ፖለቲከኞች ምን ይደስኩሩ…ሰባኪያንስ ምን ይስበኩ….ንግግር አዋቂዎች ምን ይናገሩ? ብለን ሰሞኑን ከጠየቅን አቻ የሌለውን ገንቢ ቃል ፍቅርን ይስበኩ፤ ይደስኩሩ፤ ይናገሩ። እንደእርሱ ለሰው ልጆች ፣ የሚያዋጣን ነገር እንደሌለ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በአሜሪካ የተፈጠረውና እስካሁን ጨርሶ ያልበረደው ሁከት በቂ ምስክር ነው።
ጆርጅ ፍሎይድ የ46 ዓመት አሜሪካዊና የቀድሞ የአሜሪካ ፣ እግር ኳስ ተጫዋች ሲሆን የ20 ዶላር ደረቅ ወይም የማይሰራ ቼክ ክፍያ ፈጽሟል፤ ተብሎ በፖሊስ ለጥያቄ የተፈለገ ተጠርጣሪ ሰው ነበር። ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ቃሉን እንዲሰጥ እንደሚፈለግ ይነግረዋል፤ ታዘዘላቸውና ከመኪናው ወጣ፤ የኋሊት ታሰረ፤ ወደመኪናው አስገብተው ይዘውኝ ይሄዳሉ ብሎ ሲጠብቅ፣ አስፋልቱ ላይ አጋደሙት፤ ተኛላቸው። ቾቪድ የተባለው ፖሊስም ያለርህራሄ በአንድ ጉልበቱ አንገቱ ላይ በሌላው ጀርባው ላይ ቆሞ በመነቅነቅ አተነፋፈሱን ለ10 ደቂቃዎች በማዛባት ለሞት ዳረገው።
እዚህ ላይ የፖሊሱ ገዳይነት ብቻ አይደለም፤ ህግ እና ሥርዓት ሲጣስ አጠገቡ የነበሩት ሶስት ፖሊሶች ዝምታ፣ ድርጊቱ በፊልም እየተቀረጸ ሳለም በማናለብኝነት ድርጊቱን ለመፈጸም መወሰኑ፣ ጭካኔ የተሞላበትን ግድያ ከፈጸመ በኋላ ደግሞ፣ ተነስና መኪና ውስጥ ግባ ፣ አታታልለንም ብሎ የሞተን ሰው ሰብዓዊነት በጎደለው ጎን መጎሻሸምና ይህንንም ፈጽሞ ለህክምና አለመተባበር፤ አሰቃቂ ድርጊት ነው።
እውነት ፖሊሱ የግል ቂም እንኳን ቢኖረው፣ ጠላቱን ከጣለ በኋላ በርህራሄ ጀግንነቱን ማሳየት አይሻለውም ነበር፤ ወይስ ያንን በማድረግ የጥላቻ ጥሙን ማርካት ይሻለው ነበር? ጥላቻ አባብሎና አባልጎ ልባቸውን የደፈነባቸው ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር አስከፊነት ከቶውንም ሊገነዘቡ እንደማይችሉ ዓለም እስኪታዘባቸው ድረስ በመፈጸም አሳዩት። አራት ፖሊሶች ሰባት ዓይናቸውን ጨፍነው በአንድ ጨካኝ “አንድ ዓይና” ፖሊስ በመመራት አስተዛዛቢ ግፍ በሚኒያፖሊስ ከተማ ላይ ፈፀሙ።
ነፍሰገዳዩ ፖሊስ፣ በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ ግዛት የፖሊስ ዲፓርትመንት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ነበር። ይሁንናም የዜጋውን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ በድፍረት ቅጥ የለሽ ጭካኔ ሲፈጽም ታይቷል። ጆርጅ ፍሎይድ በሚያሳዝን ሁኔታ “መተንፈስ አልቻልኩም፣ እባካችሁ አስጥሉኝ ፤ …. ተወኝ እባክህ ወንድሜ፣ ……መኖር እፈልጋለሁ”፤ እያለ ቢማፀነውም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በጭካኔ እስኪሞት ድረስ በመጫን ለህልፈተ ህይወት ዳርጎታል።
