የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባትን አስመልክተው የዓለማችን ታላላቅ ሀገራትና ታዋቂ ሰዎች የኢትዮጵያን የመልማት መብት በመደገፍ ድምፃቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ሩሲያ፤ ቻይና፤ ፈረንሳይ፤ጀርመን፤የአሜረካ ታዋቂ ሴኔተሮች ፣ጎረቤት ኬንያ፤ የአፍሪካ ሕብረት፤ የአውሮፓ ሕብረት አብረውን ስለቆሙ እናመሰግናለን።
ከአባይ ወንዝ ውሃ 85 በመቶው የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ምድር ነው። እኛ በተለያዩ ዘመናት በድርቅ እየተጠቃን በረሀብ በችግር እየተገረፍን ሕዝባችን እየረገፈ አቅም አግኝተን በአባይ ውሃ ላይ ግድብ ሠርተን እንዳንጠቀም ሕጋዊ የመልማት ጥያቄአችንን ለመድፈቅ ግብፅ ብዙ ርቀት ሄዳ ስትሠራ ኖራለች።
አሁንም የኢትዮጵያ ጥያቄ የአባይን ውሃ በመጠቀም ሀገርን የማልማት፤ ከድህነት የመውጣት ለራስ የመብቃት ጥያቄ ነው። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ በሕዝብ አቅም የተጀመረ በሕዝብም ብርታት የሚቋጭ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ረዥም ርቀት ሄዶ በሰላም በድርድር በመግባባት ልዩነቶች እንዲፈቱ ሁሉም የጋራ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መከተል የሚገባ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል፤የዲፕሎማሲ ጥረት አድርጓል፤የሚጠቅመውም ይኼው ነው። አሁንም የዲፕሎማቲክ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
ግብፅ በገዛ ሀብታችን በድህነት እየማቀቅን እንድንኖር ሴራ እየሠራች እንቅፋት ሆና ኖራለች። ድሮ እንበለው ወይም በቀድሙት ዓመታት ዞር ብላ ያላየቻቸውን የናይል ተፋሰስ ሀገራት ከጎኗ ለማሰለፍ ሰፊ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ ላይ ትገኛለች። የበለጠ ወደራሷ ለማቅረብ ዕርዳታና ድጋፍ ማድረግም ጀምራለች። የዚህ ዘመቻ ዋነኛ ግብ ኢትዮጵያን ደጋፊ ለማሳጣትና ለመነጠል ያለመ እና የእነሱን ድጋፍና ድምዕ ለማግኘት እየተሠራ ያለ ሥራ ነው።
የግብፅ መሪዎች የሚያስብ ሕሊናና አዕምሮ ካላቸው ደጋግመው ቢያስቡ ይሻላል። የአባይ ውሃና የሕይወታቸው ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗን አምነው ተቀብለው አክብረው ሊይዟት ይገባ ነበር። ግብፅ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለማጥፋት በማሴር ረዥም ዘመን አሳልፋለች።በዚህ መርዘኛ መስመሯ ልትቀጥል አትችልም። ሁኔታዎች መልካቸውን ከቀየሩ ከግብፅ ጋር ያለንን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እስከወዲያኛው ልንቆርጠውም እንችላለን። ይህ ሲሆን አንድም የግብፅ ዲፕሎማት በኢትዮጵያ ምድር የመንቀሳቀስ መብት ሊያጣ ይችላል።
