‹‹Genetically-Modified seed was never intended to support human life, but to eliminate it.›› ግሎባል ሪሰርች ነው ይህን ያለው። ግርድፍ ትርጉሙ የዘረመል ቀይስ አካል የሰው ልጅን ህይወት ለመደገፍ ሳይሆን ለማጠፋት የተፈጠረ ነው እንደማለት ነው።
የዘረ-መል ልውጥ አካል (GMOs) በሀገራችን ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል። በተለይ የአሜሪካ የግብርና ተቋም ኢትዮጵያ የዘረ-መል ልውጥ አካልን መቀበሏን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረትን ሰቧል። ምሁራንም በሁለት ጎራ ተከፍለው ክርክሩን ተያይዘውታል።
ስለ ዘረ-መል ልውጥ አካል (GMOs) ከማውራታችን በፊት ምርታማነትን ለማሳደግ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ሂደቶችን እንመልከት።
የዝርያ መረጣ
ይህ ሂደት ለአካባቢው፣ ለዓየር ንብረቱና ለአፈሩ የሚስማማ የዘር ዓይነትን የመምረጥ ሂደት ነው። ከመደበኛው ዘር ውስጥ ድርቅ፣ ውርጭ ወይም ሌላ የአካባቢ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችሉትን እየመረጡ የተሻለ ምርት ሊሰጡ የሚችሉበት ቦታ ማልማትን የሚመለከት ነው። ለምሳሌ ከተለያየ የበቆሎ ዝርያ ውስጥ የተሻለውን መርጦ እያላመዱ መዝራት ማለት ነው። በተመሳሳይ በእንስሳትም ላይ ይተገበራል። ተፈጥሯዊ በመሆኑ አካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አያስከትልም።
ማዳቀል
ሁለት ተመሳሳይ የሆኑ ነገር ግን የተለያየ ምርት የሚሰጡ እፅዋትን ወይም እንስሳትን ማዳቀልን የሚመለከት ነው። ለምሳሌ የስጋ ጣዕሙ ጥሩ የሆነን የአንድ አካባቢ የበግ ዝርያ መጠኑ ከፍ ከሚል የሌላ አካባቢ ዝርያ ጋር በማዳቀል በጣዕምም በመጠንም የተስተካከል የበግ ዝርያ መፍጠር ይቻላል። ይህ አሠራር በተለምዶ የአሜሪካን ላም ወይንም የአሜሪካን በሬ በሚል የሚታወቁት ከአበሻ በሬ ወይም ላም ጋር በማዳቀል በወተትም በቁመናም የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማውጣት ተችሏል። ይህ ተፈጥሯዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ የሚደረግ የማዳቀል ሥራ ነው። በዘር ደረጃም የበቆሎና የሰንዴ ምርትን በዚህ ሂደት ማሳደግ ተችሏል። ነገር ግን የመነሻ ዝርያዎቹ እንዳይጠፉ መጠበቅ ያስፈልጋል።
የዘረመል ቅይስ አካል (GMOs)
ይሄኛው ቴክኖሎጂ በጣም ውስብስብና በከፍተኛ ላብራቶሪ ውስጥ የሚተገበር ነው። ትልቅ እውቀትና ቴክኖሎጂንም ይጠይቃል። አሠራሩ ተፈጥሯዊ ከሆነ ውጪ የሁለት ተቃራኒ አካላትን (ለምሳሌ የእንስሳትን የዕፅዋት፣ የነፍሳት፣ የሰውን ወዘተ) ዘረ መል በመውሰድና በከፍተኛ ላብራቶሪ ውስጥ በማስገባት አንዱን ዘረ መል ከሌላው ዘረመል ጋር የመቀየስ አሠራር ነው። በቅየሳውም አዲስ ዝርያን ማውጣት ነው። ለምሳሌ አንድን በቆሎ ድርቅ እንዲቋቋምና ከፍተኛ ምርት እንዲሰጥ ከሌላ አካል ለምሳሌ ከዓሣ ዘረመል ተወስዶ ይቀየስና አዲስ ዘር ሆኖ ይወጣል። አጨቃጫቂ የሆነው ጉዳይ ከዚህ ውጤት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ተቃውሞና ድጋፍ ነው።
