
ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት፡፡ በየዘመናቱ የሀገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰውና ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉአላዊነት አስጠብቀዋል፤ለተተኪው ትውልድም አስረክበዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የጀግንነት መገለጫዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ አትሌቲክስ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሰማሩበት የሩጫ መስክ ሁሉ አሸናፊ በመሆን የሀገራቸውን ባንዲራ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ደምቃ እንድትታይ መተኪያ የሌለው ሚና ተጫውተዋል፡፡ይህን ገድል ከፈጸሙ ታሪክ የማይረሳቸው አትሌቶች መካከልም አትሌት ንጉሴ ሮባ አንዱ ነው፡፡
አንጋፋው አትሌትና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ንጉሴ ሮባ የመኖር ግዳጃቸውን ፈጽመው ከእዚህ ዓለም ከተለዩ ድፍን 32 ዓመት አስቆጥረዋል። በወቅቱ በዓለም ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎቻቸውን እና ታሪካቸውን ሲዘግቡ ቆይተዋል። እኛም እኚህ የአትሌቲክስ ስፖርት ጀግናው በሕይወት ሳሉ ምን ሠርተው አለፉ በማለት ገድላቸውን ለመዳሰስ ፈለግን ፡፡
አሰልጣኝና አትሌት ንጉሴ ሮባ ከአባታቸው ቀኛዝማች ሮባ ሌንጅሶና ከእናታቸው ወ/ሮ አበበች በሻህ በቀድሞ ሐረር ጠቅላይ ግዛት /በአሁኑ ሶማሌ ክልል/ ጅግጅጋ አውራጃ ፈራኤድ በሚባል ወረዳ በ1928 ዓ.ም ተወለዱ፡፡
በለጋ እድሜያቸው ወደ አባታቸው ትውልድ አካባቢ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ከሔዱ በኋላ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ አዲስ አበባ ታላቅ ወንድማቸው ቀኛዝማች ኃይሌ ሮባ ጋር በመምጣት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ተፈሪ መኮንን፣ በአሁኑ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤት ተምረዋል። ከእዚያም በንግድ ሥራ ኮሌጅ በሴክሬታሪያት ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ለሦስት ዓመታት ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ከእዚያም በቺኮዝሎቫኪያ ታዋቂው የቻርለስ ዩኒቨርሲቲ በአካል ማሰልጠኛና ስፖርት /ፊዚካል ኢጂኬሽን/ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
አትሌት ንጉሴ ሮባ የንግድ ሥራ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በርፓ በሚባል አስመጪና ላኪ ኩባንያ ተቀጠሩ።በ1999 ዓ.ም የመጀመሪያው የኮንፌዴሬሽኑ ተቀጣሪ ጸሐፊ ሆኑ፡፡ በመቀጠልም የኮንፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት የቦክስ የአትሌቲክስና የብስክሌት ፌዴሬሽኖችን ካቋቋሙ በኋላ በበጀት እጥረት የተነሣ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመዛወር ከጥር 1 ቀን 1950 እስከ 1953 ሰኔ 30 ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመምህርነት ሠርተዋል፡፡
አትሌት ንጉሴ ሮባ ከመጋቢት 1 ቀን 1953 እስከ ሰኔ 30 ቀን 1953 ዓ.ም በመድኃኒዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ሥራቸውን አቋርጠው እንደገና ለ6 ዓመታት ከላይ በአጋሮ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከተመለሱ በኋላ ከሐምሌ 10 ቀን 1960 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን በአትሌቲክስ ስፖርት ኤክስፐርትነት ሠርተዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በአዋጅ ፈርሶ ወደ አካል ማሰልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን ከተለወጠ በኋላ ቀደም ሲል በነበራቸው ማዕረግ ዕድሜያቸው ለጡረታ ደርሶ እስከተገለሉበት መስከረም 30 ቀን 1985 ዓ.ም በከፍተኛ ዋና አሰልጣኝነትና በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እንዲሁም በአትሌቲክስ ስፖርት ዋና አማካሪነት ለ25 ዓመት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ በቅንነትና በታማኝነት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን ያገለገሉ ታላቅ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ፡፡
