ይህ ወር በተለይም ግንቦት 9/1945 ዓመተ ምህረት ተስፋፊውን የናዚ ጀርመን ጦር ድባቅ በመምታት የተባበሩት ሃይሎች የድል ብስራት ያሰሙበት ወር ነው። የማይቻል የሚመስለውን ጦርነት እንዴት በድል ተወጡት? ብለን በመጠየቅ መልስ የምናገኝበት ታሪክ ነው፤ የቀረበላችሁ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጦርነቱ እንደተጀመረ ሒትለራዊት ጀርመን ቼክን፣ ፖላንድን፣ ምሥራቅ አውሮፓን በጥቅልሉ ስትወርር ይፋ ባልወጣ መንገድ የጀርመንን የመስፋፋት ወረራ ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተመሰረተው “ሊግ ኦፍ ኔሽንስም” ሆነ ሌሎቹ ምዕራባውያን የተስማሙ እስኪመስል ድረስ፣ በቸልታ ነበረ፤ ያዩት።
በዚህን ወቅት በጥቅል ስም በስታሊን የምትመራው ሶቪየት ሕብረት፣ ከጀርመን በኩል ከምዕራብ አቅጣጫ የሚደረግባትን ማናቸውም የጦርነት ግፊትና በምሥራቅ ከጃፓን የደሴት ነጠቃ፣ በንቃት ለመመከት ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን የጀርመን ጦር የፖላንድን ድንበር ጥሶ እንዳይገባ አንድ ጊዜ በውል ሌላ ጊዜ በትናንሽ ግጭቶች ራሷን ስትመክት ማንም “አባ-ከና” ያላት አልነበረም።
እንዲያውም ኮሚኒስቶቹን ፣ በናዚዎች የማስቀጥቀጥን ስትራቴጂ በእጅ አዙር ጠላትን በጠላት የማጥፊያ እና የማዳከሚያ ዘዴም አድርገው ሳይወስዱት አልቀሩም፤ ምዕራባውያኑ አገሮች።
ይሁንናም የጦርነቱ አዋጅና ዘመቻ ምሥራቅ አውሮፓ ላይ አልቆም አለ። አለመቆም ብቻ አይደለም ከፊል አውሮፓዊና ከፊል እስያዊ የሆነችውን ከምድር አንድ አምስተኛውን የቆዳ ስፋት ያላትን ሶቪየት ሕብረትን ማንበርከክና ለአስር ትውልድ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት የመቆጣጠር አባዜ በጀርመን ናዚዎች አዕምሮ በመስረፁ ጦርነቱን፣ በመግፋት ያለማመንታት፣ ቀጠለ።
እዚህ ላይ ለማንሳት የወደድኩት ለ900 ቀናት የተደረገውን ስታሊንግራንድን የማዳን (አሁን ወደቀደመ ስሟ ፔትሮግራድ ተመልሷል) ውጊያ ለማንሳት ስለወደድኩ ነው። ፔትሮግራድን የሚከልላት ታላቁ የቮልጋ ወንዝ ክረምት ከበጋ ይፈስሳል። የሶቪየት ሕብረትም ፀረ -ጀርመን የመከላከል ውጊያውን እንደዘበት ጀምራ በጽናት ቀጥ ላበታለች።
የጦር መሣሪያ ማምረቻ የሆኑት ፋብሪካዎች ሁሉ ወደምሥራቅ አቅጣጫ ሳይቤሪያ በየጊዜው በባቡር እየተጓጓዙ ተወስደዋል። በቮልጋ ወንዝ ዳርቻ ደቡባዊና ሰሜናዊ ክፍል የነበሩት የእርሻ ማሣዎች የሚያመርቱትን አዝመራ ለመሰብሰብ የማይታሰብ ቢሆንም ሌሎች ማሣዎች ሳያቋርጡ እንዲያመርቱ እየተደረገ እያመረቱ እየተዋጉ እየተዋጉ በማም ረት ቀጥለዋል።