ነፍሰገዳዩ ፖሊስ ፣ ቾቪድ ዴሪክ እንደ ፍሎይድ ሁሉ የአሥር ዓመት ትዳር ያለው፣ (ከዚህ ጨካኝነቱ በኋላ፣ ባለቤቱ ፍች ጠይቃበታለች) የሚሳሳለት ልጅ ያለው፤ ከሥራ በኋላ ወደቤቱ ለመሄድ የሚጣደፍ ሰው እንደነበር ተነግሯል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ዓመለኛው ቾቪድ በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተከሰሰ፣ ተዛላፊና በዘረኛ አመለካከት የታወረ፣ በዘር የበላይነት ትምክህት የተወጠረና ያንንም ያለሀፍረት የሚናገር ሰው እንደነበር በኋላ ላይ ተነግሯል። ይህንን ፀረ-ሰብዓዊ አመለካከት ያለው ሰው በፖሊስ ክፍሉ ውስጥ ለማቆየት የታላቂቱ አሜሪካ ዴሞክራሲያዊ መብት ይፈቅዳል መሰለኝ፤ ምክንያቱም ምንም አልተባለም ወይም በዚህነቱ ሰውየው ሳይኮራ አልቀረም ።
ቾቪንን ልጠይቀው የምወዳቸው 100 ጥያቄዎች ቢኖሩኝም ይህንን እድል አላገኝምና፤ የእርሱ ብጤ ዘረኞችን የምጠይቃቸው ጥቂት ጥያቄዎች አሉኝ።
አንደኛ፡- ስትወለዱ ከየትኛው ዘር ለመወለድ ጥያቄ አቅርባችሁ ነበር?
ሁለተኛ፡- ከተወለዳችሁስ በኋላ በተወለዳችሁበት ዘር በመወለዳችሁ ኩራት ይሰማችኋልን ?
ሶስተኛ፡- እንቅልፍ፣ ረሐብ፣ ውጥረት፣ ድካም፣ ፍቅር፣ የዋህነት፣ የመሳሰሉትን ረቂቅ ስሜቶች ከሰው ሁሉ ጋር እንደምታጋሩት ታውቁታላችሁን?
አራተኛ፡- ማንም ቢሆን ወደዚህ ምድር የመጣው ኑሮው ሥራውና አጋጣሚው የፈጠረለትን እድል ተጠቅሞ እንደ እናንተው ራሱን የማሳደግ ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው አታውቁምን ?
አምስተኛ ፡-የችግሮቻችሁ መነሻ ሁሉ ከተወለዳችሁበት ዘር መወለዳችሁ ነው፤ ወይስ ሌላው ዘር አጠገባችሁ በመኖሩ ነው? ወይስ ሁለቱም ነው?
ስድስተኛ፡- ያለህባት ምድር ስሟ ማንም ይሁን ምን ያወጣላት ሰው እንጂ አምላክ እንዳልሆነና ሰዋዊ ነገር አላፊ ጠፊና አርቲፊሻል መሆኑንስ አታውቅምን? ምድር በመልክዓ ምድርነት ተጠፍጥፋ ለአንድ ወገን አለመሰጠቷንስ አትረዳምን? እያልን ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ፣ አስርና ሃያ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ለመሆኑ ለእነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ውስጥ ሰብዓዊነት እኩል ክብር እንዳለው ማወቅ አይቻልምን?
