አብዛኛው ህይወታቸውን በግብርና ሥራ አሳልፈዋል። የቀንድ ከብቶችን ወደ ውጭ አገራት በመላክም ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል። በኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ከጀመሩ ጥቂት ባለሀብቶች ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ይጠቀሳል። የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ማህበርን በመመሰረት ከአስራ ሁለት ዓመታት በላይ ማህበሩን መርተዋል።
ምርታቸውን ወደ አውሮፓ፣ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ካሉ ባለሀብቶች መካከልም አንዱ ናቸው-፤ አንጋፋው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪው አቶ ፀጋዬ አበበ።
ከዛሬ ሃያ አራት ዓመታት በፊት በአበባ እርሻ ልማት ውስጥ በመግባት አቶ ፀጋዬ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሁን እንጂ በወቅቱ ጠንካራ የመሬት ፖሊሲ ባለመኖሩ መሬት ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር። በቂ መሠረተ ልማትና የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀዝቀዣ ቤትም አልነበረም። ምርቱን ለማጓጓዝ የማቀዝቀዣ መኪና እንዲሁም ኢንቨስትመንቱን ለማስፋት ከባንኮች ብድር ለማግኘትም እጅግ አዳጋች ነበር።
ቀድሞውኑ በእርሻ ሥራ ላይ መሰማራት ፍላጎቱ የነበራቸው አቶ ፀጋዬ ታዲያ በጊዜው በመንግሥት እርሻ ልማት ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ከአበባ እርሻ ጋር በተያያዘ አንዳንድ መረጃዎችን ሲነግሯቸው ወደዚሁ ልማት ለመግባት ይገፋፋሉ። በ1985 ዓ.ም ወደ ኬኒያ የመሄድ አጋጣሚም ተፈጥሮላቸው የአገሪቱን የአበባ እርሻዎች ይጎበኛሉ።
በወቅቱም በኬኒያ የነበረው የአበባ እርሻ ልማት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይረዳሉ። በዘመናዊ መልኩ በግሪን ሃውስ ውስጥ የሚመረቱ አበባዎችን ማምረት ባይችሉም፣በግልፅ ሜዳ ላይ ሊመረቱ የሚችሉ አበባዎችን ማልማት እንደሚችሉ በመተማመን ሥራውን ለመጀመር ቆርጠው ተነሱ።
በዚሁ ዓመት የአበባ እርሻ ልማት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ መሬት ከመንግሥት ማገኘት የማይቻል በመሆኑ በምሥራቅ ሸዋ ዝዋይ አካባቢ በደርግ ጊዜ በሕብረት ሥራ ተደራጅተው የነበሩና በኋላ ላይ ማህበራቸውን በማፍረስ የጋራና የግል በሚል መሬታቸውን ከለዩ ገበሬዎች መሬት ይኮናተራሉ። በወቅቱ በተለይ መሬት ከገበሬ መኮናተር የሚያስችለው ሕግ ገና ያልፀደቀ በመሆኑ ተቸግረው ነበር። ሆኖም እርሳቸውን ተከትለው ወደዚሁ የአበባ እርሻ ልማት በገቡ አልሚዎች ምክንያት መንግሥትም በዘርፉ ትኩረቱ ተሳበ።
በ1987 ዓ.ም ከፖሊሲ ውጭ መሬት የወሰዱ በሚል እርሻዎቹ እንዲዘጉ ከውሳኔ ላይ ቢደረስም፣በዚሁ ወቅት መንግሥት እንደገና ጉዳዩን በማየትና የመሬት ፖሊሲው እንዲስተካከል በማድረጉ የእርሳቸውና የሌሎች አበባ እርሻዎች ሳይዘጉ ሥራቸውን ቀጠሉ።
አቶ ፀጋዬም ከአበባው ጎን ለጎንም አትክልትና ፍራፍሬዎችንም በማምረት ወደ ውጭ አገራት መላክ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።በዚሁ መሬት ላይ በ500 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ለአስራ አምስት ዓመታት አበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ሲያመርቱ ቆዩ። በወቅቱ ያመርቷቸው የነበሩትን ከግሪን ሃውስ ውጭ የሚበቅሉ የፅጌሬዳ አበባዎችን ከሌሎች የመንግሥት እርሻዎች በተለይም ከኢትፍሩት ጋር በመሆን በአብዛኛው ወደ ሆላንድ ይልኩ ነበር።በዚህም ከ150 እስከ 200 ሺህ ዶላር በዓመት ማግኘት መቻላቸውን አመልክተው፣ቀስ በቀስም ምርታቸው እያደጉ መምጣታቸውን ያብራራሉ።
በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ አቶ ፀጋዬን የገጠሟቸው ውጣ ውረዶች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም።ካፒታላቸው በማለቁ ገንዘብ መበደር ነበረባቸው። በጊዜው ገንዘብ ከባንክ ለመበደር 125 በመቶ ዋስትና ማስያዝ ይጠበቅባቸው ነበር። አንድ ሚሊዮን ብር ብድር ከባንክ ለማግኘትም አስራ ስምንት ወራቶች ፈጀባቸው። ለዚሁ ብድር አስር የሚሆኑ መኪናዎቻቸውንና ሦስት የዘመዶቻቸውን ቤቶች በዋስትና አስይዘዋል። ሁለተኛውን ብድር በመውሰድ ወደ ኢንቨስትመነት ሳይገባ የመጀመሪያው ብድር ወለድ በቶሎ ስለሚደርስ የብድሩ አከፋፈልም ፈትኗቸዋል። ንብረታቸው ሊሽጥ ጨረታም ወጥቶበታል።
በጊዜው አብዛኛዎቹ ባንኮች የአበባ እርሻ ልማት ዘርፉን ብዙም የሚያውቁት ባለመሆኑ የአውሮፓ ሕብረት የአበባ እርሻ ልማቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ያስባል፤ሕብረቱ በ1987 ዓ.ም 200 ሺህ ዶላር በመመደብ ‹‹ካርኔሽን›› የተሰኘ ሌላ አይነት አበባ በእርሳቸው ሁለት ሄክታር የአበባ ልማት ፕሮጀክት መሬት ላይ በሙከራ ደረጃ እንዲመረት አደርጓል።
ይህ የሕብረቱ እርምጃ የኢትዮጵያን ባህላዊ የወጪ ንግድ ወደ ዘመናዊነት የመለወጥ ፖሊሲ የተተገበረበት ነበር። ይሁንና በወቅቱ የሴክተሩን አዲስ መሆን የተገነዘቡ ጥቂት የመንግሥት ሃላፊዎች ብደሩ እንዲራዘም ግፊት በማድረጋቸውና ቤተሰቦቻቸውና ዘመድ አዝማድ ረድተዋቸው ብድሩን ለመክፈል በቁ። የተያዙ የዘመድ አዝማድ ንብረቶችና ቤቶችም ከብዙ ዓመታት በኋላ ተለቀቁ።
አቶ ፀጋዬና መሰል በአበባ እርሻ ልማት ላይ የተሰማሩ አልሚዎችን ችግር በመረዳት መንግሥት መሬት ላይ የሰፈረው የአልሚዎቹ ንብረት እንደዋስትና እንዲያዝላቸው በሚል ብዙ ፖሊሰዎች እንዲስተካከሉ አድርጓል። 30 በመቶ ገንዝብ ኖሮ 70 ከመቶ የብድር አገልግሎት እንዲኖርና ለብድሩም ራሱ ፕሮጀክቱ ዋስትና ሊሆን እንደሚችልና ሌሎችም የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ ሆኗል። መንግሥት ለእንደዚህ ዓይነት አልሚዎች ድጋፍ መስጠት በመጀመሩ እርሳቸውና መሰል አልሚዎች ከችግሩ ወጥተው ከአዲሱ የመንግሥት ፖሊሲ ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል።
በሂደት እያደገ የመጣው ኩባንያቸው በአሁኑ ወቅት በአራቱም የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ድርጅቶቹ ለ2 ሺህ 700 ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በየዓመቱ እያስገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬም ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። የእያንዳንዱ ድርጅት አጠቃላይ ካፒታልም 150 ሚሊየን ብር ይጠጋል።
በእነዚህ ድርጅቶች በ280 ሄክታር መሬት ላይ እያካሄዱ ያሉት ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻም በምሥራቅ አፍሪካ አሉ ከሚባሉ ዘመናዊ እርሻዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል። ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በግልፅ እርሻ ላይ ያመርቷቸው የነበሩ አበባዎችን በማቆም በዘመናዊ መልክ በግሪን ሀውስ ውስጥ ወደሚመረቱ የፅገሬዳ አበባ እርሻም ተሸጋግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከፈረንጆቹ መጋቢት ወር ጀምሮ አስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ውጭ የሚልኩት የአበባ ምርት ችግር ውስጥ ገብቶ እንደ ነበር አቶ ፀጋዬ ይጠቅሳሉ። በተለይም የእርሳቸው ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ወደሆኑት ከአውሮፓ ሆላንድ፣ ጀርመንና ጣልያን፣ ከእስያ ጃፓን እንደዚሁም ከመካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄደው ምርት ሙሉ በሙሉ አልተላከም። በዚህ በሳምንት ብቻ ከ250 እስከ 300 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ምርት ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ሙሉ በሙሉ ሳይላክ ቀርቷል።
