እኛም በዛሬው እትማችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት የሂውማኒቲስ፣ የቋንቋዎች ጥናት፣ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል “ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት በደራሼ ብሔረሰብ” በሚል ርዕስ በዳንኤል ደጀኔ በ2009 ዓ.ም ለኤም.ኤ.ዲግሪ ማሟያነት የቀረበ ጥናትን ዋቢ በማድረግ የብሔረሰቡን የግጭት ምክንያቶች፣ ዓይነቶችና የግጭቱን መፍቻ መንገዶችና ተቋማትን በመጠኑ እንዳስሳለን። የዚህ ስርዓት እውን መሆን በብሔረሰቡ ውስጥና ብሔረሰቡ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለሚኖረው ሰላማዊ መስተጋብር የሚያበረክተውን አዎንታዊ ሚና ጥናቱን ዋቢ በማድረግም ለማመላከት እንሞክራለን። ይሄንንም በሚከተለው መልኩ ለንባብ እንዲመች አድርገን አቅርበነዋል።
የደራሼ ብሔረሰብ የሚገኘው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዷ በሆነችው ደራሼ ወረዳ ሲሆን፤ የወረዳው ዋና ከተማም ‹‹ጊዶላ›› ትባላለች። በማእከላዊ ስታስቲክስ መረጃ መሰረትም የደራሼ ህዝብ 91 በመቶው በገጠር ዘጠኝ (9) በመቶው ደግሞ በከተማ የሚኖሩ ናቸው። የደራሼ ወረዳ ተራራማ፣ ሜዳማ እና ረባዳማ መልከዓ ምድር ያላት ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ስፋቷም 40 በመቶ ቆላ፣ 35 በመቶ ደጋ እና 25 በመቶ ደግሞ ወይና ደጋ የአየር ጸባይ አላት።
የደራሼ ብሔረሰብ ቋንቋ ‹‹ዱራይታት›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ይህ ቋንቋ የብሔረሰቡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። የብሔረሰቡ አባላት ከዚህ ቋንቋ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ዶርዚኛ፣ ኮንሶኛና አማርኛን ይናገራሉ። በደራሼ አካባቢ የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና የሙስሊም እምነት ተከታዮች ይገኛሉ። የብሔረሰቡ ዋንኛ መተዳደሪያ እርሻ ሲሆን፤ የእርሻ ስራውን የሚያከናውነው ‹‹ፓውራ›› በተሰኘ ባለሁለት አፍ የዕጅ መሳሪያ ነው። በበሬ ማረስ አልፎ አልፎ የሚታይ እንጂ ቀዳሚ የእርሻ መሳሪያነት የሚጠቀስ አይደለም። ይህን መሳሪያ በመጠቀም በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ስንዴ የመሳሰሉት የእህል ዘሮችን ያመርታሉ። ብሔረሰቡ አብዛኛውን የእርሻ ስራ የሚያከናውነው በቡድን ሲሆን፤ የእርሻ ስራ ከመጀመሩ በፊት ከብት በማርባት ይተዳደር እንደነበረ ይነገራል። አሁንም ቢሆን የከብት እርባታን ከእርሻ ስራ ጎን ለጎን በገቢ ምንጭነት ይጠቀሙበታል።
