አንባቢዎቻችን ባለፈው ሳምንት የቅዳሜ እትማችን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በግልና በፖለቲካ ህይወታቸው እንዲሁም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ማቅረባችንን ታስታውሳላችሁ። በዛሬው እለትም ቃል በገባንላችሁ መሰረት ከአንጋፋው ፖለቲከኛ ጋር ያደረግነውን ውይይት ቀጣይ ክፍል እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የመን ላይ ሲያዙ ለመያዞት የተለያዩ መላምቶች ሲነገሩ ነበር። በተለይም የቅርብ ጓደኛዎና የትግል አጋሮ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ራሳቸው ለኢህአዴግ አሳልፈው እንደሰጥዎት ተደርጎ በየማህበራዊ ሚዲያው ሲነሳ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት አሎዎት?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ይህን ሃሳብ ማንሳቱ በራሱ ለእኔ ትርጉም የሌለው ነው። እኔ እኮ በመርህ የምመራ ሰው ነኝ። አሳልፎ ቢሰጠኝ ኖሮ በአደባባይ አብሬው አልታይም ነበር። ምክንያቱም በጣም መጥፎ ስራ ለሚሰሩ ሰዎች ንቀት ስላለኝ ነው። ምንም ባላደርገውም እንኳ በአደባባይ አብሬው ልቀመጥ ግን አንችልም። ብርሃኑ በሳምንት አንድ ጊዜ እኛ ጋር ሳይመጣ ያሳለፈበት ጊዜ የለም። አሳልፎ ከሰጠሽ ጋር በዚህ ደረጃ መልሰሽ አብረሽ የምትሆኝበት ሁኔታ የለም። እንዳልሽው ያልተባለ ነገር የለም። ሻቢያ ነው ራሱ አሳልፎ የሰጠው ተብሎ በኤርትራውያን ላይ ለማሳበብ ጥረት ተደርጎ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ለጥቅም ያደሩ ሰዎች ለወያኔ መረጃ አስተላልፈው ነው የሚል ግምት አለኝ። ምን ያልተባለ ነገር አለ?። እውነታው ግን እስከዛሬ ድረስ አልታወቀም። የእኔ ግምት ግን በጣም ቀላል ነው። ከልምዴ ግን ወያኔ በቀላሉ በየመን አየር መንገድ እንደምሄድ ለማወቅ የተሳፋሪዎች ዝርዝርም አያስፈልገውም። ዱባይ አየር መንገድ ላይ ለመሳፈር ስትሄጂ ካሉት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ አረቦች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ናቸው። ያን ጊዜ ደግሞ እኔ መታወቅ ጀምሪያለው። እዛ ውስጥ አንድ ከወያኔ ደህንነት ጋር ዝምድና ያለው ወይም ደግሞ ራሱ የደህንነት ሰራተኛ የሆነ ሰው መገኘቱ አይቀርም። ስልኩን ብቻ አንስቶ «አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን አየር መንገድ እየሄደ ነው» ማለት ብቻ ነው የሚጠበቅበት። የሆነውም ይህ ነው። ለምን መሰለሽ ይህን የምልሽ? እኛ የግንቦት ሰባት ስራ እየሰራን ባለንበት ወቅት ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለንን ግንኝነት የሚያውቁ ሰዎች የኤርትራ መንግስት ታቃዋሚዎችን መረጃ የሚጠቁም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከነፓስፖርት ቁጥራቸው «በዚህ አየር መንገድ እከሌ የሚባል የኤርትራ ተቃዋሚ እያለፈ ስለሆነ የኤርትራ መንግስት የሚፈልግ ከሆነ ንገራቸው» ተብሎ ለእኔ ስልክ የሚደወልልኝ ጊዜም አለ። ስለዚህ ልክ ለእኔ እንደሚነገረኝ ለእነሱም ስልክ ተደውሎ ተነግሯቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
በመሆኑም ወያኔዎች እኔን ለመያዝ በወቅቱ የሚያስፈልጋቸው ነገር ቢኖር ከደህንነቶች ጋር መነጋገርና በገንዘብ መደራደር ነው። ይህም እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ምንም የተወሳሰበና ልዩ የሆነ የስለላ ጥበብ መጠቀም አያስፈልጋቸውም። በጣም በቀላል መንገድ የሚፈፀም ስለሆነ ምንም አልገረመኝም። በመሰረቱ በመጀመሪያም ይህ ነገር ሊሆን እንደሚችል ትልቅ ስጋት ነበረኝ። ምርጫ የሌለው ሁኔታ ውስጥ ስለገባሁና ሰዓት እያለቀብኝ በመምጣቱ፤ የኤርትራ አየር መንገድም ቦታ ስለተያዘብኝ እንዲሁም መጽሃፌ ላይ እንዳሰፈርኩትም 400 ዶላር ክፈል ስባል በጣም ብዙ ነው ብዬ የነበረችዋን ቦታ አጣሁ፤ የቀረኝ ምርጫ በየመን አየር መንገድ መሄድ ብቻ ስለነበረ ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤርትራ መንግስት ጋር ተነጋግሪያለሁ። በወቅቱ ለአቶ የማነ ስነግረው ትንሽ አመንትቶ ነበር። ለክፉም ለደጉም ግን ብለን የኤርትራ አምባሳደር የመን አየር መንገድ እንዲጠብቀኝ አድርጓል፤ ግን እኔ አላገኘሁትም። የኢትዮጵያ ደህንነት ነው ምርመራ እያደረገልኝ የኤርትራ አምባሳደር እንደነበረ የነገረኝ።
