አዲስ አበባ:- በእንግሊዙ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ሳይንቲስቶች በዓለም የቡና ዝርያዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ይፋ የተደረገውን የጫካ ቡና (ኮፊ አረቢካ) ምርታማነት ይቀንሳል የሚለውን ስጋት መከላከል እንደሚቻል ተገለጸ፡፡ መንግስት ደን ክልሎ ማስተዳደር እንዳለበትም ተጠቆመ፡፡
ጥናቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚለማው የአረቢካ ቡና (የጫካ ቡና) እአአ በ2080 በ85 በመቶ ቅናሽ ያሳያል እንዲሁም አሁን ቡና የሚለማበት መሬትም እስከ 60 በመቶው በምእተ አመቱ መጨረሻ ላይ ለቡና ተስማሚ ወደ ማይሆንበት ሁኔታ ይሸጋገራል የሚል ነው፡፡
የአካባቢ የአየር ንብረት እና የቡና መድረክ ከፍተኛ ተመራማሪውና አማካሪው ዶክተር ታደሰ ወልደማርያም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የሳይንቲስቶቹ ስጋት ስጋትም መልካም አጋጣሚም ሊሆን ይችላል፡፡
ዶክተር ታደሰ የደን መመንጠሩ ላለፉት ሰላሳ እና አርባ ዓመታት መታየቱን፣ የአየር ንብረት ለውጡም እንደሚታወቅ ጠቅሰው ፤ አየሩ ደረቅ እየሆነ በሄደ ቁጥር ለቡና ያለው ምቹነት እየቀነሰ እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡ ይህን ችግር እያየን ከተቀመጥን ስጋቱ በእርግጥም ስጋት እንደሚሆን ፣ እርምጃዎች ከተወሰዱ ግን ስጋቱ መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር ታደሰ ያመለክታሉ፡፡
የአየር ንብረት ለውጡ ቡና አሁን ከሚለማበት ከፍታ ወደ ላይ ወደ ሰሜንም እንዲሰደድ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረው፣ ቡናው የሚበቅልበትን ቦታ ወደ ከፍታ ቦታ ማዛወር ከተቻለ፣ ቡናው አሁን ባለበት ቦታ ላይም የተለያዩ የማኔጅመነት ስራዎች ከተከናወኑ እንዲሁም ደን እንዳይመናመን ማድረግ ፣ለቡና የሚያስፈልገው የጥላ ዛፍ መጠን እንዳይቀነስ የሚያደርጉ ስራዎች ከተሰሩ ስጋቱ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ቡና በሚመረትበት ስፍራ ላይ አስፈላጊው የልማትና እንክብካቤ ስራ ከተከናወነ የቡና ምርትን በአራት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዝም ብለን ካየን ግን ስጋቱም ስጋት ሆኖ ይቀጥላል›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹ይህን ዝርያ ለእኛም ለዓለም ቡና ኢንዱስትሪም ትልቅ ሀብት ነው›› ያሉት ዶክተር ታደሰ ፣ የኢትዮጵያ የቡና ዋጋ ሲተመን ቡናው ለአካባቢ ጥበቃ እና ለቡና ጀነቲክ ሀብት ያለው ፋይዳ መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በአየር ንብረትና ደን ኮሚሽን በደን መጨፍጨፍና መመንጠር የሚመጣ አማቂ ጋዝ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ በበኩላቸው፣ ቡናው የሚገኝበት ደን በጣም አደጋ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግስት የብዝሃ ህይወትና የጫካ ቡና መገኛ በሆነው የደን ሀብት ጥበቃ ላይ ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህን የደን ሀብት ህብረተሰቡ ይጠብቀዋል ብሎ መተው በደን ላይ ጫና እያሳደረ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ለእኔ ህዝብን አሳትፈን እንጠብቀዋለን የሚለው ከድህነቱ ጋር በተያያዘ ክፍተት ይኖረዋል›› ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ መንግስት ደኑን ክልሎ የሚያስተዳድረው ከሆነ ሊተርፍ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የተወሰኑ ደኖችን መንግስት በክልልም ይሁን በፌዴራል ማስተዳደር እንዳለበት አስገንዝበው፣ በጀት መድቦ የተማረ ሰው አሰማርቶ ብዝሃ ህይወቱን በመጠበቅ መስራት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡ መንግስት ክልሎ የሚያስተዳድረው ከሆነ ደኑ ሊተርፍ እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡
የአረቢካ ቡና ዝርያ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ነው ያሉት ዶክተር ይተብቱ፣ በዚህም ቡና ጠጪውን የዓለም ህዝብ ማሳተፍ እንደሚገባም ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ብዝሃ ህይወቱን በተቋማት መጠበቅ እንደሚገባም አመልክተው፣ ለእዚህ ደግሞ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
ሰሞኑን የወጡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዳመለከቱት ፤ በእንግሊዙ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ሳይንቲስቶች የተሰራው ጥናት፣ አሁን በስፋት የሚጠጡትን ሁለት የቡና ዝርያዎች ጨምሮ 100 የቡና ዝርያዎች የሚለሙት በደን ውስጥ ሲሆን፣ ዝርያዎቹ ከአየር ንብረት ለውጥና ከደን መመናመን ጋር በተያያዘ በመጥፋት አፋፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሊጠፉ ከተቃረቡት የቡና ዝርያዎች መካከል የወደፊቱን ቡና ለማልማት የሚያስችሉት፣ በሽታ የሚቋቋሙት እንዲሁም አስቸጋሪ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉት እንደሚገኙበት ዘገባዎቹ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ዝርያዎች አንዱ የሆነው ኮፊ አረቢካ ሊጠፉ የተቃረቡ ከሚባሉት የቡና ዝርያዎች ዝርዝር መካከል ተመድቧል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
ኃይሉ ሣህለድንግል