ጦርነትን አይተውት ኖረውበት የማያውቁት የግብፅ ጀነራሎች የካርታ ንባብና ስትራቴጂክ ንድፋቸው ከከተማቸው ካይሮ ከተቀመጡበት ወንበርና ግድግዳ አልፎ መሬት እንደማይወርድ ሊያውቁት ይገባል። ስለ ጦርነት ምንነት ኢትዮጵያውያንን ይጠይቁ። በሺ ጎራ ከጀርባ ተስልፋ ስትወጋን የኖረችው ግብፅ ነች። ግብፅ የሰላሙን መንገድ ከረገጠች ማን መጥቶ በእኛው ሀገር በአባይ ውሃ እንደሚያዝ እንግዲህ ማየት ነው።
የአባይን ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ ያለውን አዋጥቶ የጀመረውና እየገነባው የሚገኝ በቅርቡም የሚጨርሰው ነው። የትኛውም ምድራዊ ኃይል የአባይን ግድብ ሠርተን ከመጨረስ አይገታንም። ኢትዮጵያንና ልጆቿን በጦርነት ለማስፈራራት መሞከር ጅልነት ነው። ታሪካችን በሙሉ የጦርነት ታሪክ ነው።
በጦርነት ውስጥ ተጸንሰን፤ በጦርነት ውስጥ የተወለድን፤ በጦርነት ውስጥ ያደግን፤ በጦርነት ውስጥ የኖርን ለሀገር መሞትን ታላቅ ክብር አድርገን የምንወስድ ለሀገራችን ሲባል ግንባራችን የማይታጠፍ ፍጹም ኩሩና ጀግና ሕዝብ ነን። ግብፅ የጦርነት ታሪክ የላትም።
በእኛው ውሃ በእኛው ወንዝ በእኛው ሀብት በእኛው ጸጋ ሳንጠቀምበት ኖረናል። ግብፅ የአባይ ወንዝ ውሃ የራሷ እስኪመስላት ድረስ እንዳሻት ስትፈነጭበት የበረሀ ገነት ፈጥራ በምቾት ስትኖር ይህም አልበቃ ብሏት ከጀርባ በኢትዮጵያ ላይ እያሴረች ስትወጋን ስታደማን ስታስወጋን ስታስጨርሰን ኖራለች። የግብፅ መሪዎች ይህንን መሰሪነታቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያውቅ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል።
ምንጊዜም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጀርባ ሆኖ የሚያሴረው የግብፅ መንግሥት እንደሆነ ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ከእንግዲህ ለዘመናት በግብፅ መሪዎች ሲፈጸምብን የነበረው ሴራና ደባ ይበቃናል። ዲፕሎማሲም ገድብና ልክ አለው። ግብፆች ከሰሞኑ ወደ ድርድር ተመልሰናል ብለዋል። እሰየው ነው። ግን ደግሞ ከተንኮልና ከሴራ የማይጠሩ መርገምቶች መሆናቸውን እናውቃለን።ያለፉት ዘመናት ታሪካቸውም ይህንኑ ያረጋገጠ ነው።
ማንም ሆነ ምን ከእንግዲህ ኢትዮጵያ የምታባክነው ጊዜ የለም። በመጡበት መንገድ ሁሉ አፍረው እንደ ልማዳቸው ይመለሳሉ። መንግሥት እንደ መንግሥት ጉዳዩን በዲፕሎማሲ ቢይዘውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የግብፅ መሪዎችን በተመለከተ አምርሯል። በሀገራችን ውስጥም ቅጥረኛ ሰላዮቻቸውን አሰማርተው ሲሰልሉን ኖረዋል። ዋናዎቹ የግብፅ መጠቀሚያ መሳሪያዎች በኢትዮጵያዊነት ስም የሚነግዱ ራሳቸውን በተቃዋሚነት ስም የሰየሙ ገንዘብ ተከፋይ ቅጥረኞች ናቸው። ሀገራቸውን አሳልፈው የሸጡ ባንዳዎች። ድርጊታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት እይታ ውጪ እንዳልሆነ ሊያውቁ ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አስቀድሞም በሰላም በውይይት በድርድር ተግባብተን እንጨርስ አባይ ለሁላችንም ይበቃል፤ የሚያጋጨን የለም ነው ያለው። ይህ ትላንትም ዛሬም ትክክለኛ አቋም ነው። ይሄን ወርቃማ ዕድልና አጋጣሚ የግብፅ መንግሥት መጠቀም አልቻለም። አስር ጊዜ አቋሙን እየቀያየረ መጫወት ይፈልጋል።
