አሻም የአዲስ ዘመን ማዕድ ተቋዳሾች። ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ጎበዝ ኮሮና ወደ ሦስት አኀዝ (ዲጂት) ከፍ ብሏል። ይህ የምጣኔ ሀብት የዕድገት ደረጃችን የሚመስለው ተላላ ዜጋም መኖሩን ስታስታውስ በግርምት መዳፎችህን አፍህ ላይ ጭነህ “አምላኬ ሆይ!” ከማለት ውጪ ሌላ ምን ይባላል። ማንጋጠጥ ነው እንግዲህ። ከላይ ቤት ካልሆነ በቀር ምድራዊ መፍትሔ አለመኖሩንማ አየነው።
ዛሬ የትዝብት መነፅሬን ከሰው ወደ ወር አዙሬዋለሁ። ከወራት መካከል ደግሞ ትንግርታዊውን ወር ለመታዘብ ከጀልኩ፤ ግንቦትን። ጉደኛ ወር። ይህ በሀገራችንም በዓለማችንም ብዙ የተባለለት በርካታ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ወር ነው። አንድ ወቅት አስራ ሁለቱንም ወራት በአመራርነት ሚና ዙሪያ ተከራክረው ወደ ምርጫ ለመሄድ ወስነው ነበር፤ በስነፅሑፍ መድረክ። እናም ሁሉም ተወዳዳሪ ወር የመመረጫ አጀንዳውን ለመራጩ አቀረበ። ከመስከረም እስከ ነሐሴ አንድ በአንድ የጦፈ ክርክር አካሄዱ። ግና የግንቦትን ያክል ቱባ ሃሳብ ያቀረበ አልነበረም። ከሰፈር እስከ ዓለምአቀፉ የላብ አደሮች ቀን ታላላቅ ታሪኮችን ያስመዘገበ ወር መሆኑን በመጥቀስ የወራት መሪነት እንደሚገባው ሽንጡን ገትሮ ተከራከረ።
ይኸው ሰሞኑን በሀገረ አሜሪካ በአንድ ጥቁር ላይ በደረሰ የዘረኝነት ጥቃት ኮሮናን ችላ ብሎ በመላው ዓለም የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍም የዚሁ የግንቦት ወር አዲስ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ይኸኛውን በሌላ ርዕስ እመለስበታለሁ። ለዛሬው በኢትዮጵያዊው ግንቦት ላይ ላትኩር።
በመጀመሪያ በወርሐ ግንቦት ስለነበሩት ታሪካዊ ክስተቶች በአጭሩ ላስቃኛችሁ።
• በግንቦት ወር የውጫሌ ውል መፈረሙ ፣ ልጅ ኢያሱም በዚሁ ወር ለንግስና መሾማቸው፣
• መንግሥቱ ኃይለማርያም በግንቦት 19/1933/ ተወለዱ፣
• አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነትም ያቋረጠችው ግንቦት 20-1969 ነው፣
• በመንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ መንግሥታዊ ፍንቀላ የተሞከረውም ግንቦት 8-1981 ነው፣
• ኢትዮጵያ አስራ ሁለት ጄኔራሎቿ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ተገድለውባት ደም ያነባችውም ግንቦት 12-1981 ነው፣
• መንግሥቱ ኃይለማርያም ሃገር ጥለው ላይመለሱ የፈረጠጡትም ዛሬ ግንቦት 13-1983 ዓ.ም ነው፣
• መለስ ዜናዊ ግንቦት 1-1947 ተወለዱ፣
• ደርግ ወርዶ ኢሕአዴግ ስልጣን የያዘው ይኸውም በየዓመቱ አታሞ የሚደለቅለት ግንቦት 20-1983 መሆኑ ነው፣
• ግንቦት 28-1990 ኤርትራ ኢትዮጵያን ወረረች፣
• በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ምርጫ 97 የተካሄደውም ግንቦት 7-1997 ዓ.ም ነው፣
• በደርግ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ሞት ተፈረደ-ግንቦት 18-1999፣
• በእነዚህ የደርግ አመራሮች ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድም ወደ ዕድሜ ልክ እስራት የወረደው ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነው።
ወርሃ ግንቦት እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ አቅጣጫቸው ለየቅል አልሆነም።
ግንቦት 20/1983 በለንደን
አንድ ወዳጄ የ1983 ዓመተ ምህረቱን የለንደን ኮንፈረንስ ሲያስታውስ የተጨናገፈው ፅንስ በማለት ሰይሞታል። የመጀመሪያው የህወሓትና የሻዕቢያ ተንኮል የተጠነሰሰበት ዕለት መሆኑን በመጥቀስ።
ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች የለንደኑን ኮንፈረንስ “ሳይጀመር የተጠናቀቀ ድራማ” በማለት ጠርተውት ነበር።በርግጥም ኮንፈረንሱ የግማሽ ቀን ዕድሜ ብቻ ነው የነበረው።በዚያ ጊዜም የተደረገው ነገር ዋና አዳራዳሪው ሚስተር ሄርማን ኮህን ተደራዳሪዎቹን በተናጥል ማነጋገራቸው ብቻ ነው።በሚቀጥለው ቀን ግን ሚስተር ሄርማን ኮህን ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ ጉባኤ በመጥራት ኮንፈረንሱ መሰረዙን አስታወቁ።ኢህአዴግ በአዲስ አበባ፣ ህግሓኤ በአሥመራ የየራሳቸውን መንግሥት እንደሚመሰርቱም ገለጹ።
ለኮንፈረንሱ መበተን ምክንያት የሆኑት በመጨረሻው ሰዓት የኢህዲሪ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት ሌ/ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ናቸው።ጄኔራል ተስፋዬ ለሚመሩት መንግሥት ባለስልጣናት ሳያስታውቁ ሰኞ ግንቦት 19/1983 ረፋዱ ላይ ለአሜሪካ ኤምባሲ “የጦር ሠራዊቱ ከቁጥጥሬ ውጪ ሆኗል፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም ዘረፋ ተጀምሯል” የሚል መረጃ ሰጡ፤ ለራሳቸውም የኢጣሊያ ኤምባሲ ገብተው ጥገኝነት ጠየቁ (በወቅቱ ወደ ኤምባሲው አብረዋቸው የገቡት ባለስልጣናት አቶ ሀይሉ ይመኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሻምበል ብርሃኑ ባይህ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌ/ጄኔራል ሐዲስ ተድላ የኢህዲሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ናቸው)።
የአሜሪካ ኤምባሲም ከጄኔራል ተስፋዬ የሰማውን መረጃ ለንደን ለሚገኙት ሚስተር ሄርማን ኮህን አስተላለፈ።በዚህም መሰረት ሚስተር ኮህን ምሽት ላይ በኮንፈረንሱ አካሄድ ላይ ለውጥ መደረጉን አስታወቁ።አዲስ አበባ እንደ ሞቃዲሾ እና እንደ ሞኖሮቪያ እንዳትሆን የኢህአዴግ ጦር ወደ ከተማዋ መግባት እንዳለበትም ተናገሩ።የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ጦራቸው አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር ትዕዛዝ ሰጡ።በመሆኑም የኢህአዴግ ጦር ከሌሊቱ 8፡00 ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ።(ያንን ኦፕሬሽን የመሩት አዝማቾች ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፣ ጄኔራል ሀየሎም አርአያ፣ ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖትና ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ናቸው)።
ግንቦት 20/1983።ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት።አንድ የኢህአዴግ ታጋይ ከኢትዮጵያ ድምፅ ብሄራዊ አገልግሎት እንዲህ ሲል ተሰማ።“የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል፤ ግንቦት 20/1983 ዓመተምህረት።”
በሌላ በኩል ግንቦት ሃያን የሚወዱትን ያክል የሚጠሉት ወገኖች የሚያሰሙትን የተቃውሞ ድምፅ መታዘብም ለሚዛናዊነት ይጠቅማል። አንድ አንጋፋ የኦሮሞ ፖለቲከኛ በተለይ በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ለበርካታ ዓመታት ሲንገላቱ እንደነበር የምናውቃቸው ግለሰብ ግንቦት ሃያንና ባለቤቶቹን ጭምር ሲያወድሱ ለሰማ ግራገብነትን ያጎናጽፋል። ታዲያ ምን ሊባል?
