አዲስ አበባ:- የጥምቀት በዓል አከባበርን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ባህላዊ የዓለም አቀፍ ቅርስነት በወቅቱ እንዲመዘግበው የተጀመረው ጥረት መጠናከር እንዳለበት የበዓሉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የተሳተፉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆነው አቶ ኪሩቤል ነጋሽ እንደገለጸው፤ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ትልቅ ጥምቀት ፌስቲቫል በዓለም አይገኝም። በመሆኑም ክብረ በዓሉን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል።
እንደ አቶ ኪሩቤል ገለጻ፤ ጥምቀት በርካታ ህዝብ በአንድነት ወጥቶ በአደባባይ የሚያከብረው እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔው ለየት ያለ ነው። በመሆኑም በዓለም ቅርስነት አስመዝግቦ ኢትዮጵያንም ለሌላው ዓለም ይበልጥ በበጎ ጎን እንዲያውቃት ማድረግ ይገባል። ነጮች አንድ ታሪክ እና ስርዓት ካላቸው ያንን ተጠቅመው እራሳቸውን ለማስተዋወቅ የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያም ይህን ልምድ በመከተል ጥምቀትን በማይዳሰስ ቅርስነት በማስመዝገብ መጠቀም ያስፈልጋል።
በቤተሰቦቹ ኢትዮጵያዊ ደም ያለው አሜሪካዊው ወጣት ናቲና ሊዮ እንደሚገልጸው ደግሞ፤ የጥምቀት አከባበር ለተመልካቹ ሳቢ እና ከሌላው ዓለም ለየት ያለ ስርዓት ያለው ነው። በመሆኑም የበለጠ እንዲታወቅ የሚያደርጉ የቅርስ ምዝገባ ሥራዎች ያስፈልጉታል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የዩኔስኮ ምዝገባ አንዱ በመሆኑ በወቅቱ ጥምቀትን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ይገባል። ለዚህ ሥራ አሁን ካለው በላይ በውጭ እና በአገር ውስጥ ያሉ ሰዎችን አስተባብሮ ተጨማሪ ጥረት ማድረግ ይገባል ብሏል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ እንደገለጹት፤ጥምቀት ለአፍሪካም ለዓለም ህዝቦች በአግባቡ ሊያውቁት የሚገባ ስርዓትና ባህል ነው። የጥምቀት አከባበርን በዓለም የዩኔስኮ የቅርስ መዝገብ ለማስፈር የሚደረገው ጥረት ታላቅ ድጋፍ ይፈልጋል።
በሚቀጥሉት አጭር ዓመታት የጥምቀት የማይዳሰስ ቅርስነት ምዝገባው እውን እንደሚሆን እንተማመናለን ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፣ «ለዚሁ ሥራ መላው ህዝብ እና የዓለም መሪዎች እንዲሁም የሃሳብ አፍላቂዎች ጭምር ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪ እናስተላልፋለን» ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በአትዮጵያ የጥምቀት በዓል ከጀመረ 1ሺ 600 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ድርሳናት ያመለክታሉ። በአዲስ አበባ ደግሞ ልክ እንደ አሁኑ ሥርዓት ተበጅቶለት በሃይማኖታዊ ሥርዓት መከበር ከጀመረ 130 ዓመታትን እንዳስቆጠረ ታሪክ ያስረዳል። በበዓሉ ወቅት የሚታዩት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች፤ ስነቃሎች አለባበሶች እና ዝማሬዎች እና ሌሎችም የኢትዮጵያን የዘመናት ስልጣኔ የሚፈትነው ናቸው። የጥምቀት በዓል ሥርዓት ተበጅቶለት እና የኢትዮጵያውያን ትውፊት ሆኖ የዘለቀ ህዝባዊ በዓል ነው። በመሆኑን በዩኔስኮም ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል።
የዛሬ ዓመት ልክ በዚሁ ወቅት የጥምቀት በዓል አከባበር በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ አስፈላጊውን መረጃዎች ለዩኔስኮ መላኩ ተገልጾ ነበር። በጎንደር፣ በአክሱም፣በላልይበላና በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ያለውን የጥምቀት በዓል አከባበርን የሚያሳዩ የፎቶግራፍ፣ የጽሑፍ፣ የተንቀሳቃሽ ምስልና የድምጽ መረጃዎች ተደራጅተው ለዩኔስኮ ገምጋሚ አካል መላካቸው የዛሬ ዓመት የቀድሞው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ጌትነት ተስፋማርያም