የሚገርመው ውጊያውን ያንን ታላቅ ወንዝ በመሻገር ማጠናቀቅ የሚቻል ቢሆንም ማንም ሙሉ በሙሉ ወንዙን ወደምዕራብም ይሁን ወደምሥራቅ አቅጣጫ በመሻገር መቆጣጠር አልቻለም። አንዳንዴ ጀርመኖች በሬዲዮ ጣቢያቸው የኮሚኒስቶችን አከርካሪ በመስበር የተቆጣጠሯቸውን ሥፍራዎች በመናገር የህዝቡን ልብ ለማውረድ ይጥሩ ነበረ። አንዱ መንገድ ደግሞ ያዝናቸው፣ “ነፃ አወጣናቸው” ብለው በሚሏቸው አካባቢ ያሉትን ሰዎች ያናገሩ በማስመሰል ቃለመጠይቅ በመሥራት በሬዲዮ ማሰራጨት ነበረ።
ሌላ ጊዜም እንደሚታወቀው ሶቪየት ሕብረት ከተለያዩ ህዝቦች የተሰራች ናትና፤ የጀርመን የፕሮፓጋንዳ ማሽኖች ሁሉ የሩሲያውያንን ጭካኔ፣ ትምክህትና የሌሎችን ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ ወግና ልማድ እየደፈጠጡ፣ የሚኖሩ እነዚህ ህዝቦችም በምን ዓይነት ስቃይ ላይ እንዳሉ የሚያመላክቱ ነበረ። የሚገርመው ጀርመኖቹ ነበሩ፣ ስቃያቸውን “የሚያውቁላቸው”። ዘረኞች ሁልጊዜ ይሉኝታ ቢሶች መሆናቸውን የሚያሳብቀው ይኸው “ተቆረቆርንልህ” –“ተሰቃየህ እኮ”፣ የሚሉትን ህዝብ ከጫማቸው ሥር ለማድረግ ሌላውን አውሬ አድርገው በመሳል ቁጭት የሚፈጥሩበት ስልት መመሳሰሉ ነው። ግቡ ግልጽ ነው፤ ከፋፍሎ ማዳከምና መግዛት!!-
አንዳንዱ ሙሾ የሚቀርበው አሳዛኝ የዩክሬን ዜማዎችን በማንቆርቆር፣ የጂዎርጂያና የኮዛኮችን፣ የአርመንና የቱርክሜኖችን የአርሷደር ዜማዎችን በማስደመጥና እነዚህን ዜማና ግጥሞች በሩሲያ ማሰማት የሚያስገድል ወንጀል እንደሆነ በመስበክና የታጂኮችንንና የኮዛኮችን የእስልምና እምነት እንዴት ሩሲያውያን በማዋረድ ኦርቶዶክስ በማድረግ እንደቀለዱባቸው በማውሳት፣ አሁን የምንዋጋው እናንተን ከሩሲያውን የጭካኔና የዘር ማጥፋት እልቂት ለማትረፍ ነው- ነው፤ የሚሉት። እያንዳንዱ ህዝብ የራሱ የነበረውን ስልጣኔ መልሶ በመቆጣጠር ሩሲያውያንን ተባብረን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለብን፤ በማለት ቀስቅሰው፣ ለጥቀው ግን፣ አሁን እየገሰገሰ የመጣው የጀርመን ጦር የሩሲያውንን ጥጋብ በማብረድ ነፃነታችሁን ያጎናጽፋችኋልና፣ ያለማወላወል ከእኛ ጋር በመቆም ለነፃነታችሁ ተሰለፉ ነበረ፤ የሚሉት። ነገሩ አስቂኝ ነው፤ እኛ-እኛ ስንገዛችሁ “አገዛዛችን ስልጡንና ቅዱስ” ነው፤ ሌላው ሲመራችሁ ግን ርኩስና ኋላ-ቀር ስለሆነ ልትጠፉ ነው፤ ማለት የአምባገነኖች ሁሉ ዘመን ያለፈበት ብልጠት መሆኑ ነው።
ይሁንናም ጆሴፍ ስታሊን ከዚህ በተለየ መንገድ፤ ለሶቪየት ሕዝብ የተናገረው፣ የወረሩን ቼኮዝሎቫኪያንና ፖላንድን የወረሩት፣ ዩጎዝላቪያንና ግሪክን መረማመጃ ያደረጉት፣ ቡልጋሪያንና ሃንጋሪን ያስገበሩት፣ ኦስትሪያን በመጠቅለል አንድ የጀርመን ክፍለሀገር በማድረግ የጨፈለቁት ተስፋፊ ናዚዎች እንጂ ሌሎች አይደሉም፤ ሲል ነበረ የሚገልጠው። እውነቱ እርሱ ነበራ!