ይሄኛው ቴክኖሎጂ በልተው ለማደር ለሚፍጨ ረጨሩ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ድሃ ሀገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። ድርቅን በመቋቋም አርሶ አደሩ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኝ ያስችለዋል። ካገኘው ምርት ደግሞ ሸጦ ህይወቱን እንዲለዉጥ እና የተሻለ ኑሮ እንዲመራ ይረዳዋል። የአርሶ አደር መለወጥ ደግሞ የሀገር መለወጥ ነው። ይህ ከላይ ያለው ጥቅም ነው። ‹‹ይህንን ቴክኖሎጂ መተግበር አለብን›› ብለው የሚከራከሩ ምሁራን መናገር ወደ ማይፈልጉት ጉዳይ እንግባ።
የእኔ የሚባል ዘር ማጣት
የዘረ-መል ቅየሳ የተደረገላቸው ዘሮች ባለቤታቸው በዘርፉ የተሰማሩ ካምኒዎች ብቻ ናቸው። ካምፓኒዎቹ በከፍተኛ ወጪና በትልቅ ላብራቶሪ ለፈጠሩት አዲስ የተቀየሰ ዘር የባለቤትነት መብት ይወስዳሉ። ዘሩን ወስዶ የሚዘራ አርሶ አደር ሁሉ ለዚህ ካምፓኒ የባለቤትነት ክፍያ የመክፈል ግዴታ አለበት ማለት ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ በጣም አሳሳቢውና የዘር ቅኝ ግዛት የሚባለው የዘረ መል ቅየሳ የተደረገላቸው ዘሮች መሃን መሆናቸው ነው። ያ ማለት የዘረመል ቅየሳ የተደረገለት አንድ የባቄላ ዘር ዘንድሮ ቢመረት በቀጣይ ዓመት ከተመረተው ምርት ላይ ለዘር መጠቀም አይችልም። ምክንያቱ ደግሞ ስለማይበቅልና ዘሩ መሃን ስለሆነ ነው። ዘር ለማይበላ አርሶ አደር ይህ ሞት ነው። ጎተራው ውስጥ ምርቱን አስቀምጦ ከካምፓኒዎች ዘር እንዲገዛ ማስገደድ ነው። ዘሩን የሚያቀርቡ ካምፓኒዎች ደግሞ በመፃ ገበያ ‹‹ባለፈው ዓመት ጥሩ ምርት ስላገኘህ ዘሩ ላይ የዋጋ ጭማሪ አደርጌብሃለሁ›› የማለት መብት አለው። ድርጅቱ ይህንን ቢል ለዚህ አርሶ አደር ማንም ተከላካይ አይኖረውም። መሄጃም ስለማይኖረው የተባለውን የማድረግ የባርነት ዓለም ውስጥ ይገባል። ዞሮ ዞሮ ጫናው መንግሥት ላይ ይወድቃል። ቅይስ ዘሩን በዶላር ከውጭ ለማስገባት እንደኛ ላለች በዶላር ድርቅ በተደጋጋሚ ለምትመታ ሀገር ሌላ ቀውስ መፍጠር ነው። መሰረቴ ግብርና ነው የሚል መንግሥትንም አጣብቂኝ ውስጥ ይከታል።
ሌላው ከዚሁ የባለቤትነት መብት ማጣት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ በዘረ መል ቀይስ አካል የተዘራ መሬት በቀጣዩ ዓመት በሚዘራ መሬት ላይ የዘረ መል ውርርስ ማካሄዱ ነው። ኢትዮጵያ በዘረ መል ቅይስ አካል ላይ ምርምር የሚያደርግ ተመራማሪ ከምርምር ቦታው ዘሩ አፈትልኮ ወጥቶ ቢገኝ ተመራማሪው ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቀው ደንግጋ የነበረው ለዚህ ነው። አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ወደዚህ ስርዓት እየተንደረደረች እንደሆነ ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው።
ይህ አሠራር ተጠናክሮ በሄደ ቁጥር በብዝሃ ህይወት ሀብት ቀዳሚ የሆነቸው ሀገራችን ሀብቷን ሙሉ ለሙሉ አጥታ በላብራቶሪ የሚመረት ዘር ላይ ጥገኛ ሆና መቅረቷ ነው። በተለይ ከ80 በመቶ በላይ እፀዋቶቿ ለመድሃኒትነት ጥቅም ላይ ይውላሉ ለሚባልላት ሀገረ- ኢትዮጵያ ነገርዮሹ አሳሳቢ ይሆናል።
በነገራችን ላይ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እጃቸው በዶላር የረዘመ ነው። እኛ ሀገር እንዲገባ የፈቀዱትና ለጉዳዩ ወግነው የሚከራከሩ ወገኖች ይህንን ችግር ሳይረዱት ቀረተው ነው ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን ድርጅቶቹ በአፍሪካ ውስጥ የዘር መል ቅይስ አካል በህግ ደረጃ እንዲረቀቅና እንዲተገበር የዶላር እጃቸውን መዘርጋታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ስላሉ የእኛዎቹን ፈቃጆች አካውንት ፈተሽ ማድረጉ አይከፋም!!
