እንደ አለመታደል ሆኖ በመጀመር ፣ ፋና ወጊ ፣ አልፋ በመሆን ፤ መንፈሳዊውንም ሆነ አለማዊውን ዳና ፣ ፋና በመከተል የሚቀድመን የለም ። ጅምራችንን በውጥን ምዕራፍ ሳያገኝ በማስቀረትም የሚወዳደረን የለም ። እንዲህ በተቃርኖ ከወዲያ ወዲህ የምንላጋ ባተሌዎች ነን ። በወረት በአንድ ሰሞን የሆነን ነገር ፣ ሰውንና ልማድን መከተል ፣ መደገፍ ፣ መቃወም ፤ በወረት አዲስ የተከፈተ ቤተ ክርስቲያን ፣ መስጊድ ፣ ትምህርት ቤት ፣ ኤፍ ኤም ፣ ቲቪ ፣ ሞል ፣ ጤና ተቋም ፣ ምግብ ቤት ፣ የውበት ሳሎን ፣ ቡቲክ ቤት ፣ ኬክ ቤት ፣ መሸታ ቤት ፣ ወዘተረፈ ደንበኛ የመሆን አባዜ አለብን ።
ወረቱ ሲያልቅ ደግሞ እርግፍ አድርገን እንተወዋለን ። እስከ መፈጠሩም እንረሳዋለን ። ይህ አባዜያችን በምንመገበው ምግብና በምንለብሳቸው አልባሳት ሳይቀር ይንጸባረቃል ። በ19ኛው ማብቂያና በ20ኛው መ/ክ/ዘ በሀገራችን የተጀመሩ የእውቀት ፣ የስልጣኔ ሽግግሮችንና ልምምዶች ብናይ ዛሬ የሚገኙበት ደረጃ አነሳሳቸውን የሚመጥን አይደሉም ። ኢቲዮ ቴሌኮም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ቴክኖሎጂው በተፈጠረ በጣት በሚቆጠሩ ዓመታት ወደ ሀገራችን ቢገባም በአገልግሎት ጥራትም ሆነ በዋጋ እንዲሁም በተደራሽነት ትናንት ሀገር ከሆነችው ጁባና ያለመንግስት ስትተራመስ ከኖረች ሞቃዲሾ እንኳ በእጅጉ የወረደ ነው።
በነገራችን ላይ በኮቪድ – 19 ገመናቸው ከተጋለጡ ተቋማት ቀዳሚው ኢቲዮ ቴሌኮም ነው ። ድንገት ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች ኦን ላይን ይሁኑ ሲባል አይደለም ክልሎች ላይ አዲስ አበባ ላይም ወገቤን ነው ያለው። ኔት ወርኩ እጅግ ደካማና በአንዳንድ ሰፈር ደግሞ ጭራሽ ባለመኖሩ ወላጆች ራሳቸውን ለወረርሽኙ በማጋለጥ የልጆቻቸውን የቤት ስራ ትምህርት ቤታቸው ድረስ እየሄዱ በፍላሽ ለማመላለስ ተገደዋል። አበው እማት የእንጨት ሽበት እንዲሉ ።
ከማህበራዊ ወረቶች አንዱ የሆነው የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት አብሮን ለዘመናት የኖረ ቢሆንም እንደ እድሜው አላደገም። አልጎለመሰም። አለማም። አልበለፀገም። ሌላው ይቅርና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በወረት የተጀመሩ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎቶችን እንይ ፤ የአረጋውያንን ቤት መጠገን ፣ በሆስፒታሎች የአንድ ተከታታይ ድራማ ቡድን አባላት የጀመሩት የፅዳት ስራ ፣ የአካባቢ የጽዳት ስራ ፣ ተማሪዎችን የማስጠናት ፣ ችግኝ የማጠጣት ፣ ለኩላሊትና ለሌሎች ህሙማን ገንዘብ የማሰባሰብ ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴን የማስተናበር እንቅስቃሴዎች ፣ ወዘተርፈ ይቅርና ከቪድ -19 እንደገባ በወጣቶች ፣ እንደ ebs ባሉ ቴሌቪዥኖችና በታዋቂና ዝነኛ ሰዎች ያየናቸው አበረታች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ዛሬ ላይ የት ደረሱ ? የትም።
ወረታቸው አልቋላ። ሆኖም ጥቂት የማይባሉ ቅን ወጣቶችና ወገኖቻችን የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎትን የዕለት ተዕለት የህይወታቸው አካል አድርገው የሚተጉ መኖራቸው አይከዳም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መጥረጊያቸውን ይዘው ሲወጡ ካቢኒያቸው ሳይቀር አዲስ አበቤም መጥረጊያውን ይዞ ንቅል ብሎ ይወጣል። ችግኝ ሲትክሉ ፣ ሲንከባከቡና ውሃ ሲያጠጡም እንደዚሁ። ክፉ አመል። የበጎ ፈቃደኝነትም ሆነ ሌሎች ስራዎቻችን ቀጣይነት ከሌላቸውና ካልተለማመደናቸው ፤ ተቋማዊ ሊሆኑና ትውልድ ባህሉ አርጎ ሊቀባበላቸው አይችልም። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በደመ ነፍስ ፣ በአቦሰጥና በአፈተት ይደናበር የነበረውን የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ተቋማዊ ለማድረግ ራሱን የቻለ ቢሮ ከመቋቋሙ ባሻገር ፖሊሲና መመሪያ መዘጋጀቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችም ይሄን የሚያረጋግጡ ናቸው። በሌሎች ሀገራት በተለይ በበለጸጉት ግን ከህፃንነት ጀምሮ እድሜ ልክ የሚከወን ከመሆኑ ባሻገር ተቋማዊና የዜግነት የውዴታ ግዴታ ነው። አሜሪካዊቷ ዶሪ ኖያክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። ዶሪ የሆሊወድ ሎሳንጀለስ ነዋሪ ነበረች።