እናም በዚያ ደረጃ ስጋት ይዤ የሄድኩት አማራጭ ስላልነበረኝ ነው። በተለይም ደግሞ በወቅቱ በጣም መታወቅ በመጀመሬ ሁሉም ሰው እንዳየኝ ሊለየኝ እንደሚችል ይታወቃል። የሚገርምሽ ራሴን ለመደበቅ ዱባይ ላይ የፀጉር ማቅለሚያ ገዝቼ ነበር። ነገር ግን ከዚህ በፊት ተጠቅሜ ባላውቅም ቀላል መስሎኝ ገዝቼ ትዕዛዙን ሳነበው ጣጠኛ እንደሆነ ስገነዘብ ጣልኩት። ስለዚህ በደንብ ከመረመርሽውእኔ የተያዝኩበት መንገድ ልዩ ጥበብ ልዩ ክህሎት የሚያስፈልገው ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በእስር እያሉ በተሰራ ዶክመንተሪ ላይ በኢትዮጵያ ስለመጣው ልማት መደነቆት ተገልፆ ነበር። በእርግጥ እርሶ በወቅቱ በአገሪቱ ልማትና እድገት መጥቷል ብለው ያምኑ ነበር?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ይህንን ጉዳይ ከየት እንዳመጡት እኔ አላውቅም። እንዳውም በጣም አስገራሚው ነገር በሚመረምሩኝ ወቅት ምንም ያለሙትና የሰሩት ነገር እንደሌለ ነው የገለፅኩላቸው። በተለይም ከ1997ዓ.ም በፊት በነበሩት 14 ዓመታት ምንም የሰሩት ነገር አልነበረም። ሁሉም እንደሚያውቀው ከዚያ በኋላ ነው ትንሽም ቢሆን ሙከራ አድርገዋል። እናም በወቅቱ አልሰራችሁም የሚለውን ክርክራችንን ምክንያት አድርገው ቆይተው «ልማት የምትለውን ነገር ከፈለክ እኛ እናሳይሃለን» አሉኝ። እኔ ደግሞ ተዘግቶብኝ ጨለማ ውስጥ ስለምኖር እንዲህ አይነት እድል ሲገኝ ጥሩነው ብዬ አሰብኩና ተስማማሁ። አንድ ቀን ሃና ማርያም የሚባል አካባቢ ያለ ኮንዶሚኒየም አሳዩኝ። ሌላ ቀን ደግሞ ሌላ ቦታ የሚገኝ ኮንዶሚኒየም አሳዩኝ። እኔ ያ ሁሉ ሲሆን አልገባኝም ነበር። ለካ እነሱ ፎቶ ግራፍ ሊያነሱበት የሚችሉበት የተመቻቸ ቦታ ነበር የሚፈልጉት።
ሌላ ቀን የአዲስ አዳማ ፈጣን መንገድ አሳዩኝ። በእርግጥ ያ መንገድ በጣም አስገራሚ ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። የአውሮፓ መንገድ ነው የሚመስለው። ጎብኝተን ስንመለስ ለማስታወሻ ፎቶ ግራፍ እንነሳ አሉኝ። የሚገርምሽ ይህን ሲሉኝም ምንም አልገባኝም ነበር። እንዳውም የምፈታበት ቀን ደረሰ እንዴ? ብዬ አስቤ ነበር። እነሱ በዚያ ደረጃ ጭንቅ ውስጥ እንዳሉ በኋላ ላይ ነው የገባኝ ። በተጨማሪም ዳያስፖራው እጁ ወልቋል፤ አይኑ ጠፍቷል የሚል ዓለምአቀፍ ጫና ፈጥሮባቸው ነበር። እንዳውም ጉብኝት ከማለታቸውም በፊት አንድ ቀን ሰዎች ጠርተን ቃለመጠይቅ አድርግና ቪዲዮ እናንሳ አሉኝ። እኔ ግን ቪዲዮ የምትቀርፁኝ ከሆነ የአሜሪካ ድምፅና የጀርመን ድምፅ ያሉ ገለልተኛ የሆኑ ጋዜጠኞች ከመጡ እንጂ እናንተ የምታመጧቸውና እንደፈለጋችሁ ቆርጣችሁ ለምትለጥፉት መረጃ ፈቃደኛ አይደለሁም አልኳቸው። ያ በዚያ ሁኔታ ቀረ።
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ልማት የለም ብለሃልና እናሳይህ ያሉኝ። እኔ ደግሞ ዓላማቸው ፎቶ ግራፍ መሆኑ አልገባኝም ነበር። አላሳዩትም እንጂ ከደህንነት ሰዎች ጋር መሃል ሆኜ የተነሳሁት ፎቶ ነበር። እነሱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን እንዲያሳይላቸው ብለው ለብቻህ እናንሳህ ብለው አነሱኝ። በወቅቱ ምንም መዘዝና ሌላ ትርጉም ያለው አልመሰለኝም ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቃሊቲ ገብቼ የእንግሊዝ አምባሳደር እኔን ለማየት ሲመጣ «በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ መንገድ ላይ ቆመህ የተነሳኸውን ፎቶ አየንህ» አለኝ። ያን ጊዜ ይህን ሲለኝ ገባኝና ያለውን ሁኔታ ነገርኩት። ያንን እስከምናገር ድርስ አብዛኛው ሰው እውነት ነው ብሎ አልተቀበለውም ነበር። እነሱ ያንን ፎቶ ያነሱበት ዋናው ምክንያታቸው ከውጭ አካላት ይቀርብባቸው የነበረውን ትችትና ወቀሳ ለመከላከልና ምንም እንዳልሆንኩኝ ለማስተባበል ነበር። ብዙዎችም «አንተን አፍኖ ማምጣቱ ትልቅ ጥፋት አጥፍቷል» ነበር ያሉኝ። ምክንያቱም እኔ በመታሰሬ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የገቡት። ከዚያ በፊት ፖለቲካ ውስጥ አልገባም ብሎ የነበረ ሰው ሳይቀር ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል። በፈንድ ደረጃ ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግንቦት ሰባት ያገኘበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ህብረተሰቡ የውጭ ምንዛሬ እንዳትልክ የሚል መልዕክት ሲተላለፍ መንግስት በውጭ ምንዛሬ እጥረት እስከሚቸገርበት የደረሰበት ሁኔታ ነበር። ከዚያ በኋላ ጉዞው ቁልቁል ነው የሆነው። አየሽ! ለዚያ ነው እነሱ በየጊዜው የሚገጥማቸው ችግር ስለነበር ነው እኔን በዚያ አይነት መንገድ ደህና መሆኔን ለማሳየት ጥረት ያደረጉት።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ እርሶ በእስር እያሉ የሰባት ዓመት ሴት ልጆት ለእንግሊዝ ንግስት የፃፈችውን ደብዳቤ ሲያዩ ምን ተሰምቶት እንደነበር ይግለፁልኝ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- በእስር በነበርኩበት ወቅት የእኔ ትልቁ ችግር የነበረው መረጃ የማይደርሰኝ መሆኑ ነው። ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት ከአባቴ በስተቀር ማንንም አላገኝም ነበር። ለዚያውም በሳምንት ለግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ ነበር። ማንም ሰው አይጎበኘኝም ነበር። ይህንን ያደረጉት ለምን መሰለሽ? ውጭ ያለው እንቅስቃሴ መረጃ እንዳላገኝ ነው። ያሰሩኝ ደግሞ ከሁለት ነፍሰገዳዮች ጋር ነበር። እነዚህ ሰዎች ቤተሰብ የሚጠይቃቸው አይደሉም። በተለይ አንደኛው ለዓመታት ቤተሰብ መጥቶ የማይጠይቀው ሰው ነበር። ሌላው ደግሞ እነዚህ ሰዎች እንዳውም ወያኔዎች በጥቅም የያዟቸው መሆኑን ሰምቻለሁ። አንዳንድ ጓደኞቼ በጠባቂዎቹ በኩል እነዚህ ሰዎች ምን ያህል አደገኛ እንደሆኑ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሞከሩ ነግረውኛል። ከእነሱ ጋር በጋራ ምንም ነገር እንዳልሰራና መልዕክት እንዳታስተላልፍ የሚል መልዕክት ሊያደርሱኝ ጥረት አድርገው ነበር። በመፃሃፌ ላይ እንዳሰፈርኩት በእርግጥ እነዚህ ሰዎች በእኔ ላይ የፈጠሩት ችግር ብዙ ነበር። ወደ ጸብ የገባንበትም ወቅት ነበር።
