“የትናንቱ ትናንት አልፏልና፣
ዛሬ በአዲስ ሕይወት እንደገና።”
ይህንን ባለሁለት ስንኝ አዝማች ያንጎራጎረው ዘማሪ ይሁን አዝማሪ እርግጠኛ አይደለሁም። ግጥሙንና ዜማውን ግን በሚገባ አስታውሰዋለሁ። አዝማሪም ከሆነ እሰየው፤ ዘማሪም ከሆነ አበጀ። ለምንና በምን ሁኔታ ግጥሙ እንደተዋቀረ ባይገባኝም ለነገው ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተጠባቂ ድንግዝግዝ ክስተቶች ግሩም መልዕክት ያስተላልፋል ብዬ ስላሰብኩ እነሆ ለጥቅስም፣ ለመንደርደሪያ ሃሳብነትም ይጠቅም ስለመሰለኝ ለዕለቱ ጽሑፌ ሃሌታነት መርጨዋለሁ።
“አዲስ ዘመን” የሚለው ስያሜ በርዕሱ ውስጥ እንዲጎላ የተፈለገው ይህንን ዕድሜ ጠገብ ጋዜጣ ለማመልከት ታስቦ አይደለም። ወይንም በተለምዶ በአራቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ) የሚወከሉ የአዲስ ዓመት “አዲስ ዘመናትን” ታሳቢ በማድረግም አይደለም። “አዲስ ዘመን” የሚለው ገላጭ ሀረግ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በወካይነት የቀረበው ዓለምን በጭንቅ ውስጥ የጣለው ይህ ክፉ የኮቪድ ወረርሽኝ ተሸንፎ “በምልዓት ወደ አደባባይ ተገልጠን” የተለመደው የሕይወት እንቅስቃሴያችን ሲሟሟቅ ምን አዳዲስ ክስተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ለማመልከት ነው።
የተለምዶ ጉዳይ ሆኖ ዘመንን አሮጌና አዲስ ብሎ መፈረጅ ያለ፣ የነበረና ለወደፊቱም ይቀራል ተብሎ የሚታሰብ ልማድና ባህል አይደለም። ብሂሉ “የዘመን አሮጌ፤ የውሃ እድፍ የለውም” ቢለንም የሙጥኝ ብለን ይዘነው የዘለቅነው ልማድ ግን ዘመንን “አዲስና አሮጌ” እያልን በመመደብ ነው። በእኛ ዐውድ ክረምቱ በሽልም ወጥቶ መስከረም ሲጠባ፤
“ክረምት አልፎ በጋ፤ መስከረም ሲጠባ፣
በአበቦች መዓዛ እረክቷ ልባችሁ፣
ሕዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ።”
እየተባባልን “እንኳን ከዘመን ዘመን አደረሳችሁ” መባባል የተለመደ ባህላችን ሲሆን “ለአሮጌው ዘመንና ለአዲስ ዘመን መሸጋገሪያ ድንበር የሆነችው” ደግሞ ኩርማኗ ጳጉሚት ናት።
ከታሪካችን አንጻርም አንዳንድ ክስተቶችን ማስታወስ ይቻላል። ከአድዋ ድል በፊት የነበሩት ዘመናት “አሮጌ”፣ የድሉ ማግሥት ተከተለው የመጡት ዓመታት ደግሞ “አዲስ ዘመን” እየተባሉ በታሪክ ሲጠቀሱ እናስተውላለን። “አዲሱ ድህረ አድዋ ዘመን” የቆየው እስከ ኅዳር በሽታ (1911 ዓ.ም) ድረስ ለሁለት ዐሠርት ዓመታት ብቻ ነበር። ሀገርና ሕዝብን በቸነፈሩ ያጠቃው ደዌ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ “አዲስ ዘመን” የተባለላቸው የድህረ አድዋ ዓመታት “አሮጌ” ተሰኝተው በምትኩ ከ1911 እስከ 1933 ዓ.ም ያሉት ተመሳሳይ ዐሠርት ዓመታት ደግሞ “አዲስ ዘመን” የሚል ስያሜ ተሰጣቸው።