ማንኛውም ሰው የመስራት፣ የመቀበል፣ የመድረስና የመውጣት እድሉ ካለው የትኛውንም ኃላፊነት ተቀብሎ የመፈፀም ብቃት እንዳለው አታውቁምን ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሳችሁ “አዎና አይሆንም” ከሆነ የቆማችሁበትን ቦታ በቅጡ እንድትፈትሹ እጠይቃለሁ። የትኛውም የሰው ልጅ አለምክንያት በዚህ ምድር አልተፈጠረም፤ ሌላው ቀርቶ ታናናሾቹን ተሐዋሲያን እንኳን በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው በምግብ ስርዓት ውስጥ ታላቅ ድርሻ ያላቸውና ለእኛ በምግብነት ጠቃሚ ለሆኑ ነገሮች ምግብ የሚሆኑ ናቸው እኮ። እናስ ራሳችሁን ብቻ ነው፤ አስፈላጊና ተፈላጊ አድርጋችሁ የምትቆጥሩት? ኧረ፣ በቅጡ ይታሰብበት!!
በ1981 ዓ/ም. ተደርጎ በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ፤ ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዱ ጄኔራል ፋንታ በላይ ነበሩና ። ከተያዙ በኋላ ለመቆም እስከማይችሉ ድረስ ተደብድበውና እግር ተወርች ታስረው ከደረት በላይ ነበር በዘመኑ ብርቅ በነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት የታዩት።
ጋዜጠኛው ይሁን አጠገባቸው የነበረው ሰው ሳይጎሽማቸው ሁሉ አልቀረም፤ እየተሸማቀቁ ነበር፤ ቃል የሚሰጡት ። በቅርብ ከነበሩት ሰዎች አንዱ እንደተናገረው፤ መንግስቱ ኃይለ-ማርያም ጄኔራሉ ከተያዙ በኋላ መጥተው ክፉኛ አናንቀው ከሰደቧቸው በኋላ ፕሬዚዳንት ሊኮን ነበር? ብለው ሲሳለቁባቸው፤ ጄኔራል ፋንታ፣ ያለማመንታት፣ “እንኳን እኔ አንተም መሪ ሆነሃል”፤ ሲሉ መልስ እንደሰጧቸው ይነገራል። እውነት ነው፤ ራሳቸውን የነገር ሁሉ መነሻ አድርገው የሚያዩ፣ ያለ እነርሱ ፀሐይ ጠልቃ እንደማትወጣ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገርግን አንዳንዴ ለእውነት ሲሉ ለራስ ሳይሳሱ ሊነገራቸው ይገባል፤ ሰው ኃላፊነት ከተሰጠውና ምክር መስማት የሚችል ከሆነ፣ ሊያከናውነው የማይችለው ኃላፊነትና የማይወጣው ዳገት የለም።
በሌላ አባባል ፣ የሰው ልጅ ፣ ሁኔታው ሲመቻችለት፣ በተሰጠው ስፍራና ጊዜ ኃላፊነቱን በሚገባ ለመወጣት ትከሻው አያንስም ። ቁምነገሩ የተሰጠውን ኃላፊነት ልክ መረዳቱና ተጠያቂነትን ለመቀበል መቻሉ ነው፤ ቁምነገሩ። ኃላፊነቱን በቅጡ ከተረዳ በሚገባ በመወጣት ሥራው የሚያስገኘው ትሩፋት ለሌሎች እንዲተርፍ ምክንያት ይሆናል።
