ወዳጄ፤ “አየር መንገዳችን ኩራታችን፣ መታወቂያችን..” የሚሉ ዲስኩሮችን ደጋግመህ ሰምተኸ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም መሬት የረገጠውን እውነት ማስተዋል ስትጀምር ልክ እንደእኔ የዲስኩሩን ትክክለኛነት በራስህ አንደበት መመስከር ትጀምራለህ። ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲህ ዓለምን እያተራመሰ ባለበት በዚህ ክፉ ወቅት አየር መንገድህ አሁንም በኩራት ሰማዩን ሰንጥቆ የሚያልፍና ለሐብታሙም፣ ለደሀውም አገራት ደራሽ መሆኑ ባያኮራህ ይገርማል።
ሰሞኑን የአክቲቪስት ታማኝ በየነ የምሥጋና ቃል ዩቲዩብ ላይ ስሰማ አንዳች ጥሩ ስሜት በውስጤ ተለኩሷል። ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አሊያንስ) የሚመራው አክቲቪስት ታማኝ በየነ እንዲህ አለ። በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኮቪድ 19 ለመከላከል ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶች ለመግዣ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባሰብ ከርሟል። በመጀመሪያ ዙር ብቻ ወደ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶችን ገዙና ወደ ኢትዮጵያ መላኪያው ችግር ሆነ። አንዱ ችግር ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የአውሮፕላን ትራንስፖርት በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ ነው። ሁለተኛው ቢገኝም የማጓጓዣ ዋጋው ዕቃው ከተገዛበት የማይተናነስ ወይንም ውድ መሆኑ ነበር። እናም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የትብብር ጥያቄ አቀረቡ። አየር መንገዱ ያለምንም ማንገራገር ዕቃዎቹን በነጻ ሊያጓጉዝ ተስማምቶ ፈጸመ።
በዚህም ምክንያት ግሎባል አሊያንስ የህክምና ቁሳቁሶቹን ሰሞኑን ለጤና ሚኒስቴር ለመለገስ በቃ። አክቲቪስት ታማኝ በየነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላበረከተው ወገናዊ አስተዋጽኦ በግሎባል አሊያንስ እና በዲያስፖራው ወገኖች ስም ምሥጋናውን በይፋ ያቀረበውም በዚህ ምክንያት ነው።
አዎ!.. የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በርካታ አየር መንገዶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ሥጋት ጋር ተያይዞ እጃቸውን አጣጥፈው በተቀመጡበት፣ ብዙዎቹም ኪሳራ እያጣጣሙ ባሉበት በዚህ ሰዓት በእጅጉ ያሽቆለቀለውን የመንገደኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ለጊዜው ቆም አድርጎ ወደ ካርጎ ቢዝነስ ፊቱን አዙሯል። የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ጭምር የጭነት (የካርጎ አገልግሎት) እንዲሰጡ እየቀየረ ይገኛል። በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ በዚህ አስቸጋሪ የችግር ወቅትም የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚረዱ መድሃኒቶችና ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን ኩራት፣ መከታ ሊሆን በቅቷል።
ኮቪድ 19 እና አየር መንገዱ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሰረተው ከዛሬ 74 ዓመት በፊት ሲሆን እ.ኤ.አ በ2018/19 ብቻ 431 ሺ 859 ቶን ካርጎ አጓጉዟል። ከአምስት በላይ የአፍሪካ አየር መንገዶችን በማኔጅመንት ኮንትራት እና ሼር በመውሰድ ያስተዳድራል። በሳምንት 2 ሺ 204፣ በቀን 354 በረራዎች የነበሩት ሲሆን በጠቅላላው 127 መዳረሻዎች አሉት። ከ17 ሺ በላይ ሠራተኞችን በቋሚነትና በጊዜያዊነት የያዘ ሲሆን በአየር መንገዱ ጋር ተያይዞ በተዘዋዋሪ የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲካተቱ ቁጥሩ ከአንድ ሚሊየን በላይ ይዘልቃል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መቀስቀስ ከተሰማ በኋላ ሐብታሞቹ አገራት ጨምሮ ወዲያውኑ የወሰዱት እርምጃ አየር መንገዶቻቸው በረራ ማቋረጥ ነበር። ይህን እርምጃ ከወሰዱት መካከል የእንግሊዙ አየር መንገድ፣ ከአፍሪካ ደግሞ የግብጽ አየር መንገድ ተጠቃሽ ነበሩ። የሚገርመው እነዚህ አገራት በራቸውን በዘጉበት ሁኔታም የኮሮና ወረርሽኝን አገራቸው እንዳይገባ መከላከል አልቻሉም። እንግሊዝ ከዜጎችዋም አልፎ ጠቅላይ ሚኒስትርዋ ጭምር የበሽታው ሰለባ ሲሆኑ ግብጾች የህዳሴን ግድብ እናጠቃለን በሚል ያስፈራሩ የነበሩ ሁለት የጦር ጀኔራሎቿን በሞት አጥታለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥብቅ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎች በመተግበር በተለይ የወረሽኙ መነሻ ወደሆነችው ወደ ቻይና የሚያደርገው ጉዞ መቀጠሉ ለከፍተኛ ትችት ዳርጎት ቆይቷል። ትችቱ ሁለት ዓይነት መልክ የነበረው ነው። አንዱና ብዙ ሰዎች ያራመዱት ለአገርና ለወገን ከመቆርቆር የመነጨ ሲሆን ሁለተኛው ግን ይህንን መነሻ በማድረግ የዘር ፖለቲካ ትርክት እና ቀረርቶ እያራመዱ የአየር መንገዱን መልካም ስምና ዝና መናድ የሚፈልጉ ግለሰቦች የሚያቀነቅኑት አፍራሽ አካሄድ ነበር። ከእነዚህ አፍራሾች መካከል እንደሕዝብ ስልክ ሳንቲም ሲገባባቸው ብቻ የሚሰሩ አክቲቪስት ተብዬዎች አየር መንገዱ “የኮሮና ቫይረስ አከፋፋይ ሆኗል” ብለው እስከመዘባበት ደርሰዋል። ሆኖም አየር መንገዱን ጨምሮ የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት አገራት በረራ በማቋረጥ በር መዝጋታቸው ብቻውን ወረሽኙን ለመከላከል መፍትሔ አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ሲሰጡ የነበሩት ማሳሰቢያዎች እውነትነት ቢዘገይም በገሃድ የታየ ነበር።
የኮቪድ 19 መስፋፋት ተከትሎ አየር መንገዱ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ወደ 30 አገራት የሚያደርገውን በረራ እንዲያቋርጥ በመንግሥት ሊወሰን ችሏል። በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ በየካቲትና በመጋቢት ወር (2012 ዓ.ም) ብቻ 190 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አጥቷል። በኋላም የገቢ እጦቱ በጠቅላላው ከ 550 ሚሊየን ዶላር በላይ ከፍ ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ጭምር በሰለጠኑ የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ለጭነት (ካርጎ) አገልግሎት በመቀየር ሥራውን በስፋት የገባበት ከዚህ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በሥልጠና እና የጥገና አገልግሎቶችን በማስፋት ተጨማሪ ገቢ የማፈላለጉ ሥራ አጠናክሮ የቀጠለውም የመንገደኞች ገቢው ከተቋረጠ በኋላ ነው።
የአየር መንገዱ ከኮቪድ 19 መከሰት በፊት ከ80 በመቶ በላይ ገቢው በመንገደኞች ማጓጓዝ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ነበር። ወረርሽኙን ተከትሎ የአየር መንገዱ ከ90 በመቶ በላይ አውሮፕላኖቹ ሥራ በማቆማቸው በገቢው ላይ አሉታዊ ጫና ተከሰተ። ይህን ቀውስ ለማለፍ አየር መንገዱ መላ መዘየድ ነበረበት። በእጁ ያለውን ሐብት እና ዕውቀት በመጠቀም የካርጎና የጥገና አገልግሎቱን በሦስት እጥፍ በማሳደግ የሚደርስበትን ኪሳራ የመቋቋም ሥራ ውስጥ ሊገባ ችሏል። በዚህም ምክንያት ከማንም በፊት ከ17 ሺ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞቹ የስራ ዋስትና አረጋግጧል።
በቅርቡ እንደምናስታውሰው አየር መንገዱ ከቻይናዊ ባለጸጋ ጃክ ማ ለ54 የአፍሪካ አገራት የተለገሱ የህክምና ቁሳቁሶችን በሦስተኛ ዙር በማዳረስ ታሪክ ሰርቷል። ለ54ቱ የአፍሪካ አገራት የተለገሱት 61 ሺህ ኪሎ ግራም የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ሲሆን ከዚህ በፊትም በመጀመሪያው ዙር 100 ሺህ ኪሎ ግራም፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 160 ሺህ ኪሎ ግራም አጓጉዟል።
ካጓጓቸው ቁሳቁሶች መካከል ለኮቪድ 19 መካላከያ የሚውሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች፣ መመርመሪያዎች፣ የመተንፈሻ መሳሪያዎች፣ የሕክምና አልባሳትና የፊት መሸፈኛዎች፣ የሙቀት መለኪያዎችና 500 ሺህ ጥንድ የእጅ ጓንቶች… ይገኙበታል።
