ከታሪክ መጻሕፍት ጀርባ ማጣቀሻ ሆኖ እናገኘዋለን። የታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪክ ሲጻፍ ምንጭ ሆኖ ይገኛል። የታላላቅ ደራሲዎችና ፖለቲከኞች ሥራዎች ይገኙበታል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የሆኑ ሁነቶች ተሰንደው ይገኙበታል። ከ80 ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጥበባዊ ሁኔታዎች ይገኙበታል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ!
አዲስ ዘመን ጋዜጣ እነሆ 79 ዓመታትን ተጓዘ። ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ተመሰረተ። እነሆ ለ79 ዓመታት የአገሪቱ ብቸኛ ዕለታዊ ጋዜጣ በመሆን የሦስት ሥርዓተ መንግሥታትን ምንነት ሰንዶ አስቀመጠ። የእነዚህ መንግሥታት ባህሪም የሚታወቀው በዚሁ ጋዜጣ ነው። አሁን ላይ ያለ ወጣት ንጉሣዊ ሥርዓቱ ምን አይነት እንደነበር አያውቅም። ቤተ መጻሕፍት በመግባት ግን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማግኘት ይችላል። የጋዜጣ ሰነድነት ከመጻሕፍትና ከሌሎች ሰነዶች ይለያል። ምክንያቱም ዜናዎች አሉበት። ዜና በወቅቱ ዜና ይሁን እንጂ ከዘመናት በኋላ ግን ታሪክ ይሆናል። ምክንያቱም የመንግሥታት ዕለታዊ ክንውኖች ስለሚጻፉበት።
ስለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዘት፣ ዕድገት፣ ለውጥ እና አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታው በየዕለቱ የሚነገር ይሆናል። ለዛሬው ግን በዚህ በኪነ ጥበብ ገጽ የምናተኩረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ለኪነ ጥበብ ሥራዎች ያበረከተው አስተዋፅዖ ላይ ብቻ ይሆናል። ምናልባት ግን ኪነ ጥበቡን ከፖለቲካው ጋር የሚያገናኘው ነገር ካለም እናያለን።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስሙ ከታላላቅ ደራሲዎች ጋር ይነሳል። የእነዚህ ደራሲዎች ስም ሲነሳ አዲስ ዘመን፤ የአዲስ ዘመን ስም ሲነሳ የእነዚህ ደራሲዎች ስም ተያይዞ ይጠራል። በተለይ የበዓሉ ግርማ እና የጳውሎስ ኞኞ ግን ይደጋገማል። ምክንያቱም እነዚህ ደራሲዎች በታሪክ እና በፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለፈጠሩ ነው። ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን እና ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የሰሩ ታላላቅ ደራሲዎች ናቸው። ብርሃኑ ዘሪሁን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ነበር። ሌሎች አንጋፋና ወጣት ደራሲዎችም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በቋሚ ተቀጣሪነትም በፍሪላንሰርነትም፣ በውጭ ፀሐፊነትም የሰሩ ብዙ ናቸው። እነ ማዕረጉ በዛብህ፣ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ አንተነህ ይግዛው…. ይጠቀሳሉ። የሶስቱን ታላላቅ ደራሲዎች እና የአዲስ ዘመን ጋዜጣን የጥበብ ትዝታዎች እንቃኛለን።
በዓሉ ግርማ
በዓሉ ግርማ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ እና የስነ ጽሑፍ አርበኛ ነው። በዓሉ ግርማ በተለይም ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘው መጽሐፉ ጋዜጠኝነትንም ስነ ጽሑፍንም አሳይቷል። አሟሟቱ ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነ ቢቀርም ለመሞቱ ሰበብ የሆነው ይሄው ‹‹ኦሮማይ›› የተሰኘው መጽሐፉ ነው።
ኦሮማይ በደርግ ዘመነ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን የጦርነት ሁኔታ የሚገልጽ ነው። ደርግ ደግሞ በዚህ መጽሐፍ በዓሉን ጥርስ እንደነከሰበት ይነገራል። እርግጥ ነው በዘመኑ የነበሩ የሙያ ባልደረቦቹ ክርክር ላይ ናቸው። በተለይም የቅርብ ጓደኛው የነበረው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ደርግ በፍጹም በዓሉን አያስገድለውም የሚል አቋም አለው። እንዲያውም የደርጉ ሊቀመንበር እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለበዓሉ ልዩ ፍቅር እንዳላቸው ስብሃት በተለያዩ ቃለመጠይቆቹ ተናግሯል። የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን የህይወትና የአስተዳደር ታሪክ የጻፈችው ገነት አየለም ‹‹የሌተናንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች›› በሚለው መጽሐፏ ይሄንኑ ገልጻለች። ራሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለበዓሉ ግርማ ፍቅርና አክብሮት እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ማንም ይግደለው ማን እንግዲህ በዚህ መጽሐፉ ሰበብ በዓሉ ግርማ በህይወት አልተገኘም። መጽሐፉ ጋዜጠኝነትንና ስነ ጽሑፍን የያዘ ነው። እንደ ጋዜጠኛ ያየውንና የሰማውን ጽፏል። የጋዜጠኛን ድፍረት አሳይቷል። ጋዜጠኛ አድርባይ፣ ወላዋይና ፈሪ መሆን እንደሌለበት አሳይቷል። የጋዜጠኝነት ሙያ ህይወትን እስከማጣት መስዋዕትነት የሚከፈልበት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
እንደ ስነ ጽሑፍ ካየነውም፤ እነሆ መማሪያ እስከመሆን ደርሷል። ለብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ምንጭ ሆኗል። በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤትም በስነ ጽሑፍ ትምህርት ቤትም ማነፃፀሪያ ተደርጓል። የስነ ጽሑፍ አላባውያን ለሚባሉት መሰረት ሆኗል። በየስነ ጽሑፍ ውይይቱ የበዓሉ መጽሐፎች ስም ይነሳል። አገላለጾቹ ስነ ጽሑፋዊ ውበት ያላቸው ናቸው። ረቂቅ አገላለጽ ይጠቀማል። ተምሳሌታዊ ትርጓሜን አሳይቷል። ፍቅርን አሳይቷል።
ለህይወቱ መጥፋት ምክንያት እና ፖለቲካዊ ይዘት ስላለው ‹‹ኦሮማይ›› ተደጋገመ እንጂ ሌሎች መጽሐፎቹም ድንቆች ናቸው። የቀይ ኮከብ ጥሪ የሚለው መጽሐፉም እንዲሁ ፖለቲካና ስነ ጽሑፍን የያዘ ነው። ከአድማስ ባሻገር በብዛት የሚደጋገመው በስነ ጽሑፍ ሰዎች ዘንድ ነው። ሀዲስ፣ ደራሲው እና የህሊና ደወል የሚሉትም ቢሆን ተደጋግመው የተነበቡ ናቸው። በአጠቃላይ በዓሉ ግርማ ለስነ ጽሑፍና ለጋዜጠኝነት ሙያ መስዋዕት የሆነ ሰው ነው።
ጳውሎስ ኞኞ
ጋዜጠኛ የሆኑም ያልሆኑም ሰዎች ስለ ጳውሎስ ኞኞ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ነገር ያውቃሉ። ይሄውም ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› የሚለው የጳውሎስ ኞኞ ጽሑፍ ነው። የትም ቦታ የጳውሎስ ኞኞ ስም ከተነሳ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የነበረው ይሄ ዓምዱ ይጠቀሳል። ጳውሎስን ለማስታወስ ሲባልም የሬዲዮ ፕሮግራም እና የህትመት ዓምዶችም ወጣ ገባ እያሉ ተሰይመዋል። በኩረጃ ሳይሆን እሱን ለማስታወስ መሆኑን እየጠቀሱ ማለት ነው።
ስለጳውሎስ ኞኞ የጋዜጠኝነት ፍቅር አንድ ጓደኛው የነበረ ሰው በሬዲዮ ሲናገር የሰማሁትን ገጠመኝ ላካፍላችሁ።
ጳውሎስ ታሞ ተኝቶ ነው። ጓደኞቹ ሊጠይቁት ከቤቱ ይሄዳሉ። ሲሄዱ በፀና ታሞ ተኝቷል። ብዙም አያናግራቸውም፤ በህመም ላይ አናጨናንቀውም ብለው ዝም ብለዋል። በቤቱ ውስጥ የተከፈተው ሬዲዮ እያወራ ነው። ጋዜጠኛው አንድ ስህተት ይሳሳታል። ይሄኔ ጳውሎስ ‹‹አይ! አዳምጡትማ ይሄን ጋዜጠኛ…›› ብሎ የጋዜጠኛውን ስህተት አስተካክሎ ነገራቸው። እንግዲህ በህመም ላይ ያለ ሰው እንኳን ስህተትን ነቅሶ ማውጣት ስለምን እየተወራ እንደሆነ ራሱ ልብ አይልም ነበር። ጳውሎስ ኞኞ ግን በህመም ውስጥ ሆኖ እንኳን መረጃን እያጣራ ይሰማ ነበር ማለት ነው።
ስለ ጳውሎስ ኞኞ የሚነገር ሌላ አንድ አስቂኝ ገጠመኝ ደግሞ አለ። ለስቴዲየም ማስሪያ ተብሎ መዋጮ እየተዋጣ ነው። የኳስ ነገር ያልጣመው ጳውሎስ ‹‹ኧረ ይሄ ነገር ይቅር›› ይላል። በጣም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሲነግሩት ‹‹አሥራ አንድ ጅሎች አንድ ቅሪላ ሲከታተሉ ለማየት አላዋጣም›› ብሎ የተሰበሰበው ብር ለሆስፒታል ግንባታ መዋል እንዳለበት ተናግሯል።
ጳውሎስ ኞኞን የሚያውቀው ሁሉ አንድ የሚያውቀው ታሪኩ ደግሞ በመደበኛው ትምህርት ከ4ኛ ክፍል በላይ ያልተማ ምሁር መሆኑ ነው። የታሪክ ተመራማሪ ነው። በኢመደበኛ ትምህርት እና በጥልቅ ንባብ ምሁር መሆን እንደሚቻል ያሳየ ሰው ነው። ‹‹የሴቶች አምባ፣ አጤ ምኒልክ ፣ አጤ ቴዎድሮስ ፣ አስደናቂ ታሪኮች ፣ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ፣ አራዳው ታደሰ ፣ የኔዎቹ ገረዶች ፣ የጌታቸው ሚስቶች ፣ ምስቅልቅል፣ እንቆቅልሽ ፣ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች›› የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፎች ናቸው። ይሄ ሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የታሪክ ተመራማሪ ብቻ አልነበረም። በእርሻ ሚኒስቴር (ለዚያውም ገና በ17 ዓመቱ) የእንስሳት ሐኪም ሆኖም ሰርቷል።