እንዳልኩሽ በእስር እያለሁ ምንም አይነት መረጃ አይደርሰኝም ነበር። የኢምባሲ ሰዎች በወር አንድ ጊዜ እንዲያገኙኝ ቃል ቢገቡም አንዳድ ጊዜ ሶስትና አራት ወራት እንዳያገኙኝ የሚደረግበት ሁኔታ ነበር። ከእነሱ ጋርም ቃል የተገባቡትና ጉብኝቱም እንዲቀጥል የሚፈልጉ ከሆነ ጤንነቴን ከመጠየቅ ባለፈ ስለሌሎች ጉዳዮች እንዳያነጋግሩኝ ነው። እናም አራት ዓመት ሙሉ ምንም መረጃ አልነበረኝም። ከወጣሁ በኋላ ነው በእኔ ዙሪያ የተደረጉትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ ማየት የቻልኩት። እንዳልሽው ለንግስቲቱ ደብዳቤ ስትፅፍ ልጄ በወቅቱ የሰባት አመት ልጅ ነበረች። ንግስቲቱም በመንግስት ስራ ውስጥ እንደማትገባ ግን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቱን መላኳን ገልፃ መልስ ሰጥታታለች። ለእኔ በዛ እድሜዋ ይህንን ማድረጓ በጣም ነው ያስገረመኝ።
በሌላ በኩል ግን የነበረችበት አስጨናቂ ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን ስትመለከቺ በጣም ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነው። በተለይም ከቴሌቪዥን ቃለመጠይቋ ላይ እንባዋ አይኗ ላይ እንደተንጠለለ ከወሰዱት አንድ ፎቶ ጋር «እንባሽጠብ አይበል» የሚል የተፃፈው ግጥም በጣም ልብ የሚነካ ነበር። የነበረውን ሁኔታ አሁን ላይ ሆኜም ሳየው በጣም ነው የሚረብሸኝ። እስርቤትም ሆኜ
የሚያሳስበኝ የእነሱ ጉዳይ ነበር። በጣም ህፃን ቢሆኑ የሚያስታውሱት ነገር ላይኖር ይችላል። ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ ትላልቅ ልጆች ቢሆኑ ይፅናናሉ ብዬ አስብ ነበር። እነዚህ መንታ ልጆቼ ግን የነበሩበት እድሜ የእኔን መታሰር አምነው ሊቀበሉበት የሚችሉበት አልነበረም። ምንአልባት በማህበራዊ ሚዲያው አይተሽ ከሆነ ከእኔ ጋር የተነሱትን ፎቶ ከእኔ ጋር የተለየ ቅርበት እንደነበራቸው ያስረዳል። እኔ በየቀኑ የምገኝ አባት ስላልሆንኩ እነሱ ጋር በተገኘሁ ጊዜ ሁሉ እንደልባቸው ከእነሱ ጋር አሳልፍ ነበር። በዚህ ምክንያት በእነሱ ጭንቅላት እንደዚህ አይነት አባት በምድር ላይ የለም ብለው ነው የሚያስቡት። የሚገርምሽ እኔ ስመጣ እናታቸውን እንኳ አይፈልጓትም ነበር። ስመጣ መሬት ላይ አንጥፈው በቀኜና በግራዬ ሆነው የሚተኙት። በዚያ ደረጃ የነበራቸው ቅርበት በጣም ያሳስበኝ የነበረው። ስወጣም ደግሞ ያየሁት ነገር በጣም አስገርሞኝ ነበር። በእንግሊዝ ሚዲያዎች ሁሉ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር። አንድ ጊዜ ድራማ ይሰራሉ፤ ሌላ ጊዜ ክሊፕ ይዘው ይቀርባሉ። በመጨረሻ ስፈታ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሙሉ መሬት ቁጭ ብለው ልብ የሚነካና ስለጥቁሮች ትግል የሚያወሳ መዝሙር ዘመሩልኝ። ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ ስሜት የሚቀሰቅስና የሚረብሽ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ግን ከእስር እፈታለሁ ብለው ጠብቀው ነበር? ከእስር በተፈቱበት ወቅት የነበረውን ሁኔታም አብረው ያስታውሱን?
አቶ አንዳርጋቸው፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ በእስር በነበርኩበት ጊዜ ከሰው ተገልዬ ስለነበር ምንም አይነት መረጃ አልነበረኝም ነበር። እኔ የታሰርኩበት ቦታ ከሴቶች እስር ቤት ጋር ይወሰን ስለነበር አልፎ አልፎ የሚመጣ የቴሌቪዥን ድምፅ በስተቀር ምንም የምሰማው አልነበረም። እኔ የተሳርኩበት ክፍል ከሌላው በተለየ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን የለም። ለምን እንደዚያ ያደርጉ እንደነበር ግን አውቃለሁ። ምክንያቱም እንኳን መረጃ አግኝቼ መረጃም ሳላገኝ እንደልቤ ነው የምናገራቸው። ስለዚህ «መረጃ ካገኘ የበለጠ እብሪት ይሰማዋል» ብለው እንደሆነ እረዳለሁ። እናም ለውጡ በመጣበት ወቅት ሴቶቹ እስረኞች እኔ እዛ መታሰሬን ስላወቁ የቴሌቪዥኑን ድምፅ ከፍ ማድረግ ጀመሩ። አንድ ቀን በተለይ ለማና ዶክተር አብይ የተናገሩት ንግግር በጣም ነበር ያስገረመኝ። በተለይም የለማ «መሞትም ሆነ መኖር ካለብን መለወጥ አለብን» የሚለው ንግግር በጣም ትኩረቴን የሳበው። ደግሞም የኢሃፓንም ነገር አስታውሶ ሲያነሳ ሰማሁት። ይህ ነገር እንዴት ነው? ምንድንው እየተካሄ ያለው? ስል ራሴን ጠየኩኝ።