ከ17 አመቷ ጀምራ ያለማዛነፍ ለ93 ተከታታይ ዓመታት በሆስፒታሎች የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ሰጥታለች። ሕሙማንን በማፅናናት ፣ በማስታመም ፣ በማገዝ ሳታሰልስ ፣ ሳትሰለች ትተጋ ነበር። ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለህይወቷ ትርጉም ከመስጠት አልፎ ደስተኛና የረጅም እድሜ ባላፀጋ እንዳደረጋት በኩራት ትናገራለች። ዶሪ የ110 አመት የእድሜ ባለፀጋ ስለአደረጋት ሚስጥር ስትጠየቅ ፤ ሌሎችን በቅንነት ፣ በበጎነት ማገልገሏ እንደሆነ ትናገራለች። እዚህ ላይ ከ1ኛ ደረጃ ትምህርታችን ጀምሮ በአርዓያነቷ ስንማራት የኖርናት ማየት የተሳናት ግን ባለ ብሩህ አእምሮዋ ሄለን ከለር በአንድ አጋጣሚ የተናገረችውን ብናስታውስ የዶሪን ሃሳብ ያጠናክርልናል ፤ “ The unselfish ef¬fort to bring cheer to others will be the begin-ning of a happier life for ourselves . “ / ያለ ስስት የሌሎችን ህይወት ለማጣፈጥ የምናደርገው ጥረት ፤ የገዛ ህይወታችንን ደስተኛ የማድረግ ጅማሮ ይሆናል ። / ወደ ሀገራችን ሲመጣ ይሄን የዶሪ መንገድ እንጀምረዋለን ለዛውም በወረት። ዳሩ ግን አይደለም መጨረስ ሲሶውን አንዘልቀውም ።
ለዚህ ነው የመጣጥፌን ርዕስ የዶሪን መንገድ የጀመረው እንጂ የጨረሰው ኢትዮጵያዊ የለም ለማለት የዳዳኝ ። ለምን !? በጎ ፈቃደኛ ትውልድና ይሄን የሚያለማምድ ተቋም እስከ ትናንት መፍጠር ስላልቻልን። ምሳሌና አርዓያ የሚሆን መሪና ተቋም ስላልነበረን ። ለማንኛውም በጎ ፈቃደኝነት ከስጋ መሻት የሚሻገር መንፈሳዊ ተግባር መሆኑን ጭምር ልብ ማለት ያሻል። ለመሆኑ እንዲህ የሚያነዛንዘን በጎ ፈቃደኝነት ትርጓሜው ምን ቢሆን ነው ? እውቀትን ፣ ጉልበትንና ጊዜን ያለ ክፍያ በፈቃደኝነት ለሰው ፣ ለቤተሰብ ፣ ለማህበረሰብ ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ግልጋሎት እንዲውል በማበርከት የተቀደሰ ተግባራ የመፈፀም መርህ ወይም ሥርዓት በጎ ፈቃደኝነት ይሰኛል። የዕለት ጉርስን ለማሸነፍ ጥድፊያና ሩጫ በበዛበት ፣ ዓለም ዘጠኝ በሆነችበት በዚች ጎደሎ ምድር ጊዜውና ጉልበቱ ከየት ተገኝቶና ተርፎ ነው ደግሞ በጎ ፈቀደኛ የሚሆነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ።
ሆኖም ፈቃደኝነቱ ፣ ቅንነቱና ቁርጠኝነቱ ካለ ጊዜንና ጉልበትን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለበጎ ፈቃደኝነት የሚብቃቃ ጊዜም ሆነ ጉልበት አይገድም። በጎ ፈቃደኝነት የሚጠቅመው ግልጋሎቱን ለሚያገኙ ግለሰቦች ፣ ማህበረሰቦችና ተቋማ ብቻ ሳይሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚሰጡትም በርካታ ጥቅም እንዳለው በስፋት እየተቀነቀነ ይገኛል። ይህን የተገነዘቡ ዜጎችም በስፋት በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት እየተሳተፉ መሆኑን መረጃዎች ያረጋግጣሉ። በሀገረ እንግሊዝ የተደረገ አንድ ጥናት ይፋ እንዳደረገው እኤአ ከ2012 እስከ 2013 ከሕዝቡ 29 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች (ጎልማሶች) ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ ። በአሜሪካ ደግሞ ከሕዝቡ 25 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች ( ሴቶች ይበዛሉ)በበጎ ፈቃደኝነት ያገለግላሉ። ከእነዚህ በጎ ፈቃደኞች ከፍ ያለውን ድርሻ የሚይዙት ወጣቶች ናቸው።
