በኮምፒዩውተር አለም 3ዲ የሚባለው ሶስት የተለያዩ ጎኖችን የሚሳይ ስዕል ሲሆን፣ በዋነኝነት ጥልቀትን ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላል። የ3ዲ ምስል በምንመለከትበት ወቅት ምስሉ አጠገባችን እንዳለ ሆኖ ይሰማናል። ይህ ደግሞ ምናባዊ እይታ በመባል ይታወቃል። ማንኛውም ሰው የ3ዲ ምስል ለመመልከት ለ3ዲ የተዘጋጀ መነፅር ማድረግ ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ምናባዊ ምስሎች ለመመልከት የተለያዩ መሳሪያዎችም ጥቅም ላይ ይውላሉ።
የ3ዲ ምስልን ለመፍጠር ሶስት ሂደቶች ያስፈልጋሉ። እነሱም የምስል መዘግየት፣ ጂኦሜትሪና ምስል የመስጠት ሂደቶች ናቸው። በመጀመሪያው ሂደት ምስልን በማዘግየት የተለያዩ አይነቶች ሞዴሎችን በመፍጠር ለየብቻ የሚታዩ ምስሎች ይፈጥራሉ። በሁለተኛው ሂደት ደግሞ የተፈጠሩት ምስሎች ጨረር ሲያርፍባቸው ምስሉ በጂኦሜትሪ መልክ እንዲታይ ያደርጋል። በሶስተኛው ሂደት ምስሉ በ3ዲ ሞዴል ተለውጦ እያንዳንዱ ጎን የሚታይበት ሁኔታ ይፈጠራል። በአሁኑ ወቅት የ3ዲ ምርቶች በብዛት የሚገኙ ሲሆን፣ ለዚህም ኤክስትሪም 3ዲ፣ ላይትዌቭ 3ዲ፣ ሬይ ድሪም ስቲድዮ፣ 3ዲ ስቲድዮ ማክስ፣ ሶፍት ኢሜጅ 3ዲና ምናባዊ ምስል የሚሉት በምሳሌነት ይጠቀሳሉ። የምናባዊ ምስል ሞዴሊንግ ቋንቋ እያንዳንዱ ምስል የራሱ ቋንቋ እንዲኖረው እድል ይሰጣል።
3ዲ ማተሚያ
የተለያዩ ቁሳዊ የ3ዲ ምርቶችን ለመፍጠር የሚያስችል መሳሪያ ነው፤ 3ዲ የሆኑ ሞዴሎች ማለትም ለትልልቅ ግንባታ የሚሆኑ ግንብ መሳይ ብሎኮች እና ማዕከፎችን ማምረት ያስችላል። 3ዲ ማተሚያ ባህላዊ የአመራረት ዘዴዎችን በመቀየር በተለይ እቃዎችን በመቁረጥ፣ በመንደፍ እና በማስተካከል የሚፈጀውን ጊዜ የሚያሳጥርና የሚያስቀር ቴክኖሎጂ ነው።
በ3ዲ ማተሚያ በሂደት የሚወጡ ምርቶች በአንድ ቦታ ያለቁ ምርቶች ማግኘት ያስችላል። በመጀመሪያ ማተሚያው ከኮምፒዩውተር የምርቱን ንድፍ ይቀበላል። ይህም በኮምፒዩውተሩ ውስጥ ቅድሚያ የሚፈለገውን ምርት እያንዳንዱን ቅርፅ ንድፍ ይሰራል። የተሰሩትን ንድፎች ወደ 3ዲ ማተሚያው በመላክ የሚፈለገውን ምርት እንዲያትም ይታዘዛል። በመቀጠል ማተሚያው የገባለትን የምርቱን ንድፍ በመከተል አትሞ ማውጣት ይጀምራል።
3ዲ ቴክኖሎጂ ማንኛውንም ነገር ለማምረት የ3ዲ ማተሚያን ይጠቀማል። የሚመረቱትም ባለሶስት እይታ ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ ኩባያን ብንመለከት ስፋት፣ ከፍታና ርዝመት አለው። ስለዚህ ኩባያ ሶስት የእይታ ጎኖች አሉት ማለት ነው። በወረቀት ላይ የሚሳሉ ግራፎች ሁለት አይነት እይታ አላቸው። እሱም ቁመትና ስፋት ሲሆን ጥልቀት ግን ማሳየት አይችሉም።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የህትመት ስራ በወረቀት ላይ በመፃፍና በመሳል የሚከናወን ነበር። የ3ዲ ህትመት ቴክኖሎጂ ከመጣ ወዲህ ግን በሶስት እይታ ባለው መንገድ ህትመቶችን ማውጣት ተችሏል። 3ዲ ማተሚያ በኮምፒዩውተር ቁጥጥር ስር ሆኖ የተለያዩ እቃዎችን በሶስት ጎን እይታ እንዲኖራቸው በማድረግ የሚሰራ ነው። በሌላ በኩል የግንባታ እቃዎችን ቅድመ ሙከራ ለማምረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ነው።
የ3ዲ ቴክኖሎጂ አዳዲስ ፈጠራዎች