በአመዛኙ በእርሻ ስራ የሚተዳደረው የደራሼ ብሔረሰብ ሶስት ሀገር በቀል (ኢንዲጂኒዬስ) የእርሻ ጥበብ አለው። እነዚህም የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የእህል ዘርን ለረጅም ጊዜ ማቆየትና የእርሻ ስራውን የሚያከናውንበት ባህላዊ የቀን /ወቅቶች/ መቁጠሪያ ናቸው። በተለይም የአካባቢውን የአፈር መሸርሸር ለመግታት የእርከን ስራ በመስራትና አፈራርቆ በመዝራት ‹‹ታሪጋ›› እና ‹‹ፓታይ›› በተባሉ ባህላዊ የአፈር ጥበቃ ዘዴ ምርቱን ያመርታል። ያመረተው ምርት እንዳይበላሽ ‹‹ፓውላ›› የተሰኘ ጥልቅ የእህል ጉድጓድ በመቆፈር እንደጎተራ ምርቱን በጉድጓዱ ውስጥ በማስቀመጥ ለረዥም ጊዜ እንዳይበላሽ የሚያደርግበት ዘዴ አለው።
የደራሼ ብሔረሰብ ትውልድን የሚቀርጽበት ወግና ባህልን የሚጠብቅበት ባህላዊ የማስተማሪያ ጥበቦች አሉት። እነዚህ ባህላዊ የስነ-ምግባርና የሞራል ማስተማሪያ ጥበቦች ከብሔረሰቡ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅርና ከረጅም የሕይወት ልምድ ፍልስፍና የሚቀዱ ናቸው። የደራሼ ብሔረሰብ በዚህ መልኩ ከሚገለጹ የእውቀት ጥበቦቹ በተጓዳኝ፤ በአብሮነትና ትብብር ጉዞው የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን፤ ካልሆነም ከማህበራዊ እሴቶቹ አፈንግጠው በሚታዩ ግድፈቶች ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶችን አርሞ የሚያርቅበት፣ ገስጾ የሚፈታበት የራሱ የሆነ ባህላዊ እሴት ያለውም ነው። ግጭቶቹ በጠለፋ፣ በሰው እርሻ ላይ ሆን ብሎ እሳት መልቀቅ፣ ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር በሚኖር ግንኙነት፣ ከብት በሌላኛው ብሔረሰብ እርሻ ውስጥ ገብቶ በመብላት፣ በነፍስ ማጥፋት፣ በይዞታ ይገባኛልና መሰል ምክንያቶች የሚከሰቱ ናቸው።
በብሔረሰቡ ተዘውትረው የሚፈጠሩ ግጭቶች የጎሳ ግጭት፣ ከአጎራባች ብሔረሰቦች (ከአላ፣ ኮንሶ፣ ዘይሴ) ብሔረሰቦች ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶች፤ እና የነፍስ ግድያ ግጭት ናቸው። የእነዚህ ግጭቶች መነሻ ምክንያት ተብለው የሚጠቀሱት ደግሞ ድንበር መግፋት፣ በሰው ንብረት ላይ ሰደድ እሳት መልቀቅ፣ መካካድ(ክህደት) መሆናቸው ናቸው። ብሔረሰቡ እነዚህን ግጭቶች የሚፈታበት አራርሳ (ሆሮታ) ተብሎ የሚጠራ የግጭት መፍቻ ሥርዓት ያለው ሲሆን፤ የግጭት መፍቻ ተቋማቱ ደግሞ የቤተሰብ መሪ (ኦስማረ)፣ ሻና፣ ሼላ፣ ፓልዳ እና በንጉሱ (በዳማው) የአራፋይታ ችሎት ናቸው። ግጭቶቹም የሚፈቱት በሽምግልና፣ በዳኝነትና በእርቅ ሥርዓት መሆኑን በዚህ ጥናት ተቀምጧል።
በመሆኑም የደራሼ ብሔረሰብ እነዚህን ግጭቶችና አለመግባባቶች የሚፈታበት የራሱ ጥንታዊ የሆነ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር አለው። እነዚህ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅሮች በአራት ዋና የባህላዊ አስተዳደር ምሰሶዎች ማለትም በዳመ፣ በፓልዳ፣ በሼላ እና በሻና ተብለው በሚጠሩ መሪዎች የቆሙ ናቸው። እነዚህ አራት ዋንኛ ባህላዊ (የአስተዳደር መዋቅሮች) በየውስጣቸው እንደ ማህበራዊ መሠረታቸው የሚያቅፏቸው ንዑስ የአስተዳደር መዋቅሮች አሏቸው። የትኛውም ዓይነት ግጭት የሚፈታውም ይሁን ዳኝነት የሚሰጠው በእነዚህ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅሮች ነው።
