የሰው ልጅ አእምሮ በሰከነ መንፈስ የማሰቢያ ጊዜ ካገኘ አስቸጋሪ የሆኑ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ጭምር ወደመልካም አጋጣሚ መቀየር ይችላል። ችግር ብልሀትን ይወልዳል እንዲሉ የአየር ንብረቱ በጣም ቀዝቃዛና ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል ምድራቸው በበረዶ ግግር ተሸፍኖ የሚቆይ ሀገራት እንኳን የበረዶ ሸርተቴ (Outdoor ice skating sport) ፈጥረው ለዓለም በማስተዋወቅ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ሲችሉ ይስተዋላል።
ሳንፈልግ ተገደን ከምንገባባቸው ሁኔታዎች እና ካልታሰቡ አጋጣሚዎች በርካታ አስገራሚ ግኝቶች በታሪክ ተመዝግበው እናያለን። ለአብነት እ.አ.አ. በ1853 አሜሪካን ሀገር ጆርጅ ክራም የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ ሼፍ ለአንድ ራቱን ሊመገብ ለመጣ ደምበኛው ፍሬንች ፍራይስ ሰርቶ ያቀርባል። ደምበኛው በቀረበው ምግብ ‘ድንቹ ወፍሯል’ ሲል ከአንዴም ሁለት ጊዜ ምግቡ ድጋሚ እንዲሰራለት በማዘዙ የተበሳጨው ክራም ‘እንዲህ ዓይነት ተመጋቢ እዚህ ድርሽ ማለት የለበትም’ ብሎ ስላሰበ ይበልጥ ሊያበሳጨው ድንቹን በጣም ስስ አድርጎ ከከታተፈ በኋላ ጨው በብዛት በመጨመር በጣም እንዲበስል አድርጎ ይጠብሰውና ያቀርብለታል። ሰውየው የቀረበለትን ምግብ ከቀመሰ በኋላ ምንም ቅሬታ ሳያሰማ ደስ ብሎት ሲመገብ ያየው ሼፍ በእጅጉ ይገረማል። ዛሬ በመላው ዓለም ተወዳጅ የሆነው ችፕስ በዚህ መልኩ የተፈጠረ ነበር።
በሀገራችንም ተወዳጅ ከሆኑት የባህል ምግቦቻችን አንዱ የሆነው ጥሬ ስጋ መብላት እንዲሁ ባጋጣሚ እንደተጀመረ ይነገራል። ስላጀማመሩ ከሚነገሩት ጥቂት መላምቶች ውስጥ ሚዛን የሚደፋው አባቶች በጦር አውድማ አደን አድነው ያመጡትን ምግብ አብስለው ለመብላት የማይችሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው የሚለው አንዱ ነው። ምክንያቱም ምግብ ለማብሰል እሳት ሲያያይዙ ጠላት ጭሱን አይቶ ሊያጠቃቸው እንደሚችል በመስጋት ሲሆን በዚህ ምክንያት በጥሬው ለመብላት ቢገደዱም በዚያው ለምደውትና ተመችቷቸው ቀረ። ቀስ በቀስም ኅብረተሰቡ እየለመደው መጣ የሚለው ይገኛል።
ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ ከኮቪድ 19 መከሰት ጋር ተያይዞ ዛሬ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦች በሮቻቸውን ቆልፈው ከቤት ሳይወጡ ለመቀመጥ ተገደዋል። ለበርካታ ዓመታት ጠዋት ከቤት በመውጣት ሲሰራ ውሎ ምሽት ላይ ወደቤቱ መግባት የለመደ ሰው ከቤት አትውጣ ሲባል ለያስጨንቀው ይችላል። ሥራህን ከቤት ሆነህ ሥራ ሲባልም ይበልጥ ግር ሊሰኝ ይችላል።
ሆኖም ግን እዚህ ሀገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ያሉ አብዛኞቹ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከቤት ሳይወጡ ባሉበት ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛል። በርካታ ሥራዎች የኢንተርኔት አቅርቦት እስካለ ድረስ ከቤት ሳይወጡ የሚሰሩ ናቸው። ይህም በመላው ዓለም አዲስ አስተሳሰብ ፈጥሯል። ዓለም ከኮቪድ 19 ነፃ ከወጣች በኋላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገፅታዋ በጎላ መልኩ እንደሚቀየር ከወዲሁ እየተነገረ ነው። ከዚህ አኳያ በመላው ዓለም እውቅናን ያተረፉ አንዳንድ ተቋማት በዚህ አስተሳሰብ ላይ የያዙትን አቋም በመጠኑ ለመመልከት እንሞክርና ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያነፃፀርን ለማየት እንሞክራለን።
