እድሜ ዘመናቸውን ለፍትህና ዲሞክራሲ መስፈን ከታገሉ ፖለቲከኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ስማቸው ይጠቀሳል። በተለይም ባለፈው 27 ዓመታት የገዢውን ፓርቲ አሰራር በመቃወምና ፊት ለፊት በመታገል ብዙ ዋጋ መክፈላቸው በብዙዎች ዘንድ አንቱታን አትርፎላቸዋል። በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የካቲት 12 ሆስፒታል የተወለዱት እኚሁ አንጋፋ ፖለቲከኛ ታዲያ በመምህራን ወላጆቻቸው ምክንያት የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከአዲስ አበባ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደብረሲና እና ደብረብርሃን ከተማ በመዘዋወር ነው። ለቤተሰቦቻቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደተወለዱባት አዲስ አበባ ከተማ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተመለሱ።
ወሰን ሰገድ፣ ልዑል መኮንን፣ ትንሳኤ ብርሃን፣ አስፋ ወሰንና ተፈሪ መኮንን አንደኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ሳይንስ ትምህርት ቤት ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ገብተው ለሁለት አመታት ከተማሩ በኋላ እድገት በህብረት ዘምተዋል። ከዘመቻው ተመልሰው ትምህርታቸውን ቢቀጥሉም በአገሪቱ ተቀጣጥሎ የነበረው አብዮት እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። ኢህአፓ ያደርግው የነበረውን ትግልም ትግራይ በርሃ ላይ ተቀላቀሉ። ይሁንና ብዙም ሳይቆዩ በልጅነት ህልማቸው ለህዝብ ነፃ መውጣትና ለአገር ብልፅግና ተስፋ የጣሉበት ድርጅት ከድል ይልቅ ወደ ሽንፈት፤ ከስኬት ይልቅ ወደ ክስረት አመራ። እናም ወታደራዊውን አገዛዝ ሽሽት ወደ ሱዳን ብሎም ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ። በእንግሊዝም የፍልስፍና ትምህርት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ከአመታት በኋላ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የደርግን ሰራዊት አሸንፎ የአገሪቱን በትረ መንግስት ሲረከብ አገሬን መደገፍ አለብኝ በሚል ወደተወለዱባት ምድር ተመለሱ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ። የአዲሱ መንግስት ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋልና የምዝበራ አካሄድ አልመች ይላቸውና በወቅቱ ለነበሩት ባለስልጣን በግልፅ የህዝብና የሃገርን ሃብት ምዝበራው አልተባበርም በማለት ስራቸውን ለቀቁ፤ ወደመጡባት አገር እንግሊዝ ተመለሱ። ከፖለቲካ ታሳትፎ ለረዥም አመታት ራሳቸውን አግልለው ተቀምጠው ቆዩ። በ1997ዓ.ም ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በዚህች አገር እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን በይፋ መናገራቸውን ተከትሎ ብሎም የቅርብ ጓደኛቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ«አግዘን» ጥሪ ዳግም በፖለቲካው መስክ የበኩላቸውን ለማድረግ ወደ እናት አገራቸው እንዲመለሱ አደረጋቸው። ተስፋ ለተጣለበት ቅንጅት ፓርቲ በሁለት እግር መቆም ከልባቸው ሰሩ።
ምርጫው ተካሂዶ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ግን ገዢው መንግስት የገባውን ቃል አፍርሶ ተቃዋሚዎቹንና ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ ጠራርጎ አሰረ። በዜግነት እንግሊዛዊ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑት የዛሬው እንግዳችንም ምንም እንኳን በምርጫው ባይወዳደሩም ደግፈሃል በሚል ለእስር ተዳረጉ። ከአንድ ወር በኋላ የእንግሊዝና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና እና ብርቱ ድርድር ተፈቱና ወደ መጡበት አገር ተመለሱ፡ ይሁንና አብዛኞቹ የትግል አጋሮቻቸው በእስር እየማቀቁ እጃቸውን አጣጥፈው መቀመጥ ስላልቻሉ በመላው አለም ያሉ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ በማስተባበር ፓርቲው ከቀድመው ይልቅ ተጠናክሮ እንዲወጣ ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። ባልደረቦቻቸው ከወህኒ ሲፈቱም በአቅምም ሆነ በአደረጃጀት የተሻለ ድርጅት እንዲሆን በማድረግ አስረከቡ።
የኢህአዴግን መንግስት በትጥቅ ትግል ለመጣል ጥረት በማድረግ ላይ ሳሉም የመን ላይ ተይዘው ዳግም ወህኒ ገቡ። ከአራት አመታት አስከፊ የእስር ቆይታ በኋላ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለመፈታት ቻሉ። አዲስ ዘመን የሁለት ወንድና ሴት ልጆች አባት ከሆኑት ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ቆይታ አድርጓል። በግል ህይወታቸውና በፖለቲካ ዙሪያ ያጫወቱንን በሁለት ክፍል ሰንደነዋል፤ የመጀመሪያውን ክፍል እነሆ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- ውይይታችን የልጅነት ጊዜዎት ምን ይመስል እንደነበር በማንሳት እንጀምር? እግረመንገዶትንም ቤተሰቦችዎ ‘አንዳርጋቸው’ የሚለውን ስያሜ የሰጡበት የተለየ ምክንያት ካለም ቢነግሩን?
