ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ የተደረገውን ረጅሙንና እጅግ ፈታኝ የሆነውን ትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ በድል አድራጊነት የፈጸመው የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባ የገባው የዛሬ 29 ዓመት ግንቦት 20 / 1983 ዓ.ም ነው። ዕለቱ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተስፋ፣ ጭንቀት፣ ስጋት እና ግራ መጋባት የሞላበት፤ የተዘበራረቀ ስሜት የተስተናገደበት ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ዕለቱ ልዩ ስፍራ ያለው ነው።
ስለዚህች ቀን ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም አፍላ ወጣቶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ በተለይም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ የከፈለው መስዋዕትነት እጅግ ከፍተኛና በታሪክም ትልቅ ስፍራ የሚይዝ ነው። ከ60ሺ በላይ የሆኑ የትግራይ ወድሞቻችንና እህቶቻችን ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ያለ ማንገራገር ሊመጣ ለተሰበኩት ዘመን ተስፋ ገብረዋል። ከዚህ አሀዝ ያላነሱም አካላቸውን መስዋዕት አድርገው ሰጥተዋል።
ይህም ሆኖ ግን ትልቁ እውነታ አዲስ አበባ የመግባቱ ጉዳይ የትግሉ አልፋና ኦሜጋ ያለመሆኑ ነገር ነበር። ከዚያ ይልቅ የመስዋዕትነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ድል መሆኑና የመስዋዕትነቱን ዘር ፍሬ መኸሩን ለመሰብሰብ በሕይወት የተረፈው ድሉን ያበሰረው ታጋይ የበለጠ የሚፈተንበት ሌ ላ ቀጣይ የትግል ምዕራፍ መኖሩ ነበረ።
ለትግሉ የተከፈለው ብዙ መስዋዕትነት ግቡ አዲስ አበባ መድረስና በቤተመንግሥት መሰየም አልነበረም፤ ይልቁኑ ትግሉ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ የተደረገ ትግል ከመሆኑ አንጻር ቀጣይ ብዙ ሥራዎች የሚጠብቁት ነበር። እንደ ትጥቅ ትግሉ የሕይወት መስዋዕትነት ባይጠይቅም ሕይወትን ሰማዕታቱ ለተሰዉለት አላማ መስዋዕት አድርጎ ማቅረብንና የዓላማ ጽናትን የሚጠይቅ ነበር።
ሰማዕቱ ሳይሰስቱ ሕይወታቸውን ዋጋ አድርገው የከፈሉለት ትግል ፍሬው በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠር፤ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦች ከመጡበት አስከፊ የጭቆና ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነፃ ወጥተው፤ በነፃነት እና በእኩልነት የሚኖሩባት ፍትህና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር መገንባት ነበር።
ይህ የሰማዕታቱ የሕይወት ራዕይ እንደታሰበውና እንደ ትጥቅ ትግሉ በድል ብስራት ሊጠናቀቅ አልቻለም። በአንድ በኩል የትጥቅ ትግሉ ድል ትግሉን በመሩት የፖለቲካ ልሂቃን ውስጥ የፈጠረው ያልተገባ መፋነን (ከልክ ያለፈ የአሸናፊነት መንፈስ) የፈጠረው የተዛባ ስሜት፤ ስሜቱ ያስከተለው የተዛባ አስተሳሰብ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሰማዕታቱን ደም ሀገርን የመግዛት ልዩ ካርድ አድርጎ የማየቱ እውነታ ትግሉንና መስዋዕትነቱን ፍሬ አልባ አድርጎታል።
ከትጥቅ ትግሉ ድል ማግስት ጀምሮ ወደ ሥልጣን የመጣው ቡድን ሰማዕታቱ የሕይወት ዋጋ የከፈሉለትን ዓላማ ትርጉም በማሳጣት በተለመደው የመጠላለፍ የፖለቲካ እርግማን ሁለንተናው ታስሮ ስለ ነፃነት እና እኩልነት፤ ስለ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉሮሮው እስኪደርቅ በየበረሀው፤ ተራራ ኮረብታው፤ በየሰፈር መንደሩ ሲሰብክ የነበረውን ስብከት ውጦ ማነው ባለተራ ወደሚያስብል የተረኝነት ባለአደራነት ተሸጋግሯል።
ለፍትህና ዴሞክራሲ የተከፈለው ዋጋ በጥሩ ቋንቋ እና በበለጠ የማስመሰል ብቃት የተካኑ ባለተራ አምባገነኖችን ወደ ሥልጣን ማምጣት አስችሏል። የነፃነት ጉዳይ «ላም አለኝ በሰማይ»፤ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳይ «ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ –» ዓይነት ሆኖ ዓመታትን ያስቆጠረ የባከነ ጊዜን ወልዷል።
ከብዙ መስዋዕትነትና (የደም ግብር) በኋላ የነፃነት፤ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳይ ዳግም ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ የሕዝብ ጥያቄ በመሆን ትውልድ ዳግም የሕይወት ዋጋ እንዲከፍልበት አድርጓል። ትውልድ ዳግም አደባባይ ወጥቶ የሚሞትበት የሕዝብ ጥያቄም ፈጥሯል። ትግሉ በአምባገነኖች ሥርዓት መቃብር ላይ ሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት አምጦ የማዋለጃ አቅም ሆኗል። የሆነውና ታሪክም የሚመሰክረው ይህንኑ ነው። በሌላ አነጋገር የጥሉ ውጤት አሮጌውን ወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ከመያዝ ያለፈ አልሆነም።
ባለፉት 27 ዓመታት ስለ ነፃነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ በተደረገ ትግል እና በተገኘ ድል ለነፃነት ግድ የሌለው፤ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ከቋንቋ ያለፈ ደንታ ቢስ የሆነ፤ በሀገሪቱ ታሪክ በተገለጠ ዘረፋ የደለበ የፖለቲካ ሥርዓት ከመፍጠርና እሱኑ ከማንቆለጳጰስ ያለፈ የሆነም የተደረገም ነገር የለም።
ይህንን ታሪካዊ እውነታ በትክክለኛ ገጽታው ልንረዳው ይገባል፤ ለዚህ የሚሆን ብርታት ያስፈልገናል። ለዚህም ዛሬ የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ በድል አጠናቀን በአሸናፊነት መንፈስና ተስፋ ያሰብነው የነፃነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ራዕያችን እውን ሆኖ ለማየት ከትናንቱ ምጣችን ብዙ መማር አለብን። ዛሬ በምናምጠው ምጥ የጨነገፈ ተስፋ እንዳንወልድና ቀጣይ ዘመናችንም የባከነ እንዳይሆን ከቀደመው ስህተት እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር መማር ይኖርብናል!