አገር በቀል ከሆኑ የባህል እሴቶችና ፍልስፍናዎች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ሥርዓት ነው ። የገዳ ሥርዓት ደግሞ ሰላም፣ ልማት፣ ፍትህና በጋራ ተደጋግፎ መኖር ቀዳሚ አስተምህሮቶቹ ናቸው ። የገዳ ሥርዓት ሁል ጊዜ ታሳቢና መሰረት ያደርጋል ተብሎ የሚነገረውም ሰላምን፣ ፍትህን እና ልማትን ነው ። ከዚህ አንጻር ይህ አገር በቀል ፍልስፍና ከአገር አልፎ አፍሪካን በመልካም ሊያስመለክት የሚችል፤ ከምዕራባውያኑ ተቀድተው የሚቀርቡ ነገር ግን ሰላም፣ ልማትና ፍትህን ለማስፈን ያላስቻሉ እሳቤዎችን ተክቶ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሰላም፣ ልማትና ፍትህን በማምጣት መመኪያ ሊሆን የሚችል እሳቤ ስለመሆኑም ይነገራል ።
ለመሆኑ ይህ ስርዓት እንዴት ተጀመረ፤ አስተምህሮቶቹ በተለይም ከሰላም፣ ልማት፣ መደጋገፍና ፍትህ አንጻር እንዴት ይገለጻሉ፤ ይሄን አስተምህሮ ከማጎልበት አንጻርስ ምን እየተሰራ ነው፤ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳት ዶክተር ጫላ ዋታ ደረሶ ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።
የገዳ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ይታወቅ የነበረው የሚቲዎች አስተዳደር (የንጉሳውያን ወይም የመሳፍንት አገዛዝ) በሚል እንደነበር ይነገራል ። እነዚህ ሞቲዎች ደግሞ እንደመሰላቸው ሲነሱና አሸንፈው ሌላውን ሲያስገዙ ይኖሩ ነበር ። በዚህም መጀመሪያ ላይ የወንዶች የአገዛዝ ዘመን ነበር ። የወንዶች አገዛዝ የከፋና አስቸጋሪ ሲሆን ደግሞ ሴቶች ቢመሩ ይሻላል በሚል በመሃል ላይ ሴቶች እንዲመሩ ተደርጓል ። በዚህም እነ አኮ መኖዬንና ቀሲ ቀሶዬን ጨምሮ አምስት ያክል ታዋቂ የሴት ሞቲዎች/ነገስታት ለማስተዳደር ችለው ነበር ።
ይሁን እንጂ በወንዶች ጉልበትን መሰረት አድርጎ በዝርፊያና ቅሚያ፣ የሰው ሚስት መውሰድና ሌሎችም ከሰላም እጦት ጋር የተስተዋሉ በደሎች ተማርሮ እድሉ ለሴቶች የሰጠው ህዝብም በሴት ነገስታቱም ሌላ ችግር ተፈጠረበት ። ምክንያቱም የሴቶች ነገስታትም ህዝቡ በወቅቱ ሊያደርገው የማይችለውን በማዘዝ (ለምሳሌ፣ ከመሬት ከፍ ብሎ ከሰማይ ዝቅ ብሎ የሚበር ፈረስ አምጡ በማለት) ህዝቡን ማስጨነቅ ያዙ ። እነዚህ ፍትሃዊ ያልሆኑ ጥያቄዎችም ህዝቡን እጅጉን ስላስጨነቁት በተነሱ የመልካም አስተዳደር አይነት ቅሬታዎች ወንዶች መልሰው ስልጣንን ከሴቶች ቀምተው ይረከባሉ ።
ሆኖም በጉልበት የሚመራው የወንዶች አስተዳደር አሁንም የተፈለገውን የፍትህ፣ የአብሮነትና የሰላም ድባብ ለህዝቡ ማምጣት አላስቻለውም ። እናም ህዝቡ ይሄን ችግሩን ሊያቃልልለት፣ እኩልነትና ፍትሃዊነትን አስፍኖ ሰላሙንም ሊያረጋግጥለት የሚችል ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት በመወሰን የገዳ ሥርዓትን እውን ማድረግ ችሏል ። ከዚህ አንጻር ሲታይ የገዳ ሥርዓት በችግር የተፈተነው የዛን ዘመን ትውልድ ለአስተዳደራዊ ችግሮቹ መፍቻ ቁልፍ አድርጎ የዘረጋው ስርዓት ሲሆን፤ በወቅቱ በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረትም ህዝቡን ሊመሩ የሚችሉ ሰዎች የስልጣን ጊዜያቸው ገደብ ሊኖረው ይገባል፤ ሁሉም እንቅስቃሴና ሽግግርም ሰላማዊ መሆን አለበት፤ ህዝቡም በሰላም ሊኖር ይገባል፤ ልማቱም ፍትሃዊ ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፤ በሚል እሳቤ ውስጥ ሆኖ የተጀመረ ሥርዓት መሆኑን ነው በጉጂ አካባቢ የሚነገር የገዳ ሥርዓት አጀማመር ትርክት የሚያሳየው ።