አቶ አንዳርጋቸው፡- እኔ የተወለድኩት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ኃይለስላሴ አሁን ደግሞ የካቲት 12ሆስፒታል ሰኞ ከቀኑ 7፡00 ላይ ነው። ከሁለት አስተማሪ ወላጆች የተገኘሁ እንደመሆኔ የተወለድኩበትን ቀን ብቻ ሳይሆን ሰዓቱንና ያዋለደኝንም ፈረጅ ዶክተር ስም ሳይቀር ፅፈው ነው ያስቀመጡት። እንዳልሽው የስሜ አወጣጥ የተለየ ምክንያት ነበረው። ከቤተሰቦቼ እንደሰማሁት አባቴ ሁለት ወንድሞቹ በጣሊያን በመገደላቸው ምክንያት የወንድሞቹ ማስታወሻ የሚሆን የመጀመሪያ ወንድ ልጅ እንዲኖረው ሲመኝ ነው የኖረው። ይሁንና እናቴን እንዳገባ የመጀመሪያ ልጃቸው ሴት በመሆንዋ በወላጆቼ መካከል ቅሬታ ይፈጠራል። ለሁለተኛ ጊዜ ሲወልዱ ግን እኔ በመወለዴ የአባቴ እናት የነበረው ቅሬታ ተፈቶ አንድ ያድርጋቸው በሚል አንዳርጋቸው የሚል ስያሜ ሊሰጡኝ ቻሉ።
የመጀመሪያ ወንድ ልጅ በመሆኔ ምክንያት እናቴ ከወንድሞቼና ከእህቶቼ በተለየ መንገድ በእንክብካቤ ነው ያሳደገችኝ። እናቴ ለእኔ የተለየ ፍቅር ስለነበራት አይን ያወጣ አድሎ ታደርግ እንደነበርም አስታውሳለሁ። እኔም ብሆን ከአባቴ ይልቅ እናቴን እቀርብ ስለነበር የምፈልገውን ሁሉ የምጠይቀው እናቴን ነው። ከውጭ ስትመጣ ተቀብዬ እግርሽን ካላጠብኩሽ፤ ቡና ካላፈላሁልሽ እላታለሁ። ታማ ሆስፒታል ስትገባም ውዬ የማድረው እኔ ነበርኩ።
የሚገርምሽ እናቴ ለእኔ በምታደርገው ማሞላቀቅና ቀረቤታ ምክንያት ብዙ ሰዎች ከእናቱ ተለይቶ መኖር አይችልም ብለው ይሰጉ ነበር። በተለይም በደርግ ጊዜ ወጣቶች አፈሳ ሲመጣ ጎረቤቶቻችን ሳይቀሩ «ይሄ ልጅ አንድ ነገር ቢሆን እናትየው ምን ይሆናሉ?» በሚል ስጋት ውስጥ ገብተው ነበር። በመጽሐፌ ላይ እንዳስቀመጥኩት እናቴ ለእኔ ከነበራት የተለየ ፍቅር የተነሳ ወደ ሱዳን በምሰደድበት ጊዜ ቁልቢ ገብርኤል ድረስ በመሄድ ራቁቷን በመሆን ፈጣሪ እኔን እንዲጠብቅላት ተስላለች። እናም ከልጅነቴ ትውስታዎች ሁሉ በእናቴና በእኔ መካከል የነበረው የተለየ መቀራረብና ፍቅር የሚዘነጋኝ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአፓን የተቀላቀሉበትና የተሰደዱበት አጋጣሚ ምን እንደነበር ያስታውሱን?
አቶ አንዳርጋቸው፡- የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀኩኝ በቀጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ለአንድ አመት ፊዚካል ሳይንስ ከተማርኩኝ በኋላ ወደ ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ገብቼ መማር እንደጀመርኩ እድገት በህብረት ዘመቻ ላይ እንድሳተፍ ተደረኩኝ። ከዘመቻው እንደተመለስኩ ትምህርቴን ብቀጥልም አብዮቱ እየተፋፋመ በመምጣቱ ትምህርቴን ለማቋረጥ ተገደድኩ። ቀይሽብሩ ሰማይ በደረሰበት በ1970 ዓ.ም ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስቼ ወደ አስመራ በአውሮፕላን ሄድኩኝ ፤ ከአስመራ ወደ ትግራይ በርሃ በመሄድ የኢህአፓን ሰራዊት ተቀላቀልኩ። አንድ አመት ከቆየሁ በኋላ ግን የማይመች ሁኔታ በመፈጠሩ ወደ ሱዳን ተሰደድኩኝ። እንደ እድል ሆኖ ሁለት እህቶቼ በእንግሊዝ አገር ይኖሩ ነበርና በእነሱ ድጋፍና በእንግሊዝ መንግስት ትብብር ከሱዳን ወደ እንግሊዝ ገባሁኝ። ትግሉን ስቀላቀል ህዝቡን የዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ተጠቃሚ ለማድረግ አስቀድሞ ነፃ መውጣት ይገባዋል የሚል አላማ ሰንቄ ነበር።
ፓርቲውም ሆነ አባላቱ የሄዱበት የፖለቲካ መስመር በአግባቡ የተጠና እና የታሰበበት ባለመሆኑ ትግሉ ከስኬት አልደረሰም። በርካታ ወጣቶች የት እንኳ እንደተቀበሩ እንኳ የማይታወቅበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጠረ። በዚህ ምክንያት አብዛኞቻችን ተሰደድን።
አዲስ ዘመን፡- እንግሊዝ አገር እንደሄዱ ባቋረጡት የኢንጅነሪንግ ዘርፍ ለመቀጠል ያልቻሉበት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ምንም እንኳን እንደ እድል ሆኖ እኔ ከዚያ ስቃይ አምልጬ እንግሊዝ አገር ብገባም ያን ሁሉ ሰው በጅምላ በደርግ ካጣን በኋላ ኑሮን መቀጠል ከባድ ሆነብኝ። በደረሰብን ጉዳት ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገባሁኝ። እህቶቼ በሚኖሩበት 19ኛ ፎቅ ቤት ውስጥ ቀኑን ሙሉ ብቻዬን እቀመጥ ስለነበረም የህይወትን ትርጓሜ ምንነት ማብሰልሰል ጀመርኩኝ። አንዳንድ ጊዜም ለጥያቄዎቼ ምላሽ ሳጣ ራሴን ከ19ኛ ፎቅ ወርውሬ እራስን ማጥፋት እመኝ ነበር። በዚህም ወቅት መሰረታዊ የሆኑና ከህይወት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መፈተሽ ያዝኩኝ። እንዳልሽው የኢንጅነሪንግ ተማሪ ብሆንም የህይወትን ትርጓሜ ለማግኘት ስል የፍልስፍና ትምህርት ቤት ገባሁኝ።