ሰውን በዘሩ ማንነት መምራት አይችልም ፤ በቆዳው ቀለም ታናሽ ነው ብሎ ማሰብ ፤ በአፍንጫው ማጠር ጨካኝ ፣ በአፍንጫው መርዘም ርህሩህ አድርጎ መጠቅለል ወይም በተቃራኒው በመንጣትና ቅላቱ ራሱን የመልካምነት ምንጭና የተገቢነት ዋልታ አድርጎ ማሰብ እጅግ ጅልነት ነው።
በሥነ-ጽሑፍ የኖቤል አሸናፊና የተውኔት ደራሲው ብሪታኒያዊው (ሰር) በርናርድ ሾው፤ (1856-1950) በኖቤሉ ሽልማት ሳቢያ በተደረገ የእራት ግብዣ ላይ በርካታ ሥመ-ጥር ሰዎች ተጋብዘው ነበር። ከእነዚህም አንዷ ፣ በወቅቱ ወይዘሪት ብሪታኒያ በመሆን የቁንጅና ውድድር ያሸነፈች ሴት ነበረችና ተገናኙ። አድናቆቷን ከፍ ባለ ስሜት ነገረችው። እርሱም በአክብሮት ተቀበላትና ስሟን ጠየቀ። ስሟን ባለማወቁም ተገርማ ነገረችው።
አድናቆቷን ተቀብሎም ለጥቂት ጊዜ ሲያወራት ስለእርሱ ሽልማትና ሥራዎች ብዙ ባይገባትም፣ ግን ዝናው ያማለላት ይህች ቆንጆ ሴት፣ ማን መሆኔን ተረዳህን ? አለችው፤ ሰር በርናርድ ሾውን ለማስደመም።
በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የብሪታኒያ ቆነጃጅት መካከል አንዷ ነች ብዬ አስባለሁ፤ አላት። ብቻ እኮ አይደለሁም ፤ የወቅቱ የብሪታኒያ የቁንጅና ንግስት ነኝም፤ አለችው ኮራ ብላ። አጨበጨበና ስለተዋወቅሽኝ አመሰግናለሁ፤ ሌሎች እንግዶችም ስላሉኝ፤ ከመሄዴ በፊት ግን የምትነግሪኝ ሌላ ነገር ይኖር ይሆን?
በሚገባ ፤ እስቲ እንደዚህ አስብ አለችውና ፣ እኔና አንተ ብንጋባ እኮ ከእኔ ውበትና ካንተ ጭንቅላት የሚወለደውን ሰው መገመት ትችላለህ ? ውብና አስደናቂ ጭንቅላት ያለው ሰው ፤ ለዓለም አበረከትን ማለት እኮ ነው፤ አለችው ፤ ፈርጠም ብላ። በወቅቱ የ61ዓመቱ ባለቅኔ፣ ትክ ብሎ በኀዘኔታ እያያት ፣ “የተገላቢጦሽ ከሆነስ?” ”ማለት፤” አለችው።
ካንቺ ጭንቅላትና ከእኔ መልክ ወስዶ ቢወለድስ፤ ምን ትያለሽ፤ አላት። ምንም፤ ነበረ መልሷ፤ እናም በቆመችበት ጥሏት ሄደ። ህጻንነት በእርጅና፣ ወጣትነት በጉልምስና፣ ውበትም በመገርጀፍ፣ ሃይልም በድካም ፤ጉልበታማነት በዝለት፣ ከፍታ በዝቅታ፣ ሹመት በሽረትና ፣ እስር በመፈታት፣ ወዘተ… ይለወጣል። ባሉበት ቆሞ ራስን ማግዘፍ የትም አያደርስም። ይህች ሴት ያላወቀችው ትልቁ ነገር ደግሞ ለቁንጅናዋ ንኡስ ነገር አለማዋጣቷን ነው። በቃ ቆንጆ ሆና ተወለደች፤ ተወለደች።
ዘረኛ ሰዎች የሚፈልጉትን ቀድመው ወስነው፣ በሌላው ሰው ላይ የሚጭኑና ካልሆነ ደግሞ፣ ለመቀበል የተዘጋጀ ልብ የሌላቸውና ውስጣቸው ባልተገባ ኩራት የተደፈነ ምናምንቴ አሳቢዎች ናቸው። ማናችንም ወደዚህ ምድር ከተሰጠን ነገር ጋር እንወለዳለን እንጂ፤ ራሳችንን ቅድመ-ወሊድ አንወልድም ። የተሰጠንን ሆነን እንወለድና በሰው መለኪያ ብናምርም ፣ ባናምርም ዓለምን ቆንጆና ውብ ስፍራ አድርገን እንኖርባታለን። ያኔም ውበታችን ይገለጣል። በቀይነታችን ብልህና ጠቢብ ፣ በጠይምነታችን ድንቁርና፤ በነጭነታችን ባለጸጋነት በጥቁረታችን ድህነት የተሰጠን አይደለንም ፤ ብሎ ነገርም የለም።
