በርእሱ እንደተገለፀው ኬሚካሎችን ሲጠቀሙ ጤናዎ የሚታወክ ከሆነ፣ ሁኔታው ኤም ሲ ኤስ (MCS) ወይም መልቲፕል ኬሚካል ሴንሲቲቪቲ (multiple chemical sensitivity) ይባላል። ብዙዎቹ የመልቲፕል ኬሚካል ሴንሲቲቪቲ (multiple chemical sensitivity) ገጽታዎች ግራ የሚያጋቡ ናቸው። በመሆኑም የበሽታውን ባሕርይ በተመለከተ በሕክምናው ማኅበረሰብ መካከል ትልቅ አለመግባባት ይታያል። አንዳንድ ዶክተሮች የኤም ሲ ኤስ መንስኤ አካላዊ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ነው ይላሉ። አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶችን የሚጠቅሱም አሉ። አንዳንድ ዶክተሮች ደግሞ ኤም ሲ ኤስ የጋራ ባሕርይ ያላቸውን በርከት ያሉ በሽታዎች የሚወክል ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ።
የኤም ሲ ኤስ ምልክቶች የሚታዩባቸው ብዙ በሽተኞች ለበሽታው መንስኤ የሆነባቸው ነገር መጀመሪያ ላይ እንደ ተባይ ማጥፊያ ላለ መርዝ በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ዝቅተኛ መጠን ላለው መርዝ በተደጋጋሚ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ መጋለጣቸው የበሽታው ተጠቂ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። በሽተኞቹ አንዴ በኤም ሲ ኤስ ከተያዙ በኋላ እንደ ሽቶና የጽዳት መገልገያ ኬሚካሎች ያሉ ቀደም ሲል ይቋቋሟቸው የነበሩና ምንም ዓይነት ዝምድና ያላቸው የማይመስሉ የተለያዩ ኬሚካሎች የተለያዩ የበሽታ ምልክቶች ያስከትሉባቸዋል። በሽታው “በተለያዩ ኬሚካሎች በቀላሉ መጠቃት” የሚል ስያሜ የተሰጠውም ለዚህ ነው።
አንድ ሰው ከቤት ውጪም ሆነ በቤት ውስጥ ዝቅተኛ መጠን ላለው መርዝ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጥ ይችላል። ይህም ኤም ሲ ኤስ ሊያስከትልበት እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ። እንዲያውም ባለፉት አሥርት ዓመታት በቤት ውስጥ የኬሚካል ይዘት ያላቸው ቁሶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ በመገኘታቸው ሁኔታው በስፋት እየተስተዋለ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። እንዲያውም በቤት ውስጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚከሰት የአየር ብክለት የሚያስከትላቸው ተደራራቢ ችግሮች “የቤት ውስጥ የተበከለ አየር ድምረህመም” የሚል ስያሜ ወጥ ቶላቸዋል።
ይህ የጤና ችግር አንዳንዳችን ሲያጠቃ ሌሎቻችን ላይ ተጽእኖ የማያሳድርብን ለምንድነው?
