዳ ምርጫው መተላለፍ እንዳለበት እኔም ሆንኩኝ ፓርቲዬ ጽኑ አቋም ይዘናል። ህውሓትን በተመለከተ የሚያሳፍር ነገር ነው እየሰማሁ ያለሁት። ልምድ እንዳለው ፖለቲከኛ ሆነው አላገኘኋቸውም። ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳትና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመዳኘት አሁን እየፈጠሩት ያለውን ጡዘት ማርገብ ይጠበቅባቸው ነበር። ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ ማለት በአሁኑ ዘመን የሚያዋጣ የፖለቲካ አካሄድ አይመስለኝም። አጎንብሶ ማለፍ እኮ ደካማነት አይደለም። ህውሓት አሁን ላይ አገሪቱን የሚጎዳ አክራሪ አቋም ይዞ ተቀምጧል። በሽታው አደገኛ መሆኑ እየታወቀ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለታቸው ህዝብንና አገርን ከመጉዳት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ኮሮና አደገኛ በሽታ ነው።
አዲስ ዘመን:- የህዳሴ ግድብን በተመለከተ አንዳንድ ፓርቲዎች የባንዳነት ባህሪ እንደሚያሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- ጠቅላይ
ሚኒስትሩ ይህንን ቃል
የተናገሩት በምርጫው መራዘም
ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች
ገር ባደረጉት የውይይት
መድረክ ላይ ነበር።
በዚህ ውይይት ላይ
እኔም ነበርኩ። ጠቅላይ
ሚኒስትሩ የተናገሩትን ስሰማ
በጣም ነው የደነገጥኩት።
መቼም መንግሥት መረጃ
ሳይኖረው ዝም ብሎ
አይናገርም። እኔ ያሰብኩት
ካልሆነ ሀገሪቱን አጠፋለሁ፤
እበትናታለሁ የሚል እልህ
ውስጥ የገቡ ፓርቲዎች
ካሉ ግን ለሁላችንም
አደጋ ነው የሚሆኑት።
አሁን ባለው ሁኔታ
ደግሞ ፓርቲዎች የተሻለ
ዕድል ያገኙበት ወቅት
ነው። ቀድሞ ተሰደው
በውጭ አገር ይኖሩ
የነበሩ ፓርቲዎች ሳይቀሩ
አገር ወስጥ ገብተው
የመንቀሳቀስ ዕድል አግኝተዋል።
የተገኘው ዕድል በቀላሉ
የሚታይ አይደለም። ስለዚህም
የእገሌ ፓርቲ ይህንን
ያደርጋል ብዬ ባልጠረጥርም
ጠቅላይ ሚነስትሩ ግን
ዝም ብለው ይናገራሉ
ብዬ አልገምትም። እሳት
በሌለበት ጭስ አይኖርምና።
አዲስ ዘመን:- የዶክተር አብይ አስተዳደር ከመጣ በኋላ ከኤርትራ ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት ተፈጥሯል፡ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የወንድመዎትን የበዛብህ ጴጥሮስን ጉዳይ ለመጠየቅ አልሞከሩም ?
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- በተለያዩ ደረጃዎች ጥያቄዬን ሳቀርብ ቆይቻለሁ። ነገር ግን ምንም ተጨባጭ ምላሽ አላገኘሁም። የእኛ ባለሥልጣናትም ከኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ቢገናኙም ጉዳዩን የማንሳት ፍላጎት እንደሌላቸው ተረድቻለሁ። ስለዚህ ስለበዛብህ የማውቀው ነገር የለም። በቃ ይሄ ነው፤ በአጭሩ።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ:- እኔም ስለሰጣችሁኝ ዕድል አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
እስማኤል አረቦ