ይህንን ምሳሌ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም ። የበርናርድ ሾው ባለቅኔ ልብ የዚህችን ከቁንጅናዋ በቀር ምንም ማስተዋል የሌላትን ሴት የሐሳብ ፍጻሜ ቀድሞ ስላገኘው ነው፤ ያዘነባት። ልታገባው የፈለገችው ወይም ልትጣመር የፈለገችው ከ”ሰር በርናርድ ሾው” ዝና ጋር እንጂ ፤ ከሰውየው ሰብዓዊ ክብርና ልዕልና ጋር አይደለም ።
ብዙ ጊዜ፣ የተደፈነ ልብ መነሻው ባዶ ዝና ነው፤ በዝናው ውስጥ የሚገኘውን በምንም መልክ የቀለመ ቦታ ለመያዝ ይጣደፋል። ውጤቱ ካላማረም ተስፋ መቁረጥና ጥላቻ ቤቱ ይሆናሉ፤ ይህም ራስን አግዝፎ ከሚነሳ አእምሮ የሚመነጭ እቅድ ፍጻሜው የማያምር አካሄዱ የሚዘገንንና ለሰውልጆች በጎነት የሚሰጠው አስተዋጽዖ ገንቢ ያልሆነ ነው። ጥላቻ አቻ የሌለው አጥፊ ነው።
ወደ መነሻ ነገሬ ልመልሳችሁና ፣ ጥላቻ ሲከፋ ሰብዓዊ ክብርን ያስረሳል። ጥላቻ ሲበረታ ገድሎ ጀግና ጀግና ያጫውታል። ጥላቻ ሲያይል ለምህረትና ርህራሄ ምክንያት ያሳጣል። ጥላቻ ሲከረፋ ሸታው ሰብዓዊነትን ያቀረናል። ጥላቻ እንዲህ ሲያድግ ገድሎ ሟችን አታላይ አስብሎ ያሰድባል።
ቾቪድ ዴሪክ የተባለው ፖሊስና ግብረ አበሮቹ ያደረጉት ይህንን ነበር። ኮሮና ትንፋሽ እንደሚያሳጥር ሁሉ ጤናማውን ሰው እንደኮሮና ትንፋሽ አሳጥተው፣ ገድለውት ተዝለፍልፎ ወድቆ ሊያታልለን ስለፈለገ ነው ያልተነሳው፤ ብለው ሪንግ ውስጥ እንደተዘረረ ቦቅሰኛ፣ ተነስ ብለው ይቆጥሩ እንደነበር ተነግሯል። ይህን ዓይነቱን ጭካኔ ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ሲገልጹት ፤ ጅብ እንኳን ወንድሙን እስካልሞተ ድረስ ላይበላው እርም አለበት፤ የሰው ልጅ ግን ከጨካኙና ስጋ በሉ፤ አውሬ እንስሳዊነት ሲያንስ ወንድሙን ለሞት ያበቃዋል፤ ቆሞ ሳለ ይበላዋል ይሉታል። (ሐምሌት በተሰኘው የትርጉም ሥራቸው ላይ ወንድም ወንድሙን ገድሎ ዙፋን በያዘበት ትዕይንት ላይ)
ቾቪን በጆርጅ ላይ ያሳየው ጭካኔ የሰው ልጅ በሌላው የሰውልጅ ላይ፣ በሰላማዊ ቀን የፈፀመው አውሬነት ነው። ጥላቻ ጠይውን ከሰብዓዊነት አውርዶ እንስሳዊ ማንነት ያላብሰዋል። ይህንንም በዓይናችን በብሌኑ አይተናል። የትኛውም ጭካኔ በወደረኛነት አይቀርብለትም። እርስ በእርሳችን ካለፈው ደርግ መንግሥት ጀምሮ ተጨካክነናል፤ አዎ፤ ተጨካክነናል። አዎ ተራርደናል፤ እርዱ እንዲህ በቀን ቢታይ ኖሮ እንዲህ በመምሰሉ ነው፤ የተዘገነንነው እንጂ በድብቅማ ባል ሚስቱን ፣ እናት ልጇን ፣ ወንድም ወንድሙን ይገድል የለ?