ለገጠመኝ የስነልቦና ቀውስ መፍትሄ ይሆናል ብዬ የገባሁበት የፍልስፍና ትምህርት ግን ዲግሪዬን ስጨርስ ምላሽ ሊሰጠኝ አልቻለም። ለጥያቄዎቼ መልስ ይሰጠኛል ብዬ የተማርኩት ትምህርት ጭራሽኑ ከነበሩኝ በተጨማሪ መልስ የማይገኝላቸው ጥያቄዎችን ይዤ እንድወጣ አድርጎኝ ነው ትምህርቴን የጨረስኩት። ስመረቅ አስተማሪዬን ለጥያቄዎቼ መልስ ከማግኘት ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄ ይዤ ነው የጨረስኩት ስላት «እኛም በአግባቡ ማስተማራችንን የምናረጋግጠው በዚህ ነው» በማለት ነው የመለሰችልኝ። ፍልስፍና መልስ አይሰጥም፤ እንደሌሎች የትምህርትአይነቶች ለጥያቄዎቻችን መልስ ቢሰጥ ኖሮ ትምህርቱም እስካሁን አይቀጥልም ነበር።
ትምህርቴን በከፍተኛ ውጤት ጨረስኩኝ፤ ያ ውጤት በቀጥታ የዶክትሬት ትምህርት ለመማር የሚያስችለኝ ቢሆንም ከውስጤ የነበረው ቀውስ ቀጣይ ትምህርት እንዳልማር አደረገኝ። ደግሞስ «ዶክተር አንዳርጋቸው» የሚል ቅጥያ ካልፈለኩኝ በስተቀር በርካታ መጽሐፍን ባነብ በዶክትሬት ከሚገኘው በላይ እውቀት አገኛለሁ ብዬ ደመደምኩኝ። እውነት ለመናገር ፈተና ለማለፍና አስተማሪዎችሽ ጥሩ ውጤት እንዲሰጡሽ ብለሽ ከምትማሪ በራስሽ መንገድ እውቀትን ለማግኘት የምትሄጅበት መንገድ ነው ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግሽ። እርግጥ ነው፤ በእኛ አገር እውቅት ተገኘም፤ አልተገኘም ከስም ፊት ዶክተር የሚለውን ማዕረግ መለጠፍ ትልቅ ነገር ነው። ለነገሩ ገዝተውም የሚይዙት አሉ። እኔ የፍልስፍና ተማሪ ስለሆንኩም ለምንድን ነው ዶክትሬት ዲግሪ የሚያስፈልግኝ? ብዬ ራሴን ጠየኩኝ። ፍልስፍና ትምህርትን በአግባቡ የምትማሪው ከሆነ የሚሰጥሽ ጉልበት አለ።
ለእኔ ደግሞ ፍልስፍና ከአጠቃላይ ህልውናዬ ጋር የተሳሰረ ነው። ከትምህርቱ ሁሉ ደግሞ የሰው ልጅ ነፃነት ጋር ተያይዞ ያገኘሁት እውቅት የበለጠ ከነፃነት ጋር በማይለያይ መልኩ እንድቆራኝ አድርጎኛል። ያም ነው በትግል እንድቀጥል ፅናት የሆነኝ። ነፃነት ስልሽ ግን የመናገርና የመፃፍ ብቻ አይደለም። ፍልስፍና ነፃነት ሰው በመሆንሽ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ሰው ያደረገሽ ነፃነትሽ መሆኑን ነው የሚያስተምርሽ። ነፃነት የሚባለው ነገር እኛ ጭንቅላት ውስጥ ትርጉም ባይኖረው ኖሮ በእኛ እና በእንስሳት መካከል እንኳ ያለውን ልዩነት መገንዘብ አንችልም ነበር። ያ ነፃነት ከማንነታችን ጋር የተሳሰረ ነው። ብዙ ጊዜ ነፃነት እስከሞት ድረስ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሰዎች ነፃነትን እንደሸሹ ነው የሚኖሩት። የፖለቲካ ተሳትፎዬም በተጋነነ መልኩ የሚገለፅበት ምክንያት ያለነፃነት የውሸት ህይወት መኖር ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎች በሚመኙት የእንግሊዝ የተደላደለና ሰላማዊ ኑሮ መኖር እየቻሉ ዋጋ ወደሚያስከፍለው ፖለቲካ ውስጥ የገቡት ለዚሁ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ አንዳርጋቸው፡- አንድ ነገር እንድታስቢ እፈልጋለሁ፤ እኔ ለፖለቲካ ውስጥ የገባሁት ነፃነት ከእኔ ጋራ ባለው ትርጉም የተነሳ ነው። ምፅዋት አይደለም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ በምገባበት ወቅት ተማሪዎች ሆነን እናስብ እንደነበረው ለህዝቡ እርጥባን ልንሰጥ አልነበረም። በዚያን ጊዜ ህዝቡ ተበድሏል፣ ተገፍቷል፣ ተርቧል፣ እኛ መብት አምጪዎች፣ እኛ ብልፅግና አምጪዎች፤ እኛ ችግር አቃላዮች ሆነን ነው የገባነው። በፍልስፍና ትምህርት ካለፍኩ በኋላ የተረዳሁት ነገር የህዝቡ ረሃብ የእኔ ረሃብ ነው፣ የህዝብ መብት መገፈፍ የሚባል ነገር የለም፤ የእኔ መብት መገፈፍም ጭምር እንጂ። በዚህ የተነሳ እኔ እየታገልኩ የነበረው አንድን ህዝብ ነፃ ለማውጣት አልነበረም። በህዝብ ባርነት እኔ ባርያ ሆኛለሁ። የምታገለውም ራሴን ከባርነት ላወጣ ነው። ከጥጋብ ከነበረበት ቦታ መጥቶ ትግል የማደርገው ረሃብተኛን ህዝብ ምግብ ለመስጠት ሳይሆን ራሴን ነፃ ለማወጣት ነው።
ለምሳሌ እኔ እንደፀሃፊ የምደሰተው አስር ሰዎች ሲያነቡልኝ ሳይሆን ሚሊዮኖች ሲያነቡልኝ ነው። ስለዚህ ሚሊዮኖች እንዲያነቡልኝ መሃይምነት መጥፋት አለበት ማለት ነው። ይህ ብቻ አይደለም አንጀቱን እየሞረመረው የእኔን መጽሐፍ ማንም ሊያነብልኝ አይችልም። ስለዚህ የምግብ ጉዳይ ይመለከተኛል። እያመመውም ሊያነብ አይችልም። አንድ ጸሐፊ ያለአንባቢ ግማሽ ነው የምሆነው። ስለዚህ ሙሉ እንድሆን ከፈለኩኝ የእነሱን ማንኛውም ሰብአዊ ጉዳት የእኔም ጉዳት ሆኖ መገኘት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እርሶ አሁን እኔ የታገልኩት ለራሴ ነው እያሉ ነው?