የግሪኩ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ የህይወት ትርጉሙ ፣ “ to serve others and do good, ” / ሌሎችን ማገልገልና መልካም ማድረግ ነው ። / እንዳለው ፤ ከቀን ወደ ቀን የበጎፈቃደኝነትን አገልግሎት በመስጠት እግረ መንገድ ህይወታቸውን ለማጣፈጥ በየቀኑ እልፍ አእላፉ ሰዎች በጎነትን እየተቀላቀሉ ነው። በጎ ፈቃደኝነት በሰዎች ፣ በማህበረሰቡና በአካባቢው ዘንድ አስፈላጊና ትርጉም ያላቸው ድጋፎች የሚደረግበት ሰውኛ ክዋኔ ስለሆነ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው። በእርግጥ በርካታ ድርጅቶችና ግብረ ሰናይ አካላት አላማቸውን ለማስፈጸም ባለሙያ ለመቅጠር አቅማቸው ስለማይፈቅድ በጎ ፈቃደኞችን ሥርዓታዊ በሆነ አግባብ ያሳትፋሉ። በዚህም በሀገርና በሕዝብ ዘንድ የሚዳሰስና የሚጨበት ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። በተለይ እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ወረርሽኞች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ያለ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ተሳትፎ ውጤታማ መሆን አይታሰብም ። በጎ ፈቃደኝነት ከሚያጎናጽፈው መንፈሳዊ እርካታ በላይ ስነ ልቦናዊ ጫናን ፣ ድብርትንና ጭንቀትን ለመከላከል ከማገዙ ባሻገር ለሰው ልጆች የሚኖሩለትን ዓላማ በማስጨበጥም ድርሻ አለው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በተደጋጋሚና በተከታታይ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት መስጠት ፤ የዛኑ ያህል የበዛ የጤና ጥቅም ያስገኛል። ይህ ማለት ግን የግድ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ማለት አይደለም።
የአጫጭር ጊዜና ለበጎ ፈቃደኛው ቀላል ለተጠቃሚው ግን ትልቅ ትርጉም ያላቸው የበጎነት ስራዎች ማበርከት ይቻላል። እስኪ በጎ ፈቃደኛ ከመሆን ከሚገኙ ዋና ዋና ጥቅሞች አንድ ሁለቱን እንመልከት። 1ኛ . በጎ ፈቃደኝነት ከሰዎች ጋር የመገናኛ ድልድይ ነው። ብቸኝነትና ባይተዋርነት የሚሰማን ከሆነ ወይም ማህበራዊ ግንኙነታችን የማስፋት ፍላጎት ካለን በምንኖርበት አካባቢ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በመስጠት ከሰዎች ጋር በቀላሉ የመግባባት አጋጣሚ ይፈጥርልናል። በተለይ የመኖሪያ ከተማችንን አልያም ሀገር የምንቀይር ከሆነ ፤ ከማህበረሰቡ ጋርም ሆነ ከሰው ጋር በቀላሉ ለመቀራረብ በጎ ፈቃደኝነት ቀናው መንገድ ነው። በተለይ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመጎዳኘት ያግዛል። በጎ ፈቃደኛ ስንሆን በሌላ አጋጣሚ ከማናገኛቸው እና የተለያየ ማንነት ካላቸው ሰዎች ጋር እንተዋወቃለን። በጎ ፈቃደኝነት ለሁሉም ማንነቶች ክፍት ነውና። በጎ ፈቃደኝነት ዘር ፣ ጎሳ ፣ ሃይማኖት ፣ መደብ ፣ ወዘተረፈ አይጠይቅም።
2ኛ . በጎ ፈቃደኝነት በራስ መተማመንና ለራስ የሚሰጥን ክብርና ግምት ያጎለብታል። በምንኖርበት አካባቢና ማህበረሰብ ይሁን ለሀገርና ለሕዝብ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ስንሰጥና ትርጉም ያለው ለውጥ ስናመጣ። የመጣው ለውጥና ውጤት አካልና ምክንያት ስለሆን በራስ መተማመናችንና ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ከፍ ይላል። ይህ ለቀጣይ ህይወታችን መሰላል ሆኖ ያገለግለናል። 3ኛ . በጎፈቃደኝነት ለአካላዊም ሆነ ለአእምሯዊ ጤንነት ይጠቅማል። የደም ግፊትን በመቀነስ እድሜን ከመጨመሩ ባሻገር ድብርትንና ጭንቀትን በመቀነስ አእምሮን ጤናማ እንደሚያደርግ በዘርፉ የተደረጉ በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
እንደ መውጫ
አንድን ነገር መጀመር በራሱ ግብ አይደለም። ዳር ማድረስ ፣ ማዝለቅና ለውጤት ማብቃት እንጂ።ያለፈውን እንተወውና የለውጡን መባት ተከትሎ የተወጠኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ግራምጣቸው እንደተራሰ ፣ ሰበዙ እንደ ቀራረበ ፣ ወስፌው በውጥኑ እንደተወጋ ትተናቸው እይደል። እስከ መቼ ዳር የማድረስ ፣ የማጠናቀቅ ፣ የመፈጸም ሾተላይ እንደሆን እንቀራለን።