በእርግጥ የተወሰነ እንቅስቃሴ እንደነበር ተረድቼ የነበረ ቢሆንም ይህንን ያህል መንግስትን የሚያንገዳግድ ለውጥ ይመጣል ብዬ ፈፅሞ አልጠበኩም ነበር። ከዚያ ማታ ማታ ሴቶቹ ቴሌቪዥናቸውን ከፍ አድርገው እንድሰማ ያደርጉ ጀመር። እከሌ ተፈታ የሚል ነገር በየቀኑ መስማት ጀመርኩ። ከእስር የሚፈታው ዜና በተሰማ ቁጥር በሴቶቹ ክፍል የሚሰማው ጭብጨባ አስገራሚ ነበር። ኮነሬል ደመቀ ተፈታ ሲባል የሰማሁት ጭብጨባ ዛሬ ድረስ ያስገርመኛል። ማነው ይሄ ኮነሬል ደመቀ? ብዬ ተደነቅኩኝ። በኋላም አብዛኛውን ሰው ፈተው ጨረሱና እኔ ብቻ ቀረሁ። ሶስት ወራት አለፉ። አባቴን ሳገኘው ምንም ነገር የለም። ከዚያም ዶክተር አብይ ስልጣን ያዘና ንግግር ሲያደርግ በሴቶቹ ቴሌቪዥን ሰማሁት። እንደዚህ አይነት ነገር የሚናገር ሰው በዚህ ዘመን መገኘቱ በጣም አስደነቀኝ። አገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው? ብዬም ራሴን ጠየኩኝ። በተለይ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር የሚለው መልዕክት በጣም አስደነቀኝ።
ከዚያ በኋላ እንደሚመስለኝ በዶክተር አብይ ግፊት ቴሌቪዥን ተፈቀደልኝ። በእርግጥ ሳተላይት የለውም። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መዝናኛና የኦሮምኛና የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃንን ማየት እችል ነበር። ያም ቢሆን ግን ለእኛ በቂ ነበር። እስከምፈታ ድረስ በነበሩት ስድስት ሳምንታት ቴሌቪዥን በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ለማየት ችያለሁ። በዚህ ሁኔታ ሳለን አንደኛው ከእኔ ጋር ታስሮ የነበረው ግለሰብ እንደማበድ ሲል ሌላ ቦታ ወሰዱት። አንደኛው ደግሞ ቴሌቪዥኑን ከጠዋት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አያጠፋውም። የድምፁ ጩኸት በራሱ ሊገለኝ ሆነና በዚህ የተነሳ ተጣላን። ከዚያ ሌላ ቦታ ወሰዱትና ብቻዬን ማየት ጀመረኩ። አንድ ቅዳሜ የአባቴን መምጣት እየተጠባበኩና ሳህኔን በጨርቅ እየወለወልኩ ሳለሁ ቴሌቪዥን የሚዲያ ዳሰሳ ላይ የእኔ ስም ሲነሳ ሰማሁ። እኔ እንድፈታ በተለያዩ አገራት የነበረውን ግፊትና እንቅስቃሴ በሚመለከትና ለዚህ እንቅስቃሴ መንግስት ምላሽ መስጠቱን ሰማሁ። እኔና ሌሎች 500 የሚሆኑ ሰዎች እንዲፈቱ ተወስኗል የሚለውን ዜና ስሰማ ምንም አላልኩም። ብቻ እ?… ነው ያልኩት። ከዚያ አባቴ ወዲያውኑ ሲመጣ የሰማ አልመሰለኝምና ልነገርው ስል ለካ እሱ ቀድሞኝ ሰምቶ ኖሮ ከወትሮ በተለየ ያለመደገፊያ ተነስቶ ዘሎ አቀፈኝ። ይሁንና እለቱ ቅዳሜ ስለነበር ልፈታ አልቻልኩም። ሰኞም ግንቦት 20 ስለነበር ማክሰኞ ከሰዓት ተፈታሁ።
ከዚያ እንደወጣሁ የት እንደምሄድም አላውቅም ነበር። ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ ወስደው ይጥሉኛል የሚል ግምት ነበረኝ። ወደ አባቴ ቤት እንደሚወስዱኝ ያወኩት ቦሌ መንገድ ላይ ደርሰው አንደኛው ስልክ ደውሎ አቅጣጫ ሲጠይቅ ስሰማ ነው። በወቅቱ ደግሞ አባቴ ጠብቆ ጠብቆ ሲሰለቸው በጭንቀት አንድ ነገር ይሆንብኛል ብዬ ሰግቼ ነበር። ስመጣ እንዳውም ለቀናት ሲደግሱና ሲዘጋጁ ነበር የቆዩኝ። ከቦሌ መገንጠያ ጀምሮ ሰው ሁሉ ማለፍ የማይችልበት ሁኔታ ነው የጠበቀኝ። ወደ ቤታችን በታቀረብን ቁጥር ያን ሁሉ ሰው ሳይ በእነዚህ ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ እንዴት ቢበዛ ነው እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር። ደግሞም በአንቡላንስ ስላመጡኝ ከውጭ ወደ ውስጥ አያሳይም ነበር። በጣም እየተቃረብን ስንመጣ ጭራሽ ማለፊያ አጣን። አንድ ሰው ተጠግቶ «እዚህ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም» ብሎ ሲናገር ሰማሁት። ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች እኔን ነው እንዴ የሚጠብቁት? አልኩ። ከመኪናው ያ ህዝብ ተሸክሞ ነው ያወረደኝ። ዝናብ እየዘነበ አቅፈው አባቴ ቤት አስገቡኝ።
እንዳልሽው ግን እነ አንዷለም፣ እነእስክንድርና እነ ዶክተር መረራ ከተፈቱ በኋላ እድል ሊኖር ይችላል የሚል እምነት ነበረኝ። ከዚያ በፊት ግን ወያኔ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ በምንም መንገድ እፈታለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር። እንዳውም ልጆቼ አድገው፤ በሽታ ገሎኝ ነው የምወጣው የሚል ግምት ነበረኝ። ለነገሩ የተፈታሁበትን ምክንያት ሌላ ቦታም ዶክተር አብይ የገዛ ስልጣኑን መስዋዕት እስኪሆን ድረስ ኃላፊነት ወስዶ ነው ያስፈታኝ ብዬ ተናግሪያለሁ። ይህንም ራሱ ነው የነገረኝ። በወቅቱ ሁሉም ሰው ከተፈታ በኋላ ወያኔዎች አንዳርጋቸው አይፈታም ብለው ነበር። አብይ ግን «እሱ ከተፈታ ስራዬን እቀጥላለሁ፤ ካልተፈታ በጋዛ ፍቃዴ ስልጣኔን እለቃለሁ›› ነው ያላቸው። ይህንን ነው ለበቢሲ ጋዜጠኛ የነገርኳት። እናም አብይ ያደረገው ነገር ቀላል አይደለም። ሌላው ቀርቶ ቴሌቪዥን ከገባልን በኋላ ንግግር ባደረገ ቁጥር ለእኔ መልዕክት የሚመስል ነገር ያስተላልፍ ነበር። ንግግሩን ስሰማ ሆን ብሎ ያደርገዋል ብዬ ስላልጠበኩ ግራ እጋባ ነበር። ይከነክነኝም ነበር። መልዕክቱ ለእኔ እንደነበር ያወኩት ግን ከተፈታሁ በኋላ ነው። ሲነግረኝ በጣም ነው የገረመኝ። የአንድ አገር መሪ ስራዬ ብሎ በዚህ መንገድ መልዕክት እንዲደርሰኝ እና ብቻዬን ታስሬ በተቀመጥኩበት ክፍል ሊሰማኝ ይችላል ብሎ ይህን ማድረጉ እስካሁን የሚገርመኝ ነው። ምን ያህል እንደጨነቀውም የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በኋላ ያሉት ሁለት ዓመታት በእርሶ እይታ ምን ይመስላሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- በዚህ ጉዳይ ላይ መናገር የምፈልገው ነገር በዋነኝነት ብዙ ሰው የማይገባው አለ። ለውጡ የፈለገ ችግር ይዞ ቢመጣም እንኳን መስመማት ያለብን ነገር አለ። እኔ እስር ቤት ከመግባቴ በፊት እዚህች አገር ላይ ያየሁት አደጋ ነበር። ያ አደጋ ቀደም ብለን በማንኛውም የትግል ስልት አመፅንም ጨምረን ወያኔ መወገድ አለበት ብለን ስንነሳ የአረብ አብዮት አልተካሄደም ነበር። በዴሞክራሲ ስም የተነሱ እንቅስቃሴዎች ከአመፅ ጋር ተቀላቅለው ሶሪያን፥ ሊቢያን፥ የመንን፥ ቱኒዚያንና ግብፅን እንዳመሷቸው ወደ እኛ ከመጣ ተመሳሳይ እጣ ይደርስብናል የሚል ስጋት ነበረኝ። እነዚህ አገሮች አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ፥ አንድ አይነት ሃይማኖት ያላቸው በዴሞክራሲ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ እንደማይሆኑ አድርጎ በዚህ ደረጃ ብትንትናቸውን ካወጣ እኛ በዴሞክራሲ ስም የምንጀምረው ያውም በደንብ የታሰበበት የአመፅ እንቅስቃሴ ምን ሊያመጣብን እንደሚችል ግልፅ ነው።
ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ አገር ናት። የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩበት፤ የተለያዩ እምነት ተከታዮች ያሉበት አገር ናት። ከዚህም ባሻገር ከታሪክ ጋር ተያይዞ የራሱን ቁስል የሚቆሰቁስ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች ባሉበት አገር ላይ የምንጀምረው የጠበንጃ ትግል አንድ ወረዳ ላይ እንኳን ቢይዝ ወያኔን ከሃርጌሳ አንስቶ እስከ አፋርና እስከጋንቤላ ድረስ አልገዛም የሚል ህዝብ ይፈጥራል። በየቦታውም በጎበዝ አለቆች የሚተራመስ መንግስት መቆጠጣር የማይችለውና አገር የሚያፈርስ ነገር እናመጣለን የሚል ጥናት በፅሁፍ ደረጃ አስቀምጬ ነበር። እናም የአመፅ ትግላችን በተጨባጭ መታሰብ አለበት፤ አገር እናድናለን ብለን አገር ልናፈርስ የምንችልበት ሁኔታ የአረብ የፀደይ አብዮት አሳይቶናል የሚል ስጋት ውስጥ ነበርኩ።
ስለዚህ አገር ውስጥ ያለው ወጣት በሁሉም ቦታዎች ባደረገው ትግል ከውጭ ካለው ህዝብረተሰብ ጋር ተዳምሮ ኢህአዴግን አስገድዶ በውስጡ ለውጥ እንዲያደርግ አድርጎታል። ከአመፅ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ሊያስቆም በሚችል ደረጃ ሁላችንም ማምጣት መቻሉ አንድ ትልቅ በምንም ነገር ልታንኳስሺው የማትችዪው ነገር ነው። በዚህ መልክ ለውጥ መምጣቱ አገሪቱን እንደ ሊቢያና ሶሪያ ከመሆን አድኗታል። እናም የአገሪቱ የፖለቲካ ሰዎች በዚህ ደረጃ መረዳት አለባቸው። ይህንን የአገር ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የነበረውን አደጋ በአግባቡ ተገንዝበን እና ችግሩን ፈትተን የበለጠ ጠንካራ መሰረት ላይ ማስቀመጥ አለብን። ኢህአዴግ ፓርቲ ራሱ ያቀረበው ግምገማ አገርን ከሚያስተሳስረው ከአንድነታችን የበለጠ ልዩነታችን ላይ በማተኮር አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ልዩነት ላይ ተሰርቷል። ስለዚህ ሚዛኑን ለዓመታት ረስተነው ወደ ነበረው አንድነት መሳብ ይገባናል።
በተግባር መለወጥ ካለባቸው ነገሮች መካከል በዋነኝነት የሰራዊት አደረጃጀቱ ነው። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ክልሎች የራሳቸውን ጦር ሰራዊት ወይም ልዩ ሃይል ገንብተዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ የራሳቸው የደህንነት ተቋም በመገንባት አንዱ ክልል ሌላውን እየሰለለ፥ አንዱ ከአንዱ ጋር ለመዋጋት እየተዘጋጀ ያለበት ሁኔታ እናያለን። ይህ ደግሞ በሱማሊና በኦሮምያ ክልል ታይቷል። በሁለቱ ክልሎች ልዩ ሃይሎች በተደረገ ግጭት አንድ ሚሊዮን ኦሮሞ ከሱማሌ ክልል ሲፈናቀለ አይተናል። እውነት ለመናገር ትግራይ ክልል ያከማቸው ልዩ ሃይል የትግራይን ህዝብ ሰላም ለማስከበር እንዳልሆነ ይታወቃል። በዚያ ክልል ከልዩ ሃይሉ ባሻገር ለላፉት 27 ዓመታት ያከማቹት የጦር መሳሪያ አለ። እስከ ሚሳኤል ድረስ መታጠቃቸው ይታወቃል።
በዚያ ደረጃ የአገር ህልውና የሚያናጋ የሰራዊት አደረጃጀትና ልዩ ሃይል ይዘሽ በምን አይነት መንገድ
ነው የአገር አንድንትን የሚፈታተነውን ነገር በተግባር ልታስወግጂው የምትቺይው? ይህ በጣም አሳሳቢና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህንን አይነት ሃይል ወደአገራዊ መስመር መልሰሽ አሁን ያለውን ፍጥጫ የምታስቆሚበት መንገድ ካላመጣሽ በስተቀር በአንድ ክስተት ሁለት ክልሎች እርስበርስ ወደሚዋጉበት ሁኔታ ሊፈጠርና አገር ሊበታተን ይችላል። በደህንነትም በኩል አገራዊ የደህንነት አካል የሚያዘው የክልል የደህንነት አካል ሊኖር ይገባል። እንኳን ልዩ ሃይል ጨምረሽበት ፖሊስ እንኳ በዘር በተደራጀት ሁኔታ የሌላን አካበቢ ህዝብ ለማፈናቀልና ለመዝረፍ በቀላሉ ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ አመፅ ሊቀሰቅስ የሚችል የደህነነት ተቋም ሊፈጠር ይችላል፤ አዛዡና በጀት መዳቢው የፌዴራል መንግስት ካልሆነ ቅድም ያልነው የአንድነት ጉዳይ ከቃላት አልፎ በተግባር ሊታይ አይችልም።