“እኛ ዓለማቀፋዊ ጭቆናን የምንቃወም፣ ለሰው ልጆች እኩልነት የቆምን ሶሻሊስቶች እንጂ እነርሱ እንደሚሉት ዓይነት ወራሪዎች አይደለንም። እንደምታውቁት በዚህ መርህ መሠረት የሶቪየት ሪፐብሊክ መሪና የፓርቲው ፀሐፊ የሆንኩት ሰው እንኳን፣ በትውልድ ጆርጂያዊ መሆኔን ታውቃላችሁና ይህንን የናዚዎች ሙሾ በመስማት እንዳትታለሉ። የሚጠብቀንን ፈተና በጋራ ካልተቋቋምን የማናመልጠው መከራ የሚጠብቀን ከመሆኑ ሌላ ከተለያየን ግን፣ የናዚዎች ቁርስ ለመሆን የተዘጋጀን ትኩስ ድንቾች ነን። እኔ ለሀገሬ እየተዋጋሁ ለመውደቅ በመካከላችሁ የምገኘው ጓዳችሁ ጆሴፍ ስታሊን ነኝ፤ ቅድም ጠዋት በሰሜን ቮልጋ ዳርቻ በሚገኘው የአዛዦች ምሽግ ውስጥ ነበርኩኝ፤ የሠራዊታችንን የውጊያ ሞራል ብታዩት እየተዋጋን ያለነው ጠላት በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያለ መሆኑን ለመረዳት አያቅታችሁም። ይልቅ ትኩስም ባይሆን ዳቦ ለሠራዊቱ ስለሚያስፈልግ ኩስኩስት እየሠራችሁ አቅርቡልንና እንላክላቸው፤” ሲል ነበረ የሚቀሰቅሰው።
አደገኛ በሆኑ የጦርነቱ ሰዓቶች ሁሉ ሀገራችሁን ነቅታችሁ እየጠበቃችሁ ነው? ፔትሮግራድ እየተዋጋች ነው፤ ናዚዎች ምነው ሶቪየቶችን ባልሞከርናቸው እያሉ ነው። ማቆሚያችን በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ነው፤ ነበረ የሚለው።
ግን እውነተኛው ነገር በጣም ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክት ሠራዊት እየገበረችና ህልውናዋን ለማስከበር ሀገሪቱ እየተዋጋች ነበረ። 900 ቀንና ሌሊቶች መዋጋት ቀላል አልነበረም፤ ጥይቱ ይጎድላል፤ ቀለቡ ይጠፋል፤ ታክቲኮች ይሰለላሉ፤ ይጠለፋሉ፤ የጎደለውን ለመሙላት የሚደረገው የማምጫ መንገድ ውጊያና መስዋዕትነት ይጠይቅ ነበረ።
የሰው ሃይል መተካት ቀላል አልነበረም፤ ሰው እንደቅጠል እየረገፈ ጦርነቱ ይቀጥል ነበረ። ገላጋይ አልነበረም፤ የነበረው (League of Nations) ፣ የመንግሥታቱ ማህበር የናዚዎችና ፋሺስቶች ፈቃድ ማስፈፀሚያ ጦር ማወጃ ጥሩምባ ከሆነ ከራረመ። እጅጉን አቅመቢስ ከመሆኑ የተነሳ ናዚ፣ ቼኮዝሎቫኪያን ሲወርር እነብሪታኒያና ፈረንሳይ፣ ናዚ ጀርመን ያንን ጎርሶ ያቆማል፣ ብለው ይጠብቁ ነበረ፤ ፖላንድን ሲወርር፣ ሩሲያን አይደፍርም ነበረ፤ የሚሉት። ግን ከግምታቸው ውጭ ሆነና አረፈው።