በመላው ዓለም ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ጐግል እና ፌስቡክ ኩባንያዎች በቅርቡ ሁሉንም ሠራተኞቻቸውን እስከ 2021 ድረስ ወደ ቢሮ እንዳይመጡ ነግረዋል። ባላችሁበት ስሩ እያሉ መሆኑን ልብ ይበሉ። እነዚህ ሁለት አንጋፋ ተቋማት አሁንም ለመላው ዓለም የሚሰጡት አገልግሎት ግን በነበረበት ሁኔታ እየቀጠለ እንደሆነ ሁላችንም ምስክሮች ነን። ከዚህ አንፃር ለምሳሌ በአሜሪካ ገጠራማ ስፍራዎች የሚኖሩ ሰዎች እንደኒውዮርክ ያሉ ትልልቅ ከተሞች በመምጣት ለመስራት የሚገደዱበት ሁኔታ ሲፈጠር ቤተሰቦቻቸውን ተለይተው በኒውዮርክ አንዲት አነስተኛ አፓርትመንት በውድ ዋጋ ተከራይተው ለመኖር ይገደዱ ይሆናል። በተገኘው አጋጣሚም ቤተሰባቸውን ለማግኘት ረጅምና አድካሚ ጉዞዎችን ለማድረግ ይገደዳሉ። አሁን በወረርሽኙ ምክንያት ወደቤታቸው ተመልሰው ባሉበት ሆነው ከዚህ ቀደም ሲያከናውኑት የነበረውን ሥራ መስራት ችለዋል። ይህ ለሠራተኞቹ ብቻ ሳይሆን ለቀጣሪ ድርጅቶች ጭምር ያልታሰበ እፎይታን ፈጥሯል። ቀጣሪ ድርጅቶች ‘ለምን በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ለቢሮ ኪራይ፣ ለሠራተኞች ትራንስፖርት፣ ለመብራት፣ ውሃ፣ ወዘተ አወጣለሁ? ለካ እንዲህም መስራት ይቻላል?’ የሚል አዲስ አስተሳሰብ መያዛቸው ትኩረት እየሳበ ይገኛል።
በትላልቅ ከተሞች በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት የሚስተዋሉ የትራፊክ መጨናነቆችና የሚባክኑ ጊዜያት ስለማይኖሩ ጊዜንና ገንዘብን መቆጠብ ይቻላል። በተለይ በመላው ዓለም እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ሰዎች በመቅጠር የሚታወቁ በርካታ ኩባንያዎች እነዚህን ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው በተለይ ቪዛ ከማግኘት ጋር የሚገጥሙ መሰናክሎችን ስለሚያስቀር እጅግ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። ሰዎች አሰሪያቸውን በአካል እንኳን ሳያውቁ ተቀጥረው የሚሰሩበት ሁኔታ ይኖራል። በተጨማሪም ወረርሽኙ ከመላው ዓለም በተወገደ ማግስት በርካታ ሰዎች ምናልባትም ከትላልቅ ከተሞች ወደትውልድ መንደራቸው የሚመለሱበት ዕድል ሰፊ ስለሚሆን የበርካታ ከተሞች ገፅታ ሊቀየር ይችላል የሚሉ በርካቶች ናቸው።
በሀገራችንም ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ከቤት ሳይርቁ ሥራን ማከናወን መቻሉ እና ወረርሽኙ ከመከሰቱ ቀደም ብሎም በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የተጀመሩ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ የማዋል አሠራሮችን ስንመለከት ምንም እንኳን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንዳንድ ተጓዳኝ የሆኑ ተግዳሮቶች ያሉት ቢሆንም ጠቀሜታው ግን በእጅጉ የላቀ ነው።
ከትንሹ ብንጀምር አንድ አባወራ ዘመኑን ሁሉ ውጭ ሲሰራና የቤት ወጪ ከመስጠት ውጭ ቤት ውስጥ ያለውን ችግር በተጨባጭ ለመረዳት የሚያስችለው አጋጣሚ የሚያገኝበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነው። ይሁንና በወረርሽኙ ምክንያት እቤት ለመዋል በመገደዱ ግን ነገሮችን በቅርበት ለማየት ዕድል ያገኛል። ቀደም ብሎ የተሳሳተ ግንዛቤ ይዞ ቆይቶ ከነበረ ከስህተቱ ይታረማል፤ ለልጆቹ በቂ ጊዜ ይሰጣል።
ቀደም ሲል በሀገራችን የተጀመሩ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች፤ ማለትም ሰዎች ባሉበት ገንዘብ ማዘዋወር፣ ውሃ፣ መብራት፣ የስልክነና ኢንተርኔት ወርሀዊ ክፍያ ባሉበት መጀመራቸው ጊዜንና ገንዘብን በእጅጉ አድኗል። ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተመሳሳይ መልኩ ኤሌክትሮኒክ ቫት ሪፖርት የማድረጊያ ዘዴ መቀየሱም የሚታወቅ ነው። ከወረርሽኙ መከሰት አንፃር የዚህ ዓይነት መልካም እርምጃዎች መታየታቸው የሰዎችን ዝውውር ይቀንሳል። እነዚህ ዲጂታል ቴክኖሎጂን የመጠቀም አሠራሮች አዳዲስና ያልዳበሩ ከመሆናቸው አንፃር ለጊዜው የጎላ ፋይዳ ባይኖራቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያበረክቱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ይሆናል።
