አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዛሬ የ79 ዓመት አልማዛዊ የልደት በዓሉን ሻማ የሚለኩስበት ዕለት ስለሆነ “በእንኳን አደረሰህ” መልካም ምኞት መዘከሩ አግባብ ብቻም ሳይሆን ተገቢም ነው። ጋዜጣው የኢትዮጵያን ታሪክ በጫንቃው ላይ የተሸከመ ባለ አደራ “ቤተ መዘክር” ጭምር ስለሆነ የአገልግሎቱ ውለታ በሚገባ ሊታወስ ይገባዋል። ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በድህረ ፋሽስት ወረራ ማግሥት የአዲሱን መጻኢ ዘመን ተስፋ እንዲያበስር በማሰብ “አዲስ ዘመን” ብለው ሰይመው የመጀመሪያ ዕትሙ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የተጓዘባቸው ጎዳናዎች በብዙ ገጠመኞች የዳበሩ ናቸው። ጋዜጣው የዕለት ዜና አብሳሪ ብቻ ሳይሆን ትናንትን የምንመረምርበት ሀገራዊ የመረጃ ማይስክሮኮፓችን ጭምር እንደሆነ የምንመሰክረው በእውነትና ስለ እውነት ነው።
መንግሥታዊው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የየሥርዓተ መንግሥታቱን ትንሣዔና አወዳደቅ፣ ብርታትና ሽንፈት፣ ልማትና ጥፋት፣ ኀዘንና ደስታ፣ መውጣትና መግባት፣ ፍልሚያና ጥሎ መነሳት፣ አሸናፊነትና ተሸናፊነት ወዘተ. ሁለንተናዊ ዜና መዋዕል የመመዝገብ ኃላፊነት የነበረው ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ሞቅ፣ አንዳንዴም ቀዝቀዝ እያለም ቢሆን የነጠረ የሕዝብ ድምጽ በመሆን ማገልገሉም የሚካድ አይደለም። አንዳንድ ተቺዎች የጋዜጣው ሁለንተናዊ ነፍስ የሚንቀሳቀሰው በየሥርዓቱ ገዢዎች የፖለቲካ እስትንፋስ ብቻ እንደሆነ ደምድመው ሲሄሱ “አለማወቃቸው እንደሚያስተቻቸው” የገባቸው አይመስልም። በጸሐፊው የግል እምነት “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የተሸከመው ስም በራሱ የማይደበዝዝ፣ ትርጉሙ ላቅ ያለና ፋይዳውም እጅግ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ምስክርነቱን የሚሰጠው የረጅም ዓመታት ቤተኛ ጸሐፊነቱን ዋቢ በማድረግ ጭምር ነው።
የጸሐፊውና የ“አዲስ ዘመን” ትውውቅ፤
ጸሐፊው ዳግላስ የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ገጾች በመግለጥ የንባብ ድክድኩን የጀመረው ገና በጨቅላነቱ የዕድሜ ዘመን ነበር። “ንባብ ወዳድ” የሆኑት የቤተሰቦቹ አባላት በየዕለቱ ምሽት ወደ ቤት ይዘው በሚመጡት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ክርክርና ውይይት ይደረግ የነበረው ትርክክ ያለ የከሰል ፍም በታቀፈ እንክርት (ምድጃ) ዙሪያ ከበው እንደነበር ትዝታው ዛሬም ትኩስ ነው። በቤተሰቡ የኖረ ልማድ መሠረት በሚደምቀው የቡናና የሻይ ጭውውት መሃል አዲስ ዘመንም በዋነኛነት የመወያያ ርዕስ መሆኑ ልዩ ትዝታ ያጭራል።