በ1933 ዓ.ም በፋሽስት ጦር ላይ ድል የመቀዳጀቱ ዜና እውን ሲሆን ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ያሉት ዓመታት “አዲስ”፣ ከዚያ በፊት ያሉት ደግሞ አሮጌ ተብለው በታሪክ ካዝና ውስጥ ሊቆለፍባቸው ግድ ሆነ። የአዲሱን ዘመን መግባት ያበሰሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንበረ ሥልጣናቸውን ባረጋገጡበት ዕለት ዘመኑ ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ዘመን መባቻ ላይ ውልደቱ እውን የሆነው ይህ ጋዜጣም ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም “አዲስ ዘመን” ተብሎ በመሰየም የአዲስ ዘመኑ አዲስ ብሥራት ማወጃ ልሳን ሆኖ ፀደቀ።
አንዳች ታሪካዊ ክስተትና የዐውድ ዓመት ሽግግር መንስዔ ሆኖ ዓመታትን በአዲስና በአሮጌ ዘመንነት መመሰልና መሰየም የተለመደ ሰብዓዊ ልማድ ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን ልማዱ የሚሸከማቸው ትልልቅ ተስፋዎችና ስጋቶች የሚንፀባረቁበት እንደሆነም መገመቱ አይገብድም። ለዚህም ነው በድህረ ኮቪድ ድል ማግስት የምንቀበለው ዘመን “አዲስ” እንደሆነ ከወዲሁ የሚተነበየው።
የ“አዲሱ ዘመን” ዓለም አቀፍ ተገማች ክስተቶች፤
የምድራችንን መሠረት ያናወጠው፣ መላውን የሰው ዘር የናጠውና ያብረከረከው፣ ነባር የዓለማችንን የሕይወት ዑደትም በአዳዲስ ክስተቶች ሊለውጥ ዳር ዳር የሚለው የድህረ ወረርሽኙ መጻኢ “አዲስ ዘመን” ብዙ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ ጠቢባን እየገመቱ ሲተነብዩና ሲያስጠነቅቁ ይደመጣል። የወረርሽኙ መሸነፍ በአዳዲስ የሕክምና ጥበቦች በቅርቡ እውን እንደሚሆንና አቅሙ ተሽመድምዶና የገዳይነቱ ሰንኮፍም ተነቅሎ ታሪክና ተረት እንደሚሆንም “በመሃላ ጭምር ሲያረጋግጡልን” ተስፋው ልባችንን ማሞቁ አልቀረም።
በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ኃያላን እየተባሉ ከበሮ የሚደለቅላቸው ገናና ሀገራት በድህረ ኮቪድ “አዲሱ ዘመን” ተሸናፊ ሆነው ለአዳዲሶቹ አሸናፊዎች እንደሚገብሩ የዘርፉ ጠቢባን በአሳማኝ ማስረጃዎች ትንተና ግምታቸውን እያፀኑ ይገኛሉ። “How the World Will Look After the Coronavirus Pandemic” በሚል መሪ ርዕስ ሥር በቅርቡ አሥራ ሁለት ያህል የዓለማችን ታላላቅ ጠቢባን ያቀረቡት ትንታኔ ብዙዎችን ያስማማ ግምት ሆኗል። እነዚህ ተመራማሪዎች “የኃያልነቱ በትረ ሥልጣን” ከምዕራቡ ዓለም ወደ ምሥራቁ እንደሚተላለፍ አስረግጠው ጽፈዋል። ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ቻይና “የገናናነት ትንቢቱ” ከደረሳቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ተደነቃቅፈው ከወደቁባቸው መሰናክሎች አቧራቸውን አራግፈው እስኪያገግሙ ድረስ እነዚህ ሦስት ሀገራት ጥለዋቸው እንደሚገሰገሱ ትንታኔያቸው ያመላክታል።
