ሕይወትዎን ለማዳን ሕይወታቸውን ለሚከፍሉ፣ ልጆችዎ እንዳይበተኑ ልጆቻቸውን ለአደጋዎች አጋልጠው ለሚኳትኑት ጤና ባለሙያዎች አስበው ያውቃሉ? አዎ ባለሙያዎቹ ጦርነት ላይ ናቸው። እነሱ የጦርነቱን ድል እንዲቀዳጁ የእርስዎን በቤት መቀመጥ ይሻሉ። ለእርስዎ ጤና ሲሉ ጤናቸውን ለሚያጡ ማግለሉም ሆነ ሰላማዊ ኑሯቸውን ማናጋት ጦሱ ለራስዎ፣ ለቤተሰብ እና ለአገርዎ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ ቢያንስ አራት ዶክተር፣ ነርስ፣ አዋላጅ ሐኪምና የጤና ባለሙያ ለአስር ሺ ሕዝብ ያስፈልጋል። አሁን ያለበት ደረጃ ግን ከአንድ በታች ነው። ይሄ በመደበኛ አገልግሎት ጊዜ እንጂ በወረርሽኝ ጊዜ ከዚህም በላይ መሆኑ አይቀርም። የጤና ባለሙያዎች ቁጥር በእጅጉ አናሳ በሆነባት አገር በሰፊው ለችግሮች እንዲጋለጡ ማድረግ የኮሮና ተህዋስ የመከላከል ሂደቱን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል።
የጣልያን የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከል ጦርነት የከፈሉት መስዕዋትነት የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የፊት፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛውን ከፊታቸው ላይ የሚያነሱበት ጊዜ በማጣታቸው ለረዥም ሰዓት ይለብሱታል። በዚህ የተነሳም ፊታቸው እስከ መላላጥ ደርሶ ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም ያደረጉት ተጋድሎ በመንግሥታቸው ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አስመስግኗቸውም ነበር። እየዋለ ሲያድር የጤና ባለሙያዎቹ አስታዋሽ ማጣታቸውንም አልደበቁም። የተፈጠረባቸውን ስሜት ለዓለም መገናኛ ብዙኃን እንዲህ ተርከውት ነበር።
ፓውሎ ሚራንዳ በጣልያን ሎምባርዲ የጽኑ ሕሙማን ክፍል ነርስ ነው። ‹‹ብስጩ ሆኛለሁ። ከሰው ጋርም እጋጫለሁ። የደረሰብንን መቼም ቢሆን መዘንጋት አልፈልግም። ከጠላት ጋር እየተዋጋን ነበር። አሁን መለስ ብዬ ለማሰብ ጊዜ ሳገኝ አቅጣጫ ቢስነት ይሰማኛል። ቁስለኛ ሆኛለሁ። ›› ሲል ስሜቱን አጋርቷል።
‹‹ያየሁት ሁሉ አብሮኝ ይኖራል፤ መተኛት አልችልም፤ በክፉ ቅዥት እሰቃያለሁ፤ በየሌሊቱ ልቤ በየደቂቃው እየመታ ትንፋሽ አጥሮኝ እባንናለሁ›› ያለችው የጽኑ ሕሙማን ክፍል ነርስ ሞኒካ ማሪዎቲዎ ነበረች።
ጥናቶች እንደሚያሳዩትም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክፉኛ በተጠቁት አካባቢዎች ይሰሩ የነበሩ 70 በመቶ የሚሆኑ የጣልያን ነርሶች አሁን ላይ ተዳክመዋል። የጥናቱ ጸሐፊ ዶክተር ሰሪና ባሬሎ ‹‹ይህ ወቅት (ከሕክምና ግብግቡ በኋላ ያለው) ለዶክተሮችና ለነርሶች ከባድ ነው›› ትላለች።
የሰው ልጆች አደጋ ውስጥ ሲሆኑ ጭንቀትን መቆጣጠር የሚያስችል ንጥረ ነገር በአካላቸው ይመረታል። ሆኖም ግን ያሳለፈውን ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜ ሲያገኝ ጭንቀት ሊከተል እንደሚችል ታስረዳለች።
ብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ከአደጋው በኋላ የሚመጣ ጭንቀት ሊገጥማቸው ይችላል። በሥራቸው ላይ የማተኮር ችግርም ሊደርስባቸው እንደሚችል አጥኝዋ ትጠቁማለች።
ከወረርሽኙ የታማሚዎችን ሕይወት ለማትረፍ በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን ሕይወት የሚያጡት የሕክምና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከወረርሽኝ ሕይወት ለማዳን በሚያደርጉት ትንቅንቅ የተነሳ 23 ሺ የጤና ባለሙዎችና ሠራተኞች የበሽታው ተጠቂ መሆናቸውን ገልጿል። ጀኔቭ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የነርሶች ምክር ቤት (International councel of Nurses) በበኩሉ ከማህበሩ አባላት፣ከሚዲያዎች፣ ከመንግሥት አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት 90 ሺ የጤና ሠራተኞች በወረርሽኙ መያዛቸውን በሰኔ ወር መባቻ አስነብቧል። በዚህ ሳቢያም 260 ነርሶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለዚህ ችግር ያጋለጣቸውም የቅድመ ዝግጅት ማነስና ራሳቸውን የመጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት በመኖሩ እንደሆነ ማረጋገጡን በምክንያትነት ጠቅሷል።
