እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ፣ የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት/ጦር በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ:: ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር:: ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪካን ምድር ለቅቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ:: ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር::
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም:: ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃንኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉሥ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና ‹‹የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ›› በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው:: ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ:: ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ::
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች:: ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች::
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም:: ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ጫካው፤ ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ:: የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራችው ኢትዮጵያም ሉዓላዊቷን በመዳፈር በመዳፏ ሥር ሊያስገባት ያሰበውን ኃይል ድል አድርጋ መለሰችው:: ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ነበሩ::
ኃይለማርያም ከደጃዝማች ማሞ ኃይሌ እና ከወይዘሮ ወለተየስ ወልደሚካኤል በ1905 ዓ.ም ተወለደ:: በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያ ስትወር ወደ ማይጨው ዘምቶ ከጠላት ጋር ሲፋለም ቆሰለ:: ከማይጨው ዘመቻ ተመልሶ ጫጫ፣ ኤጀርሳ ሞጆ ከሚገኘው ቤቱ እረፍት ላይ በነበረበት ወቅት የጠላት ጦር ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ እንደሆነ ተነገረው:: ልጅ ኃይለማርያምም አመቺ ስፍራ ይዞ መጠባበቅ ጀመረ:: ሚያዝያ 26 ቀን 1928 ዓ.ም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ደጃዝማች ኃይለማርያምና አርበኞቻቸው ጫጫ፣ ሱኪ ሱራቢ በተባለው አካባቢ በጠላት ጦር ላይ አደጋ ጥለው፤ ብዙ ካሚዮኖችን ሰብረው በውስጣቸው የነበሩትን 140 የጠላት ወታደሮች ገድለው ሰባት ማረኩ:: ከወታደሮች በተጨማሪም ብዙ የጦር መሣሪያ፣ የሕክምና ቁሳቁሶችንና አልባሳትን ማረኩ::