ጳውሎስ በጋዜጠኝነት ዘርፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለዓመታት መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት ህዝብን በማንቃት በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፏል።
ነገ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ 79ኛ ዓመት ነው። ዛሬ ይሄን ጽሑፍ ስታነቡ የሚገርመው አጋጣሚ ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ ህይወቱ ያለፈው በዛሬዋ ቀን ግንቦት 29 /1984 ዓ.ም ነው። እነሆ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውልና ሲወደስ ይኖራል።
ብርሃኑ ዘሪሁን
በ1925 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የተወለደው ብርሃኑ ዘሪሁን የቤተ ክህነት እና ዘመናዊ ትምህርቱን እዚያው ጎንደር ከተከታተለ በኋላ በ1945 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባም ትምህርቱን ተግባረዕድ ትምህርት ቤት ሲከታተል ቆይቶ በ1948 ዓ.ም በሬዲዮ ቴክኒሻንነት ተመረቀ። ከትምህርት ቤቱም የከፍተኛ ውጤት ተሸላሚ ነበር። እዚሁ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ የአገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ደራሲዎችን ሥራዎች ያነብ ነበር። እዚያው ትምህርት ቤት እያለም ለመጽሔቶች መጻፍ ጀመረ።
በዚያው በተግባረዕድ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ ሰርቷል። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመሄድ የጋዜጠኝነት ሥራን የጀመረው። የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። ከዚያ በኋላ ነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው። ብርሃኑ ዘሪሁን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እያለ ከመንግስት ጋር ይጋፈጥ እንደነበርም ይነገራል።
ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ አሻራ አስቀምጧል። ለታሪካዊ ልቦለድ አጻጻፍ ፈር ቀዳጅ ሆኗል። የተውኔት ሥራዎችን እና የታሪክ ምርምሮችን ሰርቷል።
‹‹የቴዎድሮስ እንባ፣ የታንጉት ምስጢር፣ ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ፣ ማዕበል የአብዮት ማግስት፣ ጨረቃ ስትወጣ››፣ አማኑኤል ደርሶ መልስ፣ የእንባ ደብዳቤዎች፣ የበደል ፍፃሜ›› የሚሉት መጻሕፍት ሲሆኑ፤ ‹ባልቻ አባነፍሶ፣ ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ፣ የለውጥ አርበኞች፣ ሞረሽ…›› የተሰኙ ተውኔቶችን ጽፏል።
ከነገ በኋላ የሚኖረው የአዲስ ዘመን ዕድሜ 80 እየተባለ የሚጠራ ነው። 80 ዓመታትን ያስቆጠረ ብቸኛ የአገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ ነው። ዛሬ ላይ ግን ማህበራዊ ድረ ገጾችን ጨምሮ ብዙ ተወዳዳሪ አማራጮች አሉበት። እነዚያን አሸንፎ መውጣት ካልቻለ ‹‹አዲስ ዘመን ድሮ ቀረ›› እየተባለ መወቀሱ አይቀርም። ምክንያቱም ስማቸው እየተጠራ ያለው ቀደም የነበሩት ፀሐፊዎች ናቸው። እርግጥ ነው ይሄ የጋዜጣው ችግር ብቻ አይደለም፤ የዘመኑም ባህሪ ነው። ያኔ የነበረው አማራጭ አዲስ ዘመን ብቻ ነበር፤ ማንም ወዴትም መሄድ አይችልም ነበር። ዛሬ ብዙ አማራጭ አለ፤ ጋዜጣና መጽሔት ቢያጣ እንኳን የራሱን ጦማር ይከፍታል። ቢሆንም ግን ይሄን ሰበብ በማድረግ ጋዜጣው ከለውጡ ወደኋላ ሊል አይገባም።
ለስነ ጽሑፍ አሻራ ማስቀመጥ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ባህሪ ነው፤ ምክንያቱም የጽሑፍ ውጤት ነው። ስነ ጽሑፍ ደግሞ የየዘመኑን ባህሪ ያሳያል። በሬዲዮና ቴሌቭዥን የሚተረክ ትረካም ሆነ የሚነበብ ግጥም ከዓመታት በኋላ ለህዝብ ተደራሽነት የለውም። አዲስ ዘመን ግን እነሆ የ80 ዓመታት ሁነትን እየነገረን ነው።
አንተ ጋዜጣ እንኳን ለ79ኛ ዓመትህ አደረሰህ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
ዋለልኝ አየለ