በትንተናቸው አጽንኦት ከሰጡባቸው ሌሎች በርካታ ጉዳዮች መካከል ሀገራት ለስደተኞች ወለል አድርገው ሲከፍቱ የኖሩትን በራቸውን ሙሉ በሙሉ ባይከረችሙትም ገርበብ አድርገው ነፃነቱን እንደሚያጠቡትም ተንብየዋል። በልግስናቸው የሚታወቁት ሀገራትና መንግሥታት እንደ ቀድሞው ከሀብታቸው እየመዠረጡ በሚመጸውቱትና በሚለግሱት ሀብት ላይ እጃቸውን ሰብሰብ እንደሚያደርጉም ተገምቷል። የዲፕሎማሲው ጥበብ እጅግ እንደሚረቅና እንደሚወሳሰብም ይጠበቃል። የዓለም ሕዝቦች ችላ ያሉትና በሳይንስ ጥበብ ተመክተው ወደ ጎን ገፋ ያደረጉት “የፈሪሃ ፈጣሪ” ጉዳይ እስከ መቼ እንደሚቀጥል ባይታወቅም ለጊዜው የመሻሻል ሁኔታ እንደሚታይበት ጭምር ተንብየዋል። ሰዎች ወደ “ነፍሳቸው ፈጣሪ” መለስ ማለታቸው በመልካምነቱ ቢጠቀስም በአንጻሩ ደግሞ እምነትን የተመለከቱ ብዙ ዝብርቅርቅ ክስተቶች እንደ አሸን እንደሚፈሉ ተመራማሪዎቹ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
የሕዝቦች ሰብዓዊ መስተጋብር በዘመን ወለድ የቴክኖሎጂ ግኝቶች እየተተካ ዛሬ ላይ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው አካላዊ መራራቅ ተጠናክሮ በመቀጠል በመንፈስ ጭምር ሰብዓዊ ግንኙነቱ እንደሚሸረሸር ሕዝበ አዳምም “የቴክኖሎጂ ተንበርካኪ” በመሆን ሕይወቱን እንደሚመራ ብዙ የማስጠንቀቂያ ደውሎች እየተሰሙ ነው። የቤተሰብ ቅርርቡ ከላላ፣ ማሕበራዊ ተራክቦው ከተውሸለሸለና በሰው ለሰው ግንኙነት ላይ ጥላውን ካጠላ “የአዲስ ዘመኗ” ዓለማችን ምን መልክ ሊኖራት እንደሚችል መገመቱ አይከብድም።
ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገሩ የመጡ ሕዝባዊ ባህሎችና ትርክቶች ዋጋቸው ቀንሶ አዳዲስ ታሪኮችንና ትርክቶችን ለመጻፍ የዘመኑን ገጽ መግለጥ እንደተፈራው እውን የሚሆን ከሆነ ውጤቱን ለመተንበይ ሳያዳግት አይቀርም። ድህረ ኮቪድ በመላው ዓለም ይዞ የሚመጣው “የአዲስ ዘመን” ጓዝ ጉዝጓዝ እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያበቃ ስላይደለ ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም ስለምናየው ወደ ራሳችን ጉዳይ ተመልሰን “እህ!” መባባሉ ይሻል ይመስለኛል።
“የአዲስ ዘመኗ” ሀገሬ የነገ መልክ፤
እንደ የትኞቹም የዓለም ሀገሮችና ሕዝቦች እኛም ከኮቪድ ጥቃት ለማምለጥ አልቻልንም። ሀገራዊ ርብርቡ ፍሬ ማፍራቱ አይቀሬ መሆኑ እውን ቢሆንም መከራችን በአጭሩ እንዲገታ ግን ዋነኛ መፍትሔ አመንጪዎቹ እኛው ዜጎች ስለመሆናችን ደጋግሞ ተነግሮናል። የሚሰጡንን ትእዛዞች ያለመጠበቅ፣ በዓይን የሚታየውን የቫይረሱን አደጋ እንዳልተፈጠረ በመቁጠር በምንፈጽማቸው ስህተቶች አሳራችንን ማስረዘማችን እንደተጠበቀ ሆኖ “የመከራ ጀንበር ዕድሜው አጭር ስለሚሆን” ወረርሽኙ ያደረሰውን ጉዳት ካደረሰ በኋላ ተገትቶ በቁጥጥር ሥር መዋሉ አይቀሬ ነው። “አድርጉና አታድርጉ” ለሚሉት የጤና ባለሙያዎች ምክሮችና ትዕዛዞች ከተገዛንና ከታዘዝን የፈጣሪ ርዳታ ታክሎበት በወረርሽኙ ላይ ድል የምናውጅበት ጊዜ ሩቅ ያለመሆኑ ግን እርግጥ ነው።