ሌላው አንገብጋቢው ጉዳይ ሚዲያው ነው። በፌዴራል ደረጃ ያለ ሚዲያ ብዙ ሚዛኑን የጠበቁ መረጃዎች ሊሰራ ይችላል። ይሁንና የክልል ሚዲያዎች የተመሰረቱት በክልል መንግስታት ነው። ለአንድ ክልል ህዝብና ፓርቲ የቆሙት ሚዲያዎች አሁን ባለው ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካን ወደ ዘር የመመንዘር ሂደት የሩዋንዳን አይነት እልቂት ማስከተላቸው አይቀርም። አንድ የሬዲዮ ጣቢያ አንድ የዘር ጉዳይ አንስቶ እልቂት ሊያስከትል የሚችልበት እድል አለ። ይህንን የምልሽ የክልል ሚዲያ መኖር የለበትም ብዬ አይደለም። እንዳውም እስካሁን እድሉን ባላገኙ ቋንቋዎችም ሚዲያ መከፈት አለበት ባይ ነኝ። ይሁንና ልክ ሌሎች አገራት እንዳለው ሁሉ ማዕከላዊ መንግስት የሚቆጣጠረው ወይም የሚከታተለው መሆን አለበት። ማዕከላዊ መንግስት ኤዲቶሪያል ፖሊሲውን ያፀደቀለት፤ በጀት የሚሰጠው፤ እንዳውም በነፃነት ክልሎችን ሌባና ዘራፊን እንዲሁም አፋኝን መተቸት የሚችልበትና ጋዜጠኛውም ይህንን በመስራቱ ከስራ የማያባርረው መሆን አለበት። በዚህ መልኩ ነፃነት ያለበት ካላደረግነው እውነተኛ ሚዲያ ማድረግ አንችልም። አሁን ላይ በየክልሉ የተፈጠሩት የዘር ሚዲያዎች የሚሰሩትን ስራ ስናይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ዘረኛ በሆነ መንገድ አገርን ለማጥፋት እንደማይመለሱ ማየት ችለናል። እንደዚህ አይነት ተቋሞች ናቸው ልዩነት በማስፋት ላይ ተመስርተው እንዲገነቡ የተደረጉት። እነዚህን ችግሮች መልክ ሳይዙ አገር አንድ ሆኖ የመቀጠል እድሉ ጠባብ ነው። በዚህ መንገድ የተወሰደ ምንም አይነት እርምጃ የለም። ምንአልባትም እነዚህን ነገሮች ለመነካካት መንግስት ጉልበትና አቅም ላይኖረው ይችላል። ጊዜ ያስፈልጋል ተብሎ የተወወ ነገር ሊሆን ይችላል። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ሲነጋገሩ አለማየቴ ያሳስበኛል።
ሌላው ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ሊያስቀጥላት የሚችለው ዝም ብሎ የአገር አንድነት ብቻ አይደለም። ዴሞክራሲ መኖር አለበት። ህዝብ በራሱ መንገድ በነፃነት በመረጣቸው ወኪሎቹ የሚተዳደርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በፈለገ ሰዓት የሚሾማቸውና የሚያወርዳቸው ነፃነት እስካልተሰጠው ድረስ በፕሮፖጋንዳና በተቋም ብቻ አገርን አንድ አድርገሽ ማስቀጠል አትችይም። ስለዚህ በዴሞክራሲ በኩልም የምናያቸው ፈተናዎች አንዱ ይሄ የክልል አደረጃጀት ይዞ የመጣው ነገር ነው። ዴሞክራሲ በአንድ አገር ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ከፈለግሽ የፌዴራል ተቋማት ነፃ ገለልተኛ ሆነው መቆም አለባቸው። መከለከያው በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር እስከሆነ ድረስ ይሄ ፓርቲ ሲሸነፍ መከላከያውን በማዘዝ ተቃዋሚውን ሁሉ እስር ቤት ሊጨምር ይችላል።
ደህንነቱም ሆነ ፖሊሱ በአንድ ፓርቲ የሚታዘዝና ከዚያ ፓርቲ ጋር ህልውናው የተቆራኘ እስከሆነ ድረስ ያ ፓርቲ ከስልጣን እንዳይወርድ አድርግ የተባለውንም ሁሉ ያደርጋል። በዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ በፌዴራል ደረጃ ነፃ ተቋማት ገንብተናል ወይ? የሚለው ነገር አሁንም አልተመለሰም። በተለያየ ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮም ሆነ ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሞከርን ነው ይላሉ። ግን ሙከራው አጥጋቢ ነው የሚል እምነት የለኝም። በአንድ ጀንበር ነፃ ተቋማት ይገነባሉ ተብሎ ስለማይተመን የሂደት ነገር ነው ብለን እንተወው። ምክንያቱም ፈተናው ቀላል አይደለም። ሰራዊት ማስተማር አይደለም ሰራዊቱን የሚያስተምር አስተማሪ መኖሩ ራሱ አጠራጣሪ ነው። ግን ትልቁ ችግራችን እሱ አይደለም። በፌዴራል ደረጃ ያለው ወታደርና ፖሊስ በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ከሚፈጥረው እንቅፋት የበለጠ በክልል ደረጃ ያሉት ናቸው የሚበልጡት። ምክንያቱም የፌዴራሉ ሰራዊት በራሱ የሚያዝበት ወረዳ የለውም። እነዚህ ተቋማት አይን ባወጣ ወገንተኝነት ተይዘዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት እዛ ቦታ ላይ የክልሉን ሚዲያ መጠቀም ይችላሉ?፤ የክልሉ ሚሊሻ ሳያዋክባቸው ህዝብ ማግኘት ይችላሉ?፤ የክልሉ ልዩ ሃይል ሳያዋክባቸው ስብሰባ ማካሄድ ይችላሉ?፤ እንደዚህ አይነት ነገሮች ታልፈው እንኳ ቢሆን የክልሉ ፓርቲ ቢሸነፍ ወገንተኛ የሆነ ተቋም ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም።