ሩሲያን በማያባራ ሁኔታ በምድር፣ በሜካናዝድ ጦር፣ በሰማይ ቦንብ በማዝነብ የታወቁትን አውሮፕላኖቹን ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ የሆኑ የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም እያርከፈከፈ ሲወርር፣ ድርጅቱ አቅመቢስ ነበረ፤ የሆነው። የሩሲያን ህዝብ ቅስም ለመስበር ያልተጠቀመው አጥፊ መሣሪያ፣ ያልቀሰቀሰበት መርዛማ ፕሮፓጋንዳ፣ ያልተጠቀመው የውጊያ ስልት አልነበረም። በፖላንድ ዳርቻ የነበሩትን የሩሲያን ግዛት መፈተሻ ግጭት ሲቀሰቅስ የገባው ከፖላንድ “ሶቢቦር”ና ሌሎች የማረሚያ (ማሰቃያ ቢሉት ይመረጣል) ካምፕ ሸሽተው ያመለጡ አይሁዶች ሩሲያ ገብተዋል፤ ካለ በኋላ ለማረጋገጥ በዚህ አካባቢ ያሉትን አይሁዶች ካልሰጣችሁኝ አልወጣም ፤ ሲል ነው ፤ የሞገታቸው።
የሚገርመው ስታሊንም በዚያ የሚያቆሙ ስለመሰለው፣ አይሁዶቹን አሳልፋችሁ ስጧቸው ብሎ ነበረ። የሚገርመው ናዚዎቹ የሩሲያ ተወላጅ አይሁዶቹን ጭምር አሳልፈው ሰጥተዋቸው ለቅቀው ከመውጣት ይልቅ የያዙትን ግዛት ይዘው ነበረ፤ የቀሩት።
ቀድሞውኑ ሰበብ እንጂ እውነተኛ ምክንያት ስላልነበራቸው ነው፤ ችክ ያሉት። የፔትሮግራዱ ውጊያ የመጣው ከዚህ በኋላ ዓመት ቆይቶ ነው። ናዚዎች ሁሉንም ወይም ምንም ብለው የሚያምኑ ወራሪዎች እንጂ በተጠየቅ የሚያምኑ አልነበሩም። እንዲያውም መርሃቸው “ስንዝር ለመልቀቅ የተስማማን ወገን ክንድ አስለቅቀህ ትከሻውን ተለካካው” ነው። ስለዚህ አምላክም ከአሸናፊዎችና ጠንካሮች ጋር እንጂ፤ ከቀሰስተኛና “ከእሺ ባዮች” ጋር አይደለም፤ ብለው የሚቀሰቅሱና የሚተገብሩ ነበሩ።
ተዋጊዎቹንም ጀርመናውያን፤ የምታደርጉትን ሁሉ የምታደርጉት ከምንም በላይ ለምርጡ መለኮታዊ ዘር ታላቅነት ስለሆነ ከእያንዳንዱ ሃይለኛ እርምጃችሁ በኋላ የመታሰቢያ ፎቶ በማስቀረት ትውልዱ በጀግንነት እንዲያስባችሁ አድርጉ፤ ነው ያላቸው። የሰው ሀገር የሚወርሩት ለጀርመን ታላቅነት፣ የሚገድሉት ለጀርመን ታላቅነት፣ የሚያፈስሱት ደም ሁሉ የጀርመንን ታላቅነት የመገንቢያ ሲሚንቶ ማቡኪያ ውሃ ተደርጎ ነበረ፤ የሚቀሰቀሰው። የሚገርመው በየትውልዱ እንደነዚህ ያሉ ቅስቀሳዎችን ተቀብለው በሰው ዘር ላይ የጭካኔ እጃቸውን ለመሰንዘር የማያመነቱ አጋሰሶች መገኘታቸው ነው።