ደጃዝማች ኃይለማርያምም የተማረኩትንና ሲሸሹ የተያዙትን ወታደሮች በሰብዓዊ ርህራሄ አስተያየት
ተመልክቶ ደብረ ብርሃን ለሚገኘው የፋሺስት ጦር አዛዥ ላከለት:: ፋሺስቱ የጦር አዛዥም ‹‹ … በወታደሮቻችን ላይ ያደረግከውን በደል በይቅርታ አልፈነዋልና ወደ እኛ ግባ፤ ባልደረባም ደጃዝማች ወዳጄን ሰጥተንሃል …›› የሚል መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ላከለት::
ደጃዝማች ኃይለማርያም ለተፃፈላቸው ደብዳቤ መልስ ሲሰጡ ‹‹ … የእኔ መግባት እስከደብረ ብርሃን ብቻ የሚወሰን አይደለም:: ይኸውም እንድገባ በምትጠባበቁት ጊዜ ሳይሆን በማትጠባበቁበት ጊዜ ሊሆን ይችላል:: መግባቴም ይህን ያህል ተፈላጊ ከሆነ በመንገዱ ላይ ያለውን እንቅፋት በማስወገድ ጥርጊያው እስከ አዲስ አበባ ድረስ እንደሚዘልቅ ይሆናል:: ይህንን ሲፈፀም ለማየት እግዚአብሔር የፈቀደለት ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባለዕድል ሊሆን ይችላል …›› በማለት የፋሺስት ጦር እርሳቸውን በዘዴ ምርኮኛ ሊያደርግ ማሰቡ ከንቱ እንደሆነ አሳወቁት::
ከጫጫ፣ ሱኪ ሱራቢው ድላቸው ጥቂት ቀናት በኋላ ደጃዝማች ኃይለማርያም ወደ ሰላሌ ሄዱ:: እግረ መንገዳቸውንም በሱኪ ሱራቢው ውጊያ ላይ ከተማረኩት የፋሺስት ወታደሮች መካከል ወደ ደብረ ብርሃን ያልተላኩትን የካቶሊክ አስተማሪ ለነበሩ መነኩሴ አስረከቡ:: ደጃዝማች ኃይለማርያም በውጊያ ላይ የማረኳቸውን ምርኮኞች ወደ ደብረ ብርሃን መላካቸውም ሆነ ለመነኩሴው ማስረከባቸው ለሰብዓዊነት የነበራቸውን ቦታ እንዲሁም ‹‹እኛ የሰለጠንን ስለሆንን ያልሰለጠነውን ሕዝብ ልናሰለጥልን መጣን›› ብለው አረመኔያዊ ተግባራትን ሲፈፅሙ ከነበሩት ፋሺስቶች በተቃራኒ የነበራቸውን ላቅ ያለ ሰብዕናና የሞራል ከፍታ የሚያሳይ ተግባር ነው::
ከቀናት በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ እና ሽንኩርት ሄደው ከፊታውራሪ ዘውዱ አባ ኮራን እና ከደጃዝማች አበራ ካሣ ጋር ተገናኝተው ስለቀጣዩ ፍልሚያ ተወያዩ:: ምክክራቸውን በመቀጠልም አዲስ አበባ ገብተው በጠላት ላይ ጥቃት ስለሚከፍቱበት ሁኔታ ተነጋገሩ:: ይሁን እንጂ በቅንጅት ጉድለት ምክንያት ዘመቻው ባለመሳካቱ እነደጃዝማች አበራ ሕይወታቸውን መስዋዕት አደረጉ:: ከደጃዝማች አበራ ሞት በኋላም ደጃዝማች ኃይለማርያም ለፋሺስት አስተዳደር የጎን ውጋት ሆነው ቀጠሉ:: የፍቼና አካባቢው የፋሺስት ጦር አዛዥ ‹‹ … የምህረት እጃችንን ዘርግተን እንጠብቅሃለን፤ ግባ …›› የሚሉ ተደጋጋሚ መልዕክቶችንለደጃዝ ማችኃይለማርያም ቢልክባቸውምደጃዝማች ኃይለማርያምከአቋማቸው
ፍንክችአላሉም::የፋሺስት ወታደሮችንበሚረዱባላባቶች ላይምጥቃት እየከፈቱ ምርኮ ያገኙ ነበር::
ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ጥር ስድስት ቀን 1929 ዓ.ምበከፍተኛ የፋሺስት ሹማምንት ከተመራ ጦር ጋር ውጊያ ገጥመው ድልበማድረግ ብዙ ምርኮ አገኙ:: ጥር 11 ቀን 1929 ዓ.ም ያያ ቀጨማ በተባለው ስፍራ በተደረገ የሙሉ ቀን ውጊያ የደጃዝማች
ኃይለማርያም አርበኞች በብዙ ጀኔራሎች እየተመራ
