ቅድመ- ታሪክ
ዓመታትን በትዳር የዘለቁት ጥንዶች መሃላቸው ቅያሜ ከገባ ሰንብቷል። እስከዛሬ የቤታቸውን ገመና ሰው ሰምቶት አያውቅም። አንዳቸው የሌላቸውን አመል እየቻሉ በትዕግስት ሊያልፉ ሞክረዋል። አሁን ግን ይህ ልማድ አብሯቸው የሚቆይ አይመስልም። ንትርካቸውን ጎረቤት፣ ገመናቸውን ወ ዳጅ ዘመድ ያው ቀው ጀምሯል።
ባልና ሚስቱ በትዳር ዘመናቸው ሰለሞንና ሜላት የሚባሉ ልጆችን አፍርተዋል። እስከዛሬ በቅያሜ ውስጥ ሆነው የመጣመራቸው ሚስጥርም የሁለቱ ልጆቻቸው ጉዳይ መሆኑን ያውቁታል። እስካሁን ባልተመቸ ህይወት ካንገት በላይ ሲኖሩ ላለመለያየት ሰበባቸው እነዚሁ ልጆች ነበሩ ። አሁን ግን ይህ እውነት በነበረ የሚዘልቅ አይመስልም። ጠብና ቅያሜያቸው ጫፍ ደርሶ ለመለያየት ወስነዋል።
ሽምግልና
የጥንዶቹን ችግር በእርቅ ሊፈቱ የሞከሩ ወዳጅ ዘመዶች ሃሳባቸው አልተሳካም። ባልና ሚስቱ የትናንቱን አብሮነት ‹‹ለልጆቻችን›› እንዳላሉ ዛሬ ነጻነትን ሽተው መለያየትን መርጠዋል። ይህን ያወቁ አስታራቂዎችም በጉዳዩ ተስፋ ቆርጠው በመጡበት ተመልሰዋል።
ፍቺ
በወዳጅ ዘመድ ሽምግልና በእርቅ ያልዳነው የትዳር ጉዳይ ውሎ አድሮ ከፍርድቤት ደርሷል። ማመልከቻው የደረሰው ፍርድቤት የፍቺውን ጥያቄ አይቶ ለይሁንታው አልቸኮለም። ሁለቱም ጊዜ ወስደው ያጤኑት ዘንድ የማሰላሰያ ጊዜን ሰጥቷል። የኖሩበትን ዓመታትና ያፈሯቸውን ልጆች ዕጣ ፈንታ ከግምት አስገብቶም ጉዳዩ ዳግም በቤተዘመድ ጉባኤ እንዲታይ ወስኗል።
ባልና ሚስቱ የተሰጣቸውን ዕድል መጠቀም አልፈለጉም። ውስጣቸው የከረመው ጠብና ነገር በመለያየት ይቋጭ ዘንድ የፍቺ ይሁንታቸውን በስምምነት አጸደቁ። ፍርድ ቤቱ ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ሲያውቅ ህግና ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት የባልና ሚስቱን ጉዳይ በፍቺ አጽድቆ አለያየ ።
ትዳሩ በፍቺ እንደተቋጨ የሁለቱ ልጆች ሃሳብ ለሁለት ተከፈለ። የእናት አባታቸው መፋታት እውን መሆኑን ያወቁት ህጻናት ከማን ጋር እንደሚሆኑ ጨነቃቸው። ወላጆቻቸውን በእኩል ፍቅር ያያሉና በሰቀቀን ሆነው ለውሳኔ ተቸገሩ።
የንብረት ክፍፍሉ አልቆ ወላጆች የግላቸውን ህይወት ሲጀምሩ ሰለሞን የተባለው ልጅ አባቱ ዘንድ ለመሆን ወሰነ። ሜላት ደግሞ እናቷን መርጣ ከአባቷ ተለየች።
አዲስ ህይወት
የሁለቱ ህጻናት ወላጆች ከተለያዩ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ባል ከባለቤቱ እንደተፋታ ሌላ ሚስት አግብቶ አዲስ ጎጆ ቀልሷል። ከቀድሞ ሚስቱ የወለደው ሰለሞን ዛሬም ድረስ አብሮት ይኖራል። ሴቷ ልጁ ሜላት ኑሮዋ ከእናቷ ጋር ቢሆንም ባመቻት ጊዜ አባቷን ትጠይቃለች።