ከዚህ አንጻር የገዳ ሥርዓት ውስጥ ሁል ጊዜ የወንድ የበላይነት ወይም የሴት የበላይነት ወይም የዚህኛው መንደር የበላይነት አልያም የዛኛው መንደር የበላይነት የሚባል ነገር የለም ። ሥርዓቱ ሁሉንም እኩልና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እና በፍትሃዊነት ማገልገል፣ ማስተዳደር፣ መምራትን እና እንዲበለጽግ መስራትን የሚያዝ ነው እንጂ ከዚህ በተቃራኒው መጓዝን አይፈቅድም ። ከብዙ በጥቂቱ በሚነሱ በእነዚህ መመዘኛዎች ሲታይም የገዳ ሥርዓት ለሰላም ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል ። ይሄንን የበለጠ ለማጠናከር እና የገዳ ሥርዓት አንድ እሴት የሆነውን ሰላም ለማረጋገጥ መከወንና መታሰብ ስላለባቸው ጉዳዮች ያስቀመጣቸው ነገሮች አሉ ።
ምክንያቱም በገዳ ሥርዓት መሰረት ሰላም ለማረጋገጥ በሚታሰብበት ጊዜ የሰላም ምንጭ የት ነው? የሚለውን ለይቶና ያንን ታሳቢ በማድረግ መስራት እንደሚገባ ያስቀምጣል ። በዚህ መልኩ ከተቀመጡት መካከል አንደኛው የሰላም ምንጭ ሰው ከራሱ ጋር መታረቅ መቻሉ ነው ። በዚህ መሰረት ሰላም ይመጣ ዘንድ ሰው በውስጡ ያለን መልካም ያልሆነ ነገር ማስወገድ፤ ከህሊናው ጋር የሚያጋጩት ነገሮችን ለይቶ ከህሊናው ጋር የሚያጋጩትን በመተው ከህሊናው ጋር ሊስማማባቸው በሚችሉ ነገሮች ላይ ማተኮርና የውስጡን ሰላም ማጽናት እንዳለበት ነው የሚያስቀምጠው ። ይህ ሲሆን ሰው ያለበትን ሁኔታ ተቀብሎ እንዲኖር ብቻ ሳይሆን በመልካም እሳቤ አካባቢውን መለወጥና ሰላማዊ ለማድረግ የሚያስችለውን እድል የሚፈጥርለት ።
ሰው ከራሱ ጋር ታርቆ ሰላም መፍጠር ከቻለ፣ ሁለተኛው የሰላም ምንጭ የሚሆነው ደግሞ ሰው ከሰው ጋር ሰላም መፍጠር መቻሉ ነው ። ይህ ደግሞ አባት ከልጆቹ፣ ባል ከሚስቱ፣ እናት ከልጆቿ፣ ልጆችም ከወላጆቻቸው ከሚኖራቸው ሰላማዊ ግንኙነት የሚጀምረው የቤተሰብ ሰላም፤ አድጎ ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ ጎረቤት ከጎረቤት፣ አንድ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር፣ በጥቅሉ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ እርስ በእርሱ ሰላማዊ ግንኙነት ፈጥሮ በሰላም መኖር አለበት የሚለው እሳቤ ነው ። ይህ እሳቤ እንደ አንድ ግለሰብ ከራሱ ጋር እንደሚፈጥረው ሰላም ሁሉ፣ አጠቃላይ በሰዎች መካከል ሰላም እንዲፈጠር የሚያስችል ነው ።
በዚህ መልኩ በሰዎች መካከል ሰላም ከተፈጠረ ደግሞ፤ ሰዎች ሰላማቸው የበለጠ ወደ ምሉዕነት እንዲሸጋገር በሰውና በተፈጥሮ መካከልም ሰላም መፍጠር ሌላኛው የሥርዓቱ የሰላም ምንጭ እሳቤ ነው ። ይሄን መነሻ በማድረግም የገዳ ሥርዓት በባህሪው ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ቦታ ይሰጣል ። ለዚህም ነው የገዳ ሥርዓት ጠንካራ በሆነባቸው አካባቢዎች ደንን ከማውደም ይልቅ ደንን የመንከባከብ ጠንካራ ባህል የሚስተዋለው ። ከደን ባለፈ የሰው ልጆች ከእንስሳት ጋርም ሰላም መፍጠር እንዳለበት ያመላክታል ። ለከብቶች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠውም ከዚህ አንጻር ነው ። ለምሳሌ፣ በጉጂ አካባቢ አንድ ሰው ያሳደገውን ከብት በአብዛኛው አርዶ ከመብላት ይልቅ የሚሸጠው እንደራሱ አድርጉ ስለሚያየው ነው ።
