ኮሮና ቫይረስ በቻይናዋ ኡሀን ከተማ ተከሰተ ከተባለበት ወቅት ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሁኔታ የተለየ መልክ ይዟል። በመሆኑም ዓለም ከመሰንበቻው ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ ለመኖሩ ነጋሪ የሚያሻን አይመስለኝም። አገራችንም የዚህ ወረርሽኝ አካል በመሆኗ በተለየ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። በሽታው የአገራትን የጤና ሁኔታ ከመፈተን ባለፈ ዘርፉን ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል። ሁኔታው ከጤና ዘርፍ ባለፈም ኢኮኖሚን በማሽመድመድ ዘላቂ አደጋ እንዳይሆን የየአገራቱን መሪዎች የፈተነም ሆኗል።
የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ የተለየ የሚያደርገው ምን ነገር ይኖር ይሆን ብለን መጠየቃችን ተገቢና ወቅታዊ ይሆናል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ ልዩ ስብሰባውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይ ደግሞ የወጪ ንግድ እና የፋይናንስ ዘርፉን የኮረና ዱላ እንዳይበረታበት መንግስት ምን ሰራ? ምንስ ለውጥ አመጣ? የሚሉት ጉዳዮች የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ይሆናሉ።
መንግስት ኢኮኖሚውን በኮረና ወቅት መምራት ከፈተናው ይልቅ ውጤቱ ሁሉንም ያጓጓ ሆኗል። እነዚህን ጉዳዮች በተለይ ከምክር ቤቱ አኳያ መመልከት ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን ዘጠኝ በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ይህን ያህል ለማሳደግ የተያዘው እቅድ ኮረና ባስከተለው ፈተና ምክንያት በዚህ ልክ ማደግ እንደማይችል መንግስት በቂ ግንዛቤ ይዟል ብለዋል። ቢሆንም ኢኮኖሚው ቢያንስ ቢያንስ ስድስት በመቶ ያድጋል በሚል እቅድ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል።
ኢኮኖሚዋ በዚህ ልክ ያድጋል የምትባል አገር ባለችበት ሁኔታ ከ170 በላይ አገራት እድገታቸው ቁልቁል እንደሚሆን ደግሞ የአለም ባንክ አስታውቋል። ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን እድገት ስድስት በመቶ ያድጋል አላለም እንጂ ከሶስት በመቶ በላይ እድገት እንደምታስመዘግብ አረጋግጧል። እናም በኮረና ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እድገት ሊመጣ ቻለ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተውታል።
‹‹ምን የተለየ ስራ ስለሰራን ነው ትንሹም ትልቁም ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ባለበት ኢትዮጵያ እንዴት እድገት ልታመጣ ቻለች›› የሚለው ጥያቄ ተፈጥሯል ብለዋል። እድገቱ እውነተኛ እና ተጨባጭ ለመሆኑ ምክንያቶችንም አስቀምጠዋል። በጀት አመቱን በሐምሌ ወር መጀመሩና ዘመን አቆጣጠሩ ከሌሎች አገራት የተለየ በመሆኑ ከሐምሌ እስከ መጋቢት ለስምንት ወራት በኤክስፖርት ገቢ በእያንዳንዱ ወር ከ100 ፐርሰንት በላይ እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዳመለከተው በሚያዚያ ወር ከወጪ ንግድ 329.3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብሏል። በ2012 በጀት ዓመት በሚያዚያ ወር ከግብርና ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ፣ ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ እና ከሌሎች ምርቶች 365.1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተከናወነው 329.3 ሚሊዮን (90%) የአሜሪካን ዶላር መገኘት የተቻለው ብሏል።
ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተገኘው 249.5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ79.8 (32%) ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስረዱት፣ ኮሮና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ያመጣው ባለፉት አራት ወራት ብቻ ሲሆን፤ ስምንቱ ወር በታሰበው እና በታቀደው ልክ መልካም የሆነ እድገት እየተመዘገበ ቆይቶ አራቱ ወሮች እንደሌሎቹ አገራት ባይሆንም ፈተና ስለገጠማቸው በተወሰነ ደረጃ ከእድገት እቅዱ መቀነስ ችሏል ይላሉ።