የመጣውን የፋሺስት ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳያስተርፉ ደመሰሱት:: ጥር 21 ቀን 1929 ዓ.ም በዚያው ቦታ ላይ በተደረገ ውጊያ አርበኞቹ አሸንፈው የፋሺስት ጦር ወደ ፍቼ ተመለሰ:: የደጃዝማች ኃይለማርያም እና የባላምባራስ ዘውዴ አባፈርዳ አርበኞች የካቲት 11 ቀን 1929 ዓ.ም ከፋሽ ስት ወገን ተሰልፎ ሲዋጋ ከነበረው ከልጅ ዓለሙ ኤጀርሳ ጋር ሙገር፣ በቾ ጎንጋ ላይ ውጊያ ገጥመው ድል አደረጉት:: መጋቢት 14 ቀን 1929 ዓ.ም ደግሞ የደጃዝማች ኃይለማርያም እና የባላምባራስ ዘውዴ አርበኞች በባንዳዎች መሪነት ሊያጠቃቸው የመጣውን የፋሺስት ኃይል ድል አድርገው መለሱት:: ከቀናት በኋላ የተሰነዘረባቸውን ተመሳሳይ ጥቃት በድል ተወጡት:: እነደጃዝማች ኃይለማርያም በየቀኑ ያስመዘገቧቸው ድሎች የጦር መሣሪያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን በምርኮ እንዲያገኙ አስችለዋቸዋል::
ሚያዝያ ስምንት ቀን 1929 ዓ.ም አርበኞቹ ወደነበሩበት ዮሎ ሚካኤል ወደተባለው ቦታ የመጣው የጠላት ጦር አውሮፕላን በአርበኞች ተመትቶ ወደቀ፤ በውስጡ የነበሩት ወታደሮችም አለቁ:: ሚያዝያ 11 ቀን 1929 ዓ.ም 15ሺ የሚገመት የፋሺስት ጦር ሞረት ወደተባለው ስፍራ አምርቶ በአርበኞቹ ላይ ጥቃት ከፈተ:: እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በዘለቀው ውጊያ ድሉ የአርበኞቹ ሆኖ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን ማረኩ:: በዚያው ሰሞን ዓሊዴራ በተባለው ስፍራ ላይ በባንዳዎች ከተመራ የጠላት ጦር ጋር ውጊያ ገጥመው ድል አደረጉ::
ግንቦት አንድ ቀን 1929 ዓ.ም በባንዳዎች የተመራ የጠላት ጦር በደጃዝማች ኃይለማርያም ላይ ድንገተኛ አደጋ ጥሎ አቆሰላቸው:: ግራ ዓይናቸውና ቀኝ እጃቸውን ክፉኛ ተጎዱ:: መንፈሰ ጠንካራው ደጃዝማች ኃይለማርያም ግን ‹‹በአልጋ ተሸክማችሁ ወደ ጦርነት ቦታ ውሰዱኝ›› ብለው አዘዙ:: አርበኞቻቸውም የደጃዝማቹን ትዕዛዝ ፈፀሙ:: ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ማለት ክፉኛ ቆስለው ቃሬዛ ላይ ሆነው መትረየስ እየተኮሱ ጠላትን ድል ያደረጉ ሰው ናቸው!
እነደጃዝማች ኃይለማርያም በሰኔና በሐምሌ 1929 ዓ.ም ከጠላት ጋር ያደረጓቸውን ውጊያዎች በድል በመወጣት በርካታ ስፍራዎችን በቁጥጥራቸው ሥር አደረጉ፤ ብዙ የጦር መሣሪያ፣ ወታደርና ቁሳቁሶችን ማረኩ:: ከነዚህ ውጊዎች መካከል በጀኔራል ቤሊኒ እና በራስ ኃይሉ የተመራው ግዙፍ የፋሺስት ጦር ከነደጃዝማች ኃይለማርያም ጋር ያደረገው ፍልሚያ የሚጠቀስ ነው::
በጀግንነታቸውና በጦር አመራር ስልታቸው እጅግ የተደነቁትና የተከበሩት አርበኛው ደጃዝማች ኃይለማርያም በጠላት ጦር ላይ ባደረሱት ተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት የፋሺስት ጦር ደጃዝማች ኃይለማርያምን ከዋነኛ ጠላቶቹ መካከል አንዱ አደርጎ ፈርጇቸው ነበር:: በደብረ ብርሃንና አካባቢው የነበረው የፋሺስት ጦር ደጃዝማች ኃይለማርያምን መቋቋም ስላልቻለ በየጊዜው በርካታ ወታደርና ትጥቅ ከሌሎች አካባቢዎች ለመውሰድ ተገድዶ ነበር::
ዕለተ ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 ቀን 1930 ዓ.ም ለደጃዝማች ኃይለማርያምና ለአርበኞቻቸው መልካም ቀን አልሆነችላቸውም:: በዕለቱ ቡልጋ፣ ኩሶ ደብር በተባለው ስፍራ በተደረገው ውጊያ ደጃዝማች ኃይለማርያምና አርበኞቻቸው እንደለመዱት በጀግንነት ሲዋጉ ዋሉ:: ለሁለት ዓመታት ያህል የፋሺስትን ጦር ሲደመስሱ የነበሩት ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ በዚህ ውጊያ ተመትተው ሕይወታቸው አለፈ::