እ.አ.አ በ2018 ታህሣሥ በ3ዲ ቴክኖሎጂ ላይ ምርምር ያደረጉ ሳይንቲስቶች እንዳመለከቱት፤ በ3ዲ ማተሚያ መስታዎቶች ማምረት ተችሏል። በተመሳሳይ ዓመት በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ አማካኝነት በ3ዲ ማተሚያ የጉሉኮስ መጠን መለኪያ ማሽን መስራት ችሏል። ይህ ማሽን የስኳር ህመምተኞች በደማቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በየጊዜው እንዲለኩ ያግዛቸዋል። ሲዛር የተባለው የ3ዲ ማተሚያ ቴክኖሎጂ አምራች ድርጅት ደግሞ በቀጣይ በ3ዲ ማተሚያዎች ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ለመገንባት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
በ3ዲ ቴክኖሎጂ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት እንዳስታወቁት፤ በቀጣይ በቴክኖሎጂው ከፍተኛ የሆኑ ምርቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስራት ዝግጅት ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት በግለሰብ ደረጃ የ3ዲ ማተሚያ ማሽን የሚጠቀም የለም። አሁን ባለው ሁኔታ 3ዲ ማተሚያ ማሽን ለከፍተኛ ፋብሪካ እና ለህክምና ቁሳቁስ ማምረት ስራዎች እንዲሁም ለግንባታ፣ ለህዋ ምርምርና ለሌሎች አገልግሎቶች እየዋለ ይገኛል።
የምግብ አምራች ፋብሪካዎች የ3ዲ ቴክኖሎጂን በማሳደግ ለምግብት እንዲውል ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ናቸው። የፋሽን ኢንዱስትሪዎችም በቴክኖሎጂው ተስበዋል። የፋሽን ንድፍ ሰሪዎች በአሁኑ ወቅት በ3ዲ ቴክኖሎጂ ጫማና ልብስ ለማምረት ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ጥናትና ምርምር የሚሰሩ ሰዎች እንደሚናገሩት፤3ዲ ማተሚያዎች በኢንዱስትሪ፣ በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ በቅርቡ መታየት ይጀምራል።
በ3ዲ ማተሚያ አማካኝነት ቤቶችን ገንብቶ መንደር መመስረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል። በዚህ ቴክኖሎጂ የሚገነባው መንደር በዝቅተኛ ወጪ እና በአነስተኛ ጊዜ ቤቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በአለም የቤት አልባ ሰዎችን የመጠለያ ችግር ለመፍታት መታሰቡ ተነግሯል። የ3ዲ ማተሚያ ላለፉት አስርት ዓመታት በህክምና፣ ኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በሌሎች ዘርፎች ፈርቀዳጅ አዳዲስ የፈጠራ ግኝቶችን በማቅረብ የሰዎችን አኗኗር እያቃለለ ነው። በቤቶች ልማት ዘርፍ ደግሞ በአውሮፓዊያኑ 2013 አንድ የቻይና ኩባንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ዲ ማተሚያ የተገነባ አንድ ቤት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ አንድ ሲዊዘርላዳዊ ታዋቂ የቤት ንድፍ አውጪ ዋይቭስ በሀር ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዘላቂነት የሰዎችን የቤት ችግር ለመፍታት መቃረቡን አስታውቋል። የቤት ንድፍ አውጪው አዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂ በማከል በዝቅተኛ ወጪ እና በአጭር ጊዜ ተጠናቀው የሚገነቡ ቤቶችን ለተጠቃሚ ማቅረብ እንደሚቻል ተናግሯል። እንደመነሻም ቴክኖሎጂው በላቲን አሜሪካ በሚገኙ ሀገራት ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምርም ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012
መርድ ክፍሉ