አዲስ አበባ:- በእነ ጎሀ አጽብህ መዝገብ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፖሊስ እየተጣራባቸው ከሚገኙት 41 ግለሰቦች መካከል ትናንት በአምስት ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ህግ ለቅድመ ምርመራ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤቱ ዘጠኝ ቀናት ፈቅዷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ የታየው ተጠርጣሪዎች ኮማንደር አለማየሁ ሃይሉ፣ምክትል ኢንስፔክተር ዩሱፍ ሀሰን፣ኢንስፔክተር ምንላርግላህ ጥላሁን፣ ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ ሲሆኑ፤ ዐቃቤ ህግ በሁሉም ተጠርጣሪዎ ች ላይ ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡
ከአንዳንዶቹ ምስክሮች ቃል ለመቀበል ጥበቃ ማድረግ ስለሚያስፈልግ የተመቸ ቦታ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የቀረቡለት የህክምና ማስረጃዎች ላይ ጥርጣሬ ስላደረበት ማመሳከርና የባለሙያ ማብራሪያ ማግኘት እንዳስፈለገው አመልክቷል፡፡ ማስረጃ እና ምስክርን ለማስጠበቅ ዋስትናቸው እንዲገደብም ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ቀጠሮ ተሰጥቶ የነበረው ምርመራ ለመጨረስ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ፖሊሶች መሆናቸውን በመጠቆምም፤ ዮኒፎርም ለብሰው በስራ አካባቢያቸውና በሚዲያ ጭምር ብዙዎች ስለሚያውቋቸው ማንነታቸውን ለማስለየት እንደምክንያት የቀረበ እንጂ እንደማይከብድ ተናግረዋል፡፡ የህክምና ማስረጃ ማጣራት ተገቢ ቢሆንም ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የቀረበባቸው እንደሌለም አመልክተዋል፡፡ የህክምና ውሳኔ የምንሰጥ ባለሙያዎች አይደለንም፣ በህክምና ተቋም ገብተን ማስረጃ የማጥፋት አቅም የለንም ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ጉዳዩ ለዋስትና መንፈጊያ ምክንያት ሆኖ መቅረብ እንደሌለበትና ልጆቻቸውን በትነው ከሁለት ወራት በላይ መታሰራቸው ከባድ በመሆኑ በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
ኮማንደር አለማየሁ ‹‹በለውጡ ከማንም በላይ ደክሜያለሁ ምርመራው አግባብ አይደለም ስላልኩ ነው የታሰርኩት›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሴት ልጅ የደፈረ ብልት የሰፋ በዚሁ ፍርድ ቤት በዋስ እየተፈታ እኛ ለምን እንታሰራለን›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መብቴን እያስከበረ አይደለም ወደ እዚህ የመጣሁት የራሱ ምክንያት ያለው ነው ሲሉ በችሎት ተናግረዋል፡፡ እንደመከራከሪያ የቀረበባቸው ውሃ እንደማያነሳ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በዋስ እንዲያሰናብታቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ምስክር ማስለየት የተባለው ስለጠፋ ፍለጋ ላይ ናቸው ያሉት ኢንስፔክተር ምንላርግልህ፤ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ድብደባ መሆኑን ድርጊቱ የዋስትና መብት እንደማያስከለክልና በዋስ ወጥተው ምርመራው እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ ምስክሮች ያባብላሉ፣ ያጠፋሉ በተባለው ተጎጂዎች ነን ብለው እየመሰከሩ ያሉትን ማባበል እንደማይቻልም ጠቁመዋል፡፡
ዋና ሳጅን ርዕሶም በበኩላቸው፤ ጥቂት ባለስልጣኖችን ለማስደሰት እጣ ፈንታ የደረሰበትን ሰው ማሰቃየት ነው የተያዘው ብለዋል፡፡ መንግስት ህጋዊ ስልጣን አግኝቶ የአሰራር ስርዓት አበጅቶ የሰራውን ግለሰብ ሊጠየቅበት አይገባምም ነው ያሉት፡፡ እኔ ምን ፈልጌ ሰው አስራለሁ፣ የማሰር ስልጣንም የለኝም ፍርድ ቤት ህግና ስርዓት ባለው መልኩ ይዳኘኝ ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በማይመለከታቸው ጉዳይ እንደተጠየቁ፣ዕጣ ፈንታቸውም አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የሚጣራ ነገር ካለም በዋስትና እንዲያሰናብታቸው፣ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ቀዳሚ ምርመራ ጉዳያቸው በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚታዩ የወንጀል ጉዳዮች እንደሚደረግ፣ የህግ ክልከላ እንደሌለው፣ የህክምና ማስረጃዎቹ አሁን በባለሙያ ማመሳከር እንዳስፈለገው ዐቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰት መድረሱን ሂደቱ ላይ ክፍተት እንዳገኙ አንስተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሙሉ አድራሻ ስላላቸው ብቻ ይገኛሉ ማለት አይቻልም፣ በምርመራ ስራ የቆዩ መሆናቸውም አያስተማምነኝም ከነባራዊ ሁኔታ አንጻር ታይቶ ዋስትናቸው ይታገድልኝ፣ የጠየቅኩት ጊዜ ይፈቀድልኝ ብሏል፡፡
ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት የወንጀል አይነት በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑ፣ የቀዳሚ ምርመራ የሚካሄደው ክስ ከመመስረቱ በፊት እንደሆነ አገናዝቦ ከትናንት ጀምሮ የሚቆጠር ዘጠኝ ቀናት ፈቅዷል፡፡ ፎቶ ግራፍ አለመነሳት የሚለውን እንደምክንያት ሲወስድ፤ የህክምና ማስረጃ ማመሳከር እንደምክንያት ሆኖ የቀረበውን አልተቀበለውም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
በዘላለም ግዛው