እስካሁን በተጓዝንባቸው ሰማንያ የዝግ ቀናት ውስጥ የወረርሽኙ ስፋት በሁለንተናዊ መልኩ ምን ያህል ሀገራዊ መናጋት እንደፈጠረ እያስተዋልን ነው። “በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ ለማደግ ዳዴ እያለ ባለው ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን ላይ እየደረሰ ያለውን የሚያንገደግድ ስካር በነጋ በጠባ እያስተዋልን ነው።
“ቱባ” እያልን ስናንቆለጳጵሳቸው የኖርነው ማሕበራዊ ጽኑ እሴቶቻችን ጨርሰው ባይፈረካከሱም ስንጥቆች ግን እዚያም እዚህም እየተስተዋሉ መሆናቸውን ግን አንክድም። የየትኞቹ እሴቶቻችን ጉልበት እየላላ በመብረክረክ ላይ እንደሚገኝ ዝርዝሩ በጥናት ተደግፎ ወደፊት ስለሚቀርብ ምልክቶቹን ብቻ ጠቋቁሞ ማለፉ ይሻላል። የበሽታው ወረርሽኝ በስፋት እንዳይሰራጭ ስንገናኝ በእጅ እየተጫባበጥን ሰላምታ መለዋወጣችን፣ መሽቶ ሲነጋ ጉንጭ ለጉንጭ መሳሳማችን፣ ከታዳጊ ልጆቻችን እኩል በትከሻችን እየተጓሸምን “ፒስ ነው!?” እየተባባልን መልካም ምኞት መለዋወጣችን ድህረ ኮቪድ “በአዋጅ እንኳ ቢታዘዝ” ወደ ነበረበት ይመለስ ይሆን ወይ የሚለው ሥጋት የብዙዎቹ ፍርሃት ነው። ባህሉ ሙሉ ለሙሉ ይደመሰሳል ማለት ሳይሆን ንፋስ ሳይገባው እንደማይቀር ግን ለመገመት አይከብድም።
የሠርግና የቀብር፣ የእድርና የእቁብ፣ የቤትና የውጭ ባህሎቻችንና ልማዶቻችን “ከኮቪድ እስራት” በተፈታን ማግስት ባስቀመጥናቸው “የባህል መሶብ” ውስጥ እንደነበሩ ሆነው ይቆዩናል ብሎ በድፍረት መናገር ያዳግታል። ከመለስተኞቹ እሴቶቻችን ጀመርኩ እንጂ በግዙፍነት የምንጠቅሳቸው ባህሎቻችን፣ ሃይማኖታዊ ልምምዶቻችንና በርካታ ማሕበራዊ መስተጋብሮቻችን እንደነበሩ እንደሚቆዩን ለመመስከር አፍ ይይዛል? መወያየቱና ለመፍትሔውም በጋራ መምከሩ የመጻኢዎቹ የነገ አዳዲስ ክስተቶች ሲደርሱ እንዳንደነግጥ ሊያግዘን ይችላል።
የሀገራዊው ኢኮኖሚያችንን አካሄድና የፖለቲካ መጫወቻ ምህዳሩን እንደነበረ ይዘናቸው እንሻገራለን ማለት የዋህነት ነው። ሲያናቁሩንና ሲያራኩቱን የባጁት የግልና የቡድን አመለካከቶች የቱ በአሸናፊነት እንደሚዘልቅ፣ የቱ ተሸንፎ ትቢያ እንደሚለብስ የአዲሱ ዘመን ጀንበር ወለል አድርጎ ስለሚያሳየን እስከዚያው በትእግሥት መጠበቁ ይመረጣል። በአጭር ገለጻ ይህንን ክፍል መቋጨት ካስፈለገ ግን ማለት የሚቻለው የድህረ ኮቪዱ “አዲሱ ዘመን” የሚሸምነውን ቡቱቱ ላለመልበስ ተጠይፈን የሚያምርብንን “ጃኖ” ለመጎናጸፍ ዝጅታችንን ከወዲሁ ልንጀምር ይገባል።
እናስ መጻኢውን ዘመን እንዴት እንቀበለው?
