ግንቦት 20 በግልብ ትንተናና በፈጠራ ትርክት ድቡሽት ላይ የተመሰረተ አማጺና አንጋችን ለአገዛዝነት ያበቃ ዕለት ነው። ሀገራችን ዛሬ ለምትገኝባቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መባቻም ነው። እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ የገባንበት ቅርቃር አሀዱ የተባለበት ቀን ነው ማለት ይቻላል። አምባገነናዊውን የጊዜያዊ ወታደራዊ አገዛዝ /ደርግ/ን ገርስሶ በሌላ አምባገነንና አፋኝ አገዛዝ በመተካት አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ዕለት ነው። የተማሪዎችን አብዮት ቀምቶ ስልጣን የጨበጠ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ 70ሺህ የሚጠጉ ታጋዮች የተሰውለትን፣ ከ120ሺህ በላይ አካል ጉዳተኛ የሆኑለትን የነፃነት አብዮት ቤተሰባዊ በሆነ ቡድን ጠልፎና አግቶ ስልጣን በመዳፉ ያደረገበት ክፉ ቀን ነው። ግንቦት 20 ኤርትራንና ሕዝቡን እንድናጣ አበክሮ ሕዝበ ውሳኔ የተሰጠበት፣ የባሕር በር ያጣንበት፣ የ3ሺህ ዓመትና ከዚያ በላይ ታሪካችን ወደ 100 ዓመት የወረደበት፣ ጥንታዊው የሀገረ መንግሥት ታሪካችን የተካደበት፣ ስንቶች በዱር በገደሉ የተዋደቁለት ሰንደቅ ጨርቅ ተብሎ ዱቄት የተቋጠረበት፣ ጥላቻና ልዩነት የተቀነቀነበት፤ የጋራ ታሪክ፣ ብሔራዊ ጀግናና ምልክት /አይከን / እንዳይኖረን የታወጀበት፤ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነት የተወገዘበት ጥቁር ቀን ነው።
ግንቦት 20 የሀገር ሀብት በጥቂቶች እጅ የገባበት፣ እንደ ኤፈርት ያሉ ድርጅቶችና ቡድኖች እንዳሻቸው እንዲዘርፉ ካዘና የተከፈተበት፣ ለዘመናት የተገነቡ ተቋማትና እሴቶች እንዲወድሙ ደማሚት የተቀበረበት፣ ዜጎች እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የሚሰራ ተቋም የተመሰረተበት፤ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ሕዝብ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በሌሎች ማንነቶች እንዲከፋፈል የተሴረበት፣ በጎሳና በቋንቋ ብቻ የተመሰረተው የልዩነትና የጥል የባቢሎን ግንብ /ክልል/ መሰረተ ድንጋይ የተጣለበት፣ ሀገር ለብተና የታጨችበት፣ ሀገር በደም ካሳና በዕዳ የተያዘችበት፣ አናሳዎችና ህዳጣን በአፈሙዝ ብዙኃኑን ቀጥቅጠው የገዙበት፣ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የተፈጠረበት፣ ወዘተረፈ የኀዘን ቀን ነው። ታሪክ የአሸናፊው ነው እንዲሉ ይህ ሁሉ ቀውስ ውድቀት መወገዝ ሲገባው እንደ ድል በዓል የሚከበረበት ቀን ነው።
ግንቦት 20 የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሳይውል ሳያድር ወደ ቀቢጸ ተስፋነት የቀየረ መናጢ ቀን ነው ማለት ይቻላል። ለ17 ዓመታት በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች አምራቹና ወጣቱ የሰው ኃይል በግዳጅና በወዶ ገብነት ለጦርነቱ ተማግዷል። የሀገር ሀብት፣ ጥሪት፣ ኢኮኖሚና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። የሀገሪቱ እድገት አሽቆልቁሏል። ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ማህበራዊ ቀውስ ተንሰራፍቷል። የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት «ትግል» ገና ከጅምሩ መጨንገፉ ነው። ነፃነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ እኩልነትንና ዴሞክራሲያዊነትን ያዋልዳል ተብሎ የተጠበቀው ጽንስ ውርዴ ሆኖ ቀርቷል። ግንቦት 20 በተለይ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ እስከ ለውጡ ዋዜማ በፅኑ ሕሙማን ማቆያ /አይ ሲ ዩ/ በጠመንጃ በአፈና እና በከፋፍለህ ግዛ የቅኝ ገዥዎች መርህ ቆዬ እንጂ የተነሳለትን አላማ ገና ከመነሻው የዘነጋ ስለነበር ህልው አልነበረም።