የጋዜጣው ጽሑፍ ዳር እስከ ዳር ተነቦ እንዳበቃ ለታሪክ ፍጆታነት እንዲቀመጥ የሚመረጠው የጋዜጣው ቁራጭ ተቀዶ ይወጣና ቀሪው ገጾች የቤታችንን ሳሎንና የመኝታ ክፍሎችን ግድግዳዎች ያስውቡበት ነበር። ከዚህ በኋላማ ያለ ምንም ከልካይና ክልከላ ከግድግዳው ዳር እስከ ዳር የተለጠፉትን የጋዜጣውን ገጾች እንደ ልብ እየተዟዟሩ ቀኑን ሙሉ ሲያነቡ መዋል የእኔና የእህቶቼ ዋና ስራ ነበር። ምናልባትም ለብዙ እኛን መሰል የዘመኑ ታዳጊ የኢትዮጵያ ልጆችና ወጣቶች ጋዜጣው ለንባብ አፍ መፍቻነት ባለውለታ ነበር ቢባል ዋሾ አያሰኝም።
ከልጅነት የጀመረው የጸሐፊውና የጋዜጣው ወዳጅነት ይበልጥ በቤተኛነት የተጠናከረው ከዛሬ ሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት ጋዜጣው በጎልማሳነት፣ ጸሐፊው ደግሞ በአፍላ የወጣትነት ዕድሜ ላይ በነበሩበት ዓመታት ነበር። ጥር 3 ቀን 1977 ዓ.ም “ሀ – በጽጌሬዳ ብዕር” በሚል ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጣው ሥነ ጽሑፋዊ የሂስ ሀተታ ደግሞ በመነሻነት ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዜና፣ የመረጃና የአዝናኝነት አገልግሎቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙ ጎምቱ የሀገራችን ደራስያን እንደ ከዋክብት እንዲደምቁ ምክንያት መሆኑም ጎልቶ ይዘከራል። ለአብነት እንዲረዳም እውነታውን በማስረጃ አስደግፌ ልዘርዝር። ጋዜጣው ከሰኞ በስተቀር በሳምንት ስድስት ቀናት በሁለት ገጽና በ10 ሺህ ቅጂዎች ለንባብ ከበቃበት ከግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 24 ገጾች መታተም እስከ ጀመረበት እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ ጋዜጣውን በዋና አዘጋጅነት ይመሩ የነበሩት አምስት ጋዜጠኞች ከሙያቸው ጎን ለጎን ሁሉም የሀገራችን “ከባድ ሚዛን” ጎምቱ ደራስያን ነበሩ።
ዝርዝራቸው እንደሚከተለው ይወሳል። ከ1933-1953 ዓ.ም የመጀመሪያውና ለረጅም ዘመን ያገለገሉት የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ በተለያዩ ዘውጎች ለአንባቢያን የቀረቡ 13 መጻሕፍት የደረሱ ብርቱ ብዕረኛ ነበሩ። “ታሪክ አይሙት እንዲያጫውት 1957 ዓ.ም” እና “አግዓዚ 1960 ዓ.ም” በሚል ርዕስ የሚታወቁት ሁለቱ መጻሕፍታቸው ቀድመው ይጠቀሱላቸዋል።
ሁለተኛው የጋዜጣው አዘጋጅ (ከ1953-1960 ዓ.ም) የነበሩትና የጋዜጣውን “ርዕሰ አንቀጽ” በስያሜነት ያስተዋወቁት ነጋሽ ገ/ማርያም “ሴትኛ አዳሪነት” በሚል ርዕስ የብዕር ስም በመጠቀም አንድ ልቦለድ መጽሐፍና ሁለት አይረሴ የሙሉ ጊዜ ቴያትሮችን (የድል አጥቢያ አርበኛ እና የአዛውንቶች ክበብ) ለሕዝብ ያቀረቡ አንጋፋና ተወዳጅ ደራሲ ነበሩ። እኒሁ ሰው በውጭ ሀገር በሙያው ሰልጥነው ከመጡ ጥቂት ጋዜጠኞች መካከልም በቀዳሚነት መጠቀሳቸው እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን ከምሥረታ እስከ አመራር የዘለቀ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሀገር ባለውለታና ተጠቃሽ ባለታሪክም ናቸው።
