የአዲስ አበባ ጎዳናዎች አልፎ አልፎ ሽው ሲሉ ከሚታዩት ተሽከርካሪዎች ውጪ በእግረኞች ተሞልተዋል፡፡ ገና ከረፋዱ ከቤታቸው የሚወጡት እናቶች ነጠላቸውን ትከሻቸው ላይ ጣል አድርገው በጥበብ ልብስ ይታያሉ፡፡ ህፃናት በየመንገዱ ይቦርቃሉ፡፡ ወጣቶች በተለየ ሁኔታ ከፀጉር እስከ እግር ጥፍራቸው አምረው ተውበዋል፡፡ ወንዶቹ በትንሽ ርቀት ውስጥ ከአምስት እስከ 10 ብር የሚሸጡ የፕሪም ፍሬ የያዙ እሽጎችን ይገዛሉ፡፡ በየመንገዱ ያሉት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በየአቅ ራቢያቸው ወዳሉ አብያተ ቤተክርስቲያናት ይተማሉና እኛም ይህንኑ እየተመለከትን ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ዘለቅን፡፡ ድንገት ታዲያ ስርዓቱን በምስል የሚያስቀሩ ጎብኚዎች ላይ ዓይናችን አረፈ፡፡
በዜግነት ጀርመናዊ በአሁኑ ወቅት ኑሯቸውን በአሜሪካ የከተሙት ቤረንት ባሶሊክ አፍሪካን የሚያውቋት ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን የመ ጀመሪያቸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በታሪክ መጽሐፍት ባነበቡት በአገሪቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ታሪኮቿ ተደመዋል፡፡ ከአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች አስገራሚ አገር ከራሱ አልፎ ለሌሎች ክብር የሚሰጥ አስደናቂ ሕዝብም አላት፡፡ የጥምቀት በዓልም አከባበር ከሚያውቁት በተለየና በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሆኖም አግኝ ተውታል፡፡
የአገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ማስተዋወቅ ላይ ሰፊ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ቤረንት ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ምንም እንኳ እንደ ሆቴል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የተሻለ ነገር ቢታይም ትልቅ አገርና በርካታ ለጉብኝት የሚበቃ ቅርስና ታሪክ ባለቤት በመሆኗ መሠረተ ልማቱ ላይ በትኩረት መሠራት አለበት፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በመኪና ላይ የሚያልፈው ሰፊ ጊዜ ለማሻሻል ፈጣን መንገዶች አገልግሎት ቢመቻች የተሻለ ነው፡፡
ከአሜሪካ የመጣችው ሌላኛዋ ጎብኚ ጄሪ ካስዋ ናት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣም የመጀመሪያዋ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ በቆየችባቸው ሶስት ሳምንተት በአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ኣኽሹም፣ ላሊበላና ኦሞ ላይ ከተመለከተቻቸው የቱሪዝም መስህቦች በተጨማሪ አገሪቱ የሕዝቦቿ ተግባቢነትና መልካምነት ከተፈጥሯዊ ገጽታዋ ጋር ተደማምሮ ፈርጥ አድርገዋታል ስትል ደስታዋን ገልፃለች፡፡
ጂሪ፤ አንዳንድ የዓለም አገራት ጥምቀት እንሚያከብሩ ቢታወቅም የኢትዮጵያ ግን የተለየ ሆኖ እንዳገኘችው ትዝብቷን ተናግራለች፡፡እርሷ በምትኖርበት አገር ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው ዕውቀት እምብዛም መሆኑን የምታነሳው ጎብኚዋ፤ በጣም ደስ የሚል አስገራሚ አገር፣ ሕዝብና ባህል በመሆኑ ሌሎች እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በተያያዘ በርካቶቹ ሆቴሎች የሚሰጡት አገልግሎት ጥሩ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ላይ ግን ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ የተወሰነ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደተመለከተች በመግለጽም፤ በቀጣይ መሠረተ ልማት ላይ ተጠናክሮ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁማለች፡፡
