የሀገራችን ጋዜጠኝነት የአጤ ምኒልክ አባት ጋዜጠኛ ይባሉ በነበሩት ደስታ ምትኬ ይጀምር ወይም በብርሃንና ሰላሙ ትንታግ ጋዜጠኛ ተመስገን ገብሬ አልያም ሩቅ ዘመን ወደ ኋላ ተጉዞ በዜና መዋዕል ጸሐፍት አሀዱ ይባል ወይም በ”አእምሮ” ጋዜጣ ይጀመር አልያም በ”ብርሃንና ሰላም “ጋዜጣ ይለጥቅ ለሙግትና ለውይይት በይደር አቆይተነው፤ “አዲስ ዘመን” ግን የቀደሙትን ሰልሶ እንደነሱ በአጭር ሳይቀጭ፤ ዛሬ ላይ ደርሷል። ከጣሊያን የአምስት ዓመቱ ተጋድሎ እና ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከእንግልጣር / ኢንግላንድ / ስደት እንዲሁም የሀገሪቱ ሉዓላዊነትና ነጻነት ከተመለሰ በኋላ ያለውን ብሩህ ዘመን “አዲስ ዘመን” ብለው ሰየሙት። መቼም ይሄን ገራሚ ስያሜ አለማድነቅ ንፉግነት ነው። ይህን ብስራተ ዜና ተከትሎ ዘመኑን፣ ትውልዱን የሚዋጅ ጋዜጣ ማዘጋጀት፣ ማሳተም አስፈለገ።
ጋዜጣውም ግንቦት 30፣ 1933 ዓ.ም የመጀመሪያ ዕትሙን ይዞ መጀመሪያ በቤተ መንግስት ቀጥሎ በሸገር ጎዳናዎች ብቅ አለ። ይህ አንጋፋ፣ ጎልማሳ ጋዜጣ “አዲስ ዘመን “ነው። የተቋማት በሽታ፣ ሾተላይ በሆኑ አገዛዞች አልፎ “አዲስ ዘመን “ዛሬ ግንቦት 30፣ 2012 ዓ.ም 79 ሻማዎችን ለኩሶ፣ ድፎ ቆርሶ ልደቱን አክብሯል። በዚህ አጋጣሚ፤ እንኳን አደረሰህ!!! አደረሳችሁ!!! እንድል ይፈቀድልኝ። ተቋሙ ያለበት ቁመና ምንም ይሁን ምን ከተቋቋሙ፣ ከተመሰረቱ በኋላ 10 ዓመት የሞላቸው ተቋማትን ማየት ብርቅ በሆነባት እምዬ ኢትዮጵያ፤ 100ኛ ዓመታቸውን ለማክበር እየገሰገሱ ያሉ እንደ” አዲስ ዘመን “ያሉ ተቋማትን ማየት በራሱ ብርቅ ነው። ይሁንና የመጣው የሄደው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በአምሳሉ ሲጠፈጥፋቸው፣ ሲያፈርስ ሲሰራቸው መኖሩ የዕድሜአቸውን ያህል የጎለመሱ፣ የተጠበቡና የደረጁ ባለመሆናቸው በተግባርም በምግባርም የታፈሩ፣ የተከበሩ እንዳይሆኑ እጀ ሰባራ አድርጓቸዋል። ሆኖም እነ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሔር የመሰሉ የሙያው ጉምቱዎች የጻፉበት፣ የተሰናዘሩበትና የተሟገቱበት የሀገረ መንግስታት የታሪክ ገጽ መሆኑን ልብ ይሏል።
ለቀደሙት 27 ዓመታት ለምዕራባውያንና ለዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ታይታና ፍጆታ ሲለፈፍ የነበረው አስመሳይ፣ መልቲና አጭበርባሪ “የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ “፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በዘመነ ቀዳማዊ ትህነግ/ኢህአዴግ ይተወን እንደነበረው በምዕራባውያን ዘንድ ቅቡልነትንና እርዳታን ለመቀላወጥ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት መስዋዕት የሆኑለትን የነጻነትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥያቄን በማያዳግም ሁኔታ ለመመለስ ሀቀኛ፣ እውነተኛና ተቋሟትን ለማቆም የሚደረገው ጥረት መጪው ዘመን ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ ብሩህ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። ለዚህ ነው በመጣጥፌ ርዕስ ላይ ከለውጡ በኋላ ያሉትን ሁለት የተስፋ ጎህና የለውጥ ዓመታት ለማሳየት በመደመር ምልክት የለየኋቸው።