ለአጭር ወራት ያህል ቢሆንም ሦስተኛው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበረውና ዕድሜውን በሙሉ ከጋዜጠኛነት ያልተለየው ጳውሎስ ኞኞ ሃያ ያህል መጻሕፍትን በመድረስ በሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የጎላ አሻራ ያሳረፈ ጋዜጠኛና ደራሲ ነበር። ደራሲው በአፀደ ሥጋ ከተለየን በኋላም በ2003 ዓ.ም የታተሙት ሁለቱ መጻሕፍቱ (አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች) ታሪካችንን የተሸከሙ ግዙፍ ሰነዶች ናቸው። ይህ ጸሐፊ የሁለቱ መጻሕፍት ኤዲተር በመሆንና መጻሕፍቱ ታትመው ለሕዝብ እንዲደርሱ ባደረገው አስተዋጽኦ ልቡ በሀሴት ይሞቃል።
አራተኛው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበረው ብርሃኑ ዘሪሁን (ከ1961-1963 ዓ.ም) ከጋዜጠኛነቱ ጎን ለጎን በሥነ ጽሑፋችን ታሪክ ውስጥና በደራስያን ማኅበር ምሥረታና አመራር ሰጪነት ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ ከሥነ ጽሑፍ ባለታሪኮቻችን መካከል በመሠረት ጣይነት የሚጠቀስ ነው። ደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁን አሥር የልቦለድ መጻሕፍትና ስምንት ያህል ቲያትሮች በመድረስ የአኩሪ ታሪኩን አሻራ አትሞ አልፏል። ከመጻሕፍቱ መካከል “የቴዎድሮስ እምባ፣ ሦስቱ ተከታታይ በማዕበል አብዮት (ዋዜማ፣ መባቻና ማግሥት) የተሰየሙ መጻሕፍቱና ተነቦ የማይሰለቸው “የታንጉት ምሥጢር” ልቦለድ መጽሐፍቱ በዘመን ተሸጋሪነታቸው ሲጠቀሱ የሚኖሩ ናቸው። “ሞረሽ፣ ጣጠኛው ተዋናይ እና ባልቻ አባ ነፍሶ” በሚሉ አርእስት ለመድረክ የበቁት የተውኔት ሥራዎቹም የጋዜጠኛና ደራሲ ብርሃኑን ስም አግዝፈው የማወጅ አቅም ያላቸው ናቸው።
የጋዜጣው አምስተኛ አዘጋጅ በዓሉ ግርማ ነበር። በዓሉ በጋዜጠኛነቱ ብቻ ሳይሆን በደራሲነት የላቀ ክህሎቱም በተወርዋሪ ኮኮብነት የሚገለጽ የጥበቡ ኩራት ነው። ስድስቱ መጻሕፍቱ (ከአድማስ ባሻገር፣ የኅሊና ደወል፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ ደራሲው፣ ሐዲስ እና ኦሮማይ) ዘመንና ትውልድ እየተሸጋገሩ የሚነበቡ የድርሰት ሥራዎቹ ናቸው። በተለየ ሁኔታ ግን “ኦሮማይ” መጽሐፉ ሰበብ ሆኖበት አማሟቱ ምሥጢራዊ ሆኖ የመስዋዕት በግ ሆኖ በመቅረቱ እንቆቅልሹ አልፈታ እንዳለ ዛሬን ደርሷል። እንዲያም ቢሆን ግን በዓሉ በሥራዎቹ ሕያው ሆኖ እንዲኖር ስሙን ከመቃብር በላይ ተክሎ ማለፉ በብዙ ያጽናናል።