አቶ አንዳርጋቸው፡- አዎ፤ አየሽ እዚህ ጋር መገንዘብ ያለብሽ ትልቁ ቁምነገር የነፃነት ጉዳይ የራስሽ ጉዳይ ነው። የአንቺን ነፃነትና ምሉዕነት የሚጎዳ ሁሉ የራስሽ ጉዳይ ነው። አንዲት እናት ሶስት ልጆች ይዛ መንገድ ላይ ተርባ ደጅ ብታድር አንቺ «ይህችን ሴትዮ ልርዳት» ብለሽ የምትሄጂ ከሆነ በእኔ አመለካከት ከፍተኛ ስህተት ነው የምትፈጥሪው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ እኔን በብዙ መንገድ ከተሟላ ሰውነት ያወርደኛል ብዬ ነው የማስበው። የማደርገው ነገር ሁሉ ለራሴ ክብር ነው። የእሷ ድህነት እኔን እያወረደኝ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ስትመጪ ግን አደገኛ ነው ብዬ የማስበው ነፃ አውጪውና ችግር አቃላይ ሊሂቅ ከደሃው ህይወት፤ ከድሃው ህዝብ ጋር በማይበጣጠስ ክር አለመተሳሰሩ ነው። እሱ ደስ ካለው ያደርግላቸዋል፤ ደስ ያላለው ቀን ይተዋቸዋል። ለእሱ እርጥባን ነው። እሱ ለእነሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ በደግነቱ ነው። እኔ ግን በደግነቴ አይደለም የማደርገው። በማይበጣጠስ ክር የተሳሰረ ነገር ስላለኝ ነው ህዝቤ መብቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር የምፈልገው። የእነዚህ ነገሮች መጓደል በሙሉ እኔን ጎዶሎ ሰው ያደርገኛል። የተሟላ ሰው ሆኜ ኖሬ መሞት አልችልም። የዚህ አይነት ጥልቅ የሆነ መረዳት ሳይኖር በምንም አይነት አንድን ህዝብ መርተው ከግቡ የሚያደርሱ መሪዎች ይመጣሉ ብዬ አላስብም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚጨምረንም ይህ ነው።
ወያኔዎች ስንት አበሳቸውን አይተው መጥተው ሁለት ወር ሳይመላቸው ያንን ሁሉ ችግር አብሯቸው ያለፈውን ህዝብ ረስተው በውድ ዋጋ በዲዛይነር የተሰራ ሱፍ ለብሰው የ300ዶላር ጫማ አድርገው የደርግ ላንድሮበሮችን ወደ መከፋፈል ነው የገቡት። አሁን የእኔ ነው እያሉ የሚጮሁለትን የትግራይ ህዝብ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ረስተው መኖር ለመጀመር ጊዜ አልወሰደባቸውም። ለምን የሚባል ጥያቄ እንኳ መጠየቅ አልፈለጉም። ከዚያ ሲለፍፉለት የነበረው ደሃ ህዝብ ጋር የሚያስተሳስራቸው ነገር አልነበረም። እነሱ ራሳቸው የተዋረዱበት፣ እነሱ ራሳቸው የተራቡበት ፣ እነሱ ራሳቸው መብት አጥተው የኖሩበት አድርገው አላዩትም። እነሱ እዚህ መጥተው ከማንም በባሰ መብት ገፋፊና ዘራፊ ነው የሆኑት። አሁንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በዚህ ደረጃ ብስለት ያላቸው ፖለቲካ ሃይሎች የሉም። ይህንን አይነት ችግር ሳያቃልል መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ መሪዎችን ማምጣት እዚህ አገር ላይ አስቸጋሪ ነው። ይሄ ደግሞ በቀላሉ የሚመጣ አይደለም። በቋሚነት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚሰጥና ለዚህ ደግሞ በርከት ያሉ ሊሂቃንን ማፍራት የሚችሉ ጥራት ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ይጠይቃል። የፍልስፍና ዲፓርትመንቱ እያመረተ የሚያወጣቸው ተማሪዎች በዚህ ደረጃ ተምረው ነው የሚወጡት? ከእነሱ ተርፈው ማህበረሰቡን በዚህ ደረጃ ተፅዕኖ ማሳደር የሚያስችል ሃይልና ጉልበት ይዘው ነው ወይ የሚወጡት? አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ሰው ማግኘት ይቻላል ወይ ? ይሄ ከሌለ እንዴት አድርጎ ነው ከዚህ ችግር የምንወጣው? እኔ የሚያሳስበኝ አንዱ ነገር ይሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጽሐፎት ላይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር አብራችሁ መማራችሁንና በአጋጣሚ ተቀራርባችሁ ጓደኛ የሆናችሁበት ሁኔታ እንደነበርም ፅፈዋል። ከዚያ ጊዜ የጀመረው ጓደኝነት ውሎ ሲያድር ጫፍ ወደ ረገጠ ርዕዮተ አለም ልዩነት የተሻገረበት ምክንያት ምን ይሆን?