መጪው ዘመን ብሩህ ቢሆንም፤ ማህበራዊ ሚዲያው በቀኝ እጁ መልካም አጋጣሚን፤ በግራው ደግሞ ስጋትን ይዞ ብቅ ብሏል። “አዲስ ዘመን “በህመሙ፣ በእባጩ ላይ ማህበራዊ ሚዲያው በአናቱ ተጨምሮ ህልውናው ላይ አደጋ ደቅኗል። አደጋው በእኛዎቹ ጋዜጦች፣ መፅሔቶች በአጠቃላይ በህትመት ጋዜጠኝነት ብቻ የተጋረጠ አደጋ አይደለም። ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ በዓለም ሁሉ ባሉ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ያንዣበበ አደጋ እንጂ፤ እኔም በእነዚህ የ “አዲስ ዘመን” የልደት ሻማዎች ወገግታ ማህበራዊ ሚዲያን ተከትሎ የመጣውን አደጋና መውጫ በሩን ለማመላከት ከመሞከሬ በፊት ማህበራዊ ሚዲያው ይዞት የመጣውን መልካም አጋጣሚ ላነሳሳ።
ማህበራዊ ሚዲያው ይዞት የመጣው ጥቅም፣ ዕድል፣ መልካም አጋጣሚ ነፃ የመረጃ ፍሰት ዴሞክራሲያዊና /data democratization/ እና ተደራሽ ማድረጉ ነው። መረጃን ከጥቂት ኩባንያዎች፣ ተቋማት መዳፍ ፈልቅቆ በማውጣት ለግለሰቦች አስረክቧል። ዛሬ መረጃ ያለ አንዳች ድካም በእጅ ስልክ፣ በላፕቶፕና በጠረጴዛ ኮምፒውተር አማካኝነት በደቂቃዎች ይዘረግፋል።
በሚቀጥሉት ዓመታት 5G ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ሲውል በማይታመን ፍጥነት በሰከንዶች ዳጎስ ያለ መፅሐፍን፣ ፊልምን በሰከንድ፣ በማይክሮ ሰከንድ ማውረድ ያስችላል። ይህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት ዜጋው በተሻለ ሁኔታ በመረጃ ላይ ባለመብት ባለስልጣን empower እንዲሆን አስችሎታል። በዚህም ዜጎች በቀላሉ መግባባት፣ መገናኘት፣ መማር፣ መመራመር፣ ወቅታዊ መረጃን ማግኘት፣ …፤ ችለዋል። ማህበራዊ ሚዲያው በህትመት ጋዜጠኝነት ላይ የደቀነውን አደጋ ከመመልከታችን በፊት፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቶማስ ጄፈርሰን በአንድ ወቅት፣ ጋዜጦች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምን ያህል የማይተካ ሚና እንዳላቸው የገለፁበትን ባለ 24 ካራት ወርቅ ይትብሀል ላስታውስ፤ “የመጨረሻውን ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ቢኖረኝ፤ ካለ ጋዜጦች ከሚኖር መንግስት ይልቅ ያለ ምንም ማቅማማት ካለ መንግስት የሚኖሩ ጋዜጦችን እመርጣለሁ።
