ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፤ ዘመናት ነጉደው በአዲስ ሲለወጡ፤ በተመሳሳይ የሰው ልጅ በየፈርጁ የኑሮ ዘይቤውን፣ አመለካከቱን እና የሥልጣኔ ደረጃውን ከጊዜ ጋር እየተሽቀዳደመ ይቀያይራል። ይህ ብቻ አይደለም። በተፈጥሮ ኡደት የሚከሰቱ አስቸጋሪ ለውጦችን የሚቋቋምበት ብልሃትም ይዘይዳል። ስሪቱም እራሱን ከሁኔታዎች ጋር አላምዶ እንዲኖር ይፈቅዳል። ይህ ስጦታው ደግሞ በርካታ ዘመናትን አሻግሮት አሁን ያለንበት አስደናቂ የኑሮ ደረጃ ላይ አድርሶታል። ለዛሬ በዘመን ጥበብ አምዳችን ላይ ልናነሳው ለወደድነው ርእሰ ጉዳይ የሚጠቅሙንን ማሳያዎች ከስር እንደሚከተለው ለማንሳት እንሞክር።
የሰውን ልጅ የሥልጣኔና የዘመናዊነት ግስጋሴ በየጊዜው ለመገደብ የሚሞክሩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያቶች ይከሰታሉ። ከእነዚህ መካከል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ረሃብ፣ የተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ፣የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ድርቅ)፣ ጦርነት ጨምሮ ሌሎችም በምሳሌነት ይነሳሉ። ከሁሉም በከፋ ሁኔታ ግን እንደ ተዛማች በሽታ የዚህን ሰብአዊ ፍጡር ህልውና የተፈታተነው የሚገኝ አይመስልም። ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ቫይረስ የመኖር ህልውናውን በተደጋጋሚ ፈትኖታል።
ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ)፣ ኤች አይቪ ኤድስን ጨምሮ ታላላቅ የሚባሉ በሽታዎች ጎብኝተውታል። የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ፣ ቁስሉ ቢሽርም ጠባሳው ሳይጠፋ ክፉውን ዘመን በድል ተሻግሮታል። እነዚህ በሽታዎች በመቅሰፍታቸው ኃይል በጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈሩ ይሁን እንጂ በሌላ ጎን የሰውን ልጅ የመመራመር፣ የመፍጠርና የመከላከል አቅሙን ቀድሞ ከነበረው በተለየ መልኩ አሳድገውታል። ችግር መፍትሄን ይወልዳል እንደሚባለው።
ህልውናው ላይ ጥፋት የሚቃጡ ቫይረሶችን በተሰጠው ጥበብ ተመራምሮ መድኃኒት ከማግኘት ጀምሮ ክፉውን ዘመን አጎንብሶ ሥነ ልቦናውን አደድሮ የሚያልፍበት መላ ከመዘየድ ወደ ኋላ አላለም። ይህ ጥረቱ እዚህ ቢያደርሰውም የተፈጥሮ ለውጥ ደግሞ ተመሳሳይ ፈተናዎችን ከማምጣት አትቦዝንም። ለዚህም ይመስላል አሁንም ዓለምን በአንድ ከረጢት ውስጥ ከትቶ ከወዲህ ወዲያ የሚያላጋ አዲስ ፈተና የገጠመን።
ወቅታዊ ጉዳያችን ኮቪድ19 የኮሮና ቫይረስ ነው። ቫይረሱ የሰው ዘርን በሙሉ እያስጨነቀ በሽምጥ ግልቢያው መላውን ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል። ነገ ምን እንደሚፈጠር ባናውቅም እስካሁን ባለው መረጃ ሊገታው የሚያስችል አንዳችም ፍቱን መድኃኒት አልተፈጠረለትም። ሆኖም ካለፈው የሰው ልጅ ልምድና ኑረት እንደምንረዳው ይህም ጊዜ በድል እንደሚያልፍ ነው። እስከዚያው ግን እንደ ማስታገሻ አንዳች ሌላ መፍትሄ የሚያሻ ይመስላል።
ለመግቢያ አሁን ላይ ስለገጠመን ፈተና ይህን ማለት ከቻልን ወደ ዋናው ርእሰ ጉዳያችን መግባት እንችላለን። ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በዚህ አምድ ላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን ስናቀርብ ቆይተናል። በዋናነትም የጥበብ ዘርፉ የገጠመውን ፈተና እና መውጫ መፍትሄዎች እያሳየንም ነበር። አሁንም መላው ዓለምን ፈተና ውስጥ የከተተው ወረርሽኝ መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ ጉዳያችን ይህን በመሰሉ ሃሳቦች ዙሪያ ማጠንጠኑ የማይቀር ይመስላል።