ይሁን እንጂ የአውሮፓው መዳረሻ ሲከፈት እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ ምርቶቻቸውን በትንሹ ሲልኩ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም የአበባ ምርት ዋጋ ከመዋዠቁ ውጭ ምርቶቻቸውን ወደነዚሁ መዳረሻዎች በቋሚነት መላክ ጀምረዋል።
በአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ሰፊ ልምድ ያላቸው አቶ ፀጋዬ፣ይህም በዚህ የኢንቨስትመነት ዘርፍ አሁን የሚታዩ ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችላቸው መሆኑን ይናገራሉ። ኢንቨስትመነቱን ለማስፋት የቦታ ችግር ሊያጋጥም ወይም የገበያ ችግር ሊኖር ቢችልም፣ችግሮቹን መቋቋም እንደሚቻልም ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ወቅት የዘርፉ አንዱና ዋነኛው ተግዳሮት የሃይል መቆራረጥ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ምክንያት የማቀዝቀዣ ቤቶች፣ የመስኖ ሞተሮችና ሌሎችም በርካታ እቃዎች እየተቃጠሉ እንደሚገኙም ያመለክታሉ።
በአበባ እርሻዎች ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ዝርፊያዎችም የዘርፉ ተግዳሮት መሆናቸውን አቶ ፀጋዬ ይጠቁማሉ። ከመሬት ጋር በተያያዘም አሁንም ችግሮች እንዳሉ ተናግረው፣በዚህ ላይም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።አገሪቱ የአበባውን ያህል በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍም ብትሠራ ትልቅ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል የሚናገሩት አቶ ፀጋዬ፣መንግሥት ለዚህም ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ይጠቁማሉ።
በተለይ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የውሃ ሞተርና ችግኞችን በመስጠት የጀመራቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች በሁሉም ክልሎች ቢስፋፉ ዘርፉን የማሳደግ ዕድል እንዳለም ይጠቁማሉ። ለዚህም ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግና ዓለም የሚፈልገውን ምርት በጥራት ማቅረብ የግድ እንደሚል ይገልፃሉ። መንግሥትም ዘርፉ የሚጠይቀውን መሠረተ ልማት ማስፋፋት፤በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ አልሚዎችን መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባውም ይጠቁማሉ። ህብረተሰቡ አትክልትና ፍራፍሬን የመመገብ ባህል እንዲያዳብር በአትክልትና ፍረፍሬ ላይ የሚጣለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ሊነሳ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
‹‹አሁን እየሰራሁት ያለሁት ገንዘብ ለማግኘት ብቻ አይደለም›› የሚሉት አቶ ፀጋዬ በቀጣይ በአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ እያደረጉ ያሉትን ኢንቨስትመንት በማስፋት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዚህም ከመንግሥት በኩል መሬት እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ። በአካባቢያቸው ያሉ አነስተኛ አርሶ አደሮችን በመያዝ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎችን ወደውጭ ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸውም ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ፀጋዬ ንፁህና ጥራት ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ግበአት ማለትም ዘርና ኬሚካል በማቅረብ አርሶ አደሩን በተመጠጣኝ ዋጋ ለማገልገል እንደሚሰማሩም ያስረዳሉ። አሁን እያመረቱ ካሉት አትክልትና ፍራፍሬ ሦስት እጥፍ ቢያመርቱ ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት እንዳለና ወደ ውጭ አገር የመላክ ዕድል እንዳላቸውም