በዘመነ ኢንተርኔትና ማህበራዊ ሚዲያ፤ የህትመት ኢንዱስትሪው ተፎካካሪ ሆኖ በመውጣት 80 በመቶ የሚሆነውን የማስታወቂያ ገቢውን አስጠብቆ ማስቀጠል እየተሳነው፤ ከ20 በመቶ በማይበልጥ የጋዜጣ ሽያጭ ገቢ /ሰርኩሌሽን /ብቻ ሕልውናውን ማረጋገጥ እንደማይችል ሰሞነኛ ጥናቶች እየለፈፉ ነው። በተደራሲው በኩልም ዜናን መረጃን ከመደበኛው ሚዲያ ማለትም ከሬዲዮ፣ ከቴሌቪዥን፣ ከጋዜጣና ከመፅሔት ከማግኘት ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያው ተመራጭ መሆኑ ነገሩን በእንቅርት ላይ ቆረቆር አድርጎታል። እንደ ታማኙ የአሜሪካ የሕዝብ አስተያየት አጠናቃሪ ፒው / Pew/ ትንተና፤ እኤአ ከ2016 እስከ 2018 ዜናን ከቴሌቪዥን የሚያገኙ አሜሪካውያን ቁጥር ከ57 ወደ 25 በመቶ ሲቀንስ፤ በአንጻሩ መረጃን ከድህረ ገፆች የሚያገኙት አኃዝ ደግሞ ከ28 ወደ 33 በመቶ ከፍ ብሏል (አንዳንድ ጥናቶች ይሄን አኃዝ ወደ 60 በመቶ ያደርሱታል)፤ ከጋዜጦች ዜና የሚቃርመው አንባቢ ቁጥር ከ20 ወደ 16 በመቶ ዝቅ ሲል፤ በተቃራኒው ዜናን ከማህበራዊ ሚዲያ የሚያገኙ አሜሪካውያን ቁጥር ከ18 ወደ 20 በመቶ አድጓል።
እነዚህ የመቶኛ ከፍታና ዝቅታዎች ላይ ላዩን ለተመለከታቸው እዚህ ግቡ የሚባሉ አይመስልም። ሆኖም ኢንተርኔት ጥቅም ላይ ከዋለባቸው ከ1980ዎች ጀምረን ብናሰላቸው ሙሉ ስዕሉን ያሳያሉ። በአሜሪካ የዕለታዊ ጋዜጦች ስርጭት በ80ዎቹ ከነበረበት 63 ሚሊዮን ቅጂ ወደ 31 ሚሊዮን አሽቆልቁሏል። የጋዜጦች የማስታወቂያ ገቢም እኤአ በ2005 ከ49 ቢሊዮን ዶላር በ2017 በሚገርም ሁኔታ ወደ 17 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል ። ዛሬ በተለይ በዘመነ ኮቪድ 19 ከዚህ በእጅጉ ያሽቆለቁላል። በዚህ የተነሳም በኢንዱስትሪው ተሰማርቶ የነበረው የሰው ኃይል ከ74ሺህ ወደ 39ሺህ ወርዷል። እንደ ፒው ያለ የሕዝብ አስተያየት አጠናቃሪ ገለልተኛ ተቋም በሀገራችን ኖሮ ባይገልፅልንም የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የመረጃ፣ የዜና ምንጭ መደበኛ ሚዲያው ሳይሆን ማህበራዊ ሚዲያው መሆኑን በአመጽ፣ በብጥብጥ የሚናጡ ጎዳናዎችና ዩኒቨርሲቲዎች፤ በደባ በሴራ ኀልዮት፣ በሸፍጥ ከውዝግብና ከውርክብ አልወጣ ያለው ፖለቲካችን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
የመደበኛ ሚዲያው መዳከም በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ከደቀነው አደጋ በላይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና የሕግ የበላይነት ቃፊርነቱን፣ አቃቢነቱን፣ ተቆጣጣሪነቱ በሂደት እንዳያጣ በሚል የተፈጠረው ስጋት ነው። ይህ ስጋት ባዶ ስጋት አልያም ዝም ብሎ በስጋት ላይ ያነጣጠረ ስጋት አይደለም። በተጨባጭ መሬት ላይ ባሉ ተለዋዋጭ አኃዞች የተረጋገጥ እንጂ። አዎ ! የመደበኛ ሚዲያው መዳከም፤ የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እያቀዛቀዘው ከመሆኑ ባሻገር በተለይ መደበኛ ሚዲያው በ90ዎቹ በአህጉራችን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የነበረው የማይተካ ሚና እየተዳከመ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የሀርቫርዱ ጉምቱ ፕሮፌሰር ሮበርት ፑትናም ጣሊያንን በናሙናነት