አቶ አንዳርጋቸው፡- እንዳልሽው መጽሐፌ ላይ በዝርዝር ሄጄበታለው። እኔና መለስ በተመሳሳይ አመት ነው ዩኒቨርሲቲ የገባነው፤ እሱ ፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሲገባ እኔ ሳይንስ ነበር የማጠናው። የተገናኘንበት የተለየ አጋጣሚ አለ። አንድ የገና እረፍት ላይ እሱም ወደአድዋ አልሄደም፤ እኔም ገና ከቤት የተፈታው ጥጃ በመሆኔ ወደ ቤት ከሄድኩኝ የቤተሰቦቼን ቁጥጥር ስለማልወደው እዚያ ባዶ የነበረው ጊቢ ውስጥ ተሻርከን ወደ ቁማር ገባን። ወደ አነሳሽው ነጥብ ስመለስ ይሄ ታሪክ አንዳንድ ጊዜ የሚገርም ነገር አለው። አንዳንድ ነገሮች ካለፉ በኋላ ሁሉም ነገሮች በእቅድና በፕላን የተሰራ የሚመስልበት ሁኔታ አለ። በአብዛኛው በእቅድ ሳይሆን በግርግር የተፈጠረ ነው። ለምሳሌ አብዛኛው ወጣት ኢህአፓ እንደሆነው ሁሉ እኔም ሆኛለሁ። በጣም በበሰለ እውቀት ተጠቅመን የፓርቲውን ፕሮግራም አጥንተንና በብቃት ላይ ተመስርተን የገባንበት አይደለም። በወቅቱ ኢህአፓን በከፍተኛ ደረጃ ይመሩ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። በዚህ ምክንያት መለስ ኢህአፓ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት እድል ነበር። ይሁንና የብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ከጀመሩ ሰዎች ጋር ቅርበት ስለነበረው ህውሓትን ተቀላቀለ። ይህም ቢሆን ግን እሱም ልክ እንደእኛ ይሄኛው ከዚህኛው ይሻሻል ብሎ መዝኖ የገባበት ሁኔታ እንዳልነበረው አውቃለሁ።
ስለዚህ የመጀመሪያ መለያየታችን በትልቅ እውቅት ላይ ተመስርቶ የተፈጠረ ልዩነት አድርገሽ አትመልከችው። የኋላ ልዩነታችን ግን መሰረታዊ ልዩነት አለው። እነሱ ያንን አመለካከት እንደያዙ እዛው በርሃ ነው የቀሩት። እነሱ 17 አመታት ያሳለፉትና እኔ ያለፍኩበት መንገድ የሚገናኝ አይደለም። እነሱ ትንሽ ትንሽ ተግዳሮቶች እያጋጠሟቸው እንጂ ብዙውን ጊዜ እያሸነፉና የአሸናፊነት ስነልቦና እየገነቡ ነው የመጡት። የአሸናፊነት ስነልቦና ደግሞ የምሰራውና የምከተለው ስትራቴጂ ሁሉ ትክክል ነው ብለሽ እንድትሞኚ የሚያደርግ ቅዠት ውስጥ ነው የሚጨምርሽ። በሁለተኛ ደረጃ ወያኔዎች ከአለም በተገለለና በጣም ጠባብ የሆነ የእውቀት ክምችት በነበረበት በርሃ ውስጥ እንደመቀመጣቸው ከእነሱ ውጪ ያለውን አለም ማየት እንዲሳናቸው አድርጎ ነበር። አለም በብዙ መንገድ ፈትሾ ችግር አለበት ያለውን የማርክሲስት ፍልስፍና ከቻይና እና ከራሺያ ተሰብስቦ አገር ውስጥ የገባ ፍልስፍና ሲያነቡ ነው የከረሙት። እኔ ደግሞ አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ኢህአፓ ካጋጠመው ሽንፈት ጋር ተያይዞ እኔ ውስጥ ህይወት ምንድነው? ወደ ማለት ምስቅልቅል ውስጥ ገብቼ ነው የኖርኩት። የነፃነትና የፍትህ ትርጉም ተቀብዬ የመጣሁበት መንገድ አይደለም እነሱ ያለፉት። በእነሱና በእኔ መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነው ያለው። እነሱ ነፃ አውጪዎች ናቸው። «ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ» ብዬ ለመፃፍ የተገደድኩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።
ስልጣን እንደያዙ እኔ ከእንግሊዝ ላግዛቸው ስመጣ እነሱ ያላቸውን የአሸናፊነት ስነልቦና ተላብሼ አልነበረም። ይልቁንም ከህዝቤ ጋር ላይበጠስ በተሳሰረው ስነልቦና እንጂ። ባዶ እግሩን የሚሄድ አንድ ኢትዮጵያዊ እሳከለ ድረስ እነ መለስና እኛ ከኮንጎ ጫማ ከፍ ማለት የለብንም የሚል እምነት ነው ያለኝ። በዚያ ደረጃ ነው መተሳሰር ያለብን ባይ ነኝ። በምንበላው ምግብ፣ በምንለብሰው ልብስ ነው የተጣላነው። « ለምንድን ነው ይህንን ቆዳ ጃኬት እየለበስክ ሁልጊዜ በቴሌቭዥን የምትቀርበው?» በሚል አጀንዳ ተደርጎ የቀረበበት አጋጣሚ አለ። በወቅቱ እኔም እልህ ውስጥ ገብቼ ስለነበር ገንዘብ የለኝም አልኳቸው። እነሱ ግን ከኢህአዴግ ካዝና ሙሉ ሱፍና ከረባት መግዢያ ሁለት ሺ ብር ወጪ አድርገው ሰጡኝ። በዚያ ደረጃ ነበር የምንጨቃጨቅ የነበረው። መጨረሻ ላይ አገሩን ለቅቄ ስሄድ ቤታችንን ለሚጠብቅ ዘበኛ በአንተ ብር የተገዛ ልብስ ነው ብዬ አስረክቤው ነው የሄድኩት። እነሱ ያ መሰረት የላቸውም። እነሱ የሽንፈት መሰረት የላቸውም። የነፃነትና የዴሞክራሲ ግንዛቤ የላቸውም። ያንንኑ የማርክሲዝም ፍልስፍና ይዘው ነው የዘለቁት።
እናም የዚያን ጊዜ የተፈጠረው ልዩነት በእኔ እምነት ተሞክሮ ላይ ከማንፀባረቅ የተፈጠረ ነው። በምንከራከርበት ጊዜ አይገባቸውም ነበር። አንዱ ትልቁ የኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካ ስህተት ብዬ የማምነው ከምዕራብ አለም ሲመጣ የምዕራብን ታሪክ አፃፃፍ፣ የምዕራብን ኢኮኖሚ ፍልስፍና ይዞ ነው የመጣው። የእኛ ማርኪስስቶች እነመለስን ጨምሮ በአለም የተተቹና የተጣሉ ፍልስፍናቸውን ይዘው ነው የዘለቁት። እኔ እንግሊዝ አገር ፍልስፍና ስማር እዚህ አገር እያለሁ ሳይገባኝ እንደ ደብተራ በቃሌ ሳጠናው በነበረው ፍልስፍና ራሴን እንድታዘብ አድርጎኛል። ስለዚህ እነሱ የቆሙበት የማርክሲዝም መሰረት ምን ያህል ደካማ እንደነበር አውቀው ነበር። በዚህ ምክንያት ስንነጋገር ልንግባባ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባነው።