ግን በጥላቻችን ምን አተረፍን፣ ምንም። ወድደንና ፈቅደን ባላመጣነው ጥቁረትና ቅላት፣ ቋንቋና የኑሮ ሥርዓት፣ ልዩነት ምን ያበጣብጠናል። ጎበዝ ! የጥላቻን ልማድ ከኮተኮትነው ግዴላችሁም በውስጡ የሰነቀው ሞትና አውዳሚነት እንጂ ርህራሄና ፍቅር አይደለም። ከቶውም ጥላቻችሁን አትኮትኩቱት፣ ውሃ አታጠጡት፣ ፍግ አትመግቡት፤ አትንከባከቡት። ጥላቻ የሚቀጣጠል ገለባ እንጂ ፣ የሚጥልልን መልካም ፍሬ የለውም። ጥላቻ ልብ የሚያፈርስ ክፉ ጦር እንጂ ፣ የሚገነባ ጋሻ የሚሸከም ትከሻ የለውም። በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች ፣ ፍጻሜያቸው አለማማሩ ብቻ ሳይሆን ጥፋታቸው ማለቂያ ለሌለው የአፀፋ ክፉ ሥራ ሁሉ መነሻ ሊሆን የሚችል ነው።
ለምንድነውጥላቻን አዝማቻችን አድርገን አንግበን የምንጓዘው ብዬ ሳስብ ምክንያታችን ሌላ አይደለም፤ በቤት ውስጥ የጥላቻ ዘር እየተዘራ ነው፤ በሥራ ስፍራ ጥላቻ አንጋሽ ወሬዎች እየሰማን ነው፤ ፖለቲካችንን በጥላቻ ቃር የተሞላ ነው፤ እዚህ ስፍራና እዚህ መሬት መኖር ያለበት የእንትን ዘር ነው እየተባባልን ነው። ጎበዝ ምድር ያላት ዘር አንድ ነው ፤ እርሱም የሰው ልጅ ዘር ነው። ቀለም ቋንቋ ነገድ፣ እምነትና አተያይ ሊከለክለው የማያስችል የሰው ዘር መኖሪያ ናት። አርመኖች መጥተው፣ ግሪኮች መጥተው፣ ጣሊያኖች መጥተው፣ ስጳኞች፣ ፖርቱጋሎች መጥተው በሀገራችን እንዳገራችን ኖረው ተዋልደውና ተራብተው ኖረዋል፤ ሲሻቸው ደግሞ ሄደዋል ፤ ትናንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፤ ሶሪያውያን በሀገራቸው የመጣው ክፉ ዕጣ አምጥቷቸዋል፤ ምግብ አልበላ ውሃው አልጠጣ መሬቱ “አላኖርም፤” አላላቸውም ። የቱንም የሰው ልጅ ዝርያ የትኛውም የምድር አፈር አላኖርምም ለቀብር አልሸከምምም ያለችበት ጊዜ የለም ። ሌላው ሁሉ ፌንጣነት ነው፤ ምድር የሁላችንም ናት፤ አበቃ!! ጥላቻ ገለባ !!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