ወስዶ ባደረገው ጥናት፤ ጋዜጦች በስፋት በሚነበቡባቸው አካባቢዎች፤ የዛኑ ያህል የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከፍ ያለ ሲሆን፤ በአንጻሩ ጋዜጦች በብዛት በሌሉባቸውና የአንባቢዎች ቁጥር አነስተኛ በሆኑባቸው የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ የዛኑ ያህል ዝቅተኛ መሆኑን አረጋግጧል። የሀርቫርዱን ፕሮፌሰር ስጋት ስለዴሞክራሲ በመጻፍ የሚታወቀው አሌክሲስ ዲ ቶኩዬቬሌ እንዲህ ሲል ይጋራዋል፤ “ጋዜጦች በሌሉበት የጋራ የሆኑ እንቅስቃሴዎች አይኖርም።” ስለሆነም መደበኛ ሚዲያውን ገለል አድርገው የበይ ተመልካች ያደረጉ ማህበራዊ ሚዲያዎች እያጋበሱት ካለው ሀብት ሊያቋድሷቸው ይገባል የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት በማግኘት ላይ ነው። ውጤቱን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።
በሚዲያ አስተምህሮ ሀ ሁ … ተደጋግሞ የሚወሳ የፕሮፌሰር ቶምስኪን ዘመን ተሻጋሪ አባባል አለ።
“ጋዜጠኝነት የታሪክ የመጀመሪያ ረቂቅ ነው። (Journalism is the first draft of history ) “የሚል፤ የዛሬ ዜና የነገ የታሪክ ረቂቅ ነው። ለዚህ ደግሞ መደበኛ ሚዲያው በተለይ ጋዜጦች ትልቅ ድርሻ አላቸው። በዘመነ ኢንተርኔት ግን ይህ የታሪክ የመጀመሪያ ረቂቅ በመሆን የሚታመንበት ጋዜጠኝነት አደጋ ተደቅኖበታል። በግንቦት 1933 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት እንደበቃ የሚነገርለት “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የአፄውን፣ የደርግን፣ የኢህአዴግን፣ የ “ዳግማዊ ኢህአዴግን “፣ የሕዝቡን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም የሀገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ አበይት የመጀመሪያ የታሪክ ረቂቆችን ከየአገዛዞቹ እይታ፣ ትርክት አኳያ ሰንዶ ይዟል። ይሁንና በማህበራዊ ሚዲያው አደጋ የተደቀነበት የህትመት ጋዜጠኝነት ይህን ፈተና በጥበብ ካልተሻገረው ከታሪክ ጥናት አንድ ገጽ ይጎድላል ማለት ነው። በዓለምአቀፍ ደረጃ እንደ ስዊድኑ ኦች ኢንሪክስ፣ የእንግሊዞቹ ታይምስ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ፋይናንሺያል ታይምስ፣ ዘ ኢኮኖሚስት፣ እና የፈረንሳዩ ሌ ፊጋሮ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ዎል ስትሪት፣ ጋዜጦች በአውሮፓም ሆነ በሌላው ዓለም ታሪክ ሲሰራ እማኞች ነበሩ።