ለነገሩ ስንቶች ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባለሙያ ተቀጥሮላቸው የተጀመሩ ትላልቅና ግዙፉ የስኳር ፣ የግድብና የመስኖ ፣ የመንገድ ፣ ወዘተረፈ ፕሮጀክቶች በጅምር አርጅተው አይደል። የሀገር ምልክት /ፍላግሽፕ ፕሮጀክት/ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብስ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ደርሰው ባይታደጉት ኖሮ ቁሞ ቀርቶ መሳቂያ ሊሆን አልነበር !? ሆኖም በአሰራርና በአደረጃጀት የታገዙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲስፋፋ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ፋና ወጊነት ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸው በልኩ እውቅና ሊሰጠው ይገባል። የአረጋውያንን ቤቶች መጠገን ፣ ችግረኛ ተማሪዎችን መርዳት ፣ ደም መለገስ ፣ ለአካል ጉዳተኞች እገዛ ማድረግ ፣ ጧሪ ደጋፊ የሌላቸውን መደገፍ ፣ የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ ፣ የአረንጓዴ አሻራ ፣ ወዘተረፈ በአርዓያነት ከሚጠቀሱ ዋና ዋናዎች ናቸው። በእሳቸው የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት ሲከተሏቸውና አስፍተው ሲፈጽሟቸው ማየት አለመቻላችን ቢያስቆጨንም። ባለፈው ክረምት በተካሄደው 17ኛው የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መርሃ ግብር ከ10 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት በመስጠት ከ22 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ትልቅ እምርታ ነው። በተለይ ወጣቶች ከክልላቸው ውጪ ሌላ ክልል ላይ የሰጧቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የበለጠ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማወቅ ፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን ለመለዋወጥ ከፍ ሲልም የበለጠ ለመቀራረብ እርሾ ሆኗቸዋል ማለት ይቻላል። በመላው ሀገሪቱ ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን ዘንድሮም በጎ ፈቃደኞችን በስፋት በማሳተፍ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ቸግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅቱ ቢጠናቀቅም በበጋ የበጎ ፈቃደኝነት ስራዎች ራሳቸውን ችለው ከቆሙበት ሲቀጥሉ ብዙ አልተመለከትንም። በጎ ፈቃደኝነትን ተቋማዊ ፣ ባህልና የዕለት ተዕለት የህይወታችን አካል ማድረግ ላይ ብዙ ስራ ይጠብቀናል።
እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎትን የባህላችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን አካል አድርገን አጎልብተን መጠቀም ካልቻልን ፤ ችግሮቻችን ለመንግስትና ለአንዳንድ መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በመተው የምንሻውን መፍትሔ እውን ማድረግ አንችልም። እንኳን እኛ የበለጸጉ ሀገራት እንኳ ያለ በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ተሳትፎ ውጤታማ መሆን እንደማይችሉ በመገንዘብ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎትን ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ በማስተማር ፣ እውቅና በመስጠት ዛሬ ባህላቸው አድርገውታል ማለት ይቻላል። በሀገራችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተቋማዊ ለማድረግ ከተደረጉ አበረታች እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን የሥርዓተ ትምህርቱ አካል ማድረግ በጎነትን ከወረት አላቆ ወደ ሙላት ያመጣዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ፈጣሪ ይጠብቅ ! አሜን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com