የደራሼ ንጉስ (ዳማ) በደራሼ ብሔረሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የበላይ መሪ ነው። የጎሳ መሪዎች በዳማው ውስጥ የታቀፉ ናቸው። የዳማው ስልጣን እምነታዊ እና አስተዳደራዊ ይዘት አለው። ይሁን እንጂ እምነታዊ መሪነቱ ጎልቶ የሚታይ ነው። በደራሼ ብሔረሰብ ‹‹ዳማው›› ዝናብ ያዘንባል አካባቢውንም በልምላሜ ይሞላል የሚል ፅኑ እምነት አለ። ዳማዎች ከሌላው ማህበረሰብ የሚለያቸው የስልጣን መገለጫ ምልክት አላቸው። ይህ የስልጣን መገለጫ ምልክት ‹‹ሚጫራ›› ይባላል።
በዳማው የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ‹‹አራፊይታ›› የንጉስ ችሎት መሪዎች ይገኛሉ። የዳማውን አጠቃላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉ እነዚህ መሪዎች ናቸው። የትኛውም የህብረተሰቡ ጉዳዮች ከበታች መሪዎች እንደ ፓልዳ፣ ሼላና ሻላ የመሳሰሉ መሪዎች ጋር በመገናኘት ወደ ንጉስ /ዳማው/ በማድረስ ውሳኔ ማሰጠት በእነሱ አቅም የሚፈቱ ካሉ የመፍታት ስልጣን አላቸው።
የጎሳ አለቃ (ፓልዳ) በደራሼ ብሔረሰብ የአንድ ጎሳ መሪ ወይም አለቃ ነው። የመሪነት ሚናው አስተዳደራዊና አምልኳዊ ቢሆንም እንደ ዳማው ሁሉ እምነታዊ (መንፈሳዊ) መሪ ተደርጎም ይታያል። የጎሳ አለቃው የስልጣን መዋቅር ሁለት ዓይነት ቅርጽ ያለው ነው። አንደኛው የፓልዳውን አምልኳዊ ስልጣንን የሚከታተል የሚመራ /ካዳይት/ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ማጋ›› የተሰኘው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን የሚከታተል የመንደር ተጠሪ ነው።
የፓልዳው ዋንኛ ተግባር የጎሳውን አባላት ደህንነትና ሠላም በመንፈሳዊ ልዩ ኃይሉ መጠበቅ ነው። ከጎሳው አባላት ውጪ የሚኖራቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች በአግባቡና በስርዓቱ መከናወናቸውን መከታተል ነው። በዚህም ማህበራዊ ግንኙነቶች አለመግባባቶች ቢፈጠሩ ጎሳውን ወክሎ ከሌሎች የጎሳ መሪዎች ጋር በመደራደር ችግሮቹ እንዲፈቱ ያደርጋል። መፈታት ካልቻሉም ወደ ‹‹ዳማው›› የበላይ መሪ ይዞ የሚቀርበው ይህ መሪ ነው። በተለይ ወንጀል ነክ የሆኑ ጉዳዮች ሲሆኑ የፓልዳ ሚና ከፍ ያለ ነው።
የእያንዳንዱ ንዑስ ጎሳ መሪ (ሼላ) እምነታዊ (መንፈሳዊ) መሪነታቸው ይለያያል። የብሔረሰቡ አባላት ከተለመደው ልማድና ወግ ወጣ ያለ ነገር ከሰሙ መከራና ቅጣትን በልዩ ኃይላቸው ያወርዳል ተብሎም ይታሰባል። ከሼላ በተጓዳኝ የመንደር መሪ (ሻና) ሌላኛው የባህላዊ የአስተዳደር ቅርጽ ሲሆን፤ በደራሼ ብሔረሰብ ውስጥ በሁለንተናዊ ሰብእናው የተከበረ፣ ለሌሎች አርኣያ የሆነ ግለሰብ ለዚህ የመሪነት ሚና ይታጫል። በሰብእናው የተሻለ ግለሰብ ለዚህ ኃላፊነት የሚመረጥ በመሆኑ እንደ መንፈሳዊ መሪ ይታያል። በመሆኑም በመንደሩ ነዋሪዎች ከፍተኛ ከበሬታ ስላለው ውሳኔዎቹም ሆኑ ትዕዛዞቹ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡
በደራሼ ብሔረሰብ የባህላዊ አስተዳደሩና የፍትህ ስርዓቱ ተዛምዶ የጠበቀ ነው። የፍትህ መዋቅሩ መነሻው የባህላዊ አስተዳደር መዋቅሩ ሆኖ በዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠሩት ‹‹ዳማ››፣ ‹‹አራፊይታ›› (የንጉሱ ችሎት)፣ ‹‹ፓልዳ›› ሻላ/ሻና እና ኦስማረ/የቤተሰብ መሪ/ ናቸው። እነዚህ መዋቅሮች በውስጣቸው ንዑስ ክፍሎችን በመያዝ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ይዳኛሉ። በብሔረሰቡ የመጨረሻው የዳኝነት ችሎት ‹‹አራፊይታ›› የንጉሱ ችሎት ተብሎ የሚጠራው ሲሆን፤ አራፊይታ የንጉሱ ችሎት አባላት ቁጥራቸው ከሰባት እስከ-12 ይደርሳል።
በዚህ በ‹‹አራፊይታ›› ችሎት የሚቀርቡ ጉዳዮች የተመረጡና የማህበረሰቡ የአብሮነት ህይወት አደጋ ናቸው ተብሎ የሚታሰቡ ችግሮች ናቸው። የተመረጡ ጉዳዮችም ቢሆኑ እንደ ስፋትና ጥልቀታቸው፤ ማህበረሰብ አቀፍ እና ግለሰባዊ መሆናቸው ተመዝኖ ዳማው (ንጉሱ) በችሎት እንዲገኝ ይደረጋል። ከዚህ ውጪ ግን ዳማው በአብዛኛው በግለሰቦች ጉዳይ አይገባም። የግለሰብ ጉዳዮች በታችኛው የፍትህ መዋቅር መፍትሔ ያገኛሉ።
በዚህ ችሎት ከበድ ያሉ ውሳኔዎች ይወሰናሉ። በተለይ በቀደመው የደራሼ ብሔረሰብ የፍትህ ስርዓት ውስጥ የሞት ፍርድ፣ የአጥፊው ወገን ንብረት እንዲወድም ማድረግ የመሳሰሉት በዚህ የችሎት ደረጃ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ነበሩ። እነዚህ ውሳኔዎች በአብዛኛው ‹‹ዳማው›› በችሎት በአካል ሲገኝ ብቻ ነው። ሌሎች ውሳኔዎች አራፊይታዎች በምክር በዳማው ስም የመወሰን ስልጣን አላቸው። በብሔረሰቡ የንጉሱ /ዳማ/ ውሳኔ ፍፁም ትክክልና ከመለኮታዊ ባህሪው በመነሳት የሚወስነው ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል።
የደራሼ ብሔረሰብ በዚህ የአስተዳደር መዋቅሩ መሰረት ከሚመለከታቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ትልቁ ለግጭቶች እልባት መስጠት እንደመሆኑ፤ በብሔረሰቡ ግጭቶች የሚፈቱበት የራሱ የሆኑ ባህላዊ አካሄዶች አሉ። በመሆኑም የደራሼ ብሔረሰብ በራሱም ውስጥ ሆነ ከሌሎች የአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር በሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን የሚፈታበት ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓት አለው። ይህን ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓት ‹‹አራርሳ››ወይም ‹‹ሆሮታ›› በማለት የሚጠራ ሲሆን፤ የቃሉም ትርጓሜ ማስታረቅ፣ ማስማማት፣ መዳኘት፣ መቅጣት የሚሉ ፍቺዎችን ይይዛል።