በዛሬው የእሁድ ገፅ የዘመን ጥበብ አምድ ላይ ልንዳስስ የወደድነው ዓለም አቀፍ የፊልም ኢንዱስትሪው የገጠመውን ኪሳራና በቶሎ የማይቋጩ ፈተናዎችን ነው። ደመና ያጠላባቸው የፊልም ፌስቲቫሎች፣ በስጋት የተዘጉ ሲኒማ ቤቶች ጉዳይን ጨምሮ አማራጭ የዲጂታል መፍትሄዎች የዘመን ጥበብ ዋና ርእሰ ጉዳዮቻችን ይሆናሉ።
ዓለም አቀፍ የሲኒማ ድርቅ
ኮቪድ 19 በሁሉም ረገድ ተፅዕኖ በማሳደር ጡንቻውን እያፈረጠመ ነው። በዚህ ወረርሽኝ ከፍተኛ ኪሳራ ከደረሰባቸው ዘርፎች ውስጥ ደግሞ ዓለም አቀፉ የፊልም ኢንዱስትሪ ይገኝበታል። ለዛሬ የፊልም ኢንዱስትሪውን ፈተና ለማንሳት ወደድን እንጂ ወረርሽኙ በአጠቃላይ የጥበብ መስክ ላይ ተፅእኖው የበረታ ስለመሆኑ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
ታላላቅ ሲኒማ ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች፣ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ወይ ዝግጅቶቻቸውን ሰርዘዋል ፣ አሊያም ለሌላ ጊዜ አዘዋውረዋል። አዝናኝ አስተማሪና ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ ወደ ጥበብ አፍቃሪው ደጃፍ እንዲደርሱ የሚደረጉ ተከታታይና አንድ ወጥ ፊልሞች ጊዜው ላልታወቀ ጊዜ እንዲራዘሙ ተደርጓል። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፉን የቦክስ ኦፊስ የኢኮኖሚ አቅም በቢሊዮን ዶላሮች እንዲያሽቆለቁል እንዳደረገው ይፋ ሆኗል።
በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ በእጅጉ በተንሰራፋበት ወቅት ላይ የመዝናኛ ዘርፉ ተመራጭ የሆነው የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሆኗል። የፊልም አውደ ርእይ አክሲዮን ሽያጭና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ እንዲገደብ ተደርጓል። የፊልም ምርት በቫይረሱ ስርጭት ብቻ እንዲቆም ተደርጓል።
የቻይናዋ ዩሃን ከተማ ቫይረሱ የተነሳባትና ወደሌላው ዓለም በፍጥነት ለመዛመቱ ምክንያት ነች። በዚህ መነሾ የቻይና የፊልም ኢንዱስትሪ እንደሌሎቹ መሰል ዘርፎች ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ይገኛል። ባለፉት ወራት በተለይ በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ መጋቢት 2020 ብቻ የፊልም መዝናኛ ዘርፉ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አስተናግዷል።
ከመጋቢት ወር ቀደም ብሎ «ግሎባል ቦክስ ኦፊስ» እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚደርስበት ተተንብዮ ነበር። ይህ መጥፎ ዜና በእጥፍ እያደገና የተፅዕኖውን አድማስ እያሰፋ ነው። አገራት ሲኒማ ቤቶቻቸው እንዲዘጉ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስቀምጠዋል። ይህን እርምጃ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች በማገድ ተፈፃሚ እያደረጉም ይገኛሉ።