ሰለሞን አባቱ ሌላ ሚስት ካገባ በኋላ የተመቸው አይመሰልም። ከእንጀራ እናቱ ጋር ያለው ቀረቤታ በጎ ባለመሆኑ ባህሪው ተቀይሯል። አንዳንዴ ድንገት ተነስቶ እናቱ ዘንድ ይሄዳል። እናት ሁኔታውን ባየች ጊዜ ያልተገባ ጠባይ እንደያዘ ገምታ ፊት ትነሳዋለች። ተመልሶ ቤት ሲገባም የአባቱና የእንጀራ እናቱ ግሳጼ ይቀበለዋል።
የነሰለሞን እናት ከቀድሞ ባሏ እንደተለየች ሌላ ትዳር መስርታ ልጆች አፍርታለች። አንዳንዴ ሰለሞን ሊጠይቃት ሲመጣ እንደቀድሞ በፍቅር አትቀበለውም። ልጁ የእጅ ዓመል እንዳለበት በመጠርጠሯ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ቅጣትን አስቀድማ ትገርፈዋለች ።
ሰለሞን የእናቱን ቅጣት ከበጎ ቆጥሮት አያውቅም። በየጊዜው የሚገጥመው ከምክር የዘለለ ፊት መንሳትም ከልቡ እንዳስመረረው ያስታውቃል። የልጅነት አቅርቦቱን ከመገለል የቆጠረው ታዳጊ ውስጡ ጥላቻና ቂም ያድርበት ይዟል።
ልዩ ቅጣት
ሰለሞንን በአይነቁራኛ የምታየው እናት በየጊዜው በልጇ ላይ ቅጣት ነው የምትለውን ድርጊት ቀጥላለች። አንዳንዴ እንደነገሩ ብትተወውም አንዳንዴ ደግሞ ጠንከር አድርጋ ትቀጣዋለች። ይህን ልማድ በመማረር የሚቀበለው ሰለሞን ባጠፋ ቁጥር ግርፊያው ቀርቶለት አያውቅም። ታዳጊው በአባቱ ቤት ያጣውን ፍቅር በእናቱም ዘንድ መነፈጉን እያሰበ ይከፋል። እናትም ስለነገው ማንነቱ ሥርዓት ልታሰይዘው እያሰበች ትቆጣዋለች ፣ትቀጣዋለች፣ ትገርፈዋለች።
አንድ ቀን የሰለሞን እናት በልጇ ላይ ጨከን አለች። ዛሬ ያለምንም ገላጋይ እየቀጣች ልታስተምረው የፈለገች ይመስላል። እጁን እየጎተተች ከቤት አስገባችና በሯን የኋሊት ዘጋች። ዱላ ሊነሳ እንደሆነ የገመተው ልጅ እንደለመደው ድምጹን ከፍ አድርጎ ጮኸ ። ይህን ስታይ እናት እልህ ገባት። ደጋግማ እየመታች አፉን እንዲይዝ አስጠነቀቀቸው። ህጻኑ ሰለሞን አልሰማትም። ያለማቋረጥ እየጮኸ ከመሬት ተንከባለ። እናት በእልህ እንደጋየች በእሳት ወደሞላው ምድጃ ቀርባ አንድ ቢላዋ ወደፍሙ አስገባች። ቢላዋው አፍታ ሳይቆይ መቅላት ጀመረ። እጆቹን እኩል ዘርግታ እያገላበጠች አቃጠለችው።
ይህን ድርጊት ያዩና የሰሙ ጎረቤቶች እናቲቱን ይዘው ፖሊስ አስጠሩ። ልጁን ለህክምና አድርሰውም በህጻናት መብት ጥሰት ከፍርድቤት አቆሟት። ሰለሞን የደረሰበት ቅጣት የከፋ በመሆኑ ቁስሉ እያንገበገበ አሰቃየው።
ውሎ ሲያድር ዕንባውን ጠርጎ እንደቀድሞው ለመሆን ሞከረ። ቁስሉ እየዳነ ማገገም ሲጀምር ነገሮችን በመርሳት ጨዋታውን ቀጠለ። ልጅነቱ እያመዘነ ከእኩዮቹ ጋር ሲውል የሆነው ሁሉ ውል እያለ ያስጨንቀዋል። በውስጡ የተለየ ስሜት መመላለስ ይጀምራል። ጥላቻ መገለልና ራስን መጥላት ይፈትኑታል።
ወጣትነት