እነ መለስ በታፈነና በታመቀ ሁኔታ እርስ በርሳቸው የማያድግ እውቀት ይዘው በመቆየታቸውና ከሚገባው በላይ ትእቢትና ትምክህት ይዘው ስለመጡ እንዲሁም ከማሸነፍና ከድንቁርና ጋር ተደምሮ ሰው የሚላቸውን ወደማይሰሙበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገቡት። የወደቁበት ዘመን እንዳውም ቆይቷል ባይ ነኝ። ለዚህ ደግሞ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፤ በዚያ አካሄዳቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ግልፅ ነበር። በዚያ ጊዜ እኔ የማወራው የነበረው ስለቅንጦታቸውና ስለሙስና ህይወታቸው ነበር። አሳፋሪ ውድቀት የምትወድቁበት ጊዜ ይመጣል በማለት የመጨረሻ ንግግር አድርጌ ነው የወጣሁት። እናም በዚያ ደረጃ ቁርጠኛ ሆኜ ስከራከር የነበረው ቅድም ባልኩሽ መንገድ መሰረት ይዤ ስለመጣሁ ነው። ያን ጊዜ የነበረኝ ልዩነት እኔ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሲሆን እነሱ አላማ ነበራቸው። በአንድ ጊዜ ስልጣን ወደመያዝ በመጡ ቁጥር በደንብ ያላሰቡበት ከህዝብ ጋር የተቆራኘ ነገር እየላላ መጣ። እንደማንኛውም ነፃ አውጪ ህዝብ መልሶ ረጋጭ በህዝብ ሃብት የቅንጦት ኑሮ ነዋሪነት ተሸጋገሩ። እንዳውም ከመጀመሪያውም ይህንን እያለሙ የመጡ ነው የሚመስለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ሁሉን ትተው ወደ እንግሊዝ ከተመለሱ በኋላ ዳግም ወደ ፖለቲካው ገብተዋል፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ምንድን ነው የሆነው መሰለሽ፤ በ1985 ዓ.ም ላይ እኔ የነበረኝን የመንግስት ኃላፊነት ስለቅ ወደ እንግሊዝ አገር የመሄድ ፍላጎት አልነበረኝም። የነበረው ሁኔታ ስላላማረኝ የተለያዩ ጽሑፎችን መፃፍ ጀምሬ ነበር። የሰራተኛ እና የመምህራን ማህበራትና ልሂቃኑን ጨምሮ ኢህአዴግን የሚደራደር ፓርቲ ማቋቋም ይቻላል ብዬ በድፍረት እናገር ነበር። ከዚህም ባሻገር ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት የጭቁን ህዝብ ፓርቲ ነኝ ይበል እንጂ ዋነኛው የጭቁን ህዝብ ረጋጭና ዘራፊ ሊሆን ስለሚችል እሱን የሚቋቋም በሰራተኛው ዝቅተኛውን ህብረተሰብ ያሳተፈ ፓርቲ ማቋቋም ይገባል የሚል ጽሑፍ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ አወጣ ነበር።
በሌላ በኩል ግን በሽግግር መንግስቱ ጊዜ የግል ሚዲያ ይፈቀዳል የሚል አላማ ስለነበራቸው እኔም ሬዲዮ ሊፈቅዱልኝ ይችላሉ ብዬ በሚገባ ጥናት አጥንቼ ነበር። ከአሜሪካ ኤምባሲ ሰዎች ጋር ተነጋግሬ ሊያግዙኝ ቃል ገብተውልኝ ነበር። ይህ የማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ ጣቢያ በማስታወቂያም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያገኘውን ገቢ መልሶ ህብረተሰቡ ላይ ኢንቨስት የሚያደርግ መንገድ ነበር ያደራጀሁት። ያንን አላማዬን ደግሞ ጓደኞቼ በደንብ ነበር የሰሙት። አንድ ቀን ሰው ልከው ተስፋ ቁረጥ ሬዲዮ እዚህ አገር አይፈቀድም የሚል መልዕክት አደረሱኝ። በዚያው ሁኔታ ሳለሁ እናቴ ጭንቅላቷ ውስጥ ደም ፈሰሰና ኮማ ውስጥ ገባች። እናም እንግሊዝ አገር መሄድ ነበረብኝ።
እንዳልኩሽ ግን በወቅቱ እኔ መንግስትን ያለምንም ፍራቻ ነበር የምናገረው። ቤተሰቦቼ በዚህ ምክንያት አንድ ነገር ያደርጉታል ብለው ይሰጉ ስለነበር ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ደጅ ወጥተው ነበር የሚጠብቁኝ። በተለይ ደግሞ እኔ እዚህ ተቀምጬ ለአሜሪካን ድምፅ በኢትዮጵያ ታሪክ በሙስና እስከዛሬ ድረስ ከመጡት መንግስታት ሁሉ በከፋ መልኩ የሚታይ መንግስት ይሆናል ብዬ ነበር የተናገርኩት። ሁለተኛ በሰራዊት ደረጃ ለረጅም ዘመናት በራሳቸው መንገድ ጠፍጥፈው የሰሩት ሰራዊት በመኖሩ የተነሳ ደርግ በአንድ ቀን ምሽት 1ሺ 500 ሰዎች ቢገድል እነሱ 200ሺ ሰዎችን በአንድ ቀን ሌሊት ገድለው ሊያድሩ ይችላሉ ብዬ ነበር የገለፅኩት። ትዕዛዛቸውን ያለምንም ማንገራገር ሊፈፅም የሚችል ሰራዊት መኖሩም በድፍረት ተናግሬአለሁ። እናም ይህንን ያህል ተናግረሽ እዚህ አገር ላይ እድሜሽ ይረዝማል ተብሎ ስለማይታሰብ ቤተሰቦቼ ከዚህ እንድወጣ በጣም ይፈልጉ ነበር። ስለዚህ አንድ ጊዜ እናቴን ለማየት ስሄድ በሙሉ ቤተሰቦቼ እዚህች አገር እንዳልደርስ ተፅዕኖ ፈጠሩብኝ። ከዚያም እናቴ ከኮማ ውስጥ ለመውጣት ረጅም ጊዜ ፈጀች። ከዚያ ወዲህ ተመልሼ የመጣሁት በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምን ነበር ምክንያትዎ?