በመጨረሻም ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከሰው ጋር እና ሰው ከተፈጥሮ ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን ከፈጠረ፤ የዚህ ሁሉ ማሰሪያ አድርጎ ሥርዓቱ በሰላም ምንጭነት ያስቀመጠው ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን መፍጠር እንደሚገባው ያመላክታል ። ይህ ደግሞ ፍጥረት ከፈጣሪው ጋር ያለው ቁርኝት ሰላማዊ ግንኙነት ላይ መመስረት አለበት ብሎ ስለሚያምን ሲሆን፤ በሥርዓቱ ምርቃት ሲከናወን “ያ ዋቃ ኑነጌሲ” ወይም ፈጣሪ ሆይ ሰላም ስጠን የሚባለውም ይሄንኑ የፈጣሪንና ፍጡርን ሰላማዊ ግንኙነት መሻት መሰረት ያደረገ ነው ።
እናም የገዳ ሥርዓት አሁን ላለው ትውልድ በተለይም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ አገር አብሮ ለመቀጠል፤ እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ዓለም ለሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነትና መስተጋብር የጎላ አስተዋጽዖ አለው ። ትውልዱም ይሄን ቢገነዘብ እንደ አገር፣ አህጉርና ዓለምም ሊያበረክት የሚገባውን አስተዋጽዖ በአግባቡ ለማበርከት የሚያስችለው ይሆናል ። የገዳ ሥርዓትም የሚያስተምረው ይሄንኑ ሲሆን፤ እንደ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ግለሰብ እያንዳንዱ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ሰላም ዋጋ ስላለው ድርሻውን መወጣት እንዳለበት የሚያስረዳም ነው ።
ምክንያቱም የሰላም ምንጩ አንድ ብሎ የሚጀምረው አንድ ግለሰብ ከራሱ ጋር ያለውን ግጭት መፍታትና ውስጡን ለሰላም ዝግጁ ማድረግ ሲችል እንደመሆኑ፤ የሰላማዊ ግለሰቦች ስብስብ ሰላማዊ ማህበረሰብን፤ የሰላማዊ ማህበረሰቦች ስብስብም ሰላማዊ አገርን ይፈጥራል ። ይህን መሰል ህዝቦች ያሉባት አገር ደግሞ ህዝቦቿ እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ሆነ ከፈጣሪ ጋር ያላቸው መስተጋብር ቀና ስለሚሆን ፍትህና መተባበር ብሎም አብሮነትን በማጎልበት በሰላም አብሮ መኖር፣ መስራትና መበልጸግ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው ። በመሆኑም ወጣቶች፣ ምሑራን፣ ፖለቲከኛው፣ ነጋዴው፣ ተማሪውና ሌላውም ሁሉ የህብረተሰብ ክፍል ሰላምን መፈለግ አለበት፤ ሁሉም ሰላም ያስፈልገናል ብሎ እያሰበ እንዲሰራም፣ እንዲጓዝም ይጠበቃል ።
ከግለሰብና ቡድኖች ባለፈም ያሉ አደረጃጀቶችም ሰላምን መሰረት አድርገው ስለሰላም መስራት ይጠበቅባቸዋል ። ምናልባት ሰላምን የማይፈልግ ኃይል እንኳን ቢኖር ከምንም በፊት ተቀራርቦ መወያየትና መግባባትን ማስቀደም እንደሚገባ የሚያስቀምጥም ስርዓት ነው ። ይህ ደግሞ ያሉ ልዩነቶችን ለማቻቻልና ልዩነትን አጥብቦ ፍቅርና አንድነትን ለማምጣት ሲሆን፤ ተግባሩም ሁሉም ለጋራ በጋራ እንዲቆም የሚያስችል ነው ። በመሆኑም ሥርዓቱ የሚመክረውም ሆነ የሚያስተምረው ይሄንኑ ሲሆን፤ ሰዎች ፈጣሪን ፈርተው እርስ በእርሳቸው ተስማምተውና ተፈጥሮን አክብረው መኖር አለባቸው የሚለው ማጠንጠኛው ነው ። አሁን ላይ የሚታየው ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ የሚለውም ሆነ የሰላምና የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳዮች ትኩረት ማግኘት ምንጭ ይሄው ነው ።