በግንቦት 20፣ ለቀደሙት 27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የነበረው ገዥ ፓርቲ ትህነግ/ኢህአዴግ መመጻደቂያዎች ቀዳሚው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ፤ በማንነታቸው እንዲኮሩ አድርጌያለሁ የሚል ቢሆንም የግንባሩ አስኳል የሆነው ትህነግ በሚመራው የትግራይ ክልል በዞኖች እንኳ እኩልነት አልነበረም። ሕዝቡም በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ ዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያውያን ተለይቶ በጭቆና ፍዳውን እየበላ ይገኛል። ልጆቹን ገብሮ ያለጧሪ ቀባሪ ቀርቶ ለሥልጣን ያበቃው ቤተሰባዊ ቡድን ዛሬም ከትክሻው የመውረድ ፍላጎት የሌለውና ይህ አልበቃ ብሎት ኢኮኖሚውን ከጅምላ ንግድ እስከ ጉልት ተቆጣጥሮ ፤ መሬቱን ፣ የተፈጥሮ ሀብቱንና ጉልበቱን እየዘረፈ ለምሬትና ለብሶት ዳርጎታል። ካለፉት ዘጠኝ ቀናት ወዲህ ግን «ፈንቅል ! » ብሎ ጭቆና ፣ አፈና፣ ዘረፋና በስሜ መነገድ ይብቃ እያለው ነው። ትጥቅ የጀመረበት ቀዬ ሳይቀር በቃ ! ብሎታል። ማጣፊያው አጥሮታል። በልጆቹ አጥንትና ደም ተረማምዶ ለሥልጣን የበቃበትን ሕዝብ በአውራጃና በጎጥ የሚከፋፍል፣ የሚያፍን፣ የቁም እስረኛ የሚያደርግ ነፃ አውጭ አስኳል የሆነበት ድርጅት በምን ተጠየቅና አመክንዮ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት የሚያረጋግጠው ? በእርግጥ የይስሙላና በእሱ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረት አስመሳይ እኩልነት አልነበረም ማለት አይደለም። በመናጆዎቹ በእነ ደኢህዴግ፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና በአጋር ፓርቲዎች መካከልና እኩልነትንና ውስጠ ድርጅታዊ ዴሞክራሲና ነፃነትን ሳያረጋግጥ በየት አልፎ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ የሚለው !?
ማለት ይቻላል። ለ17 ዓመታት በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች አምራቹና ወጣቱ የሰው ኃይል በግዳጅና በወዶ ገብነት ለጦርነቱ ተማግዷል። የሀገር ሀብት፣ ጥሪት፣ ኢኮኖሚና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል። የሀገሪቱ እድገት አሽቆልቁሏል። ድህነት፣ ኋላ ቀርነትና ማህበራዊ ቀውስ ተንሰራፍቷል። የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ዋጋ የተከፈለለት «ትግል» ገና ከጅምሩ መጨንገፉ ነው። ነፃነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ እኩልነትንና ዴሞክራሲያዊነትን ያዋልዳል ተብሎ የተጠበቀው ጽንስ ውርዴ ሆኖ ቀርቷል። ግንቦት 20 በተለይ ከ1987 ዓ.ም ወዲህ እስከ ለውጡ ዋዜማ በፅኑ ሕሙማን ማቆያ /አይ ሲ ዩ/ በጠመንጃ በአፈና እና በከፋፍለህ ግዛ የቅኝ ገዥዎች መርህ ቆዬ እንጂ የተነሳለትን አላማ ገና ከመነሻው የዘነጋ ስለነበር ህልው አልነበረም።
በግንቦት 20፣ ለቀደሙት 27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የነበረው ገዥ ፓርቲ ትህነግ/ኢህአዴግ መመጻደቂያዎች ቀዳሚው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ፤ በማንነታቸው እንዲኮሩ አድርጌያለሁ የሚል ቢሆንም የግንባሩ አስኳል የሆነው ትህነግ በሚመራው የትግራይ ክልል በዞኖች እንኳ እኩልነት አልነበረም። ሕዝቡም በአንድ ለአምስት ተጠርንፎ ዛሬ ድረስ ከኢትዮጵያውያን ተለይቶ በጭቆና ፍዳውን እየበላ ይገኛል። ልጆቹን ገብሮ ያለጧሪ ቀባሪ ቀርቶ ለሥልጣን ያበቃው ቤተሰባዊ ቡድን ዛሬም ከትክሻው የመውረድ ፍላጎት የሌለውና ይህ አልበቃ ብሎት ኢኮኖሚውን ከጅምላ ንግድ እስከ ጉልት ተቆጣጥሮ ፤ መሬቱን ፣ የተፈጥሮ ሀብቱንና ጉልበቱን እየዘረፈ ለምሬትና ለብሶት ዳርጎታል። ካለፉት ዘጠኝ ቀናት ወዲህ ግን «ፈንቅል ! » ብሎ ጭቆና ፣ አፈና፣ ዘረፋና በስሜ መነገድ ይብቃ እያለው ነው። ትጥቅ የጀመረበት ቀዬ ሳይቀር በቃ ! ብሎታል። ማጣፊያው አጥሮታል። በልጆቹ አጥንትና ደም ተረማምዶ ለሥልጣን የበቃበትን ሕዝብ በአውራጃና በጎጥ የሚከፋፍል፣ የሚያፍን፣ የቁም እስረኛ የሚያደርግ ነፃ አውጭ አስኳል የሆነበት ድርጅት በምን ተጠየቅና አመክንዮ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን እኩልነት የሚያረጋግጠው ? በእርግጥ የይስሙላና በእሱ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረት አስመሳይ እኩልነት አልነበረም ማለት አይደለም። በመናጆዎቹ በእነ ደኢህዴግ፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና በአጋር ፓርቲዎች መካከልና እኩልነትንና ውስጠ ድርጅታዊ ዴሞክራሲና ነፃነትን ሳያረጋግጥ በየት አልፎ ነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት አረጋግጫለሁ የሚለው !?