ወረርሽኙን ተከትሎ በቻይና ብቻ ወደ 70 ሺህ የሚጠጉ ሲኒማ ቤቶች ተዘግተዋል። የቻይና ፊልም ኢንዱስትሪ በሦስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የኪሳራ ማሽቆልቆል እንደደረሰበት ሲገመት ከአሜሪካው ሆሊውድ የሁለት ነጥብ 148 ቢሊዮን ዶላር አንፃር ሲመዘን ከፍተኛ መሆኑ እየተነገረ ነው። እነዚህ መረጃዎች ቀደም ባለው የኮሮና ወረርሽኝ መጀመሪያ አካባቢ የተሰሩ ጥናቶች ላይ በመመርኮዛቸው አሁን ላይ ኪሳራው ከዚህም የከፋ እንደሚሆን ይገመታል።
ጣሊያን በወረርሽኙ ዜጎቿን ከመነጠቋ ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች የኢኮኖሚ ቡጢ አርፎባታል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ተወዳጁ የሲኒማ ኢንዱስትሪዋ ይገኝበታል። ወረርሽኙ መዛመቱን ተከትሎ በፍጥነት ነበር ከ94 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሲኒማ ቤቶቿ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ከመንግሥት ትእዛዝ የደረሳቸው። በተመሳሳይ ፈረንሳይ በአገሪቱ ከሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በራቸውን እንዲጠረቅሙ ትዕዛዝ አውርዳ ነበር። የአይሪሽ፣ ማሌዥያ፣ ኳታር፣ ታይላንድ፣ሲንጋፖር፣ የጃፓን ቶኪዮ የሲኒማ ኢንዱስትሪዎች ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል።
የቶሮንቶ ፊልም ፌስቲቫል
የቶሮንቶ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል (TIFF) በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚና ተወዳጅ ፌስቲቫሎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። በዚህ ዓመታዊ ልዩ የፊልም ድግስ ላይ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በቀጥታ እስከ 480 ሺህ ሰዎች ይታደሙበታል። በአጠቃላይ በቴሌቪዥን ‹‹በላይት ቦክስ›› ስርጭትና በሌሎች መንገዶች በርካታ ሚሊዮን ሰዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት ነው።
ይህ ተወዳጅና አንጋፋ የፊልም ፌስቲቫል (ድግስ) እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ1776 ጀምሮ እስካሳለፍነው ዓመት ድረስ ሲዘጋጅ ቆይቷል። ፌስቲቫሉ በቋሚነት ዓለም አቀፍ የፊልም ባህልን በመወከል ተወዳጅና ተናፋቂ ስፍራ መሆን ችሏል። ዋነኛ ራዕይውንም የሰው ልጅ ለዓለማችን ያለውን እይታ በፊልም ማስተካከል የሚለውን ውክልና መውሰድ ምርጫው አድርጓል።
በቶሮንቶ ኦንታሪዮ አውራጃ በሚገኘው ‹‹ቤል ላይት ቦክስ›› የፌስቲቫሉ መዘጋጃ ማዕከል ፊልምን የተመለከቱ ውይይቶች፣ ትምህርታዊ ዝግጅቶች፣ ጥናቶች እና መሰል አውደ ርእዮች ይካሄዳሉ። በተለይ ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ ፕሮጀክቶች በስፍራው ይፋ ከመደረጋቸው ባሻገር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይፋ የሚደረጉበት ወርክ ሾፖችም የሚዘጋጁበት ነው።
ይህ ታላቅ ፌስቲቫል ዓለም አቀፍ እውቅናው ጉልህ መሆኑን ለመገንዘብ አንድ ምሳሌ ማንሳት ብቻ በቂ ነው። የአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2016 ሲሆን በዓመታዊ ድግሱ ላይ 397 ፊልም ከ83 አገራት ተወክለው ለእይታ ቀርበዋል። በወቅቱም ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የፊልም አፍቃሪያን፣ ባለሙያዎችና እውቅ ሰዎች ታድመውበታል።
ኮሮናና የፌስቲቫሉ አማራጭ