ደጃዝማች ኃይለማርያም አርበኞቻቸውን ‹‹እኔ እቀድምላችኋለሁ፤ እናንተም ፍለጋዬን ተከተሉ›› በማለት የቆራጥነት መንፈስ ያሳዩቸው ነበር:: ጀግንነታቸውም በጠላት ጭምር ተመስክሮለታል:: ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ እንኳ ‹‹ኃይለማርያም ማሞ የጀግኖች ጀግና ነው:: የጦር ስልትም አዋቂ ነው:: ከጦር ትምህርት ቤት ሳይገባ በእድል ያገኘው ከተፈጥሮ ፀባዩ የተቀረፀለት ጀግና ሰው ስለሆነ ከፍ ባለ አድናቆት የምመለከተው ነው:: ይህ ሰው በእጄ ቢገባ እንኳ እጁን ስሜ በቀኜ አስቀምጠው ነበር እንጂ ‹ጠላት ነው› ብዬ አልበቀለውም ነበር›› ብሎ እንደመሰከረላቸው የውስጥ አርበኛ ከነበረው አስተርጓሚው ለመረዳት ተችሏል::
ደጃዝማች ኃይለማርያም በግል ባህሪያቸው ጨዋ፣ ከሰው ጋር መግባባትን የሚወዱ፣ ፈገግታቸው የሚማርክ፣ የቀደምት ጀግና ኢትዮጵያውያንን ታሪክ የሚያወድሱ፣ ስለጀግንነት ታሪክ መስማት የሚወዱ … በአካላዊ ቁመናቸው ደግሞ መልከ መልካም፣ አቋቋማቸው የተስተካከለ፣ ቆፍጠን ያሉና በፍጥነት መራመድ የሚወዱ … ሰው ነበሩ::
ለደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ጀብድና ጀግንነት ከተገጠሙ ግጥሞች መካከል …
ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ይኸንን ሶላቶ ነዳው እንደበሬ።
መተኮሱንማ ማንም ይተኩሳል፣
ኃይለማርያም ማሞ አንጀት ይበጥሳል::
ኃይለማሪያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ፈረሱን እንደሰው አስታጠቀው ሱሬ::
ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ ፣
እያላጋው መጣ ነጬን ከነጭ በሬ ::
እንስራው ቢሰበር ይተካል ግመሞ ፣
ከነሚስቱ ተኳሽ ኃይለማርያም ማሞ ::
እንስራ ሲሰበር ይሉታል ገመሞ ፣
ከናሽከሩ ተኳሽ ኃይለማርያም ማሞ::
ሴቶች ተሰብሰቡ ኑ ጠላ ቅመሱ ፣
እንደጎፍን እናት እንድትጠነስሱ ::
ፋሺስት ተሰብስቦ ሲጫወት ገበጣ ፣
ያባጎፍን አሽከር ጅምአፍራሹ መጣ … የሚሉት ይጠቀሳሉ::
የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ደብረ ብርሃን ከተማ ውስጥ በስማቸው ትምህርት ቤት ተገንብቶላቸዋል:: አዳማ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታልም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል:: አዲስ አበባ ከተማ ውስጥም በስማቸው የተሰየመ መንገድ ይገኛል:: ከዚህ በተጨማሪም፣ 75ኛው የአርበኞች ድል መታሰቢያ ሲከበርም ከሌሎች 25 ታላላቅ አርበኞች ጋር በስማቸው የመታሰቢያ ቴምብር ታትሞላቸዋል:: ይሁን እንጂ እነዚህ መታሰቢያዎች ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ ለኢትዮጵያ ከከፈሉት ዋጋ አንፃር እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው::
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
አንተነህ ቸሬ