ስለዚህ በአገር ህልውና በዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ ገና ብዙ ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ። አሁን ላይ የኮረና መምጣት ምርጫውን አራዘመው ይባላል፤ እኔ እውነቱን ልንገርሽና የኮረና ቫይረስ መጥቶ ምርጫው መራዘሙ ለኢትዮጵያ ከሰማይ የተላከላት ስጦታ ነው ብዬ ነው የማስበው። በተባለው ጊዜ ቅድም ያልኳቸው ችግሮች እያሉ ምርጫ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያን አጠቃላይ ህልውናዋን የሚያናጋ ችግር ይፈጠር ነበር። ሁከትና ብጥብጥ ይፈጠር ነበር። እኔ እንዳውም በኮረና ምክንያት ምርጫ ተራዘመ ሲባል እውነትም ይህንን ህዝብ እግዚአብሄር ይወደዋል ወደሚል ድምዳሜ ነው የደረስኩት። አሁንም ቢሆን ኮረና ቫይረስ አብቅቶለታል በሚል መሬት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ምህዳር የሚያጠብ የክልል መንግስታት አደረጃጀት ከእሱ ጋር የተያያዙ ተቋማት ሳይስተካከሉ ትክክለኛ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት የለኝም። ይህንን ነገር በቁም ነገር የሚያነሳ የተቃዋሚም ሆነ የመንግስት አካል አላየሁም።
አዲስ ዘመን፡- የምርጫው መራዘም «ህግመንግስት ይጥሳል» የሚል ክርክር ለሚያነሱ ወገኖች የሚሰጡት አስተያየት አልዎት?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ዴሞክራሲ በአንድ አገር ላይ እንዲኖር ዓለም የተቀበለው ስምምነት አለ። ዋነኛውና ነገር ዴሞክራሲያዊ ተቋም ለመገንባት ከየትኛውም ፓርቲ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ መንግስታዊ ተቋማት መኖር አለባቸው። ሰራዊት፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ተቋማትና ሚዲያው ናቸው። በዚህ አገር ውስጥ አንዳቸውም የሉም። ስለዚህ እኔ አሁን አንዲት ብጣሽ ወረቀት ላይ ማንም ተነስቶ የፃፈውን አንቀፅ ከዚህ ወሳኝ ከሆነ ጉዳይ ጋር አላወዳድረውም። በተለይ ደግሞ እነዚህ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ደረጃ ምርጫ ማድረግ አገር የሚያፈርስ ከሆነ ህገመንግስቱን ቀዳዶ ጥሎ አገር እንዳይፈርስ ማድረግ የአንድ መንግስትና ለህዝብና ለአገር አስባለው ከሚል የተቋዋሚ ድርጅቶች ሃላፊነት ነው። ይህንን የተጋነነ የህገመንግስት አስፈላጊነት ለራሳቸው ካልሆነ በስተቀር ለእኛ የሚሰራው ነገር የለም። በእርግጥ ሌላ ማጣቀሻ ሰነድ እስከሌለን ድረስ ህገመንግስቱን እየተጠቀምን እንሂድ በሚለው ነገር እስማማለሁ። ነገር ግን ህገመንግስት አገር አፍራሽ በሆነበት ሰዓት ላይ በምንም አይነት መንገድ ህገመንግስት የሚከበርበት ምክንያት አይታየኝም። ህገመንግስቱ እኮ ወረቀት ነው፤ መነሻ ሰነድ የሚሆነን እኮ አገር ሲኖረን ነው። አሁን ያልነውን ጠቀሜታ የሚኖረው ህዝብ ሲተርፍ ነው። ህዝብና አገር ካለ በኋላ ህገመንግስቱ ምንድንነው የሚሰራልን? ። ስለዚህ ህገመንግስት የሚባለውን ነገር ከሚገባው በላይ አካብደን አገር ከምናፈርስ ህገመንግስቱን መቅደድ ነው ያለብን። ደግሞም እኮ የተፃፈበት መንገድ በራሱ አግባብነት የሌለው መሆኑን ሁሉ እያወቅን ለጊዜው እንተወው በሚል ነው። 85 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ገበሬ እንዳልወከለ በቃለጉባኤያቸው ፅፈውታል። በተጨማሪ ሁሉም ብሄሮች ሲወከል በዚያን ጊዜ ብአዴን ስላልነበር የአማራ ህዝብ አልተወከለበትም። የሰራተኛ ማህበርና የመምህራን ማህበር ተወክለውበት የህግ ባለሙያዎች ማህበር እንዲወጣ በተደረገበትና በዚህ ደረጃ ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ ጠፍጥፎ የተቀረፀውን ህገመንግስት እንደ ትልቅ ነገር አደርጎ ዘወትር ማቅረብ ዋጋ የለውም። ህዝቡ አይወክለኝም የማለት የሞራል የበላይነት አለው። ስለዚህ አሁን ላይ መደራደሪያና መነሻ ስሌለን እንጂ እነሱ እንደሚሉት አምነንበትና ተቀብለነው ልዩ ቦታ ሰጥተነው አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ከህዝብ እየተነሱ ያሉት ተቃውሞች ወደየት ያመራል ብለው ያምናሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- መጀመሪያ መሰረታዊውን ትምህርት ከዚህ እንውሰድ። ከ20ዓመት በፊት ከትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት ስናደርግ በህወሓት እየተመራ ያለው መንግስት መጨረሻ ላይ ከማንም በላይ የትግራይን ህዝብ ነው አደጋ ውስጥ የሚጨምረው የሚል ሃሳብ አቅርበን ነበር። ስለዚህ እናንተ የትግራይ ተወላጆች ይህንን ነገር ለማስቆም ከእኛ ጋር መቆም አለባችሁ፤ ስል አንዱ ተሰብሳቢ በጣም በዘር ፖለቲካ ከመስከሩ የተነሳ በእኛ ፋሽስቶች የሚያገባህ ነገር የለም ብሎ ነው የተናገረው። የእኔ ክርክር ዛሬም ትምህርት ሊሆን የሚገባው አንድ ሰው አማራ፣ አንድ ሰው ኦሮሞ፤ አንድ ሰው ትግሬ፤ አንድ ሰው ከንባታ ወይም ሃድያ በመሆኑ አይደለም ያ አካባቢ የሚያልፍለት። ህዝቡም የሚበለፅገው በአካበቢው ህዝብ ስለተመራ ሳይሆን በመልካም የአመራር ጥበብ ነው። የትግራይ አመራሮች ለህዝቡ አስበው ቢሆን ኖሮ የመጨረሻው የነፃነት ተቋዳሽ የትግራይ ህዝብ ባልሆነ ነበር። በዘር ላይ የተመሰረተ ማናቸውም አይነት የፖለቲካ እምነት ምን ያህል ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል በትግራይ ክልል የሆነው ነገር አስተምሮናል።