ቅኝታችንን ቀጥለናል ከተለያየ አካባቢ የሚሰበሰቡት ሰዎች ታቦቱን በሃይማኖታዊ ሥነስርዓቶች አጅበው ወደሚሄዱበት ጃንሜዳ አመራን፡፡ በሜዳው ላይ ‹‹ደግሞ ሌላ ደግሞ ሌላ›› የሚሉ የጨዋታ ጥሪዎች ድምጽ ይሰማል፡፡ ፈረስ ግልቢያ፣ የተለያዩ ወጣቶችን ያሳተፉ ጨዋታዎችና ወድድሮች በየቦታው ይታያሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ትዕይንቶች በመመልከት ላይ ያገኘናቸው ሌላኛው ጎብኚ ከጀርመን የጥምቀት በዓልን ለመታደም ከሶሰት ሳምንታት በፊት የገቡት ዶክተር አኪዩሌዲ ማቲኖ ናቸው፡፡
በዓሉ በርካቶችን በአንድ ቦታ አሰባስቦ የሚያሳይ ትዕይንት የተሞላበት ሲሉም ዶክተር አኪዩሌዲ አሞካሽተውታል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጓደኞች እንዳሏቸው በመግለጽ፤ ምነም እንኳ ለኢትዮጵያ በአካል ሲገኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ እንግዳ ቢያደርጋቸውም ወደ አፍሪካ ሲመጡ ግን የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለ ኢትዮጵያ ቀደምት ታሪኮች በተለያዩ ታሪክ መጽሐፎች በማንበባቸው ስለ አገሪቱ ቀድመው እንዲያውቁ እንደረዳቸው አልሸሸጉም፡፡ በመጽሐፎቹ ስለ ጣሊያን ወረራና ከዛም አስቀድሞ ስላሏት ታሪኮችና ከክርስትና ጋር ያላት ግን|ኙነት ሁሉ አንብበዋል፡፡ በዓሉ ከሃይማኖታዊነቱ ባሻገር ቤተሰብ ብሎም ወዳጅ ዘመዶች በአንድ ቦታ ተሰባስበው የሚደሰቱበት፣ የሚያከብሩበትና ለአምላካቸው ፀሎታቸውን የሚያደርሱበት መሆኑ አስደናቂ አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያን በቅጡ ለመመልከት ሶስት ሳምንታት ብቻ በቂ ባይሆንም የተመለከቷቸው የቱሪስት መስሀቦች መኖራቸውንም ሳያነሱ አላለፉም፡፡ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እንዲሁም ሐረር የደረሱባው ስፍራዎች ሲሆኑ፤ በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በታሪክ የተሞሉ መሆና ቸውንም አንስተዋል፡፡ አገሪቱ ልትጎበኝ የምትገባ በመሆኗ የቱሪዝም ዘርፉን በቀጣይ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መሥራት ይገባል፡፡ ለዚህም ደግሞ የተረጋጋ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ጠቃሚ ቢሆንም ለጎብኚዎች የቪዛ አሰራሮችን ቀላል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ሲመለሱም የተመለከቱትን ለሌሎች እንደሚያጋሩ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያውያን ትህትና ለተሞላበት እንግዳ አቀባበላቸውና እርዳታቸው ምስጋናቸውን ቸረዋል፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ጀማል፤ የጥምቀት በዓል ሕዝቦች አደባባይ ወጥተው የሚያከብሩት ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ከባህር ማዶ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሁሉ ይታደሙታል፡፡ በዓሉ ታሪካዊነት የተሞላበት፣ አብሮነት እንዲሁም ሕዝቡ በሰላምና ፍቅር በዓመት አንዴ የሚገናኝበት በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከተለያዩ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ይሠራል፡፡
በዓሉ በመላ አገሪቱ የሚከበር ቢሆንም በርከት ያለ ቁጥር ያለው ጎብኚ ግን የሚበዛባቸው ስፍራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዱ አዲስ አበባ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ጎንደር ነው፡፡ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአገሪቱ እጅጉን የበለፀጉ በዓላት፣ ታሪክና ቅርሶች እንዳሏት የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራል፡፡ በቀጣይም መንግስት በአሁኑ ወቅት ያለውን የሆቴል አገልግሎት፣ ሪዞርቶች፣ መዝናኛ፣ ሎጆች በየመዳረሻው ያሉ ልማቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ከፍተኛ ባለሙያው አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
በፍዮሪ ተወልደ