የጤና ጉዳቱ
በዚህ የዘረ መል ቅየሳ ዘዴ የተመረተ ምርት ለካንሰር፣ ለውርጃ፣ ለአዕምሮ እድገት ውስንነት፣ በሽታ የመከላከል አቅምን ማሳጣትና የመሳሰሉን እንደሚያመጣ ከGMO ገለልተኛ የሆኑ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ጥናቶቹ እንዲወገዱ በማድረግና አጥኚዎችን እስከማሳደድ የሚደርሱ ዕርምጃዎች የዘርፉ ካምፓኒዎች እንደሚወስዱ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህንን ለማረጋገጥ ሰሞኑን ዘ – ጋርዲያን በዚህ ዙሪያ የሠራውን የምርመራ ሪፖርት መመልከት ከበቂ በላይ መረጃ ይሰጣል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ይህ አሠራር መተግበር አለበት ብለው የሚከራከሩ ሰዎች በምንመገበው ምግብ ላይ መተግበሩ ጉዳት ያመጣል የሚለው ሃሳብ የሚያይል ከሆነ በጥጥ ላይ ለምን አንጠቀምበትም ብለው ይከራከራሉ። ይህ መከራከሪያም ውሃ የሚያነሳ አይደለም። የጥጥ ፍሬ ለዘይትነት ያገለገላል። በምግብ ውስጥ ዘይት ስመገባ በተዘዋዋሪ ለምግብነት ዋለ ማለት ነው። የጥጥ ፍሬው ተጨምቆ ዘይት ከሆነ በኋላ ያለው ውጋጅ ደግሞ ለእንስሳት መኖ ይውላል። ይህንን የተመገቡ እንስሳቶችን ስጋና ወትተ ደግሞ ሰው ይመገባል። በዚህ መሰረት ከላይ ለዘረዘርናቸው በሽታዎች የሚያጋልጡ ሁነቶች ይኖራሉ ማለት ነው።
ጥጥ ለልብስ መስሪያ ያገለግላል። በዚህ ምርት የተሠራውን ልብስ ሰው ይለብሳል። የሰው ልጅ ሰውነት ደግሞ በርካታ ቀዳዳዎች አሉት። የልብሱ ብናኝ በቆዳችን ውስጥ ገብቶ ወደ ሰውነታችን ይገባና ጉዳት ያመጣል።
ንቦች የጥጥ አበባን ይቀስማሉ። ማር የሠራሉ። ማሩ የዘር መል ቅይስ አካል ውጤት ሆኖ ይገኛል። ሰው ይመገባል። ተዘዋወሪ ጉዳቱ ይህንን ይመስላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ አርሶ አደሮቿ ማር አምራች የሆነች ሀገር ማር ወደ ውጭ ልላክ ብትል ገዢ ታጣለች። በዓለም ገበያ ኦርጋኒክ ማር ብቻ ነው ተፈላጊው። የቢቲ ጥጥ ውጤት የሆነው ማር በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊ አይደለም። የባሰውኑ ኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ማር የላትም በሚል የማር ገበያውን ዘግቶት ያርፋል።
ይህ ከላይ የጠቀስነው በቀጥታ ምግቡን ሳንመገበው በተዘዋዋሪ የሚያደርሰውን ጉዳት ነው። ለምግብነት በሚውሉት ላይ የሚደርሱትን ጉዳት መግልጹ ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።
ኢትዮጵያ በ130 ሄክታር መሬት ላይ ቢቲ የተሰኘ በዘረ መል ቅይስ የተደረገለት ጥጥ መዝራቷን የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቅርቡ ለሸገር ተናግሯል። ይህ የጥጥ ዘር ቅድሚያ ወደ አርሶ አደሩ እንዲሰራጭ የተደረገው ሰው ስለማይመገበው በጤና ላይ ጉዳት አያመጣም በሚል ነው። ይሁንና ከላይ በጠቀስነው መሰረት አካባቢያዊ ቀውሱን ማስላት ቀላል ነው።
መሬቱ
በዘረ መል ቅይስ አካል አንድ ጊዜ የተዘራበት መሬት በቀጣይ ዓመት ያንኑ ባህሪ ይወርሳል። ለምሳሌ ዘንድሮ የተለውጠ ጥጥ የተዘራ መሬት ቀጣይ ዓመት በቆሎ ብንዘራበት መሬቱ የወረሰውን ቅየሳ ለበቆሎው ያጋባበታል። ስለዚህ በቆሎውም የዚያን ባህሪ ይዞ ይወጣል። የቢቲ ጥጥ ባለቤት የእሱን ባህሪ የወረሰውን በቆሎም የባለቤትነት መብት ሊያነሳ ይችላል። መሬቱም ለፀረ አረምና ፀረተባይ የሚጠቀመው ኬሚካል ሱሰኛ ሆኖ ያንን ካላገኘ ምንም ነገር አላበቅልም ይላል።
ምርት