በአባይ ግድብ ጉዳይ ወሳኞቹ ባለቤቶቹ ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። ግብፆች ለሰላምና ለአብሮነት የተሰጣቸውን ሰፊ ዕድል በተደጋጋሚ ረግጠውታል። የግድቡን ግንባታ ለማቋረጥ በዲፕሎማቲክ መስኩ ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ መሪዎች ድረስ የተለያዩ ተቋማትንም በመጠቀም ዘመቻ ሲከፍቱ ኖረዋል። አሁንም ቀጥለዋል። እኛ ከድህነት ለመውጣት፤ ሀገራችንን ለማልማት፤ የመብራት ብርሃን አግኝቶ የማያውቀውን አብዛኛውን የገጠር ነዋሪ ሕዝባችንን የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የአባይን ግድብ እየገነባን ያለነው።
ግብፆች ደግሞ በእኛው ውሃ ጠግበው ፈንጭተው ድህነትን ረስተው ድርቅና ረሀብ የማያውቁ ሆነው ጭራሹንም በድህነታችን ሲሳለቁ ኢትዮጵያ ድሀ ሀገር ስለሆነች አቅም አግኝታ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ልትሠራ አትችልም እያሉ ሲሳለቁ ኖረዋል። ይህን ሁሉ የተዛባ አስተያየት በግብፅ ሕዝብ ውስጥ ሲተክሉና ሲዘሩ የኖሩት የግብፅ መሪዎች ናቸው።
የግብፅ መሪዎች በአምባገነንነት የኖሩ በመሆናቸው የሕዝቡን የተለያዩ ጥያቄዎች ለማፈንና ለማዳከም የሚጠቀሙበት አንዱ የመነገጃ ካርዳቸው የአባይ ወንዝ ስለሆነ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እየሠራች ስለሆነ ተነስ እያሉ ሕዝቡን በሚዲያዎቻቸው ጠዋት ማታ ይቀሰቅሱታል። እውነታውን የማያውቀውን ሕዝብ ያምታቱታል። የአባይ ውሃ ምንጭ ግብፅ ሳትሆን ኢትዮጵያ ነች። ይሄን እውነት ቢመራቸውም አምነው ሊቀበሉት ግድ ይላል።
እኔ ብቻ በአባይ ውሃ ልጠቀም የሚለው የግብፅ ስግብግብነት መጠን ያለፈ ስለሆነ ከእንግዲህ ይሄን ማስታመም አንችልም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ሲመጡባት መክታ ከመመለስ ውጪ ወራሪና የሰው ፈላጊ ሀገር አይደለችም።
ግብፆች ምንድነው የሚፈልጉት ? ካሉበት ተነስተው ኢትዮጵያን በመውረር የአባይን ውሃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ከሆነ ከንቱ እሳቤ ነው፡አባይ ለእኛ ሕይወታችን አንጡራ ሀብታችንም ነው። ከተፈለገም አባይ ራሱን የቻለ ትልቅ የጦር መሳሪያ ነው። ኢትዮጵያ በግብፅ ሴራ ዝንተ ዓለም ስትደማ ስትቆስል ልጆቿን ስትገብር አትኖርም። ኢትዮጵያን ለማዳከም ከጥንት እስከ ዛሬ ያልተኛች ብቸኛ ሀገር ግብፅ ናት። ሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጀርባ ግብፅ አለች።
ከዚህ በኋላ በሰላም መሄድ ካልቻለች ጨዋታው ሁሉ ያበቃል። ኢትዮጵያ በድህነት ግብፅ ደግሞ የራሷ ባልሆነው የውሃ ሀብት እየተመጻደቀች የምትኖርበት ጊዜ ያከትማል።
በቅርቡም ድርድር እንደሚካሄድ ይጠበቃል። ግብፅ ወደ ድርድር መመለሷ መልካም ቢሆንም፣ የግድቡን ህልውና ለመፈታትን መሞከር ግን ስህተቶችን መድገም ነው የሚሆንባት።
ኢትዮጵያ ግድቧን እየገነባች እስከ አሁን በተካሄዱ ድርድሮች ስትሳተፍ ቆይታለች። ግንባታውንም በወሳኝ ምዕራፍ ላይ አድርሳለች።ጥቅሟን ግን አሳልፋ አትሰጥም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
ወንድወሰን መኮንን