አየር መንገዱ ለጃክ ማ የሕክምና ግብዓቶች በብቃት ማከፋፈል መቻሉም ሌሎች ለመሰል ገበያዎች በር ከፍቶለታል። ከፍ ያለ ብቃቱ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገራት ጭምር ተመራጭ የካርጎ አገልግሎት ሰጭ ድርጅትነት አሸጋግሮታል። ከመድሃኒት ባሻገር ለአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅና እስያ አገራት ማጓጓዙንም ቀጥሏል። ከኮቪድ- 19 ጋር የተያያዙም ሆነ ሌሎች የንግድ የጭነት አገልግሎቱን ከአፍሪካ አገራት ባለፈ በሌሎች ክፍላተ ዓለማት ሁሉ እያሰፋም መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ የካርጎ (የጭነት) አገልግሎቱን በማጠናከሩ በጎረቤት አገር ኬንያ ተይዞ የነበረውን የአበባ ከፍተኛ ገበያ ለመቆጣጠር አስችሎታል። በካርጎ አገልግሎቱ የሚሰጡ የሰብዓዊ ድጋፎችን ከማጓጓዝ ጎን ለጎን አበባን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን ወደ ውጭ በማጓጓዝ ገበያ የማፈላለግ ሥራም እያከናወነ ነው። አየር መንገዱ በኢትዮጵያ ለሚገኙት ላኪዎች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራ ሲሆን በቀን ከ200 ቶን በላይ የአበባ ምርት ኤክስፖርት የማድረግ ሥራውን ቀጥሏል። ባሳለፍነው የረመዳን የጾም ወቅትን ተከትሎ በርካታ የሥጋ ምርት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ማጓጓዙም ታውቋል።
አየር መንገዱ ከኮቪድ 19 ወርሽኝ በፊት ከካርጎ አገልግሎት 15 በመቶ፣ ከመንገደኞች ደግሞ 85 በመቶ ገቢ ያገኝ ነበር። በአሁኑ ወቅት ከመንገደኞች የሚገኘው ገቢ በመቆሙ የካርጎ አገልግሎቱ ወደ 30 በመቶ ማደጉ ተገልጿል። የካርጎ አገልግሎት ገቢው የበፊቱን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ባይተካ እንኳ ድርጅቱ የገጠመውን ችግር ተቋቁሞ የሠራተኞችን ደመወዝና ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን እንዲሁም የአውሮፕላኖቹን እዳ ለመክፈል እንደሚያስችል ከአየር መንገዱ የሚወጡ መረጃዎች ይናገራሉ።
እንደመውጫ
የኮቪድ 19 በትሩን ካሳረፈባቸው ዘርፎች ግንባር ቀደሙ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ነው። በርካታ አየር መንገዶች ከስረዋል። ከኪሳራም ጋርም ተያይዞ ሠራተኞችን ወደ መቀነስ አዘንብለዋል። እንደዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሐብታም አገራት ለአየር መንገዳቸው ቀጥተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ወስነው የ58 ቢሊየን ዶላር ድጎማ አድርገዋል።
ከወራት በፊት ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ቀደም ሲል በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዘርፉ ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር ሊያጣ ይችላል ብሏል። የአፍሪካ አየር መንገዶች እስከ መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጡ ማኅበሩ አስታውቋል። በአሁን ሰዓት ይህ ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረትነቱ የመንግሥት ነው። ዓመታዊ በጀቱን በብድርና ዕርዳታ የሚደጉም የአገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኝ የቢዝነስ ተቋም ከመንግሥት ድጎማ ሊጠብቅ አይችልም። እናም ያሉትን አማራጮች ሁሉ ተጠቅሞ ገቢውን ለማሳደግ የመስራቱ ነገር ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች የተሳካ ሥራ እያከናወኑ ነው። አሁን ባለበት ደረጃ አየር መንገዱ ቢያንስ ኪሳራ ውስጥ ሳይገባ ወጪውን ሸፍኖ ሊጓዝ እንደሚችል ፍንጭ መታየቱ ለሰሚው ትልቅ የምስራች ነው።
የ74 ዓመታት ውጤታማ ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 14 ሺ ቋሚና 3 ሺ የኮንትራት ሠራተኞች አሉት። ከዚህ ቀደም እንደ ሳርስ፣ ኢቦላና ዚካ ያሉ በሽታዎችን ተቋቁሞ ያለፈ አየር መንገድ ነው። አሁንም በሠራተኞቹና በማኔጅመንቱ ጥንካሬ በርትቶ በመሥራት ይህን ክፉ ቀን ለማለፍ እየታተረ ይገኛል። እስካሁን ባሉ መረጃዎች እየተሳካለትም መሆኑ በመልካም ዜናነቱ የሚጠቀስ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
ፍሬው አበበ