የቶሮንቶ ፊልም ፌስቲቫል እንደሌሎቹ የመዝናኛ ዘርፎች ሁሉ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በሩን ለመዝጋት የተገደደ ይመስላል። መስከረም ላይ የሚካሄደውና ከግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚሳተፍበት ድግስም ከወዲሁ እንደማይካሄድ ጠቋሚ ምልክቶች ታይተዋል። አዘጋጆቹም የወረርሽኙን ስርጭት ከሚያባብሱ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች እንደሚርቁ ከመናገር አልተቆጠቡም።
ሆኖም ግን ተወዳጁን የመዝናኛ ድግስ ሙሉ ለሙሉ እንደማይሰርዙና መውጫ አማራጮች እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል። የፌስቲቫሉ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጆና ቪንሴት በተለያዩ ጉዳዮች ጋር ከሲ ኤን ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቆይታ እንዳስታወቀው፤ በዚህ ዓመት የሚደረገው የቶሮንቶ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አማራጭ ይቀርባል።
‹‹የፊልም ኢንዱስትሪው አባላትና ልኡካን መስከረም ላይ ልናካሂድ አስበነው ለነበረው ፌስቲቫል ወደ ከተማዋ መምጣት እንደማይችሉ እናውቃለን›› ያለው ምክትል ዋና ኃላፊው ጆና፤ ተሳታፊዎቹ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መምጣታቸው ፈተናውን ይበልጥ እንደሚያከብደው ይናገራል። በረራዎች መዘጋታቸው፣ በርካታ ሺህ ተሳታፊ በአሁኑ ወቅት በአንድ ላይ መሰብሰብ ለወረርሽኙ እጅግ ተጋላጭ በማድረጉ፤ ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት እንዳስገደዳቸው አንስቷል።
አዘጋጆቹ ከእስከ ዛሬው በተለየ መንገድ አዲስ አቀራረብ እያዘጋጁ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። ይህ ዝግጅትም ከመስከረም 10 እስከ 20 ድረስ እንደሚቆይም ታውቋል። ይህ በዓይነቱ የተለየ ዝግጅት በዲጂታል ሚዲያ ለማሰራጨት የታሰበ ሲሆን የጤና ባለሙያዎችን በማማከር የሚቀርብ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።
‹‹በዲጂታል አማራጭ ጠንካራ የፊልሙ ኢንዱስትሪ ውጤቶችን ይዘን ለመቅረብ አስበናል›› ያለው ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ፤ (ሃይብሪድ ፌስቲቫሉ) በምን ያህል ስፋትና መጠን ለማዘጋጀት እንደታሰበ በሰኔ ወር መሃከል ላይ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እየሰሩ እንደሆነም አስታውቋል። በየዓመቱ በሚካሄደው ታላቅ ድግስ ላይ ይሳተፉ የነበሩ የፊልም ኢንዱስትሪው ቤተሰቦች በዚህ ዓመት በልዩ መንገድ የሚገናኙ ይሆናል።
እንደ ቪንሴንት ገለፃ ወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ‹‹በቤቶት ይቆዩ ሲኒማ›› በሚል መርህ ‹‹በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ›› የፊልም ባለሙያዎችንና አፍቃሪዎችን በአንድነት ያገናኘ ስርጭት እያካሄደ መሆኑንም አስታውቋል። ዳይሬክተሩ ዕድለኛ ሆነን በመጪው መስከረም ዝግጅቱን በተሳካ ሁኔታ ማቅረብ ከቻልን፤ የፊልም ድግስ፣ ውይይት፣ የኢንዱስትሪ ድጋፍ አማራጮች እናቀርባለን ብሏል። ይህ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል በብዙዎች ከሚጠበቁ ተወዳጅ ድግሶች አንዱ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2012
ዳግም ከበደ