አሁን ሰለሞን የልጅነት ዕድሜውን ሸኝቶ ወጣትነቱን ጀምሯል። ይህ ጊዜ የትናናንት ማንነቱን የሚያይበት መስታወት ሆኗል። ያለፈውን ኑሮ ከአሁኑ የሚያወዳድርበት ሚዛኑ። ባሳለፋቸው ዓመታት በህይወት መንገዱ ብዙ አጋጣሚዎችን አልፏል። ከዚህ ቀድሞ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ቆይቷል። የሚያድርበት ጠፍቶም የሚቀምሰው አጥቷል። ይህ ሁሉ ግን ለእርሱ ዛሬ በነበር ያለፈ ታሪክ ነው። ስለሆነው ሁሉ የማያስብበት አውነት ከሆነም ዓመታ ተቆጥሯል።
ሰለሞን እነዚህን ሁሉ ረስቶ ራሱን ለመለወጥ በተለያዩ ስራዎች ተሰማርቶ ቆይቷል። በትምህርቱም ቢሆን የተሻለ ለመሆን እየሞከረ ነው። ለዚህ ለውጥ ማሳያም እስከ ቴክኒክና ሙያ ድረስ ዘልቋል። አሁንም ግን ዘወትር የሚያስታውሰውን ልጅነቱንና የእናቱን ቅጣት መርሳት አልቻለም። እናቱ በእሱ ላይ በፈጸመችው በደል ተከሳ ያለቅጣት መለቀቋን ያውቃል። ይህን ባሰበ ጊዜ ንዴትና እልህ ይይዘዋል። የዛኔው ለቅሶና ስቃዩ እየተመላለሰ ይፈትነዋል።
ሁሌም ቢሆን ይህን ያለፈ ታሪክ ለመርሳት ከራሱ ጋር ይሟገታል። በእጆቹ ላይ የታተሙት ፈዛዛ ጠባሳዎች ግን አሁን የሆነ ያህል እያስታወሱ ወደኋላ ይመልሱታል። እንዲህ በሆነ ጊዜ የእናቱ ጥላቻ ይጨምራል። በእሳት ግሎ ያቃጠለው ቢላዋ ውል እያለው የእሳቱ ግለት ወስጡ ደርሶ ያጋየዋል።
ሰለሞን በዕድሜው ከፍ ባለ ጊዜ በእናቱ ላይ የቋጠረው ቂምና ጥላቻ አየለ። እናቱ ሌላ ባል አግብታ አዲስ ህይወት መጀመሯ በእሱና በእህቱ ላይ በደል ለመፈጸም እንደሆነ ያምንበት ያዘ። ይህ እምነት ጎልብቶ በውስጡ ውሎ ሲያድር ቀድሞ በእሱ ላይ የሆነውን ሁሉ እያሰበ በእናቱ ጥላቻ እንዲብከነከን ምክንያት ሆነ።
መጋቢት 10 ቀን 2011 ዓም
ሰለሞን ይህ ቀን ከመንጋቱ አንድ ቀን አስቀድሞ ከተወለደበት ገርጂ ሰፈር ፈቀቅ ብሎ መብራት ሃይል ከተባለ አካባቢ ሲጠጣ አድሯል። ሁሌም መጠጥ በቀመሰ ቁጥር ውል የሚልበት ልማድ ዛሬም ከእሱ ጋር አምሽቶ አንግቷል። ለሊቱን ሙሉ መጠጥ በሞላው ብርጭቆ ጠረጴዛውን እየመታ ሲቆዝም እናቱንና የልጅነት እድሜውን እያስታወሰ ነው።
ሌቱ በብርሃን ተተክቶ ንጋቱ ሲበሰር ሰለሞን በመጠጥ ደክሞ እንደደነዘዘ ነበር። የነበረበትን ስፍራ ለቆ ወደቤቱ ሲያመራም ያደረበት ስካሩ አልለቀቀውም። መኖሪያው እንደደረሰ አይኖቹ አንዳች ነገር ፍለጋ ቃበዙ። ጥቂት ቆይቶ የፈለገውን በእጁ አስገባ። ከዚህ በኋላ አፍታ መቆየት አላሻውም። በሩን እንደነገሩ መለስ አድርጎ ወደእናቱ መኖሪያ ገሰገሰ።
ከእንቅልፏ ነቅታ በሌሊት ልብሷ ውሃ ለመቅዳት ከቧንቧው ጥግ የቆመችው ወይዘሮ የውሃውን መሙላት እየጠበቀች ከቤት የተኛውን ህጻን ድምጽ ታዳምጣለች። ድንገት የውጭው በሩ ተበርግዶ አንድ ሰው ወደ እሷ መቅረቡን ስታይ ግን በድንጋጤ ክው አለች። አዎ ! ከፊት ለፊቷ ቆሞ በንዴት ዓይኑን የሚያፈጠው ወጣት በቅርብ አይታው የማታውቀው ልጇ ሰለሞን ነበር።