የአለም የንግድ ስርዓት በእጅጉ የተሳሰረ በመሆኑ አንዱ ጋር ያረፈ ዱላ ብዙዎቹ ሳያስቡት የሚጎዳቸው በመሆኑ በተለይ ኢኮኖሚያቸውን ክፉኛ አጥቅቷል። በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን መልኩ የተለየ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት ከዓለም ጋር የተሳሰረው 30 በመቶ ብቻ ነው ያሉት ዶክተር አብይ ‹‹ዓለም ላይ የሚያርፈው ዱላ እኛ ጋር ዝቅ ያለ ነው። ዱላው አልቀረም፤ ነገር ግን በትስስሩ ውስንነት ምክንያት የሚያርፍብን ዱላ በዚያው ልክ ያነሳ ነው፤›› ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚያው እድገት ውስጥ ትልቁ ጉዳይ የፋይናንስ ዘርፉ ነው። ይህ ዘርፍ አልተመታም፤ እንዲያውም እድገት አስመዝግቧል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለአብነት የእስቶክ ገበያ በትሪሊየን ወደቀ ሲባል፤ ስቶክ ገበያ ውስጥ የሚሳተፉና የተሳሰሩ የፋይናንስ ዘርፎች በሙሉ ይህ አደጋ ያጠቃቸዋል። የእስቶክ ገበያ በመውደቁ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጥቃት አያገኛትም፤ በግለሰብ ደረጃ ግን ሊኖር ይችላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የካፒታል አካውንቱ ክፍት አይደለም፤ ሪከረንት አካውንቱ ብቻ ነው ክፍት የሆነው። ካፒታል አካውንት ክፍት ባለመሆኑ ሰዎች የአለም ኢኮኖሚ ሲናጋ የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ሊያወጡ አይችሉም። ይህ አካውንት እስከአሁን ባለው ሁኔታ ዝግ ነው፤ ክፍት አይደለም ብለዋል። ኢትዮጵያ በሪከረንት አካውንት ነው እየሰራች ያለችው። በዚህም ምክንያት የፋይናንሺያል ዘርፉ ሊደርስበት የነበረው ጥቃት ለጊዜውም ቢሆን ለመከላከል አስችሏል።
‹‹ባለፉት አስር ወራት ከአስቀማጭ የተሰበሰበ ገንዘብ/ሴቪንግ/ በሁሉም ንግድ ባንኮቻችን 87 ቢሊየን ብር ነው። ይህን የሰበሰቡ ባንኮች አጠቃላይ እድገታቸው ሲታይ በቁጠባ ብቻ 17.4 በመቶ እድገት ተመዝግቧል። ይህን ያህል እድገት ተመዝግቧል ማለት ለኢንቨስትመንት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በመሆኑም የተመለሰ ብድር 38 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 14 በመቶ እድገት አለው። ባንኮች ባለፉት አስር ወራት ሲታይ ደግሞ 221 ቢሊየን ብር አበድረዋል።›› ዶክተር አብይ ይገልፃሉ።
በዚህ ምክንያት ብድር 24 በመቶ እድገት አለው። በመሆኑም ቁጠባ አድጓል፤ የተሰበሰበ ብድር አድጓል፤ የተሰጠ ብድርም እንዲሁ እድገት አለው። የፋይናንስ ዘርፉ ከእነዚህ ውጭ ሌላ ወሳኝ አመላካች አለው፤የተበላሸ ብድር። ጤነኛ የሆነ ብድር መሆኑን የሚያረጋግጥ ማለት ነው። የተበላሹ ብድሮች የባንኮችን ጤነኛነት የሚፈታተኑ በመሆናቸው ትኩረት ማድረግ ይገባል። ዘንድሮ የባንኮች የተበላሸ የብድር መጠናቸው ሶስት በመቶ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በአራት በመቶ ቀንሷል። ይህ በባንኮች ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ አሀዝ ነው። የተበላሸ ብድር መጠን ባነሰ ቁጥር የፋይናንስ ዘርፉ ጤንነት እና ደህንነት ይረጋገጣል ባይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ያለው የተበላሸ ብድር ሁለት በመቶ ነው። ባለፉት አስር ወራት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 43 በመቶ የሚሆነው የተበላሸ ብድር ተስተካክሏል። ከፍተኛ የተበላሸ ብድር ያለው ልማት ባንክ ነው። ይህ ባንክ በአሁኑ ወቅት 37 በመቶ ድረስ የተበላሸ ብድር ያለው ሲሆን ዘንድሮ 13 በመቶ ቀንሷል። በድምሩ ሲታይ የፋይናንስ ዘርፉ በከፍተኛ እድገት ውስጥ ነው ያለው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ኮሮና