አቶ አንዳርጋቸው፡- ያን ጊዜ ጦርነቱ ሲነሳ በእንግሊዝ አገር እያለሁ የአገሪቱ ኤምባሲ ስብሰባ ጠራን። እኔ እንግዲህ ከኤርትራውያን ጋር የቆየ ግንኙነት ነበረኝና በዚያ ጊዜ የነበራቸው አመለካከት በጣም እያሳሰበኝ መጣ። ይኸውም እነሱ በዚያ ሰዓት ትግራይ ብቻውን ከኤርትራ ጋር የሚዋጋ አድርገው ነበር የሚያስቡት። በጣም በከፍተኛ ንቀት ከአስመራ ተነስቶ ለቁርስ መድረስ እንደሚችል ነበር የሚያስቡት። ያን ጊዜ እኔ ደግሞ ምንም እንኳ ከወያኔ ጋር የከረረ ጠብ ቢኖረንም እነዚህን ሰዎች ባልወዳቸውም አገር አገር ነው። ለሁላችንም ቢሆን የትም ቦታ ያለ የአንድ አካባቢ ህዝብ በውጭ ከሚደረግ ጦርነት መሸነፍ ማለት ትልቅ ውርደት ነው። ለእኔ የትግራይ ክልል መጠቃት ማለት የኢትዮጵያ ጥቃት ነው። በመሆኑም እንዲህ አይነቱ ነገር ሊያሳስበን ይገባል የሚል አቋም ነበረኝ። በወቅቱ ለኤርትራውያኑ በፊት ለፊት ነግሬያቸው ነበር። ስህተት እንዳትሰሩ የትግራይ ህዝብ ሲጠቃ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ ይቀመጣል ብላችሁ በተሳሳተ አመለካከት ችግር ውስጥ እንዳትገቡ ነበር ያልኳቸው። ከዚያ ጋር ተያይዞ የፈለገ ቢሆን ከወያኔ ጋር በመሆን መመከት ያስፈልጋል በሚል እንግሊዝ አገር የነበረው ህዝብ ኮሜቴ አቋቋመ። እዛ ኮሚቴ ውስጥ የገባ አንድ ጓደኛ ነበረኝና «በዚህ አጋጣሚ ለምን ወደ ኢትዮጵያ አትመጣም?» ሲለኝ መጣሁ። ከዚያ በኋላ ተመልሼ የመጣሁት በ1997 ዓ.ም ምርጫ ነው። ያኔም ያመጣኝ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ትንሽ ከርፋፋነት ስለነበረብኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ አንዳርጋቸው፡- እነመለስ «ለአገሪቱ ዴሞክራሲ በእውነት ያስፈልጋታል እኛ እንዳውም ተቃዋሚዎች ነው ያጣነው፤ ዴሞክራሲን የምንፈልገው ፋሽን ስለሆነ አይደለም» የሚል ንግግር በሚናገሩበት ጊዜ ወደ እዚህ ለመምጣት አሰብኩ። የመለስ ንግግር ዛሬ ድረስ ጆሮዬ ላይ ይጮኻል። ዴሞክራሲን የምንፈልገው ፋሽን ስለሆነ አይደለም የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ቁልፏ ነው ብሎ እስከመናገር ድረስ ሲናገሩ እነዚህ ሰዎች ገብቷቸዋል ማለት ነው በዚህ ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ የወሰኑት ብዬ አመንኩ። በወቅቱ ደግሞ ተሰባስቦ መልክ እየያዘ የመጣ ተቃዋሚ ነበር። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደግሞ እንግሊዝ አገር መጥቶ አናገረኝ። «በውጭ ያላችሁት ከገንዘብ ባሻገር መጥታችሁ ምን ልታግዙን ትችላላችሁ?» ብሎ ጠየቀኝ። እኔ ደግሞ ገንዘብ ማዋጣት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ምርጫ እንዲሆን ማገዝ እንደሚገባኝ አመንኩ። በመሆኑም ምርጫው ከመካሄዱ ከሶስት አራት ወራት በፊት ነው የመጣሁት። እናም ከቅንጅት ጋር ብዙ የማደራጀት ስራ ለመስራት ሞከርኩኝ። ያው ምርጫው አልቆ ብጥብጥ ሲመጣ የተመረጡትን የፓርላማ ሰዎች ለመጀመሪያው ዙር ማሰር ስላልፈለጉ «ማነው ከእነሱ ጋር የሚሰራው? ማነው የሚያደራጀው?» ብለው ሲያፈላልጉ እኔን አገኙኝ። እኔ በወቅቱ አልተወዳደርኩም አልተመረጥኩም ነበር። ነገር ግን እዚሁ እኔና አንቺ ቃለመጠይቅ በምናደርግበት ቤት ደህንነት ልከው ወሰዱኝ። መመታት የጀመርኩት ከቤት ነው። አንደኛው ደህንነት «ያረፍክበትን ቤት አሳየኝ» አለኝና ላሳየው ስሄድ ከጀርባዬ በዱላ መታኝ። እኔም የጠየከኝን ነገር አልፈፅምም እስካላልኩ ድረስ ለምን ትመታኛለህ ስለው ? የመለሰልኝ መልስ እስከዛሬ ድረስ ይገርመኛል። «ደብድቡት ተብሎ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል» ነው ያለኝ። በድጋሚ ሊመታኝ ሲል ዱላውን ቀማሁት፤ እሱ ግን በሌላኛው እጁ ሽጉጥ ይዞ ነበርና ሊያስፈራራኝ ይሞክር ነበር። እኔ ግን ዱላውን ቀምቼ ከግቢው ውስጥ አባረርኩት። በኋላ ሌሎች ሰዎች በመካከላችን እስከሚገቡ ድረስ አላቆምንም። እናም ነፃነትሽን ጠንቅቀሽ የምታውቂ ከሆነ ሽጉጥ የያዘም ሰው ቢሆን አትፈሪም። ከዚህ ግቢ አውጥተው አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ነው ያሳረፉብኝ። በመጨረሻም በሰደፍ አይኔን ወግተው ዝዋይ ወስደው ጣሉኝ።
አዲስ ዘመን፡- በዚያ ሁኔታ ለምን ያህል ጊዜ ታሰሩ ማለት ነው?