እዚህ ላይ ሁላችንም ለኬሚካሎች፣ ለጀርሞችና ለቫይረሶች የምንሰጠው ምላሽ የተለያየ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ሁኔታዎቹ የተለያዩ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከልዕድሜ፣ ጾታ፣ የጤና ሁኔታ፣ እየወሰድናቸው ያለናቸው መድኃኒቶች፣ ቀደም ሲል ይዞን የነበረ በሽታ፣ እንዲሁም እንደ አልኮል፣ ትምባሆ ወይም አደገኛ ዕፆች ያሉ ልማዶች ይገኙባቸዋል።
ለምሳሌ ያህል የሕክምና መድኃኒቶችን በተመለከተ አንድ መድኃኒት የተፈለገውን ውጤት ማስገኘት አለማስገኘቱና ሊያስከትለው የሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት በዓይነቱ ልዩ በሆነው ተፈጥሯችን ላይ በእጅጉ የተመካ ነው። ከእነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል አንዳንዶቹ በጣም አደገኛ ሊሆኑ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ። ኤንዛይም የሚባሉት ፕሮቲኖች ሰውነታችንን በመድኃኒቶች ውስጥ ካሉት ኬሚካሎችና በዕለታዊ እንቅስቃሴያችን ወደ ሰውነታችን ከሚገቡ በካይ ነገሮች ያጠራሉ። ሆኖም ይህን የማጽዳት ሥራ የሚያከናውኑት እነዚህ ኤንዛይሞች ምናልባትም በዘር ውርስ፣ ቀደም ሲል መርዛማ በሆኑ ነገሮች በደረሰባቸው ጉዳት ወይም በአመጋገብ ጉድለት ሳቢያ እንከን ያለባቸው ከሆኑ ወደ ሰውነታችን የሚገቡት ኬሚካሎች በአደገኛ ሁኔታ ሊከማቹ ይችላሉ።
እዚህ ላይ ሁላችንም ለኬሚካሎች፣ ለጀርሞችና ለቫይረሶች የምንሰጠው ምላሽ የተለያየ መሆኑን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው።
ኤም ሲ ኤስ ከኤንዛይም ጋር ዝምድና ካላቸው ፖርፊሪያስ ተብለው ከሚጠሩ የደም በሽታዎች ጋር በሚመሳሰል መንገድ ተገልጿል። ብዙውን ጊዜ ከተሽከርካሪዎች ጭስ አንስቶ እስከ ሽቶ ድረስ የተለያዩ ኬሚካሎች የፖርፊሪያስ ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ሁኔታ ኤም ሲ ኤስ ባለባቸው ሰዎች ላይ ከሚያስከትሉት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።
በአእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ
በበሽታው ከተያዙ አንዳንድ ሰዎች ለማወቅ እንደተቻለው የተለመዱ ዓይነት ኬሚካሎችን ሲጠቀሙ እንደሚያፈዛቸው፣ ባህሪያቸው እንደሚለዋወጥ፣ እንደ ሚቆጡ፣ መንፈሳቸው እንደሚረበሽ፣ እንደሚነጫነጩ፣ ፍርሃት ፍርሃት እንደሚላቸው፣ እንዲሁም ሰውነታቸው እንደሚልፈሰፈስ ገልፀዋል። . . . እነዚህ ምልክቶች ለጥ ቂት ሰዓታት እንዲያም ሲል በርከት ላሉ ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ ብለዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ አንጎበርና ደረጃው የተለያየ የመንፈስ ጭንቀት እንዳንዶቹ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
እነዚህ ነገሮች ኤም ሲ ኤስ ላለባቸው ሰዎች እንግዳ አይደሉም። ሰዎች እንደ ተባይ ማጥፊያ ላሉ ኬሚካሎች ሲጋለጡም ይሁን የቤት ውስጥ የተበከለ አየር ድምረ ህመም ሲይዛቸው ሥነ ልቦናዊ ችግር እንደሚገጥማቸው ከደርዘን በላይ የሚሆኑ አገሮች ሪፖርት አድርገዋል። እንዲሁም በበሽታው የተያዙ ሰዎች አሟሚ ለሆኑ ንጥረ ነገሮች ሲጋለጡ በከባድ የፍርሃት ስሜት ወይም በመንፈስ ጭንቀት የመዋጣቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ሐኪሞች ተገንዝበዋል። በመሆኑም በሰውነት ውስጥ ካሉት ሥርዓተ አባላት ሁሉ በኬሚካል በቀላሉ የሚጎዳው አንጎል ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል።
ለኬሚካል መጋለጥ ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሊያስከትል ቢችልም እንኳ የዚህ ተገላቢጦሽ ሊከሰት እንደሚችል ማለትም ሥነ ልቦናዊ ችግሮች አንድ ሰው በቀላሉ በኬሚካሎች እንዲጠቃ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ብዙ ዶክተሮች ያምናሉ። አካላዊ ችግሮች ኤም ሲ ኤስን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አጥብቀው ያምናሉ። የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ወይም ፍቺን የመሰሉ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ገጽታዎች ያሏቸው ክስተቶች በሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓት ላይ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉና አንዳንድ ሰዎችን ዝቅተኛ መጠን ባላቸው ኬሚካሎች በቀላሉ እንዲጠቁ ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ያምናሉ። በሥነ ልቦናዊና በግብረአካላዊ (physiological) ሥርዓቶች መካከል ያለው ዝምድና በእርግጥም በጣም ውስብስብ ነው። ኤም ሲ ኤስ በአካላዊ ችግሮች ሳቢያ ሊከሰት እንደሚችል እንዲሁም ውጥረት አንድ ሰው ይበልጥ በኬሚካሎች እንዲጠቃ ሊያደርገው እንደሚችል ይታመናል። በመቀጠል የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ጤንነታቸውን ለማሻሻል ወይም ቢያንስ ቢያንስ የሚታዩባቸውን የበሽታ ምልክቶች ለመቀነስ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ይኖር እንደሆን እንመልከት።
ኤም ሲ ኤስ የተያዙ ሰዎች ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል?
