አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በየክልሉ መቋቋም እንዳለባቸው በህገ መንግሥቱ ቢቀመጥም ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ የፌዴራል ጉዳዮች በተገቢው መልኩ በክልሉም ሆነ በፌዴራል ደረጃ እንዳይታዩ ከማድረጉም በላይ በክልሎች ላይ የተለያዩ ችግሮች እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
በህገመንግስቱ አንቀጽ 78 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እንደተቀመጠው፤ «የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በአገሪቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲደራጁ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊወስን ይችላል። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ አኳኋን ካልተወሰነ የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል» ይላል። ይሁንና በተወሰኑ ክልሎች ብቻ በመቋቋሙ አብዛኞቹ ክልሎች የፌዴራል ጉዳዮችን በውክልና እንዲያዩ ተገደዋል ያሉት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቂርቆስ ምድብ የባንክና ኢንሹራንስ ችሎት ዳኛ አቶ ጌታሁን ገብረመስቀል ናቸው።
እርሳቸው እንዳሉት፤ የፌዴራል ጉዳዮችን በክልል ደረጃ ባሉ ፍርድ ቤቶች በውክልና እንዲታዩ መደረጉ ክልሎችን ላልተፈለገ ወጪ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል። የፌዴራል ጉዳዮችንና የክልል ጉዳዮችን ነጥለው እንዳያዩ እንቅፋት ይፈጥራል። በተለይም የክልሎችና የፌዴራል ጉዳዮች በአንድ ፍርድ ቤት ብቻ መታየቱ የጊዜ ርዝማኔን ይጨምራል። በዚህም ማህበረሰቡ ለእንግልት ይጋለጣል። የፌዴራልና የክልል ጉዳዮችን ለይቶ የመስራቱ ሁኔታም አይኖርም። ሁለቱንም የመቀላቀል ሥራ በመስራት እንግልትን ይጨምራል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በህዝብ ተወካዮች ውሳኔ መሰረት በቋሚነት በአምስት ክልሎች የተቋቋመ ቢሆንም የአቅም ውስንነት በመኖሩ ከውክልና ባልተናነሰ መልኩ ነው እየተሰራባቸው ያሉት የሚሉት አቶ ጌታሁን፤ የተደራጀ አሰራር ተፈጥሮ በቋሚነት የማይሰራ ከሆነና በተዘዋዋሪ ችሎት የመስራቱ ሁኔታ ከቀጠለ ከውክልናው የሚሻልበት ሁኔታ አይፈጠርም ብለዋል።
እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶቹ በምክርቤት በቋሚነት የተቋቋመባቸው ቦታዎች ብዙም ጉዳይ የማይመጣባቸው ናቸው። በብዛት ጉዳዮች የሚያስተናግዱት እንደ እነ አማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ያሉ ክልሎች አሁንም ህጉ በሰጣቸው ውክልና ስለሚሰሩ የክልልና የፌዴራል ጉዳዮች ተነጥለው እንዳይሰሩ ያደርጋል። አቅም ባለው ዳኛ ጉዳዮቹ እንዳይታዩ ይሆናል።
የክልል ፍርድ ቤቶችና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ግንኙነት ጥብቅ ባለመሆኑም የተነሳ የተለያዩ የፍትህ መጓደሎች ሊያጋጥሙ ይችላል ያሉት አቶ ጌታሁን፤ የፌዴራል የፍርድ አሰጣጥና ፋይሉ ያለበትን ሁኔታ ያለመረዳት ችግሮች ማጋጠም፣ በቅርብ ተገናኝቶ ያለመወያየትና መፍትሄ ያለመስጠቱ ሁኔታ እንዲሁም የክልልና የፌዴራል ጉዳይ መደበላለቅ በሁለቱም ፍርድ ቤቶች ላይ የሥራ ጫና እየፈጠረ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ህዝቡ ላይ የፍትህ መጓደል ይፈጥርና ማህበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን አመኔታ የሚያሳጣው መሆኑን ገልጸዋል።
በየክልሉ የፌዴራል ጉዳዮችን የሚመለከት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቋሚነት ቢቋቋም የክልልና የፌዴራል ጉዳዮች ሳያቀላቅሉ መመልከት ይቻላል። ጫናውና የጊዜ ርዝማኔውም በዚያው ልክ ይቀንሳል። ስለዚህም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ህገመንግስቱ ባስቀመጠው መሰረት በክልሎች ተቋቁመው ብቃት ያለው የፌዴራል ጉዳዮችን የሚያይ ባለሙያ ተመድቦለት ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ መቋቋሙ የፌዴራል ዳኞች ጉዳዩን በፍጥነት እንዲያዩ ያደርጋል። ዜጎችም በፍጥነት ጉዳያቸው ይታይላቸዋል። በተመሳሳይ የክልል ጉዳዮችና የፌዴራል ጉዳዮች ተለይተው እንዲሰሩና እንግልት እንዲቀንስ ያደርጋል። የክልሎችንም ሆነ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ጫናም ይቀንሳል። ዳኞችም ጉዳዮችን አጣርተው የፌዴራሉንና የክልሉን እንዲለዩ አቅም እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተቋቋሙ ቢሆንም፤ በቋሚነት ሥራ እየተሰራ አይደለም፡፡ በአማራ፣ ትግራይ፣ኦሮሚያና ሀረሪ ክልሎች ደግሞ አለመቋቋሙ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው