
አዲስ አበባ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የታሪክ ጎተራ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ስነ ፅሑፍ የፎክሎር ክፍለ ትምህርት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ገብሬ ተናገሩ።
ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የ79 ዓመት የልደት በዓል አስመልክቶ እንደተናገሩት ጋዜጣው በየዘመናቱ የነበሩ የትምህርት፣ የማህበራዊ ኑሮ፣ የልማት፣ የስነ ፅሑፍ፣ የባህል እንዲሁም የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በመሰነድ ረገድ የታሪክ ጎተራነቱን አስመስክሯል ብለዋል። ከ1933 ዓ.ም ግንቦት 30 ጀምሮ ያሉትን የየዕለትም ሆነ የየዘመናት እንቅስቃሴ በሚገባ ለመገንዘብ አዲስ ዘመን እንደ አንድ የመረጃ ቋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ጋዜጣው ከተጀመረ አንስቶ ሦስት የመንግሥት ስርዓቶችን ተሻግሯል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ከአፄ ኃይለስላሴ የንግስና ዘመን እስከ ደርግ ስርዓተ መንግሥት 1966 ዓ.ም፤ ኢህአዲግ መንበረ ስልጣኑን እስከያዘበት ከ1983 ዓ.ም እስከ ከ2010 ዓ.ም እንዲሁም አራተኛ ዘመኑን እስከጀመረበት አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ድረስ የነበሩትን አስተሳሰቦች ሙሉ ለሙሉ ባይባልም በቂ በሚባል ደረጃ በመሰነድ ለታሪክ ፍርድ ማቅረብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
‹‹አንድ ሰው የዘመናዊ ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ ፖሊሲና አስተሳሰቦችን ለማጥናት ፍላጎት ቢኖረው በጊዜው የነበረውን እያንዳንዱን መረጃ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ያገኛል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በእነዚህ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤት ምስረታ፣ በስርዓተ ትምህርት ለውጥ ጭምር በቂ መረጃዎችን ተሰንደው ማግኘት እንደሚቻል ይገልፃሉ። በስነ ፅሑፍ ረገድ እስከአሁን በሚወጡት በአዲስ ዘመን ጋዜጣዎች ልዩ ልዩ አምዶች እየተከፈተ ‹ባህል ፣ሂስ፣ ስነ ግጥም፣ ፅሑፍ… › ይቀርቡበታል ይሄ ደግሞ ለዘመናት እየተሰነደ ቆይቷል።
በአንድ ወቅት የሰአሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች በጋዜጣው ላይ ታትመው ስለነበር ከዚያ ላይ ተሰብስቦ በመፅሐፍ መልክ ለአንባቢ ለመቅረብ መብቃቱ የጋዜጣውን የታሪክ ጎተራነት ያመላክታል በማለት በምሳሌነት ጠቅሰዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪን ጨምሮ የተለያዮ ምርምሮችን ለሚያደርጉ ተማሪዎችና መምህራን እንደ ትልቅ ግብአት እንደሚውልም ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ገልጸዋል።
በቀጣይ ዘመናት ጋምቤላ ጫፍ ያለ ገበሬ ምን ይላል፣ ዛላንበሳ የምትኖር እናት ፍላጎቷ ምንድነው፤ አፋርና ሱማሌ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች አስተሳሰብስ፤ አንዳቸው ስለሌላኛው ምን ያውቃሉ የሚለውን ጉዳይ አጉልቶ ማሳየት ይጠበቅበታል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ፤ ላለፉት 79 ዓመታት መረጃን በመስጠትና የተለያዩ አስተሳሰቦችን ሰንዶ በማስቀመጥ የሚታወቀው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አሁንም ይሄን ሚናውን አጠናክሮ ሌላ ብዙ ዘመናትን መሻገር አለበት በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2012
ዳግም ከበደ