ወይዘሮዋ በዚህ ማለዳ ከቤቷ መምጣቱ ለሰላም አለመሆኑን ገምታ በድንጋጤ መጮህ ጀመረች። በዚህ መሀል ከዕንቅልፉ የባነነው ትንሹ ልጇ ወደ እነሱ እየመጣ መሆኑን አስተዋለች። ሰለሞን በጎኑ የሻጠውን ቢላዋ አውጥቶ ቀረባት። አሁን የልጅነት ጊዜውንና በእሳት ግሎ ያቃጠለውን ቢላዋ እያሰበ ነው።
እናት ሁኔታውን ስታይ አጥብቃ ተማጸነቸው። ልመናዋን አልሰማም። ጥርሱን እንደነከሰ የያዘውን ቢላዋ ሰነዘረ። ራሷን ለመከላከል ሞከረች። አልቻለችም። ቢላዋው ሁለቱንም እጆቿን ሸረከታት። ደሟን እያዘራች ትንሹን ልጅዋን አየቸው። ወደ እሷ ሲመጣ በመውደቁ ድንጋይ መሀል ግንባሩን አግኝቶታል። መለስ ብላ ትልቁን ልጇን መማጸን ቀጠለች። ሰለሞን አሁንም ሰነዘረ።
ሶስት ጊዜ የተሰነዘረው ቢላዋ ደረቷን አልፎ ሆዷን አገኛት። ነፍስ ይዟት ፊቱን ቧጨረችው። ይህኔ ቢላው ሳት ብሎ እጁን ቧጨረው። የያዘውን ሳይለቅ ወደ አንገቷ ዞረ። አንገቷን በስለቱ እየገዘገዘ እልህ በሞላው ንዴት ጨኸ፣ አይኖችዋ በተማጽኖ እንደተገለጡ በትዝብት አየችው።
አሁንም ትንሹ ልጅ አምርሮ ያለቅሳል። ሰለሞን የእናቱ ሁለመና በደም ተነክሮ ከመሬት መውደቁን አየ። ዘጠኝ ወር የተሸከመው ሆዷ፣ ለዓመታት አጥብተው ያሳደጉት ጡቶቿ፣ አዝሎት የዞረው ጀርባዋ፣…. መላው ማንነቷ እንዳይሆን ሆኗል። ቢለዋውን ጥሎ መንቀጥቀጥ ጀመረ። ጥቂት ቆይቶ ጊቢው በሰዎች ተሞላ። ሁኔታውን ያዩ ጎረቤቶች ሰለሞንን ለማረጋጋት እየሞከሩ ወደ ፖሊስ ደወሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ገርጂ ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 13 ልዩ ስሙ ‹‹ካዛንቺዝ›› ከተባለ ሰፈር ሲደርስ የወይዘሮዋን ቤት በጥቆማ አገኘ። ከጊቢው እንደደረሰ ስፍራው በሰዎች መሞላቱን አስተዋለ። አንድ ልብሱ ደም የነካና ያልተረጋጋ ወጣት በሰዎች ተከቦ ተቀምጧል። ፖሊስ ተጠርጣሪው መሆኑን ገምቶ ሁኔታውን ጠየቀ፡ ፡ሰለሞን የሆነውን አልደበቀም።
ፖሊስ ከተገቢው የአስከሬን ምርመራ በኋላ የሟችን በድን ከስፍራው እንስቶ ጣቢያ ለቀረበው ተጠርጣሪ ጥያቄ አቀረበ። ሰለሞን ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረውን ህይወት አንድ በአንድ አስረዳ። እናት አባቱ በፍቺ ከተለያዩ በኋላ የደረሰበትን ችግር በሙሉ ተረከ። በአንድ አጋጣሚ ወላጅ እናቱ በጋለ ቢላዋ እንዳቃጠለችው አስታውሶም የቁስሉን ስቃይ፣ አብሮት ያደገውን ቂምና ጥላቻ በዝርዝር ተናገረ። መርማሪው ዋና ሳጂን አማረ ቢራራ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 383/11 በተከፈተው ፋይል ላይ የተጠርጣሪውን ሙሉ ቃል እስፍሮ ጉዳዩን ወደ ዓቃቤ ህግ መራው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
መልካምስራ አፈወርቅ