ገድለው የሚስቁ፤ አቃጥለው የሚጨፍሩ፣ ገርፈው ነጠላ አጣፍተው ትክሻቸውን የሚነቀንቁ፣ የሲኦል ክፋቶችን ሁሉ በምድር ፈጽመውና የወንድማቸውን አካል በዕሳት ጠብሰው ተነስተው፣ “እስቲ አንድ ትኩስ የጥብስ ወጥ”፣ ብለው የሚያዝዙ ሰው ጤፉዎች መኖራቸው ይገርማል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፣ ወንድሞቹም ዮሴፍን ደብድበው ከጣሉበት ጉድጓድ አውጥተው ወደግብጽ ለሚሄዱ ባሪያ ፈንጋዮች ከሸጡት በኋላ ምግባቸውን አቅርበው መብላት ጀመሩ፤ ነው፤ የሚለው።
“ዮሴፍን ሸጡና ብሩን ወሰዱና፤
ማዕድ ተቀምጠው ስንቁን በላሉና።
አውሬ በላው ብለው ለአባቱ በመንገር፣
በልተው ተላቀሱ አወይ የሰው ነገር!!” የተባለው ለዚያ ሳይሆን አልቀረም።
ወደቀደመ ነገሬ ልመልሳችሁና ናዚ ጀርመን ለ900 ቀናት ውጊያውን እያጧጧፈች በኖርዌይ፣ በፈረንሳይ፣ በብሪታኒያ ዓውደ- ግንባር የጀመረቻቸው ውጊያዎች ግን ሽንፈት በሽንፈት እየሆኑና ሒትለርም በውስጥ ልዩነት ሳቢያም የመፈንቅለ- መንግሥት አደጋም ደጋግሞ እያንዣበበት ልቡን ለሁለት የሚከፍል ነገር ይገጥመው ገባ።
ለሶቪየቶችም የመስዋዕትነታቸውም ተጋድሎ በማዶው ውጥንቅጥ እየታጀበ፣ ዕድልና ድልም በራቸውን እያንኳኳ፣ መተንፈሻ ያገኙ ገቡ። በ900ዎቹ ቀናት መጨረሻ የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎች ሲከናወኑ ድል አድራጊዎች ይመስሉ የነበሩት የጀርመን ወታደሮች ከዋናው ጦር ጋር ያደርጉት የነበረው የሬዲዮ ግንኙነት እየከሰመና የውጊያው እዝ እየተቆራረጠ እዚህም እዚያም ወታደሮቹ፣ ለገበሬ ጦር እጅ መስጠት አበዙ። ሽንፈት እና ችጋር ሰተት ብላ ወደ ሰው፤ የምትገባውአዋጅ ሳትናገር ነው። ድል ግን ጥሩምባ ማብዛቱ የታወቀ ነው። በባይተዋርነት፣ መንገድ ያደከማቸውና አድራሻ የጠፋባቸው፣ የተራቡና ጉስቁል ያሉ የጀርመን ወታደሮች በየጥሻው መሣሪያቸውን እየጣሉ ወደመንደሩ በመግባት ለማኞች ሆኑ።
አንድ ትንሽ ልጅ እናቱን እማዬ አንድ ወታደር ቆሞ የሚበላ ነገር በምልክት እየለመነ ነው፤ ይላታል። እናት ብቅ ብላ ታይና የጀርመን ወታደር ነው፤ ና-ና ፣ “ዳቦ በጨው”፣ ውሰድልት ስትል፤ ከ900 ቀናት በላይ፣ በኖረው ፀረ ጀርመን ጥላቻ የተሞላው ልጅ፣ በቁጣ ወደእናቱ ዞሮ፣ “እማዬ እንዴት ለጠላት ዳቦ ስጥ ትይኛለሽ? እገድለዋለሁ፣” ብሎ ከአርጩሜ ከፍ ባሉ፣ ቀጫጭን እጆቹ መምቻ ነገር ሲፈላልግ፣ እናቱ መለስ ብላ፣ ማሙሽ እንኳን እነርሱ ለልመና መጡ፤ አለችው።