የዘረ መል ቅይስ አካል አርሶ አደሮች እጅግ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የሚታሰበውም ምርታቸውን ሸጠው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ነው። ነገር ግን የዘረ መል ቅየሳ የተደረገለት ምርት የአውሮፓ ሀገራትን ጨምሮ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ ያገዱ ሀገራት በርካቶች ናቸው። የቴክኖሎጂ ዘግይቶ ተጠቃሚነት ጥቅሙ ከሌሎች ኪሳራ ለመማር ነው። እኛ ሀገር ግን ወደ ጥፋቱ እየተንደረደርን ይመስላል። በዚህ መሰረት የሚመጣውን ተጓዳኝ የጤና ችግር እንቻለው ቢባል እንኳ በዚህ ዘዴ ሀገራችን በምርት ተትረፍርፋ ወደ ውጭ እንላክ ብንል ማን ነው የሚገዛን? የሚለው ጥያቄ ሊታሰብበት ይገባል። ምን ፍለጋ ነው ወደዚህ ስርዓት ውስጥ የምንገባው? ምን ዓይነት አዙሪት ውስጥ ነው እየገባን ያለነው?
በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለው
የካርታኼና የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል በልውጥ ህያዋን የሚጠቀሙ አመራረቶች በተፈጥሮ የሚበቅሉ አዝርዕትንም ሆነ የተፈጥሮን ስርዓት ይዘው የሚራቡ የቤትና የዱር እንስሳትን እንዲሁም ሌሎች የእርሻ መንገዶችን እንዳይበክል ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድ መስፈርት አውጥቷል። ኢትዮጵያ ደግሞ የካርታኼና የስነ-ህይወታዊ አካባቢ ጥበቃ ስምምነትን ፈራሚ ሀገር ናት። ቢቢሲ አማርኛ ያናገራቸው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ምርት ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ “ኢትዮጵያ በሰፋፊ እርሻዎች በባለሀብቶች ብቻ ለማምረት ሁለት ጂ ኤም ኦ የጥጥ ዝርያዎችን ብትመዘግብም፤ ይህ በጥቅሉ አገሪቱ እነዚህን ምርቶች ተቀብላለች ወደሚል ድምዳሜ መድረስ አይቻልም” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ሁለት ዝርያዎችን ከህንድ አምጥተን ሞክረን፤ ስኬታማ ናቸው ተብሎ በዝርያ ደረጃ ተመዝግቧል። ሌሎች አገራት እንደሚያደርጉት ለእህል ግን አልፈቀድንም” ብለዋል።
ለሸገር ሬዲዮ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር አስተባባሪ ዶ/ር ታደሰ ዳባ ደግሞ በእንሰት እና በበቆሎ ላይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አልሸሸጉም። በተለይ በእንሰት ላይ ሙከራ ተደርጎ በሽታን እንደሚቋቋም ታመኖበታል ብለዋል። ዘገባው 130 ሄክታር መሬት ላይ በዘረ መል ቅይስ አካል ጥጥ ተዘርቶ እየተመረተ ነው ብሏል። ዶ/ር ዳባም የፓርላማ አባላት ሳይቀሩ ተመልክተውት ፍቃድ አግኝቶ ይህንን የሚቀራረብ መሬት መዘራቱን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ህግ መሰረት እንደዚህ ያሉ የተቀየሱ ዘሮች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የታገደ ቢሆንም በቅርቡ የተወሰነ ማሻሻያ ተደርጎ ለምርምር ብቻ እንዲገቡ መፈቀዱን ተናግረዋል። በንግግራቸው ውስጥ ሁለት የተጋጩ ነገሮች ማስተዋል ይቻላል። መጀመሪያ የተሻሻለው ህግ ለሙከራ ብቻ እንደሚፈቅድ ገልጸው አሶሳ ላይ በዚህ ምልኩ ጥጥ መልማት መጀመሩን ተናግረዋል። ስለዚህ ለምርምር ብቻ የሚለው ህግ ተጥሶ ወደ ምርት ተገብቷል ማለት ነው። ከህዝብ ተሸሽጎ የሚሠራ ሥራ መኖር የለበትም። ይህ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው።
የዘር መል ቅይስ አካል እንዳይተገበር ስትከራከር የነበረች ሀገር፣ በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ምሁራኖቿ ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሆን ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች ያሉባት ሀገር በየት በኩል እጇ እንደተጠመዘዘ አልታወቀም። ይህንን በመቃወም የተለያዩ ምሁራን የኢትዮጵያ መንግሥትን እያሳሰቡ ይገኛሉ።
የዓለም ተሞክሮ