ዛሬ በአገራችን የተስፋፋው በየአካባቢው ነፃ አውጪ ሆኖ የከረመ በሙሉ ነገ ጠዋት እድል ቢሰጠው ወያኔዎች የፈጸሙትን በሌላው ክልል የማይፈፅሙበት ምክንያት የለም። ዴሞክራሲያዊ ከሆንሽ ለአማራ ህዝብ የምታስቢውን ነፃነት ለኦሮሞ ህዝብ አትነፍጊውም። ዴሞክራሲ የሚሸራረፍ ነገር አይደለም። ሰብአዊ ከሆንሽ የትግሬ ለማኝ እንደሚያሳዝንሽ የአማራም፤ የኦሮሞ ለማኝም ሊያሳዝነሽ ይገባል። ሰው መታፈን የለበትም፤ እንደልቡ መናገር አለበት፤ የሚል እምነት ካለሽ ይህ እምነት ለኦሮሞ ተሰጥቶ ለአማራ ይከልከል አትይም። የዴሞክራሲና የነፃነት ችርቻሮ የለውም። ትግራይ ውስጥ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚያስተምረን በዚህ መንገድ ሲያዩ የነበሩ ቀድሞ ራሳቸው ወያኔዎች ትግርኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸው ለትግራይ የተለየ ነገር ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ ምን ያህል ስህተት እንደሆነ ነው። አሁንም በዘራቸው ምክንያት የተለየ ቦታ ይሰጠናል የሚል ቅዠት ውስጥ ያለ ካለ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ትልቁ ቁምነገር ዘርሽ ላይ አይደለም ያለው። ቆሜልሃለው የሚሉት ሰዎች ምን አይነት እሴት ያለው ናቸው? የሚለው ነው።
እነዚያ ሰዎች አድማሳዊ የሆነ ስብዕና ነው ሊኖራቸው የሚገባው እንጂ የአንድ ክልል ወይም አገር ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚመለከታቸው። በዚያ ደረጃ ያደገ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የትግራይ ክልል ያስፈልገዋል። በእኔ እምነት ገዚዎች ሁልጊዜ ጉራና ድንፋታቸው ቢኖርም የትግራይ ህዝብ ከተነሳ የማዕከላዊ መንግስትና የሌላው ህዝብ ድጋፍ አያሻውም። የትግራይ ህዝብ ወያኔዎችን ከዚህ በኋላ አታስፈልጉኝም ካላቸው የማዕከላዊ መንግስት ሳይገባበት ሊያነሳቸው ይችላል። ማንም ጣቱን ሳያስገባ ማዕከላዊ መንግስት የሚፈልጋቸውን ሌቦችና ወንጀለኞች አንቆ ለማዕከላዊ መንግስት እስከማስረከብ ድረስ ሊደርስ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ግን አሁን ያለው ሁኔታ ወደዚያ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ይታመናል?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ሊኖር ይችላል። ትግራይ ውስጥ ብትደምሪያቸው መቶ የማይሞሉ በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች እኮ ናቸው አሁን ያሉት። ወያኔዎች ሲዘርፉ ሲያፍኑ የነበረው የራሳቸውን ስልጣን ለማራዘም እንጂ ለህዝቡ ጥቅም ሲሉ አይደለም። አሁን ላይ እኮ እየተነሳ ያለው ስልጣን ሁሉ ወደ አድዋ ሄዷል በሚል ነው። አድዋ ውስጥ ያለ ተራ ገበሬ ፥ አስተማሪና ነጋዴ የተለየ ጥቅም ያገኘበት ሁኔታ ባለመኖሩ በመላው ትግራይ ያለው ህዝብ ነው የሚነሳው። ምስራቅና ደቡብ የሚባል ነገር አይኖርም። የማዕከላዊ መንግስት ምንም አይነት ጥረት ሳያስፈልግ ህዝቡ ራሱ ያስወግዳቸዋል። እንደለመዱት እዚህ ከተማ በስናይፐር ሰው እንደሚደበድቡት የትግራይን ህዝብ ሊደበድቡት አይችሉም። አንድ ሰው በመሞቱ ብቻ እንኳ ምን ያህል ምሬት ውስጥ የትግራይን ህዝብ እንደጨመረው አይተናል። በዚህ ረገድ የማዕከላዊ መንግስት የትግራይን ክልል በሚመለከት እስካሁን የሄደበት ስትራቴጂ ትክክል ነው። ምክንያቱም እስከ እግር ጥፍራቸው በታጠቁበት፤ ህዝቡም እነሱን ለማስወገድ ዝግጁ ባልነበረበት ሁኔታና ተከበሃል፤ ልትጨረስ ነው፤ በሚሉበት ሰዓት ላይ ህግና ሥርዓትን አስከብራለሁ ብሎ ራሱ ደግሞ የተጠናከረ አቅም ባልገነባበት ሰዓት ይህንን አካሄድ መከተሉ ትክክልነው ባይ ነኝ። ደግሞም ትተውለት የሄዱት በዘር ብትንትኑ የወጣ ሰራዊት ነው። ያንን ሰራዊት ይዞ የትኛውም አካባቢ ህግ አስከብራለሁ ብሎ በቀላሉ የማይኬድበት ሁኔታ እንደወረሰም ስለምረዳ ነው ይህንን ነገር ልቀበለው የምችለው።
ነገር ግን አሁን እየተጠናከረ እየመጣ ነው፤ ያንን ማስፈፀም በሚገባው ሰዓት ላይ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ የሚጎዳበትና የሚያልቅበት ሁኔታ ቢፈጠር ማዕከላዊ መንግስት ምርጫ የለውም። የዚያን ጊዜ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ከማዕካለዊ መንግስት ጀርባ ነው የሚሆነው። ፖለቲካዊ ሁኔታ ባልበሰለበት ሰዓት ላይ ህግና ሥርዓት ለማስከበር የሚወሰዱ እርምጃዎች ኪሰራ ነው የሚያስከትሉት። ህዝብ የደገፈው ነገር እስከሆነ ድረስ ውጊያውን ብቻ ሳይሆን ሰላምንም ነው የምታሸንፊው። የግጭቶች ሁሉ ትልቁ ችግር ሰላምን ማትረፍ አለመቻላቸው ነው። አሜሪካኖች የተለያዩ አገራት ጦራቸውን አዝምተው ጦርነት ያሸንፋሉ፤ ይሁንና ሰላምን ሲያሸንፉ አላየናቸውም። ያንን ማድረግ የሚቻለው የህዝብ ድጋፍ ሲኖር ነው። ማዕከላዊ መንግስት ሰላሙን ማሸነፍ የሚችልበት አቅምና የህዝብ ድጋፍ በሌለበት ሰዓት ላይ ጦርነት ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ለማንም የማይበጅ ባዶ ድል ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ሰፊ ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አንዳርጋቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
ማህሌት አብዱ