በ‹‹አራርሳ›› የፍትህ ስርዓት ውስጥ እንደ ግጭቶቹ አይነትና ደረጃ የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶችና ውሳኔዎች ይፈፀማሉ። እነዚህ ባህላዊ ስርዓቶችና ውሳኔዎች የሚሰጡት በዳማው ‹‹አራፊይታ› ችሎት፣ በፓልዳ የሽምግልና ተቋም፣ በሼላ/ሻና እንዲሁም በ‹‹ኦስማረ›› የቤተሰብ መሪ የእርቅ ስርዓት ነው። በመሆኑም በደራሼ ብሔረሰብ የግጭት መፍቻ ስርዓቶች የሚፈጸሙት በዳኝነት፣ በእርቅና በሽምግልና ስርዓት ሲሆን፤ እነዚህም የየራሳቸው መዋቅራዊ ስርዓት አላቸው። ለምሳሌ፣ የነፍስ ግድያ፣ በሰደድ እሳት ንብረት ማውደም የመሳሰሉት ድርጊቶች በብሔረሰቡ በከባድ ወንጀልነት የሚታዩ የግጭት መከሰቻዎች ናቸው። በመሆኑም እንደነዚህ አይነት ግጭቶች በ‹‹ዳማው›› (በንጉሱ) ችሎት ውሳኔ ይሰጥባቸዋል። አልፎ አልፎ የጎሳው መሪዎች /ፓልዳ/ዎች እነዚህን መሰል ወንጀሎች የማየት ስልጣን አላቸው።
በሌላ በኩል ድንበር በመግፋት፣ በከብቶች ስምሪት የሚወድሙ ሰብሎች፣ በባልና በሚስት አለመግባባት የሚፈጠሩ ግጭቶች መፍትሄ የሚያገኙት በባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት ነው። የሽምግልና ስርዓቱም ቢሆን የራሱ የሆኑ ሥርዓቶች አሉት። በተለይም በጎሳዎች መካከልና ከአጎራባች ብሔረሰቦች ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶች በልዩ እምነታዊና ባህላዊ የእርቅ ስርዓት መፍትሔ ያገኛሉ። ይህ የሽምግልና የእርቅ ስርዓት የሚከናወነው ‹‹ሞራ›› በተሰኘ የባህላዊ የዳኝነት ችሎት አደባባይ ነው።
‹‹ሞራ›› የዳኝነትና የፍርድ ችሎት ቦታ ሲሆን፤ በአንድ ትልቅ ዛፍ ዙሪያ በድንጋይ ካብ ከፍ ተብሎ የተሰራ ይዞታነቱ የህዝብ የሆነ ቦታ ነው። ሞራን ለየት የሚያደርገው ህፃናትና ሴቶች በዚህ የችሎት አደባባይ ላይ መቀመጥ አለመቻላቸው ነው። በአካባቢው ማህበረሰብም የተከበረ ቦታ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ባህላዊ ዳኝነቶች የራሳቸው የፍትህ ውሳኔ ያላቸው ናቸው። በባህላዊ የፍትህ ስርዓቱ ከሚወሰኑ ውሳኔዎች ዋና ዋናዎቹ ማግለል፣ እርግማንና ሞት ናቸው።
ለምሳሌ፣ የማግለል ውሳኔ በአብዛኛው ተፈፃሚ የሚሆነው በፓልዳ /የጎሳ መሪዎች/ በሚይዟቸው ጉዳዮች ሲሆን፤ ግለሰቡ ያጠፋውን ጥፋት ካላመነ እንዲሁም የተወሰነበትን ቅጣት ካልተቀበለ በማህበረሰቡ ሁሉ እንዲገለል ይደረጋል። በየትኛውም ማህበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ አይሳተፍም። የእርግማን ውሳኔን በተመለከተም፣ የደራሼ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ስልጣን ሁለት መልክ ያለው ሲሆን፤ አንዱ አምልኳዊ ሌላኛው ደግሞ አስተዳደራዊ ነው።
በዚህ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ዳማውን (ንጉሱን) ጨምሮ ካላይት፣ ሼላ፣ ሻና የመሳሰሉት የመዋቅሩ መሪዎች አምልኮአዊ (መለኮታዊ) ስልጣን አላቸው ተብሎ ይታመናል። እናም ግለሰቡ ጥፋቱን ከካደ በእነዚህ አምልኳዊ መሪዎች አማካኝነት እንዲረገም ይደረጋል።በእርግማናቸውም ግለሰቡና ቤተሰቡ አብጠውና ፈንድተው እንዲሞቱ፣ በዘር ሀረጋቸው ሁሉ የቁምጥና በሽታ እንዲኖር፣ የሚዘሩትን እንዳያጭዱና የሚወልዱት እንዳያድግ ይረግማሉ። ይሄም በብሔረሰቡ ዘንድ ይደርሳል የሚል እምነት ስላለ፤ ወንጀል የሰራ ወንጀሉን ከመናዘዝ ውጪ አማራጭ የለውም።