በአናቱ ካለፈው ታህሳስ ወር ማብቂያ ጀምሮ በቻይና ውሃን ግዛት የተከሰተው ኖቨል ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ 19/ የጋዜጠኝነትን አሰራር ጨምሮ አጠቃላይ የዓለማችንን ውሎና አዳር ቀያይሮታል። ገለባብጦታል። በይኖታል። በሁሉም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖውን በብርቱ አሳርፏል። ቅድመ ኮቪድ 19 የነበረ ነገር በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ላይመለስ ተሸኝቷል። በድህረ ኮቪድ 19 ስራው፣ ትምህርቱ፣ መዝናኛው፣ ሕክምናው፣ ጋዜጠኝነቱ፣ ሎጂስቲክሱ፣ ወዘተረፈ በአብዛኛው ለኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እጅ ይሰጣል። የዛሬ ትኩረቴ ስለ የሕትመት ጋዜጠኝነት በተለይ ስለ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ነውና በ79 የልደት ሻማዎቹ ጸዳል የታዩኝን ዝክሮች እንደሚከተለው አቀብላለሁ ።
እንደ ዝክረ ልደት
የዜጎችን አስተሳሰብ በማበልፀግና የታሪክ የመጀመሪያው ረቂቅ በመሆን ባለውለታ የሆነው የህትመት ጋዜጠኝነት በማህበራዊ ሚዲያ የተነሳ የበይ ተመልካች የሆነበት ንፉግ ዘመን እንዲያበቃ፤ ግራኒቶ የተሰኘ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ጥናት ማዕከል፤ ጋዜጦች ማስታወቂያ ማሳደዳቸውን ትተው አንባቢዎችን ለመማረክና ለመሳብ ቢታትሩ፤ የአንባቢያቸው ቁጥር ስለሚያድግ ስርጭታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ከማስታወቂያ የሚያገኙት ገቢም የዛኑ ያህል ያድጋል በሚል ዕምነት ጋዜጦች ጥራታቸውን ለማሻሻል የሚያግዙ ስልቶችን ያመላክታል። ቀዳሚው ፦ ጋዜጦች ይዘት ላይ ትኩረት ሰጥተው አበክረው መስራት እንዳለባቸው ያሳስባል። ይህን ማሳሰቢያ፣ “አዲስ ዘመን”ም ለእኔ ብሎ ያነባል። ይሰማል ብዬ አምናለሁ። ወደ ማሳሰቢያው ስንመለስ፣ ይዘታቸው ለአንባቢው ወጥ ማብራሪያ የሚሰጥ፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ያካተተ፤ ሚዛናዊ፣ ገለልተኛ፣ በታማኝ ምንጭ የተጠናቀረ፣ ተጨባጭ፣ የሙያ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ፣ አንባቢውን አሳታፊ፣ …፤ ከሆነ፤ ማስታወቂያ አሳዳጅ መሆናቸው ቀርቶ በተቃራኒው እነሱ በማስታወቂያ ጋጋታ ተሳዳጅ ይሆናሉ ይለናል። ጋዜጦችም አንባቢ አሳዳጅ ይሆናሉ። ጋዜጦችም ሆኑ መፅሔቶች የአንባቢያቸውን ቁጥር ሲያሳድጉ፤ በአዋጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሲሰማሩ እና በበጎ አድራጎት፣ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ተዋናይ ሲሆኑ ተቀባይነታቸው፣ ከበሬታቸው ከፍ ከፍ ስለሚል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይጠቁማል።
አዲስ ዘመንም ሆኑ ሌሎች እህት ህትመቶች በድረ ገፅ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተደራሽ እንዲሆኑ አበክረው መስራትና ራሳቸውን ወዲያው ወዲያው ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ ይጠበቅባቸዋል። ሙሉ በሙሉ ኦን ላይን ስለመሆንና በዲጂታል ክፍያ ለአንባቢያቸው ተደራሽ ስለመሆን አበክረው ሊተጉ ይገባል። ድረ ገጻቸው ለእይታ ማራኪና ለአጠቃቀም ቀላል ሆኖ እንደ ገና መገንባት አለባቸው። ከፎቶ በተጨማሪ በቪዲዮም መታጀብ ይጠበቅባቸዋል። እንደ ፌስ ቡክ፣ ቲዊተር፣ ዩቲውብ፣ ቴሌ ግራም ካሉ መድረኮች /ፕላትፎርምስ/በተጨማሪም በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በቀላሉ ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል። በ” ኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት “ድረ ገጽ በኩል የሚገኙት ጋዜጦችም ሆኑ ሌሎች ጋዜጦች በሒደትና በቅደም ተከተል የራሳቸው ገጽ ሊኖራቸው ይገባል። ዙሪያ ጥምጥም ለመዳከር ወጣቱ ትዕግስቱም ጊዜውም የለውም። አዲስ ዘመን፣ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ ዘመን መፅሔት፣ ወዘተረፈ በኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ስር ከሚሆኑ ራሳቸውን ችለው በድረ ገጽ ቢወጡ ተመራጭ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። የጋዜጣውን ይዘትና የርዕሰ ጉዳይ ስብጥር ከማሻሻል ጎን ለጎን ሌይ አውቱና ዲዛይኑ፤ የፎቶዎቹን፣ የወረቀቱንና የሕትመቱን ጥራት ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ከምንጊዜም በላይ ለእይታ የሚማርኩና ለማንበብ ቀላል መሆን ይኖርባቸዋል። የጹሑፍ ስራ እንደ ሽንፍላ በአንድ ጊዜ የማይጠራ ስህተት የማይጠፋው መሆኑ ቢታወቅም ከመስከ ዘጋቢ እስከ መጋቢ አርታኢ ያለውን እረጅም ሂደት አልፎ በምንም ሁኔታ ስህተት ለህትመት መብቃት የለበትም። ስህተትን አምርሮ የሚጠየፍ የአርትኦት ባህልን ተቋማዊ ማድረግ ላይም ሊሰራ ይገባል። የማሻሻያ ስራዎችን ለመተግበር ከፍ ያለ ሀብት ስለሚጠይቅ ገቢ የሚያስገኙ ዘርፈ ብዙ ስልቶችን መቀየስ፤ ፈንድና እርዳታ ማፈላለግ አለበት። የገበያ ሽያጩ /ማርኬቲንግ/ ላይ የስርጭት መጠኑንና የሚያዳርሳቸውን ክልሎች ከሁሉም በላይ ብሔራዊ ጋዜጣነቱን የሚመጥን ስራ አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል። የድርጅቱን ጋዜጦች በተለይ “አዲስ ዘመን”ን በተለያየ ስልት ስለ ማስተዋወቅም ማሰብ ይኖርበታል። ወቅታዊና ሀገራዊ ውይይቶችን፣ ሽልማቶችንና ሌሎች ሁነቶች /ኢቨንትስ / በማዘጋጀት ተቋማዊ ኃላፊነትን በመወጣት እግረ መንገድ ራሱን ለማስተዋወቅ የሚያግዘውን መድረክ መፍጠር ይቻላል።
አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞላው 21 ዓመት ብቻ እንደ ቀረው አንጋፋ ጋዜጣ በተለይ በሕትመት ጋዜጠኝነት የልህቀት ማዕከል /ሴንተር ኦፍ ኤክሰለሲ/ ሆኖ ስለመውጣት፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የሕዝብ አስተያየቶችን፣ ምርምሮችን፣ ስልጠናዎችንና ከመጽሔትና ጋዜጣ ከፍ ያሉ ህትመቶችን ስለማዘጋጀት ከፍ ሲልም ለራሱም ሆነ ለሌሎች ሚዲያዎች የሚያገለግል የተሟላ ቤተ መፅሐፍት ያለው የስልጠና ማዕከል ስለመመስረት አበክሮ ሊያስብ ይገባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com