የቡርኪና ፋሶ አርሶ አደሮች በዚህ መልኩ የተቀየሰ የጥጥ ዘር ዘርተው በርካቶች ለኪሳራ መዳረጋቸው ይነገራል። ቡርኪናፋሶ ይህንን አሠራር በጥጥ ምርት ላይ ሞክራ ከ2011-2016 ድረስ ብቻ 86 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ ደርሶባታል። ትርፉ ቀርቶ ኪሳራ ውስጥ መዘፈቅንም ጭምር ነው እንደ ሀገር እያሳሰበን ያለው። በኋላ አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመውት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እገዳ ጥለውበታል። አሶሳ ላይ የተዘራው 130 ሄክታር የጥጥ መሬት ለየትኛው ገበያ እንደሚቀርብ አብረን የምናየው ይሆናል።
የህንድ አርሶ አደሮች በዚህ አሠራር እዳ ውስጥ ተዘፍቀው ራሳቸውን እንዲያጠፉ ምክንያት የሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር የለበትም ብለው የሚሟገቱለትን ይህንን የዘረ መል ቅይስ አካል መንግሥት በምን ዓይነት መልኩ እንደሚያየው ግልጽ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት።
የዘር መል ቅየሳን ያገዱ ሀገራት
በዓለም ላይ 26 ሀገራት ይህንን የዘረ መል ቅይስ አካል አግደውታል። ስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያ፣ አወስትራሊያ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሃንጋሪ፣ ሉግዘንበርግ፣ ቡልጋሪያ፣ ፖላንድ፣ ጣልያን ከእነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ለዘረመል ቅይስ አካል ደጋፊዎች
‹‹የዘረመል ቅየስ አካል በኢትዮጵያ መተግበር አለበት›› ከሚሉ ወገኖች ጋር በአንድ ጉዳይ ብቻ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ይሆናል። ይህም የተለወጠው ዘር ባለቤቶቹ የኢትዮጵያ ካምፓኒዎች ከሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ምርምር ያወጡት ቅይስ አካል ካለ ቢያንስ ባለቤቶቹ ኢትዮጵውያን ናቸውና የተጓዳኝ ጉዳቱን ብንችለው በባለቤትነት እንካሳለን በሚል ነገሩን ማቻቻል ይቻል ይሆናል። ነገር ግን ከውጭ የመጣን መሃን ዘር ‹‹ተቀበል›› ብሎ መከራከር ዜጋን ለውጭ ካምፓኒዎች ባሪያነት አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እጅግ ሀብታም ሀገር ናት። ከዳሉል እስከ ዳሽን፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ዓለም ላይ ያለ ተፈጥሮና የአየር ንብረትን ጠቅልላ ያየዘች ግሩም ሀገር። ይህንን የተመለከቱ ሰዎች ተፈጥሯዊ የሆነውን ዘራችንን እየወሰዱ አንድም እነሱ ከሠሩት ዘር ውጪ ማብቀል እንዳንችል ሁለትም በሰው ልጅ ጤና ላይ አደጋ በመጣል በሰው ሠራሽ ቅይስ ዘር ምክንያት በቁጥጥራቸው ሥራ ለማድረግ ተነስተዋል።
ተፈጥሮ በራሷ በሚዛን የተሠራች ናት። ይህ ሚዛናዊነት ሲዛባ ነው የሰው ልጅ ችግር ውስጥ የሚወድቀው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እጅግ ሀብታም ሀገር ናት። ሰው ካልታመመ በስተቀር መድሃኒት አይወስድም። ባልታመመበት መድሃኒት ወስዶ በዚያ መድሃኒት ላይ ጥገኛ እንዲህም አይፈልግም። ለገንዘብ ያደሩት በሽታ ፈጥረው መድሃኒት ይሸጡልናል። የመድሃኒታቸው ጥገኛ ያደርጉና ደንበኛቸው አድርገው ገንዘብ ይሠሩብናል። ይህንን የምንለው የመንግሥት በምግብ ራስን የመቻል አጣብቂኝና የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ሳንረዳ ቀርተን ሳይሆን ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ እዳ ላለማውረስ ስንል ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2012