ይህ ጸሐፊ የአቀባበል ዝግጁቱን ሙሉ የመርሃ ግብር “ሜኖ” በዝርዝር ለማቅረብ አይዳዳም። አቅሙ ውስን፣ መደምደሚያውን ለመስጠትም ጊዜው ማለዳ ነው። እውነታው ይህን ቢመስልም እንደ አንድ ዜጋ “ባይሆኑ” የምላቸው በርካታ የግሌ ስጋቶች የመኖራቸውን ያህል “ቢሆኑ” ብዬ የምመኛቸውም ጉዳዮች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። አንዳንዶቹን ልጠቋቁም።
የ“ባይሆኑ” ምኞቶቼ፤
አዲሱን የድህረ ኮቪድ ዘመን ተከትሎ የሚነግሠው “የቴክኖሎጂ ትሩፋት ተፅእኖ” በዘመናት በካበተው የእርስ በእርሳችን መልካም ተራክቦ ላይ ጉልበቱን ሙሉ ለሙሉ አሳርፎ ምርኮኛው አድርጎ እንዳያስገብረን በአያሌው እሰጋለሁ። የቴክኖሎጂው ግልቢያ፣ አይቀሬነትና የመልካምነቱ ትሩፋት ተዘንግቶኝ እንዳልሆነ ግን አንባቢው ይጠፋዋል ብዬ አልገምትም። ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊና ማሕበራዊ ቁርኝታችን ላልቶ ሲውተፈተፍ መመልከት እንኳንስ ለእኛ ቀርቶ “ሰለጠንን ብለው ለሰየጠኑት” የአንዳንድ ሀገራት ሕዝቦችም አልበጀም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ “ከፋም ለማም” በአብዛኛው ሕዝብ ውስጥ ያለው የፈሪሃ ፈጣሪ አቅምም ወደ ቴክኖሎጂ አምላኪነት ተለውጦ እንዳይሰገድለት ትልቅ ፍርሃት አለኝ። እውነቱን መስክር ከተባልኩም “አምላኬ ሆይ አይሁንብን!” እያልኩ እንደ እምነቴ በጸሎት እማፀናለሁ። ማሕበረሰቡ “በጎ” እያለ ሲያከብረው የኖረው መልካም እሴቱና ሥነ ምግባሮቹ ተፈጥፍጠውና ተፈትፍተው ሕዝቡ ከእምነት ሲርቅ መመልከት ለምን አያሳዝንም፤ ለምንስ አያስከፋም። ይሄው ሰበብ ሆኖ እስከ ዛሬ የኖርንባቸውና ያኖሩን፣ እንደ ድርና ማግ አወሳስበው ዘመናት ያሻገሩን ማሕበራዊ ትሩፋቶቻችን “አትንኳቸው፣ አትቅመሷቸው” በሚል ፍረጃ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ገደብ እንዳይጣልባቸውም እሠጋለሁ።
በወረርሸኙ አረማሞ የተጠቃው ኢኮኖሚያችንም ዋግ መትቶት ለማንሠራራት ዓመታት እንዳያስቆጥርና በአረንቋ ውስጥ እንዳንዘፈቅም መባነኔ አልቀረም። ፖለቲካውም ቢሆን ዛሬ እንደምናየው ጨርቁን ጥሎ በማበድ “ወደ አዲሱ ዘመን” ተሸጋግሮ ሕዝቡን ማሳበዱን እንዳይቀጥል አጥብቄ እመኛለሁ። ለፖለቲከኞቹ ግራ ገቦችም “ድንጋዩ ልባቸው ወደ ሥጋ ልብነት ተለውጦ” ማየቱ ሌላው ምኞቴ ነው።
የ“ቢሆኑ” ምኞቶቼ፤
ኮቪድ ኮርኩዶ ካዋለን የቤት ወሸባ በድል አድራጊነት ሆ! እያልን እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንወጣ መመልከት ሁላችንንም የናፈቀን ክስተት ይመስለኛል። ኢኮኖሚያችን ክፉ ጠባሳ ሳይገጥመው እንዲያንሰራራና ሀገራዊው ምርጫ በድል ተጠናቆ የፖለቲካ ትርምስምሱ ጋብ ብሎ ማስተዋል ተቀዳሚው ምኞቴ ነው። የሥልጣኑን በትረ መኮንን በብታቸው የሚይዙ የአሸናፊዎቹ ፓርቲዎች አባላት እንደተለመደው ሹመታቸው ሺህ ሞት እንዳይሆንባቸውም በጎ በጎውን እመኛለሁ። የህዳሴው ግድባችን ኃይል አመንጭቶ በሆታ ስናጨበጭብ እየታየኝ ለብቻዬ በደስታ ፈገግታ እፍለቀለቃለሁ። የልጆቻችን የትምህርት ተቋማት ተከፍተው እንደለመድነው በአዳዲስ ዩኒፎርሞችና ራዕዮች መንገዶቻችንንና አደባባዮቻችንን ሲሞሉ በዓይነ ህሊናዬ እየታየኝ ነፍሴ በውስጤ ትዘላለች። እንዲያው በደምሳሳው የፈረሰው ተጠግኖ፣ ያመፀው ልብ ተገርቶ፣ የዛገው ኑሯችን ተወልውሎ ሀገሬ አብባ ስትደምቅ እየታየኝ ለነገው “አዲስ ዘመን” ያለኝን መልካም ምኞት ብዕሬ ሳያቋርጥ ተግቶ እንዲዘምር እማጠነዋለሁ። ሰላም ይሁን!!!
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው።
በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com