ይህ ሰላማዊ ግንኙነት ደግሞ በሰዎች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብና መደጋገፍን የሚፈጥር ሲሆን፤ የገዳ ስርዓትም ሰዎች በሰላምና በፍቅር አብረው እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን ያለው የሌለውን ሊያስብና ሊደግፍ እንደሚገባም ያስቀምጣል ። ለምሳሌ፣ በባህሉ መሰረት በአንድ አካባቢ አንድ ሰው ምንም የሌለው ከሆነ የአካባቢው ሰው ወይም ቤተዘመድ ይህን ሰው የመቋቋም ኃላፊነት አለበት ። በዚህም ቢያንስ አንድ ጊደር ወይም ወይፈን፣ ካልሆነም በቁርጥ (በቁጥር የማይገለጽ የከብት መጠን፣ ምናልባትም አምስት፣ አስርም፣ ሃያም ሊሆን ይችላል) ሊሰጠው ይችላል ። ከዚህ ባለፈ በዝናብም ሆነ በሌላ ምክንያት ምርት ጠፍቶ አንድ ሰው ለዘር የሚሆነው እህል አጥቶ ማምረት የማይችልበት እድል ሲፈጠር ያ ሰው ለማኝ ወይም የሰው እጅ ጠባቂ መሆን ስለሌለበት አዝመራው እስኪደርስ የሚቆይበትና ለአንድ ጊዜ የሚሆን እህል ይሰጠውና እንዲቋቋም ይደረጋል ።
ይህ የሚደረገው ደግሞ ሰዎች እንዳይቸገሩና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ሲሆን፤ በተቃራኒው እርዳታን ለምዶ ለመስራትና ለመለወጥ የማይሰራ ሰው ካለ በዘፈን ጭምር የሚነቀፍበት አካሄድም አለ ። በመሆኑም ይሄ ስንፍናን የሚያወግዝ መተሳሰብና መደጋገፍ በገዳ ሥርዓትና ባህል ውስጥም ያለ ነው ። ለምሳሌ፣ አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ዓለምን እያስጨነቀ ያለ እንደመሆኑ፣ በኢትዮጵያም ችግሩ እየከፋ ዜጎችንም ለችግር እያጋለጠ ያለ ችግር ነው ። በዚህ ረገድ እንደ አገር እየተሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ሲሆን፤ የህዝቡም መደጋገፍ በተለይም በወጣቶች፣ በባለሃብቶች፣ በግለሰብ ጭምር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የገዳ ባህል የሚደግፋቸው ናቸው ።
ይህ አገር በቀል ፍልስፍና ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ እና ለአገርም ለአህጉርም ማበርከት ያለበትን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ለማስቻል ደግሞ እንደ ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በገዳ ሥርዓት ላይ እያከናወኗቸው የሚገኙ በርካታ ተግባራት አሉ ። ለዚህም የገዳ ስርዓትን በትምህርት ስርዓት ውስጥ በማስገባት ጭምር የማስተማር ተግባር ውስጥ የተገባ ሲሆን፤ “ኢንትሮዳክሽን ቱ ገዳ ሲስተም” በሚል ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በኮመን ኮርስ ደረጃ መስጠት ተጀምሯል ። ከዚህ ባለፈ ገዳ ኤንድ ፒስ ስተዲስ በሚል በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይም ገዳ ኤንድ ገቨርናንስ በሚል በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት እያከናወነ ይገኛል ። ለዚህም የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ተከናውኖ የካሪኩለም ቀረጻ ላይ ተደርሷል ። ከዚህ በተጓዳኝ ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ መሰናዶ ባለው የትምህርት ደረጃ ትምህርቱን በምን አግባብ መስጠት ይቻላል በሚለው ላይም ጥናቶች እያካሄደ ይገኛል ።