አቶ አንዳርጋቸው፡- አምስት ሺ የሚሆን እስረኛ ለአንድ ወር የሚሆን ጊዜ ነው የታሰርነው። ተቃዋሚዎችና መንግስት በአውሮፓ ህብረት አማካኝነት ስምምነት ላይ ደረሱና ሁላችንም ተፈተናል። ከዚያ ከ15 ቀን በኋላ ወደ እንግሊዝ አገር ተመለስኩ። ለነገሩ የመጣሁትም እነሱን ለማገዝ እንጂ እዚህ ለመቆየት አልነበረም። ከዚያ በኋላ እንግሊዝ አገር እንደሄድኩኝ ሁሉንም ሰብስቦ እስር ቤት ጨመራቸው። እኔ እንግዲህ ፖለቲካው መልክ ሊይዝ ነው ብዬ ተስፋ ጥዬ የነበረበት ሁኔታ ታጥፎ ጭራሹኑ ከተማ ውስጥ ስናይፐር አምጥተው ያንን ሁሉ ሰው የገደሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። በተጨማሪም ከ60 እስከ 70ሺ የሚሆን ሰው በየወታደራዊ ካምፑ አሰሩ። ይህ ነገር በጣም ጭንቅላት የሚነካ ነገር ነው የሆነው። ችግር አይመጣም ብዬ ቀስቅሼ እንዲሳተፉ ያደረኳቸው ወጣቶች ታስረው ሲማቅቁ እኔ አውሮፓ ገብቼ የምተኛበት ሁኔታ አይኖርም። ዴሞክራሲን የሚጠቀሙበት መንገድ በጣም ነበር ያናደደኝ። የሚቃወማቸውን ሰዎች ሁሉ ብዙ ገንዘብ ሳያወጡ መለየት የቻሉበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው።
ዴሞክራሲን የስለላ መሳሪያ ለማድረግ አስበው እንደነበር እኔ አላውቅም ነበር። ቢያሸንፉ ስልጣናቸው በተለመደው መንገድ ሊያስቀጥሉ፤ ከተሸነፉ ግን ማነው የሚቃወመን? የትኛው ባለሃብት ነው ለተቃዋሚ ብር የሰጠው? የትኞቹስ ሰዎች ናቸው እዚህ ከተማ ውስጥ ተቃዋሚን ሲደግፉ የነበሩት? የሚለውን ነገር በአደባባይ ሰው ሃሳቡንና ስሜቱን በገለፀበት ወቅት ለማወቅ ቻሉ። ለእኔ እንደኢህአዴግ ዴሞክራሲን በዚህ ደረጃ የስለላ መሳሪያ ያደረገ መንግስት የለም። ያንን ሁሉ ሰው እስር ቤት ጨምሮ ሳይ መቀበል አቃተኝ። ስለዚህ በውጭ ያሉትን ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር መንግስት ያሰራቸውን እንዲፈታ፤ የተዘጋውን የፖለቲካ እንዲያሰፋ ፖለቲካዊ ተፅእኖ ማድረግ አለብኝ ወደሚል ነገር ውስጥ ገባሁኝ። ከዚህ ቀደም በየትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ብዙም ግንኙነት አልነበረኝም ነበር። ምክንያቱም የረባ ነገር ይሰራሉ ብዬ ስለማላምን ነው። ያን ጊዜ ግን ያለውን ሁኔታ ተረድቼ ዋናው አደራጅ ወደመሆን ገባሁ። እነሱ በታሰሩባቸው ሁለት አመታት እኔ በአለም ደረጃ ፖለቲካዊ ድጋፉንና እንቅስቃሴው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲደራጅ በማድረግ ሰፊ ስራ ሳከናውን ቆይቻለሁ። ሲፈቱ 50 አገራት ላይ በራሳቸው ህግ፣ በራሳቸው ምክር ቤት፣ በራሳቸው ስራ አስፈፃሚ፣ የራሳቸው ገንዘብ አስቀምጠው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ጥረት አድርጌአለው። እንደድሮው ተቃዋሚ ሲመጣ ዝም ብለው ብር የሚሰጡ አልነበሩም። በዚያ መንገድ የተደራጀ ድርጅት በመላው አለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመሰረት አደረግን።
ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ያደረግነው ቃለምልልስ ክፍል ሁለት በሚቀጥለው ሳምንት እትማችን ለአንባቢዎቻችን ይዘን እንቀርባለን።
ፎቶ፡- በገባቦ ገብሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም
ማህሌት አብዱል