አየህ፣ ልጄ ይሔ ማለት እኮ የአባትህ ሞት እኮ ባክኖ አልቀረም፤ ማለት ነው። እነዚህ ለማኝ ወታደሮች፣ አንድም የጦርነቱ ማብቂያ እውነተኛ ምስክሮች ናቸው፤ ጎርፉ እያለፈ ነው፤ ማለት ነው፤ ሁለትም እኛ ሰጭዎች እንጂ ተቀባይ ለማኞች አይደለንምና ደስ ይበልህ እንጂ አይክፋህ ነው፤ ያለችው።
የፔትሮግራድና አካባቢው፣ ነዋሪዎች መንግሥት የድል አዋጁን እስኪያውጅ አልጠበቁም፣ በየስፍራው በሚያዩት ነገር የተጽናናው ህዝብ በየሰፈሩ የሚያዘጋጀውን አነስተኛ ድግስ በመካፈል ደስታውን ገለፀ።
ጆሴፍ ስታሊንም ከያልታው ጉባኤ ማግስት፣ ከአሜሪካው ሩዝቬልትና ከቸርችል ጋር ስብሰባ ካደረገ በኋላ ጥቂት ቆይቶ፣ ወደሞስኮ ሬዲዮ በመምጣት፣ የናዚ ጀርመን ጦር ተሸነፈ አልላችሁም፤ “እምጥ ይግባ ስምጥ” አላወቅንም፤ በሶቪየት ሕብረት “ቀይ ሠራዊት” ፊት መቆም ከቶ አልቻለምና የተነነ ይመስለኛል። የተራረፈ ጦር መንገድ ላይ ተዝረክርኮ ካገኛችሁ፤ በምርኮ ሰጥቻችኋለሁ፤ በእንክብካቤ ይዛችሁ በማረፊያ አስቀምጧቸው”፣ ብሎ ትእዛዝ ሰጠና ድላችን ግን የሚጠናቀቀው፣ አፍንጫችን ሥር መጥተው ሞስኮ ላይ ለመትከል አስበውት የነበረውን የእነርሱን ባንዲራ አውርደን፣ በርሊን ላይ ባንዲራችንን ስንተክል ነው፤ ብሎ ፎከረ። የሶቪየት ጦር ገሰገሰ፤ በማይቻል ጊዜ የሚቻል አንዳንድ ነገር አለ።
አሁን ሀገራችን የገባችበት አጣብቂኝ ቀላል አይደለም። የምርጫው ጊዜ መራዘም ጥያቄዎች፣ ምርጫ ለብቻዬ አድርጌ ፣ “አዲስ አጠርና ቀጠን ያለች ሪፐብሊክ ወልጄ ካላደርኩኝ ሌሊቱ አይነጋልኝም” የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል ፤ የውጭ ጦር ጋባዥ የሆኑ ክፉዎች ሴራ በሌላ በኩል፣ ኮሮናውና የቁጥሩ ማሻቀብ ስጋት ሃያልነትና ውስብሳቤው ነገር፣ የኢኮኖሚው መጋሸብ፣ ክፉዎቹ ሰዎች ደግሞ በየስፍራው በከፈቱት ስም የለሽ ባለቁጥር ቻናሎች አማካይነት፣ ክፉ ክፉ ወሬ የሚያናፍሱበት ጥልፍልፍ ያለ ጊዜ ላይ ነን። እነዚህ ትርክምክም ችግሮች፣ ውላችንን እንዳያጠፉብንና የክፋት አዝማቾች ፍላጎት ማስፈፀሚያ እንዳንሆን ፣ ብልሃት የተሞላው እርምጃ ያስፈልገናል።
ላያስችል እንዳልሰጠንና አስቸጋሪው ነገራችንን መልሰን በማስቸገር፣ በሰው የመጣው ይህንን የነገር ክፉ፣ በራሱ በሰው አማካይነት ለማምከንና ወደተሻለ ደረጃ ሀገሪቱን ለማምጣት ጨከን ተብሎና ጥበብ በተሞላው መንገድ መሰራት አለበት።