ምንም እንኳ ኤም ሲ ኤስ ይህ ነው የሚባል ፈውስ ባይገኝለትም ብዙዎቹ ሕሙማን የሚታዩባቸውን የበሽታ ምልክቶች መቀነስ የቻሉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ጤናማ ሕይወት መምራት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ችግሩን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶቹ ሕመማቸውን የሚቀሰቅሱባቸውን ኬሚካሎች በተቻለ መጠን እንዲያስወግዱ ሐኪም የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። አብዛኞቹ የኤም ሲ ኤስ ሕመምተኞች ኬሚካሎችን ማስወገዳቸው በእጅጉ እንደረዳቸው ተናግረዋል።
እንደ ብዙዎቹ የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ምስክርነት ከሆነ፣ በቤት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ብዙ ኬሚካሎች ይረብሻቸዋል። በመሆኑም የጽዳት ሥራዎችን የሚያከናውኑት፣ ልብስ የሚያጥቡት ከኬሚካሎች በጠሩ ሳሙናዎችና በቤኪንግ ሶዳ ነው።
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ የኤም ሲ ኤስ በሽተኞች ችግር ከሚፈጥሩባቸው ኬሚካሎች ሙሉ በሙሉ መራቅ አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ኤም ሲ ኤስ የሚያስከትለው ትልቁ ጉዳት በሽተኛው ከኬሚካሎች ራሱን ለመጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ከሌሎች ሰዎች የሚገለልና የሚርቅ መሆኑ ነው። እንደ መፍትሔ የተቀመጠው ሕሙማኑ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንቅስቃሴያቸውን ቀስ በቀስ በማስፋት መሥራትና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን መቀጠላቸው ጠቃሚ ነው። ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን ደግሞ ዘና ማለትና አተነፋፈስን መቆጣጠር የሚቻልባቸውን ዘዴዎች በመማር የሚሰማቸውን የድንጋጤና የመሸበር ስሜት ለማስወገድ እንዲሁም የልብ ትርታቸው ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ መጣር አለባቸው። ዋናው ዓላማ ሕሙማኑ ኬሚካሎችን ጨርሶ ከሕይወታቸው ውስጥ እንዲያስወግዱ ማድረግ ሳይሆን ቀስ በቀስ ከኬሚካሎች ጋር እንዲላመዱ መርዳት ነው።
ሌላው በጣም ጠቃሚ ሕክምና ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ ማግኘት ነው። በኤም ሲ ኤስ በሽታ የተጠቃ ሰው ንጹሕ አየር እንደ ልብ በሚያገኝበት መኝታ ክፍል ውስጥ መተኛት አለበት። በተጨማሪም ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ጤንነትን ለመጠበቅም ሆነ በሽታን ለማሸነፍ ምንጊዜም አስፈላጊ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። እንዲያውም በሽታን ለመከላከል ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር ነው። ሰውነት ዳግም ጤነኛ እንዲሆን ከተፈለገ ቢያንስ ቢያንስ የሰውነት ሥርዓቶች በተቻለ መጠን በብቃት መሥራት አለባቸው። እንደ ቫይታሚን ያሉ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ ሊጠቅም ይችላል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግም ለጤና ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም ሲያልበን በሰውነታችን ውስጥ ያሉ መርዘኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በቆዳችን በኩል ይወጣሉ። ከዚህም ሌላ ጥሩ የአእምሮ ዝንባሌ ማዳበርና ተጫዋች መሆን እንዲሁም በሌሎች መወደድና ለሌሎች ፍቅር ማሳየት በእጅጉ ይጠቅማል።
ምንጭ ፤ሰርቫይቫል 101
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012