ይጠቅሳሉ። ይሁንና ይህን ለማድረግ የሚገድቡ የመሬት ጉዳዮች በመኖራቸው በመንግሥት በኩል ሊፈቱ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች ማህበርን በመምራት፣ እውቀታቸውን በማካፈልና የውጭ ባለሀብቶችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሃላፊዎች ጋር በማገናኘት የኢትዮጵያን አበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካደረጉ ሰዎች ውስጥ አንዱ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ፀጋዬ፣ ዛሬም ለማንኛውም የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን እየሰጡ እንደሚገኙና ይህ ድጋፋቸው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣሉ።
‹‹በአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ ተሳክቶልኛል›› የሚሉት አቶ ፀጋዬ፣ ይህ ባይሆን ኖሮ ምን አልባት ከዚህ ኢንቨስትመንት በመውጣት በሌላ ዘርፍ ላይ መሰማራት የግድ ሊሆንባቸው እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።ልማቱን ሃያ አምስት ዓመታት በዚህ ዘርፍ ውስጥ እያስፋፉ መቆየታቸው የውጤታማነታቸው ማሳያም መሆኑንም ይናገራሉ። የመሬት ጉዳዮችና ሌሎችም ችግሮች በመኖራቸው እንጂ ከዚህም በላይ ኢንቨስትመንታቸውን ማስፋትና የሥራ ዕድል በመፍጠር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ይችሉ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
ለዚሁ ስኬታቸው ሚሰጥሩ ታዲያ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ አሳልፈው መስጠታቸውና ተስፋ ሳይቆርጡ ሠርተው ሌላውንም ማሠራታቸው መሆኑን ይጠቁማሉ። በተመሳሳይ በዚሁ ዘርፍ ተሰማርተው ስኬታማ መሆን ለሚፈልጉ ሰዎችም የሚያገኙትን ገንዘብ ውድ በሆኑ ዕቃዎች ላይ ማፍሰስ እንደሌለባቸውና ከዚህ ይልቅ ገንዘባቸውን ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋት ሊያውሉት እንደሚገባ ይመክራሉ። ሁሌም ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ከመደናገጥ ይልቅ ችግሩ ውስጣዊ ወይም ውጫዊ መሆኑን በመረዳት ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ እንደሚኖርባቸውም ይገልፃሉ።
የሰው ልጅ መቶ በመቶ ስኬታማ ሊሆን ባይችልም ከዘርፉ ሳይወጡ ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋት ከእዚህ የስኬት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ጊዚያቸውን፣ ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን በሥራቸው ላይ ማዋላቸው እና ሠራተኞቻቸውን እንደ ጓደኛ በማየት አብረው በመሥራታቸው መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
የአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ፍላጎት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ መጥቷል። በኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን ሥራ ላይ የሚያውሉ ባለሀብቶች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። እያደገ የመጠውን የአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ፍላጎት ለማርካት ታዲያ በቂ ምርት ከጥራት ጋር ማምረት አስፈላጊ በመሆኑ በተለይ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያህል ዘርፉን ለማስፋፋት መሬት ለባለሀብቶች ማቅረብና የመሠረተ ልማቶችን መገንባት ይጠበቅበታል። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ልዩ መልኩ ሊደግፋቸውና ሊያበረታታቸው ይገባል የዕለቱ መልዕክታችን ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
አስናቀ ፀጋዬ