በኢትዮጵያም የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የዚህ ዕጣ ፈንታ ሰለባ ከመሆን አላመለጡም። እስከ አሁን ባለው ሂደት 97 የሚሆኑ የጤና ሠራተኞች የኮሮና ወረርሽኝ ተህዋሲው እንደተገኘባቸውም ታውቋል። በመሆኑም የጤና ተቋማትና ሠራተኞቻቸው በሽታውን በመከላከል ሂደት በእጅጉ ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው። መንግሥት ለሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ቢሆን የምርት እጥረት እንዳለና በቂ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ከትዝብታቸው ይናገራሉ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ተድላ ከበደ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር፣ የውስጥ ደዌና የሆርሞን ሐኪም እንዲሁም መምህር ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚጠብቁባቸው ቁሳቁሶች እንደየተጋላጭነት ደረጃቸው እየተለዩ በሁሉም ደረጃ በተለያየ መጠን በበቂ ሁኔታ ሊቀርቡላቸው ይገባል። እርሳቸው በሚሰሩበት ሆስፒታልም ቢሆን በበቂ መጠን ተዳርሷል የሚባል እንዳልሆነ ከየዕለቱ ትዝብታቸው ያስረዳሉ። ችግሩ የሚስተዋለው በበቂ ደረጃ የአቅርቦት ችግር በመኖሩ ይሁን በሎጅስቲክስ ሥርጭት ችግር ስለመሆኑ መጠየቅ፣ማነጋገርና ማጣራትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛውም በኮቪድ 19 መከላከል ላይ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች የቁሳቁስ እጥረቶች መኖራቸውንና በበቂ ሁኔታ እየቀረቡላቸው እንዳልሆነ ይስማሙበታል። ወረርሽኙ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በተለይም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ የሚነሱና የሚቀርቡ ጥያቄዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። በቂ የሆኑ ራስን የመጠበቂያ ቁሳቁሶችና ግብዓቶች እንዳልተሟሉላቸው እየገለጹም ይገኛሉ ነው ያሉት።
በሕክምና ተቋማት የሚገኙ ባለሙያዎች ከታች እስከ ላይ ድረስ ራስን መጠበቂያ ቁሳቁሶቹ ያስፈልጓቸዋል። ታካሚው ገና ከበር ሲገባ ከሚያገኘው የጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ የተጋላጭነት ችግር ሊከሰት የሚችል በመሆኑ መከላከያውን የግድ ማግኘት ይገባዋል። የመከላከያው ዓይነትና ደረጃ የሚለያይ ቢሆንም በጤና ተቋማት የሚሰሩ በየትኛውም ሁኔታ ከሕመምተኛ ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ የመከላከያ አልባሳትና ቁሳቁሶች እንደሚያስፈልጓቸው ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የሕክምና ማህበር ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት ሐኪሞችና ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን በማህበረሰቡ ቦታ አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል። በዚህ ሂደት ከእነርሱ የሚጠበቀው ሩህ ሩህና አዛኝ መሆን ነው ይላሉ። ኅብረተሰቡ ከፈጣሪ በታች ያድነኛል ብሎ እምነቱን የሚጥለው በጤና ባለሙያዎችና በሐኪሞች ላይ ነው። ስለዚህ የሙያው ሥነምግባር የሚጠይቀውን በሙሉ በመላበስ ለታካሚዎች ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል። ጥሩ ምሳሌ መሆን ተገቢ ነው። ‹‹የእኔ ሕይወት ያሳስበዋል? እየጣረልኝ ነው?›› ብሎ ታካሚው ማሰቡ አይቀርም። ለዚህ መልስ ሊሰጥ የሚችል እንክብካቤ ከባለሙያዎች ማግኘት አለበት። ይህ ሲሆንና ርህራሄ ሲያሳዩ በኅብረተሰቡ ዘንድ ይከበራሉ፤ ይታዘንላቸዋል። ‹‹ባለሙያዎቻችን ጭምር እንዳናጣ›› ብሎ የሚጨነቅ ማህበረሰብ ይፈጠራል።
በጤና ባለሙያነት ውስጥ የሚገኘው ትልቁ ሽልማት ሰውን በማገልገል የሚገኝ ርካታ ነው። ስለዚህ ሰዎች ክብር የሰጡ መስሎ ካልተሰማህ በእንደዚህ ዕረፍት የለሽ፣ አስጨናቂ፣ እንቅልፍ የለሽ፣ ማህበራዊ ሕይወትን የሚጎዳ፣ ራስንም ለበሽታ አጋልጦ የሚሰጥ ሁኔታ ውስጥ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። ስለዚህ ማህበረሰቡ ሥራቸው ምቹ እንዲሆን፣ ኑሯቸው ጥሩ እንዲሆን ካላደረ፣ የሚርቃቸውና የሚያገልላቸው ከሆነ ተጎጂው ራሱ እንደሆነ ያስረዳሉ። መንግሥትም በዚህ ደረጃ ለባለሙያዎች ኑሮና ሕይወት ማሰብ ይገባዋል። የተሟላ ግብዓት ሊቀርብ ይገባል። ምቹ ሁኔታ መፈጠር አለበት። አመራሩ ችግራቸውን ሊረዳና ሊደግፍና ችግሮቹን ሊቀርፍ እንደሚገባ ለሚዲያዎች ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የሕክምና ባለሙያዎች ጤናማነት በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜ ወሳኝ ነው። በመሆኑም ማህበረሰቡ ችግራቸውን ሊካፈላቸው፣ሊያዝንላቸው እና ቢያንስ ለምን የሚሉንን አንሰማም ማለት አለበት። ባለሙያዎች ይሄ ችግር አለብን ሲሉ እንዴት እንርዳቸው ሊል ይገባዋል። በፍጹም ማግለል ሊፈጠር አይገባም። መንግሥትም አስፈላጊውን ችግራቸውን ተመልክቶ ቅን ምላሽ መስጠት አለበት። በመተጋገዝና በመደጋገፍ ከዚህ ወረርሽኝ ማምለጥ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ሙሐመድ ሁሴን