መጋቢት 3/2012 ዓ.ም በአንድ ጃፓናዊ ዜጋ በአገራችን መከሰቱ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ እያዋዛ አድጎ ዛሬ ላይ በአጠቃላይ በአገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 968 ደርሷል። ላለፉት ሁለት ወራት በቀን አንድና ሁለት አንዳንዴም ምንም ሳይመዘገብ እየዋለና በቫይረሱ ከሚያዙትም አብዛኞቹ የውጭ ጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በለይቶ ማቆያ የነበሩ ሆነው ቆይተው ዛሬ ላይ ይሄ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል።
በሁለት ወራት ውስጥ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተጠቀሰው ያልተናነሰ ቁጥር በሁለት ሳምንት ውስጥ መመዝገቡ፣ በሽታው እጅግ በአደገኛ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን አሳይቶናልና በእጅጉ እንድናስብ ያስገድደናል። ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ 237 ሰዎች የቫይረሱ ተጠቂዎች መሆናቸው ወረርሽኙ እጅግ እየከፋ መምጣቱን አመላክቷል። ሁኔታው በዋዛ እንደማይታይ የሚያመለክተን ሌላው እውነታ፣ ከዚህ ቀደም ሲጠቀስ እንደነበረው የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ብቻ መሆናቸውና በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው ላይ መሆኑ አልፎ፣ ምንም ዓይነት የጉዞ ታሪክ ያላስመዘገቡና ከሕመምተኞች ጋር ንክኪ ያልነበራቸው ተጠቂዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ነው።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ሁሉንም የአገራችን ክፍሎችና ክልሎች እያዳረሰ እንደሚገኝም የጤና ሚኒስቴር መረጃ እያመለከተን ነው። የጤና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የቫይረሱ ሥርጭት አራት ምዕራፎች ሲኖሩት፣ አዲስ አበባ አራተኛውና የመጨረሻው የስርጭት ደረጃ ላይ መድረሷን አስታውቀዋል። ይህ እጅግ አሳሳቢ ነው። ከእስካሁኑ የበለጠ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ወቅት እየመጣ መሆኑንም አመላካች ነው።
ከአገሪቱ ካሉ 80 ዞኖች ውስጥ በ40ዎቹ ውስጥ ቫይረሱ የመገኘቱ ነገር ሲሰማ፣ የሁኔታውን አሳሳቢነት መልሰን መላልሰን እንድናጤን ግድ የሚል ነው። ዜጎች የሚያሳዩት ቸልታና ግዴለሽነት ከወዲሁ ታርቆ፣ ጥንቃቄን አብዝተው ወደሚያስተጋቡና ወደሚያስተገብሩ ሥራዎች በማተኮር መንቀሳቀስ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይም እንገኛለን።
ጤና ሚኒስቴር በየዕለቱ ለሕዝብ የሚያደርሳቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስካሁን በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው። ልብ ብለን ካጤነው ይህ ትልቅ ትርጉም አለው። በአዲስ አበባ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ከእስካሁኑ በተለየ አግባብና በተጠናከረ መንገድ መከናወን ካልቻሉ ሌሎች ላይ ተመልክተን ያሳቀቀን ችግር በእኛም ስላለመደገሙ እርግጠኛ መሆን አንችልም። በመረጃው መሠረት በአዲስ አበባ ተገኙ ከተባሉት የቫይረሱ ተጠቂዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ ልደታና አዲስ ከተማ በተባሉ ሁለት ክፍለ ከተሞች የተከሰቱ ናቸው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አደርጉ የተባለውን የጥንቃቄ እርምጃ በአግባቡ ካለመተግበራቸው ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።
ጉዳዩን ይበልጡኑ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በቀን ከ100 ሰው በላይ በቫይረሱ መያዙ እየተሰማ እንኳን ጥንቃቄው እጅግ የላላ ሆኖ መታየቱ ነው። በገበያ ቦታ፣ በአንዳንድ የእምነት ተቋማትና በትራንስፖርት ሰልፍ ላይ የሚታዩ አካላዊ መጠጋጋቶች አሁንም እጅግ አስፈሪ ናቸው። ይህ ሁኔታ ቫይረሱ ገዳይ መሆኑና የመሰራጨት ባህሪው እጅግ ከባድ እንደሆነ በቂ ግንዛቤ እንዳልተያዘበት አመላካች ነው። እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ኮሮና አደገኛ ገዳይ በሽታ መሆኑና አስፈላጊው የጥንቃቄ እርምጃ ከተወሰደ ግን መከላከል የሚቻል መሆኑን ነው።
የቫይረሱ መሰራጨትና የኅብረተሰባችን መዘናጋት ያሳሰባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ይፋዊ በሆነ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ «መዘናጋት ለኮሮና ቫይረስ መሰራጨት ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ነው። በመሆኑም ኮሮናን ለማሸነፍ ሁላችንም መዘናጋት የሚባለውን ነገር ማስወገድ ይኖርብናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው መዘናጋት በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል። መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለን ነው፤ መዘናጋትን አስወግደን እንቅስቃሴያችን በጥንቃቄ የተሞላ ማድረግ ይኖርብናል። በወረርሽኙ እየተጠቁ ያሉ ዜጎቻችን ሁለት፣ ሦስት፣ አሥር፣ ሠላሳ፣ ሰባ፣ እያለ አሁን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሆነዋል። ይህ የሚያሳየን የቫይረሱ ስርጭት አድማስ መስፋትና የእኛን ደግሞ መዘናጋት ነው። ኮሮናን ማሸነፍ የሚቻለው ሁሉም ጥንቃቄ ሲያደርግ ነውና መተባበርና መደጋገፍ ይኖርብናል። ሁላችንም በመተባበር መቆም ካልቻልን ወረርሽኙን መከላከል አይቻልም» የሚል ጠበቅ ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እውነት ነው ዛሬ ኮሮና ከማንኛውም ጊዜ ይልቅ እጅግ ቅርብ ሆኖ አጠገባችን ደርሷል። በተለይም በአዲስ አበባም ወረርሽኙ ከፍተኛ የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሷል። እናም በዚህ ወቅት መዘናጋ እሳትን በእጅ እንደ መጨበጥ ይሆናልና ያለምንም ማመንታት የጥንቃቄ እርምጃዎች ሙሉ ለሙሉ መተግበር ለነገ ይደር የሚባል ጉዳይ ሊሆን አይገባም እንላለን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 /2012 ዓ.ም