በሁለተኛው ዘመን በዘመነ ደርግ ጋዜጣውን በዋና አዘጋጅነት የመሩት ግለሰቦች በሙሉ (ማዕረጉ በዛብህ፣ ጎሹ ሞገስ፣ መርዕድ በቀለ፣ ፀሐዬ ደባልቀውና እምሩ ወርቁ) ምክንያቱ ወደፊት በሚገባ እስኪፈተሽ ድረስ ይህ ነው የሚባል የመጻሕፍት ትሩፋት ትተውልን አላለፉም። የዘመኑ ክብደት ይሁን የእነርሱ ብርታት ወደፊት በምርምር የሚጠራ ይሆናል።
በሦስተኛው በዘመነ ኢህአዴግ ዓመታት ከነበሩ የጋዜጣው ዋና አዘጋጆች መካከል ለወራት ያህል በዋና አዘጋጅነት ጋዜጣውን ከመራው ከታደለ ገድሌ (ዶ/ር) እና ከደምሴ ጽጌ በስተቀር መጻሕፍት ለማዘጋጀት የሞከሩ አልነበሩም። በሀገራችን በስለላ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ መጻሕፍትን በመተርጎም የሚታወቁትና ወደ ሃምሳ አራት የሚጠጉ መጻሕፍትን በማሳተምና ቴያትሮችን በመድረስ ዝናን የተጎናጸፉት ማሞ ውድነህም ምንም እንኳ ጋዜጣውን በዋና አዘጋጅነት ለመምራት ባይታደሉም በጋዜጣው ላይ በነበራቸው አሻራ ግን የደመቀ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሌላው ተጠቃሽ ታሪኩ ከዋና አዘጋጆቹ ጀምሮ እስከ ተሳታፊ ጸሐፍት ድረስ በብዕር ስሞች ይደረግ የነበረው “የሃሳብ ፍልሚያ” ሳይጠቀስ አያልፍም። ከምፅዓተ ደርግ በፊትና በኋላ (ለጥቂት ዓመታት ቢሆንም) በጋዜጣው ላይ ይወጡ የነበሩት የልዩ ልዩ ርዕዮት አራማጅ ቡድኖችና ግለሰቦች ጽሑፎች (መኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ ሰደድ፣ ወዝ ሊግ ኢጭአት ወዘተ.) የሚዘነጉ አይደሉም። እነዚህ የፖለቲካ ቡድኖች ከ1966 ዓ.ም የመጨረሻው ዓመታት ጀምሮ እስከ ተወሰኑ ዓመታት ድረስ ጋዜጣውን በመድረክነት በመጠቀም ያደርጉት የነበረው ክርክርና ሙግት እንደ አጀማመሩ በሰላማዊነት ቢቀጥል ኖሮ የዴሞክራሲው ጥንካሬ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ በላቀ ሁኔታ ሊጎለብት ይችል እንደነበር ብዙዎች ምስክርነት ሰጥተዋል።
ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ማሕበራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የብዕር ስም በሚጠቀሙ ጸሐፍት በጋዜጣው ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች ምናልባትም ከጋዜጣው ወርቃማ ዘመናት መካከል ተቀዳሚ ዘመን ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል። ከጸሐፍቱ መካከል የጋዜጣው ዋና አዘጋጆች፣ በርካታ ተሳታፊ የውጭ ጸሐፍት እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሳይቀሩ ጎራ ለይተው በብዕር መፋለማቸው የሚያስደንቅ ክስተት ሊባል የሚችል ነበር። ለማሳያነት እንዲያግዝ የጥቂቶቹን ዝርዝር እንደሚከተለው ለማስታወስ እሞክራለሁ።