በየዕለቱ በትላልቅ የሀገራችን ከተሞች በተለይ በመዲናዋ የተለያዩ አገልግሎቶችን ወርሀዊና ዓመታዊ ክፍያዎችን ለመፈፀም፣ ንግድ ፈቃዶችን ለማውጣትና ለማደስ ገንዘብ ለመላክ ወዘተ በሚል ምክንያቶች ከቤትም ሆነ ከሚሰሩባቸው ቦታዎች ሰዎች የሚያደርጉት ዝውውር ከፍተኛ ነው። በመንገድ ላይ ከሚባክነው ጊዜ በተጨማሪ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። የሥራ ጫናው መብዛት ደግሞ ተገልጋዩ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዳያገኝ ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ ለወንጀል መበራከትም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። አንድ ተገልጋይ የተሟላ ማስረጃ ይዞ መቅረቡን በሰው የሚረጋገጥ ሲሆን ሰውኛ ስህተቶች ሊያጋጥሙ ይችላል። ዲጂታል አገልግሎት ግን ሁሉንም መሟላታቸውን ሳያረጋግጥ ወደሚቀጥለው አሠራር እንድትቀጥል ወይም ሌላ ተፈላጊውን አገልግሎት እንድታገኝ አይፈቅድልህም። በሌላ አነጋገር ከሰውኛ ስህተት የፀዳ በመሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ይጨምራል፤ ከተጭበረበሩ ሰነዶች የፀዳ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥረው የጊዜና ገንዘብ ብክነት በተጨማሪ የሚከፈለውን ከፍሎ ቶሎ ወደሥራ ለመመለስ በሚደረግ ጥድፊያ የትራፊክ አደጋ የመከሰቱ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው። እንደሚታወቀው ሀገራችን ከመንገድ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በሚደርሱ ተደጋጋሚ አካላዊና ቁሳዊ አደጋዎች ምክንያት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የሚቀጠፍ ከመሆኑም በተጨማሪ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ይጠፋል። ከአዲስ አበባ ፖሊስ በየጊዜው ከሚለቀቁ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በቂ የእግረኛ መንገዶች ካለመኖራቸው ጋር ተያይዞ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ በእግሩ የሚንቀሳቀስ መሆኑ አንዱና ዋንኛው ነው።
ዲጂታል የአሠራር ዘዴዎች እየተስፋፉ ከሄዱ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ይወገዳሉ። ቤት ቁጭ ብሎ ሥራውን መስራት የለመደ ሰው ጠዋት ተነስቶ በመንገድ ላይ በሚፈጠር የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት በርካታ ሰዓት መንገድ ላይ አባክኖ ቢሮ ገብቶ ግን ቤት ከሚሰራው የተለየ የማይሰራ ከሆነ ቢሮ ለመሄዱ አሳማኝ ምክንያት ሊኖረው አይችልም። በተለይ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች አልፎ አልፎ ከሚስተዋሉ አላስፈላጊ የሀብት መባከኖች አንፃር እነዚህን ሁሉ ማስቀረት የሚችል በመሆኑ የሀገር ሀብትን ከብክነት ያስቀራል።
ከዚህ አንፃር ኮቪድ 19 ዓለምአቀፋዊ ቀውስ ሆኖ በታሪክ ከመታወሱ በተጨማሪ ዓለምን በአዲስ አስተሳስብ መቅረፅ ስለቻለ በጎ ጎኑም ወደፊት አብሮ ይታይ ይሆን? ይህን ጊዜ የሚመልሰው ይሆናል።
(እንጠንቀቅ!! እጆቻችንን በሳሙና በሚገባ እንታጠብ ፤በእጆቻችን አፍና አፍንጫችን እንዲሁም ዓይኖቻችንን ከመነካካት እንቆጠብ፤ ማህበራዊ ርቀታችንን መጠበቅና የፊት ማስክ ማድረግ አንርሳ!!)
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2012
በእንዳለ አሰፋ