እያለ ይሕ እድገት እና የፋይናንስ ዘርፉን መታደግ እንዴት ተቻለ? ለሚለው ‹‹ይህ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። በዘርፉ ወሳኝ የተባሉ ውሳኔዎች እና እርምጃዎች በመወሰዳቸው ነው›› ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ለዚህም የተለያዩ ተግባራትን ያነሳሉ። አንደኛ ባለፉት አመታት ከግል ባንኮች ቦንድ የሚባለውን መንግስት አስቀርቷል። ሁለተኛ ቦንድ ሲሰበሰብ የተከማቸ ገንዘብ በተወሰነ ደረጃ ለግል ባንኮች ፈሰስ አድርጓል። ለምሳሌ ከኮረና በኋላ 48 ቢሊየን ብር ነው ብሔራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች ያፈሰሰው።
የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥም የተለቀቀው ገንዘብ ብዙ አደጋዎችን በተወሰነ መልኩ አስቀርቷል ብለው፤ ይህ የባንክ ስርዓቱን በተለይ ሊፈትነው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለም። ከዚህ በተጨማሪ አነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት እንዳይጎዱ በዘርፉ ለሚሰሩ ባንኮች በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ተመድቧል። በዚህም ብድር ተስተጓጉሎ ትናንሽ የቢዝነስ ተቋማት እንዳይጎዱ ተሞክሯል።
ከዚህ በተጨማሪ ላለፉት አመታት ግብር ባለመክፈል በቅጣት በወለድ ምክንያት ከፍተኛ እዳ ያለባቸው የንግድ ተቋማት 78 ቢሊየን ብር የሚደርስ ገንዘብ ቀድሞ የተከማቸን እዳ ሰርዟል። በዚህም ለጤና አምስት ቢሊየን ብር፤ ለጥቃቅን እና አነስተኛ የተመደበውን ሲታይ በጣም በርከት ያለ ገንዘብ መንግስት ኢኮኖሚውን ለመታደግ ብዙ እንደሰራ ያሳያል። እነዚህ እርምጃዎች አንዳንድ ዘርፎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ዘርፎችን ከአደጋ በመታደግ አግዘዋል።
‹‹ከእነዚህ በተጨማሪ በጣም የረዳን ኤክስፖርት ነው። ይህ ዘርፍ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አምና ድረስ እያሽቆለቆለ ነበር። በእየአመቱ ያለው እድገት ካለፈው አመት ያነሰ ነው። በዚህ አመት መጀመሪያ ክቡር ፕሬዚዳንቷ ለተከበረው ምክር ቤት ንግግር ሲያደርጉ አንዱ በአንክሮ ያነሱት ጉዳይ ኤክስፖርትን ማሻሻል እና ወደ እድገት ማስገባት ነበር። የማክሮ ኢኮኖሚው ቡድንም በከፍተኛ ትኩረት ሲሰራ የነበረው የግብርና ኤክስፖርት ላይ ነበር። በዚህም ኤክስፖርቱ 13 በመቶ አድጓል፤››ሲሉ አመልክተዋል።
ባለፉት አስር ወራት የኤክስፖርት መጠን 13 በመቶ አድጓል። እድገቱን ካፈጠኑት ጉዳዮች አንዱ ኮረና ነው። ኮሮና ዘርፉ እንዲሻሻል ትልቅ እድል ፈጥሯል። ለአብነት ቡና 667 ሚሊየን ዶላር ባለፉት አስር ወራት ተሸጧል። በዚህም የቡና ዘርፉ 16 በመቶ እድገት አሳይቷል። ለምን ቢባል ፍላጎት ጨምሯል ዋጋም ጨምሯል። በዚህም በተፈጠረው ችግር አብዛኛውን አገራት እያመረቱ አይደለም። የገበያ ትስስሩም በመቀነሱ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ሁሉ ምርቱን ለማቅረብ ጥረት በማድረግ የተሳካ መሰራቱን አስገንዝበዋል።
‹‹በኮረና ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ከደረሰባቸው ዘርፎች ውስጥ የአበባ ዘርፍ አንዱ ነው። ይህ ዘርፍ ባለፉት አስር ወራት 440 ሚሊየን ዶላር ኤክስፖርት አድርጓል። ማመን በሚከብድ ሁኔታ 84 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ምክንያቱ ብዙ ነው። ኤክስፖርታችን ግን ከፍ ያለ ነገር እንዲያመጣ ኮረና ረድቷል። ስጋ 45 ሚሊየን ዶላር ገቢ አስመዝግቧል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዳሉ።
ይህ ዘርፍ እድገቱ 21 በመቶ ነው፤ ነገር ግን የስጋ ፍላጎት በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ በማደጉ በመንግስታት ደረጃ ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ ሆኗል። ጥራት ያለው ስጋ ማቅረብ በተቻለ ቁጥር ከፍተኛ ፍላጎትና ገቢ የታየበት የኮረና ወቅት ነው። ሆኖም ግን እጅግ ድንቅ የሆነ አየር መንገድ ስላለን የኤክስፖርት እድገቱ ከፍ ብሏል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ እንደሚታወቀው ወርቅ በኮንትሮባንድ እና ተያያዥ ምክንያቶች ዋጋው እያሽቆለቆለ ነበር። ኮረና ከመጣ ከሶስት ሳምንት ገደማ 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ነው ተጠባባቂ ክምችት የተያዘው። 27 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ ብሄራዊ ባንክ የገባ ሲሆን 19 በመቶ እድገት አለው። በድምሩ የኢትዮጵያ ኤክስፖርት 13 በመቶ ከማደጉ በላይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የነበረው ማሽቆልቆል ተቀልብሷል። ከዚያ ኮረና አግዟል። ዘርፉ ወደ እድገት መስመር የገባው ለአሁን ብቻ አይደለም፤ የገበያ ትስስር እና እምነት ፈጥሯል።
ነዳጅን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ረገድ ዋጋው ቀንሷል። በዚህም ኢትዮጵያ በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ዶላር አትርፋለች። ከዚህ ቀደም ምርት ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የአገሪቱን ወገብ የሚያጎብጠው ነዳጅ ነበር። አሁን ዋጋውም ሲቀንስ ለዚህ ተብሎ የተያዘውን ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ እናውለዋለን። ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ እንደ ማዳበሪያ መድሃኒት በተለይ ለምርት ግብዓት የሚሆኑት ዋጋቸው አልቀነሰም ጨምሯል። በውጭ ምንዛሬ ወይም በኮረና ምክንያት ወሳኝ የሆነው የግብርና ግብዓት አልቀረም ብለዋል።
ኮረና በከፍተኛ ሁኔታ በኢኮኖሚው ውስጥ የጎዳው ዘርፍ ቱሪዝም ነው። ቁጥሩ ምንም ይሁን ምንም ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገልግሎት ዘርፉም ተጎድቷል። ሆቴሎችና ትራንስፖርት ተጎድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ቀንሷል። ይህም በእየ አገሩ ያሉ ዜጎች ስራቸውን እያጡ ስለሆነ ይህን ማድረግ አልተቻለም። በመሆኑም ኮረና ድል ብቻ ያመጣ፤ ምንም ችግር የሌለው ሳይሆን በአንዳንድ ዘርፎች ላይ አደገኛ ምት ያሳረፈ፤ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ ደግሞ ውጤት ያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮረና በአገልግሎት እና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያሳደረው ጫና እንዳለ ሆኖ በቀጣይ አገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ኮረና ካለፈ በኋላ ሊጎበኙ የሚችሉ አገራት ውስጥ ምቹ ናት ተብላለች። ይህ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ‹‹አዲስ አበባ ብቻ ከዩኒቲ ፓርክ ውጭ የወንዝ ማልማት ፕሮጀክቱ፣ የእንጦጦ ፓርክ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችል በየትኛውም የአለም አቀፍ ደረጃ የጥራት ደረጃው የማያሳፍር ፤ የተናገርነውን፣ ያቀድነውን መተግበር እንደምንችል ያሳየንበት ለኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነ በፍፁም መመዘኛ ምርጥ ስራ የሆኑ ማረጋገጫዎች ተከናውነዋል። እነዚህ ገና በመገናኛ ብዙሀን አልተዋወቁም። የምክር ቤት አባላት በመዲናዋ ያሉትን ፓርኮች እንድትጎበኙ እጋብዛለሁ›› ብለዋል።
በአጠቃላይ ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳስታወቁት ኮረና በኢኮኖሚው ዘርፍ ሁለት መልኮችን አሳይቶናል። አንደኛው በወረርሽኙ ምክንያት ክፉኛ የተመቱ ዘርፉች ያሉ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ገቢያቸው እና አቅማቸውን በመጠቀም የእድገት ኮሪደር በመሆን ሰፊ እድል የተከፈተላቸው ዘርፎችንም መመልከት ተችሏል። ሁለቱንም መልኮች እንዳሉ ተረድቶ ብልህነት የተሞላበት አመራር ደግሞ ችግሩን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ህዝብን ከበሽታው፤ ኢኮኖሚውንም ከውድቀት መታደግ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ሀብታሙ ስጦታው