ይሄን ለማድረግ ያነሳሳቸው ደግሞ ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ የሚስተዋለው ሥራ መሰረታቸው አፍሪካዊ ናቸው የሚባሉ ስልጣኔዎች ብዙ ጊዜ በምርምር የተደገፉ ያለመሆኑ ሲሆን፤ በጥናት አለመደገፋቸው ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ማየት ቢቻል በትምህርት የሚሰጡ ነገሮች ሁሉ ታሳቢ ያደረጉት የምዕራባውያኑን የምርምር ውጤቶችንና ፍልስፍናዎችን ብቻ ነው ። እናም አገር አገር መሆን ካለበት እና አፍሪካም አፍሪካዊ መሆን ካለባት እንደ አገርም አገራዊ ፍልስፍናን እንደ አፍሪካም አፍሪካዊ ፍልስፍናን መነሻ ማድረግ መቻል አለበት ። ይሄን የማድረግ ሂደትም ህዝቡን ወደማንነቱ የመመለስ ዓላማን መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ በራሱ አስተሳሰብና በአፍሪካዊ የባህል እሴቱ መመለስ ካልቻለና ከምዕራባውያኑ እየተቀዳ በሚሰጠው አስተምህሮ ትውልዱን በተለይም ወጣቱን ከማንነቱ እያስወጣው ወዳልሆነ ነገር እያስገባው ነው ።
ይህ ሊሆን ስለማይገባውና አዲሱን ትውልድም ወደ ነበረ ማንነቱና ፍልስፍናው እንዲመለስና እንዲመለከት ማስቻል ይገባል ። የገዳ ስርዓትን በዚህ መልኩ ወደ ትምህርት ስርዓት ውስጥ በማስገባት ለማስተዋወቅ የተፈለገው አብይ ጉዳይም ይሄንኑ ሲሆን፤ ትውልዱ የገዳ ስርዓት ያለውን አስተምሮ እና እሴት እንዲገነዘብ የማድረግ ነው ። ከዚህ ባለፈም በሥርዓቱ ውስጥ በጥልቀት ሊታወቁ እና ምናልባትም ሪፎርም የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ በምርምር ለመደገፍ ነው ። በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ጉዞ የነበረ ባህልና ፍልስፍናውን ማስተማር፣ በምርምር መደገፍ እንዲሁም ሌሎች ማወቅ ለሚፈልጉም በተለያየ መንገድ ግንዛቤ እንዲይዙበት እና በዚሁ አግባብ እንዲሰራበት ማስቻልን መሰረት ያደረገ ሥራ ነው ።
በዚህ መልኩ የገዳ ሥርዓትና አስተምህሮን ማስተማር፣ በምርምር ማገዝና ማሳወቅ ሲቻል ደግሞ፤ በአፍሪካ ውስጥ ለሰላም ማረጋገጥ እና ለሰላም ጥሩ መሰረት ሆኖ ማገልገል የሚችል ፍልስፍና መኖርን ለዓለም ማሳየት፤ ከማሳየትም በላይ ለሰላም መስፈን ሚና እንዳለው በተግባር የሚውልበትን እድል መፍጠር ነው ። የሥርዓቱ ፍልስፍናና አስተምህሮ ደግሞ ከሰላም ግንባታ ባለፈ ለልማት ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፤ ልማት ሲሰራ ደግሞ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ ነው ። በዚህ ረገድም በእስካሁን ጉዞ ከውጭ የተቀዱ አሰራሮች ያስከተሉትን ጉዳት በመለየት ልማትና የአካባቢ ጥበቃን እውን ማድረግ የሚቻለው ከውጭ በሚቀዱ አሰራሮች ሳይሆን በራስ ፍልስፍናና አገር በቀል እውቀት ታግዞ መሆኑን ለማስረዳትም ነው ።
በመሆኑም ሰው ከተፈጥሮ ጋር ሳይጣላ እንዴት ዘላቂ ልማቱን ማረጋገጥ እንደሚችል የሚያሳይም ነው ። ይሄን ታሳቢ ያደረገ ገዳ ኤንድ ኢንቫይሮመንት የሚል አንድ ኮርስም ተዘጋጅቷል ። ከሰላምና ልማት ቀጥሎም፣ ፍትህና ፍትሃዊነትን መረጋገጥ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ ፍትህን ከውጭ በተቀዱ የሕግ ሥርዓቶች ብቻ ማረጋገጥ ስለማይቻል በህብረተሰቡ ውስጥ ፍትህን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል የገዳ ሥርዓት የሚያስቀምጣቸውን ነገሮች ማስተማር ሌላው ተግባር ነው ። በዚህ መልኩ ከተሰራም የህዝቡን የሰላም፣ የልማትና የፍትህ ፍላጎት ማሟላት ይቻላል ። ገዳን በዚህ መልኩ ማስተማር ደግሞ ለዚህ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በምርምር ጭምር በመታገዝ ለማፍራት ነው ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ወንድወሰን ሽመልስ