ሌላው መመጻደቂያው በግንቦት 20 ሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ፣ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሪፐብሊካዊ በሆነ ሥርዓት እንድትመራ ጥርጊያውን ማመቻቸት ተችሏል የሚለው ነው። በቀደሙት 27 የግፍ ዓመታት ሕገ መንግሥቱ ምሰሶ ያደረጋቸው የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት፣ የሕዝቡ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን፣ የክልሎችን ራስን የማስተዳደር ሥልጣን፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን ፣ ወዘተረፈ የሚደነግጉ ድንጋጌዎቹም ሆነ ሌሎች አንቀጾች የኢህአዴግ አዛዥና ናዛዥ የነበረው ትህነግ በአደባባይ ሲጥሳቸው ስለነበር፤ «ሕገ መንግሥት የታተመበትን ወረቀት ያህል እንኳ ዋጋ አጣ ፤» እስከማለት ተደርሶ ነበር። በአምስቱም የይስሟላ ምርጫዎች ኮሮጆ በመገልበጥ፣ በማጭበርበርና በአፈ ሙዝ የሕዝቡ ድምጽ በጠራራ በመዘረፉ የሕዝቡን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት በተደጋጋሚ በመጣሰ ሲከሰስ መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሌላው በሀገሪቱ ታሪክ ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚል መንግሥት በገዛ ዜጋው ላይ ዘግናኝና ተቋማዊ በሆነ አሠራር የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየረገጠ፣ እየጣሰና እየገፈፈ ከፍ ሲልም ሲገድል፣ ዘቅዝቆ ሲገርፍ፣ ጥፍር ሲነቅል፣ ወስባዊ ጥቃት ሲፈፅምና ሲያንኮላሽ የነበረ ቡድን ስለ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት የማውራት ሕጋዊም ሞራላዊም ልዕልና የለውም።
ግንቦት 20 የራስን አስተዳደር በራስ የመወሰን መብት፣ እኩል የመልማት ዕድል የፈጠረ እና ሁሉም ክልሎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል እንዲወስኑ ያስቻለ ስለ መሆኑን ተደጋግሞ ይነገራል። ሆኖም እኔ አውቅላችኋለሁ እያለ ክልሎች መሪያቸውን የመምረጥ መብት የገፈፈና በጀታቸውን እንዳሻው ሲሸነሽን የኖረ አሠራርና አደረጃጀት በነበረበት አግባብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አጎናጽፏል ቢባል ከልግጫ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። ለዚህ ነው አገዛዙ ፌዴራላዊም፣ ዴሞክራሲያዊም፣ ሪፐብሊክም አልነበረም የሚል የሰላ ትችት የሚሰነዘርበት። ለውጡ ከባተ ጀምሮ ግንቦት 20 ይከበር አይከበር የሚለው ሙግትና እሰጥ አገባ ገፍቶ የመጣው። ወንድም ወንድሙን ገድሎ ሥልጣን የያዘበት ፤ ሌላ አምባገነን በመንበሩ የተተካበት ሆኖ እንዴት ክብረ በዓል ይሆናል የሚል ክርክር የተነሳበት፤ መስከረም 2 በግንቦት 20 ተተካ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ እስከ ማለት የተደረሰበት። ለዚህ ይመስላል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግንቦት 20 «በዓል» አከባበርን እንደገና የበየኑት፤ ትርክቱንም ያረቁት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com