አቶ ስዩም መስፍን ለትግራይ ቴሌቪዥን “አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግንቦት ሃያ ፍቅር እየተሰቃየ ነው” በሚሉበት ሰዓት ዋልታ ቴሌቪዥን ደግሞ ግንቦት 20 አዲስ አበባን የያዘው ኃይል በዜጎች ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ግፍ እያሳየ ነበር። ልብ ይሰብራል።
ለምን? በግሌ ባላየው ይሻለኝ ነበር። በምንም ምክንያት አንድ ወገን በወገኑ ላይ ይህን ግፍ ይፈጽማል ብሎ ማሰብ ይቸግራል። ድርጊቱን ደግሞ መተረክ ከማሰብ አቅም በላይ ነው። አምባሳደር ስዩም የቱን ሕዝብ ይሆን የሚሉት? ግፈኞቹ ለሚዲያ ምንም ይበሉ እንጂ እውነቱን ያውቁታል።
የተለየ የፖለቲካ አቋም በመያዛቸው ብቻ ይህን ግፍ በገዛ ዜጎቹ ላይ ግፍ የፈጸመው የእነ አቶ ስዩም ስርዓት አልፎ ዛሬ እነሱ ጠቅላይ ሚኒስትርን ለመሳደብ የበቃ “ነፃነት” አግኝተዋል ካወቁት። በዋልታ ቴሌቪዥን ምስክርነታቸውን ከሰጡት ሁሉ በቀለ ገርባ ዛሬም እውነቱን መናገር አልፈለጉም። ይህ መቸም ሰውነት አይደለም። ያልደረሰባቸውን እንዲዋሹ አያስፈልግም።
ይሁንና በወቅቱ የደረሰውን በደል “ መናገሩ አያስፈልግም “ ብለው ነው ያለፉት። ግፍን መፈጸም ብቻ ሳይሆን የተፈጸመውን ነውር መደበቅም በታሪክ ፊት ያስጠይቃል። እውነት ለመናገር አቶ በቀለ ከግፈኞቹ የግንቦት 20 ባለቤቶች ባላነሰ ግፍን አበረታተዋል።
ከግንቦት ሃያ በፊት ሰው በአደባባይ ይረሸን ነበር!!! አስከፊው የደርግ ስርዓት ከወደቀ ከግንቦት 20 በኋላም ከሴት እንዳልተወለደ በሴት ማህፀን ውስጥ እንጨት የሚከት፣ ቢላዋ አግሎ የሴትን ጡት የሚወጋ፣ ነፍሰ ጡር ሴት ሆድ ረግጦ ፅንስ የሚያስወርድና ሴት ልጅን ቀጥቅጦ ሽባ የሚያደርግ ሰይጣናዊ ስርዓት ስለተተካ እንዲሁም ከግንቦት 20 በኋላ የተፈጠረው ስርዓት የባሰ አስከፊ ስርዓት እንጅ ለውጥ የታየበት ስላልሆነ ግንቦት 20 እንኳን የነፃነት ቀን ሆኖ ሊከበር ይቅርና መታሰብ እንኳን እንደሌለበት ብዙዎች ያምናሉ።በሴት ልጅ ማህፀን እንጨት የሚያስገቡ ጭራቆችን ያመጣብን ቀን ግንቦት 20 እንኳን መከበር መታሰብ የለበትም የሚለውን ሃሳብ እኔም ተቀብያለሁ።
ለእውነተኛ ለውጥ ሲሉ ከግንቦት ሃያ በፊትም ሆነ ከግንቦት ሃያ በኋላ የተሰው እና አካል ጉዳተኛ የሆኑ ወገኖችቻችንን ከእውነተኛ ለውጥ በኋላ የምናከብርበት እውነተኛ ቀን ይመጣል ብዬ ተስፋ እያደርግሁ ከዚህ በኋላ ግን ግንቦት 20 የሚባል በዓል ከካሌደር ላይ እንዲወርድ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ የሚሉም አልጠፉም።
ወርሃ ግንቦትን በተመለከተ ሌላው ገራሚ ጉዳይ ደግሞ በቅርቡ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፌሙስጠፌ ሙሐመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡት አስተያየት ነበር። እንዲህ ሲሉም ተደምጠዋል።