የፕሬስ ድርጅት የወቅቱ ሥራ አስኪያጅ ትንታግ ብዕረኛው ሙሉጌታ ሉሌ (ስንሻው ተገኝ እና ተርቡ)፣ መርስዔ ሀዘን አበበ (ዘለሌ ዘግንፍሌ)፣ ብርሃኑ ዘሪሁን (መርቆሪዮስ)፣ ሌ/ኮሎኔል ጌታቸው መኮንን (ጎርጎሪዮስና ማኅተመ ጌጡ)፣ እሸቱ ተፈራ (ሽጉጤ ቲመርጋ)፣ መጽሐፈ ሲራክ (ቋያው)፣ ግርማ ፈይሳ (ዳንዴው ሰርቤሎ)፣ ቀሲስ ሰለሞን ገ/ሥላሴ (ባጎር)፣ የወቅቱ የባህል ሚኒስትር ሻለቃ ግርማ ይልማ (ቡልቡላ ዘመርካቶ)፣ መንክር ወርቁ (አሸናፊ ዘደቡብ አዲስ አበባ እና ሸበሉ)፣ ጌታቸው በለጠ (ዳግላስ ጴጥሮስ እና ዳኘው)፣ ዓለማየሁ አበበ (ፉላስ ዘዮሐንስ)፣ ሻለቃ ተዘራ (መድፉ)፣ አጥናፍ ሰገድ ይልማ (አባ ገምባው) ወዘተ. እነዚህና በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ የብዕር ጀግኖች በዚህ ታሪካዊ የአዲስ ዘመን ጋዜጣና በፕሬስ ድርጅት ሥር ይታተም በነበረው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ (ከ1935-1987 ዓ.ም) መድረክነት ያደርጉት የነበረው ነጻ የብዕር መሞሻለቅ በፍጹም የሚዘነጋና የሚደበዝዝ አይደለም። እግረ መንገዴንም እጅግ ተወዳጅ የነበረውና በፕሬስ ድርጅት ሥር ይታተም የነበረው የአዲስ ዘመን ዘመነ ጓድ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ በዘመነ ኢህአዴግ ጎምቱ ሹመኞች ቀጭን ትዕዛዝ ለምን ሊቋረጥ እንደቻለ መርምሮ ምሥጢሩን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ተገቢ ስለሆነ የታሪክ ተመራማሪዎች ጉዳዩን ቢፈትሹት አይከፋም።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚሞካሸው (በአንዳንዶች ዘንድ አላግባብ መተቸቱ እንዳለ ሆኖ) ለዕለት የዜና ምንጭነት ስለሚያገለግል ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን የዓመታት ታሪኮችና የአርአያ ሰብ ትዝታዎችንና ውሎዎችን ሰንቆ በትከሻው ላይ የተሸከመ የዕድሜ ባለጠጋ ስለሆነ ጭምር ነው። በዚሁ ታላቅ አገልግሎቱ የተነሳም ቢሞገስ ያንስበት ካልሆነ በስተቀር የሚበዛበት አይሆንም። ከጋዜጣው መደበኛ ተልዕኮ ጎን ለጎንም ለበርካታ ደራስያን መፈጠር ግዙፍ ድርሻ ማበርከቱን አስታውሰን የ79 ዓመት ዕድሜውን ማክበሩ ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ለዚህም ነው ለዕድሜ ጠገቡ ጋዜጣ በልደተ ቀኑ የገዘፈውን ሀገራዊ ውለታውን በማስታወስ “መልካም ልደት” እያልን በመዘመር ወደ ሰማኒያኛው ዕድሜው የምናሸጋግረው።
በመጨረሻም፤ አዲስ ዘመን ጋዜጣችን የዕድሜውንና የሚጠበቅበትን ያህል በይዘትም ሆነ በሥርጭት ስፋት ገና ከውስንነት ስላልተላቀቀ ለነገ ይደር ሳይባል ልዩና አፋጣኝ ትኩረት ተሰጥቶት ችግሩ እንዲቀረፍ ጥቆማ መሰንዘር ብቻ ሳይሆን የከበደና ጠበቅ ያለ አደራ ለአስተዳዳሪዎቹ በመተው “የልደት ሻማውን እንለኩሳለን! ለክብሩ የተዘጋጀውን ድፎ ዳቦም እንባርካለን! “መልካም ልደት! አዲስ ዘመን!”። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2012
(በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)