አሁን አጣዳፊውና የሚያስቸግረን ነገር ኮሮና ነው፤ ኮሮናን እና የኮሮናን ውስብስብ መዘዞች፣ በጋራ ግን ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ በስልት ለማቃለል መሥራት ቀጠሮ የማያሰጥ ነገር ነው። አዕምሯችንን ከልባችን ጋር በማቀናጀት መሥራት ለህመሙ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ አቅመ-ደካማ የሆኑ ወገኖቻችንን ትኩስ ድንችም ሆነ ትኩስ ቂጣ በማቅረብ ማዕዳችንን ማጋራት የወቅቱ ምርጥ ወገናዊነት ነው።
አንዳንዶቻችን ከዳቦው የሚቀድም ረሃብ፣ ከጤናው የሚቀድም በሽታ ፣ ከመረጋጋቱ የሚበልጥ ሽብር ሰንቃችሁልን በሚገርም ሁኔታ የምትመክሩን አላችሁ። በእውነቱ በትናንትናው ሌሊት ምን አይታችሁ እንዳደራችሁ የምታውቁ እናንተ ብትሆኑም ፣ አሁን እኛ ህዝቦች የምንፈልገው ሃያላን ያልገቱት፣ አቅመኞች በሀብታቸውም በእውቀታቸውም ፣ በሙያ ብቃታቸውም መቋቋም ያልቻሉት አደጋ ከፊታችን ተደቅኗልና ሁሉ ነገራችንን ወደዚያው ማዞር ስለምንፈልግ፣ እባካችሁ ብትችሉ አፋችሁንም ፊታችሁንም ወደዚህ አዙሩልንና በጋራ እንቁም። (መቼም ክፉዎች፣ በጋራ መቆም፣ አንድነት፣ ሕብረት የሚባሉ ተቋማዊነቶች ያንገሸግሻችኋል) ካልቻላችሁ ዝም በሉ፤ አታሰናክሉን፤ በዚህ የጤና ውጊያ ላይ ሆነን የእናንተን አምሮት ማሟላት አይሆንልንም።
ሃምሳ ዓመት ሙሉ እኮ በማይደማመጥና “በእኔ ብቻ ልክ ነኝ”፣ ፖለቲካ ፣ ሁለት ሙሉ ትውልድ እኮ ሾቀ። እንዴ፣ “አቦ ተውና፣ ሣ!” አለ፤ የሐረር ሰው። ተውን እስቲ፤ ባታዝኑልን አትፎክሩብን። እኛ የምንለውን ብቻ ስሙ፣ አትበሉን። ሰማናችሁ፣ እኮ፤ ብታወሩ ሸር፣ ብትሰነዝሩ ጦር…ብቻ !!
አንዳንዴ የማይቻለውን የሚያስችል መከራንና በሽታን የሚያቆም ትከሻ አለን ፤ እኛ አእላፍ ህዝቦች፣ ነንና። ይህንን ቀን አልፈን እንዳንተዛዘብ እርስ በእርሳችን እንተጋገዝ፤ ከፋፋዮች እና “የጥንታዊ ቁስል አካኪዎች” የሚነግሩንን እየሰማንና እርሱን እሽሩሩ እያልን፣ ዓይኖቻችንን ከወሳኙ የኮሮና ጦርነት ላይ አንንቀል። ኮሮናን እና የበረሐ አንበጣን በብልሃትና በሥርዓት እየተቋቋምን፣ እንቅፋቶችን ገለል እያደረግን ወደፊት እንጓዝ ትውልድንም እናትርፍ። ከሩሲያውያን ጽኑነትንና ዓላማ ተኮር ብቃትን እንማር!!
(ቀስተ-ደመና መጽሔት 1977፣ ፕራቭዳ አሳታሚዎች፤ የ2ኛው ዓለም ጦርነት ምሥራቅ ግንባር ታሪኮች፤ የማርሻል ዡኮቭ ፣ የግል ማስታወሻዎች ቅንጭብ 1960) ትውስታዎች ተጠቅሚያለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