. በህዝብ ተሳትፎ ውጤታማ የሰላምና ፀጥታ ሥራ ተከናውኗል
አዳማ፡- በአዳማ ከተማ የህጻናት ስርቆት እየተፈጸመ እንደሆነ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎችና አንዳንድ አካላት ሲነገር የነበረው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑንና አንድም ህጻን አለመሰረቁን የአዳማ ከተማ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ተናገሩ፡፡ የከተማዋን ፀጥታና ሰላም ለማስጠበቅም ህብረተሰቡን አሳትፎ የተሰራው ሥራ ውጤታማ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ኃይሌ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለፁት፤ ሰሞኑን በከተማዋ የህፃናት ስርቆት እንዳለ በማስመሰል የሚናፈሰው አሉባልታ ሆን ተብሎ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፤ ልጆቹን ወደትምህርት ቤት እንዳይልክ ሁከት ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ ለወሬው መስፋፋት አንዱ ምክንያት የነበረው አንድ በመጠጥ ኃይል ራሱን በአግባቡ መቆጣጠር የተሳነው ሰው አንድን ህፃን ቤተሰቦቹ በሌሉበት ሁኔታ ይዞ ሲሄድ በመያዙ የተፈጠረ ሲሆን፤ ግለሰቡም ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሎ ለህግ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ውጪ ሌላ የልጅ ስርቆት አልተካሄደም ያሉት አቶ ለማ፤ አጀንዳ ፈጥረው ልጅ ተሰርቋል፤ ኩላሊት ወጥቷል፤ ሌላም ነገር ሆኗል ብለው የሚያስወሩ እንዳሉና ይህም ሆን ተብሎ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያራግቡት ሴራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ሰዎች አጀንዳ ምክንያትም አንድ አባት ልጁን ይዞ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እየሄደ እያለ «ልጅቷ አንተን አትመስልም ጠረጠርንህ» በሚል ምክንያት የተደበደበበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፤ የፀጥታው መዋቅር ደርሶም ሰውዬውን ከጥቃት ማስጣሉን አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ላይ በከተማዋ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር የሌለ መሆኑን ተገንዝቦ ህብረተሰቡ በእንዲህ አይነት አሉባልታዎች ሳይዘናጋ እንደወትሮው ሁሉ የእለት ሥራውን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡
ይሁን እንጂ በክልሉም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋለውን ችግር ተከትሎ አንድ ወቅት ላይ ገበያ የማስቆም እቅድ ተይዞ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ በተለይ በተለያዩ ተቃዋሚ አካላት ሲነዛና ሲለፈፍ የነበረው ሁኔታ አዳማ ላይ ለምን አልተከሰተም ተብሎ በዘመቻ መልክ ወጥተው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም የፀጥታ መዋቅሩ፣ በፓትሮልና በቋሚ ጥበቃ በተለያየ ቦታ ክትትል ስናደርግ ስለነበር አንድ ሁለት ቀን ገበያውን ለማስቆምና ለማዘጋት «አትዘጉም ወይ» የሚሉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል፤ በዚህ እርምጃም በአንድ ቀን 32 ሰው፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ወደ 35 ሰው መያዝ ተችሏል ብለዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በከተማዋ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆኑን አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡ ይህም የከተማዋ ነዋሪ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር የመስራቱ ውጤት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
በወንድወሰን ሽመልስ