ወረታ /ክፍያ/ ሌላው ውሳኔ ሲሆን፤ በዚህ የውሳኔ አይነት ውስጥ የሚካተቱ ጉዳዮች ደግሞ ከባድ ወይም ቀላል ግጭቶች ሆነው ነገር ግን በጥፋት ደረጃቸው የማህበረሰቡን መሰረታዊ ባህሎች የማይጥሱ የጥፋት አይነቶች ውሳኔ ነው። ጠለፋ በዚህ ውሳኔ ውስጥ ከሚያልፉ ድርጊቶች አንዱ ነው። አንድ ጠላፊ ጠልፎ ሲወስዳት ቤተሰብ በሽምግልና ስርዓት ከተዳኘ በኋላ እንደ ሃብቱ መጠንና እንደ ሽማግሌዎቹ ውሳኔ ከአንድ እስከ አምስት ከብቶች እንዲሁም እስከ አንድ ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ መስጠት ይጠበቅበታል። በሌላ መልኩ በሰደድ እሳት ንብረት ያወደመ፤ በእርሻ ቦታ ያለን ሰብል ያቃጠለ የገንዘብም የጉልበትም ቅጣት ይጣልበታል። የገንዘቡ መጠን እንደ ጠፋው ንብረት የሚወሰን ሲሆን፤ በጉልበት እርሻውን ማረስ፣ የተዘራውን ማረም፣ ሲደርስ ማጨድ ሊወሰንበት ይችላል።
ሌላው ውሳኔ ሞት ሲሆን፤ ይህ ውሳኔ በፍትህ ስርዓት ውስጥ ከሚሰጡ ውሳኔዎች አንዱ ነው። ይህ ውሳኔ የሚሰጠው በብሔረሰቡ መሪ በዳማ የአራፊይታ ችሎት ነው። ይህ ውሳኔ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥናት የሚከናወን ነው። በተለይም እንዲህ አይነት ውሳኔዎች የሚሰጡት ለህብረተሰቡ ሰላምና የአብሮነት ህይወት አደጋ የሆኑ ግጭቶች ሲፈጠሩ፣ የብሔረሰቡን እሴቶችና ባህሎች የሚገፉ ተግባራት ከተፈፀሙ ውሳኔው ተግባራዊ ይሆናል። የሞት ቅጣቱ የሚፈፀመው በስቅላት ወይም አጥፊው በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ይደረጋል። ይህንንም የሚያስፈፅሙት የንጉሱ ችሎት አንድ አካል የሆኑት ‹‹ዋሎት›› ተብለው የሚጠሩ ናቸው።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ የአስተዳደርና የፍትህ ተቋማት መዋቅር ያለው ሲሆን፤ በእነዚህ መዋቅሮች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ይዳኛል፤ ውሳኔ ይሰጣል፣ ቅጣት ይጥላል። ግጭቶች ሲፈጠሩ ከቤተሰብ መሪ ኦስማረ፣ ሼላ/ሻና፣ ፓሌልዳ፣ ዳማ ባለ መዋቅሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋል። እነዚህ የባህል ዳኝነት ሰጪ አካላት ህብረተሰቡ ዘንድ ባላቸው ክብርና ተቀባይነት የተነሳ ይህ የእርቅና ዳኝነት ስርዓትም ከመደበኛው የዳኝነት ስርዓት በተሻለ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት ያለው ሲሆን፤ ችግሮችን ስር ሳይሰድዱ እየፈቱ ከመጓዝና የብሔረሰቡን ሁለንተናዊ ትስስርና ትብብር ከማጠናከር አኳያም ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ዘመናትን የተሻገሩ ስለመሆኑም ይታመናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ወንድወሰን ሽመልስ