“ግንቦት 20 ለሶማሌ ክልል ህዝብ ካስገኘለት ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ሥርዓቱ በሱማሌ ህዝብ ላይ በታሪኩ ተፈፅሞበት የማያውቀው ግፍ፣ ግድያ፣ ማንገላታት አድርሶበታል፤ በተደራጀ መልኩ ህባችንን የማወራድ ሥራ ተሠርቷል” ነበር ያሉት።
ግንቦት 20
ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር እንደ ብ/ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ የሚያዝናናኝ ሰው የለም። ዛሬ ድረስ ደርግ በኢህአዴግ ሠራዊት እንዳልተሸነፈ ነው የሚያምኑት። “በነገራችን ላይ 90 በመቶ የሚሆኑ የግንቦት 20 ተቃዋሚዎች በሁለት ይከፈላሉ” ይለናል ወዳጄ ተስፋዬ። “ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸውና ከ40 ዓመት በታች የሆኑ ናቸው። ከ60 ዓመት በላይ የሆኑት ከሞላ ጎደል ቅልጥ ያለ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ወዳጆች ወይም የቀድሞው የደርግ ጦር ሠራዊት የነበሩ ሲሆኑ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሚገመቱት ከሞላ ጎደል የደርግ ጥይት የሳታቸው ወይም እናታቸው ማቡኪያ ውስጥ፣ዱቄት ውስጥ፣ ጉድጓድ ውስጥ ደብቃ ከደርግ ጥይት ያዳነቻቸው እውነትን ሸምጥጠው የካዱ ናቸው። ይህን ለማረጋገጥ ብዙ ማድከም አያስፈልግም ወደኋላ 30 ዓመት ብቻ መለስ ብሎ ታሪክን ማየት በቂ ነው።
ግንቦት 20 ሌላ ጨቋኝ ስርዓት አመጣብን ብለው ቀኑን ሲሰሙትም የማይመቻቸው ሰዎች ለነሱ ነጥብ እሰጣለሁ።ምክንያታቸው እውነትን ይዟል። ለማንኛውም እንደኔ እንደኔ ቢያንስ ከ40 ዓመት በታች ያሉ ፀረ ግንቦት 20 ልጆች ግንቦት 20ን በኬክ ባይችሉ በቂጣም ቢሆን ማክበር ነበረባቸው ባይ ነኝ።
በርግጥ ግንቦት 20 ሀገሪቷን የተከፋፈለ ዕለት ነው። ልክ እንደ ዶሮ ብልት 12 በታች የሆነችበት። ለምን እንደ ከፋፈላት መረዳት እንጂ ይህን መካድ አይቻልም። ዶሮን በብልት ከፋፍለን የምናስቀምጠው ለአበሳሰል ለአበላል እና እነደየድርሻ ለመከፋፈል ስለሚያመች ነው። ፌዴራሊዝም የዶሮ አበላለት ሂደት ነው ወጡ ደግሞ ዕሴት የተጨመረበት የሀገሪቱ ሀብት። ያቺን ዶሮ አሩስቶ አርጎ ከመብላት ለቤተሰብ እንድትበቃ ሆና መቃመስ የሚቻለው ወጥ ሆና ስትሠራ ብቻ ነው ተብሎ ታመነበት። በሌላ አነጋገር ይቺ ዶሮ(የሀገሪቱ ሀብት) የተበለተችው…ዶሮ ወጥ ሆና ካልተሠራችና እንደየድርሻቸው ካልተከፋፈለ የበተሰቡ ሰላም በእጅጉ ስለሚናጋ ይህንን ለመቅረፍ የተሻለው ዘዴ ዶሮዋን መበለቱ በመሆኑ ነው። እናም ወጡ ተሠራ። ፌዴራሊዝሙ ተዘረጋ። ከአሁን ወዲህ ውይይቱ ክርክሩ መሆን ያለበት “ለአባወራም ለእማወራም ለልጆችም እንደየድርሻቸው ይሰጣቸው” እንጂ ዶርዋን ገጣጥመን እንሽጣት ወይም እንደ በፊቱ አሮስቶ አድርጌ ልብላት መሆን የለበትም። የተበለተ ሁሉ አይበላሽም። ቆንጆ ዶሮ ወጥ ሆኖ ይወጣል እንጂ። የዶሮዋን ብልት ሲያዩ የሚደነግጡ ወይ ሙያ የሌለው ገልቱ ነው…አሊያም ዶሮ ብቻውን መብላት የተለመደ ስግብግብ ነው።
ቸር ያቆየን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