ከወጣትነታቸው ጀምሮ ለስፖርት የተፈጠሩት አቶ ንጉሴ ሮባ በት/ቤት ዕውቅ ሯጭ፣ ዝላይ ወርዋሪና የእግር ኳስ ተጫዋች ነበሩ። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1956 ዓ.ም አውስትራሊያ፣ ሜልቦርን ኦሎምፒክ ሲካፈል በ100 እና 200 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያን በመወከል ተወዳዳሪ አትሌት ነበሩ።እንዲሁም ኢትዮጵያ በሮም ኦሎምፒክ ማራቶን በአበበ ቢቂላ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ አትሌት ንጉሴ ሮባ በ100 እና በ200 ሜትር በመወዳደር ማጣሪያውን ሳያልፉ ተመልሰዋል። ከአትሌቲክስ ስፖርት ውጭም በእግር ኳስ ለዩኒቨርሲቲ በግብ ጠባቂነት፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በአጥቂና በተከላካይ ቦታ በመጫወት ሁለገብ ስፖርተኛ ነበሩ፡፡
ዕውቁ የአትሌቲክስ ስፖርት ጀግና ንጉሴ ሮባ ከተወዳዳሪነት ወደ አሰልጣኝነት በመዘዋወር የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ማሰልጠን የጀመሩት ኢትዮጵያ ለአራተኛ ጊዜ በተካፈለችበት ከሜክሲኮ ኦሎምፒያ ጀምሮ ነው። በወቅቱ የኦሎምፒክ ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ ለሦስት ተከታታይ ኦሎምፒክ በማራቶን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኛል ተብሎ ዓለም በሚጠብቅበት ጊዜ ያልታሰበው ጀግና ማሞ ወልዴ 42.195 ኪሎ ሜትሩን በአንደኝት ሲያጠናቅቅ ንጉሴ ሮባ አሰልጣኝ ነበሩ። በእዚህ ወቅት አሸናፊውን ማሞ ወልዴን በደስታ እምባ ነበር ንጉሴ ሮባ ያጀቡት።
አበበ ቢቂላ ባይሳካለትም ማሞ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ በማሸነፍ ሰንደቅ ዓላማዋ ከበለፀጉ ሀገሮች በላይ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ መዝሙርዋም ሲዘመር በመላ ዓለም ሕዝብ ጆሮ እንዲገባ ተደርጓል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በማራቶን በተከታታይ በማሸነፏ ስምዋ በኦሎምፒክ መዝገብ በወርቅ ተጽፎ ለዘላለም እንዲቀመጥ ተደርጓል።ንጉሴ ሮባም ዕድለኛ አሠልጣኝ በመሆን ተወድሷል።አትሌት ማሞ ወልዴ ከማራቶን ሌላ በ10ሺ ሜትር ተወዳድሮ በጥቂት ሰኮንድ ተቀድሞ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ አግኝቷል። በታሪክም አንድ አትሌት በአንድ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ሁለት ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያ ሲሆን፤ ንጉሴ ሮባም ዕድለኛ አሠልጣኝ እንዲሆን በሩ ተከፍቶለታል፡፡
ጀርመን ሙኒክ በተደረገው ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ አሠልጣኝ በመሆን ማሞ ወልዴ በማራቶን ምሩፅ ይፍጠር በ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ሲያገኙ አትሌት ንጉሴ ሮባ አሠልጣኝ ነበሩ። ካናዳ ሞንትሪያል በተዘጋጀው ኦሎምፒክ አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ጀግኖች አትሌቶች በማሰልጠን ቢዘጋጁም በዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ሳትካፈል ቀርታለች። በሩሲያ በተዘጋጀው 22ኛ ኦሎምፒያድ ጀግናው ንጉሴ ሮባ ከምንጊዜውም በላይ ጀግኖች አትሌቶችን በማዘጋጀት ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺ እና 5 ሺህ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ፣ መሐመድ ከድር በ10ሺ ሜትር እሸቱ ቱራ በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ሦስተኛ በመሆናቸው የነሐስ ሜዳሊያ በአንገታቸው ሲጠለቅ የአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ገድል እጅግ ከፍተኛ ነበር። ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱም ከፍተኛ የሕዝብ አቀባበልና ከበሬታ ተጐናጽፈዋል።
ምንም እንኳ ዓለም በሁለት ጐራ ተከፍላ ኢትዮጵያና መሰሎቿ ከሎስአንጀለስ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ሲዑል ኦሎምፒኮች ባትካፈልም አቶ ንጉሴ ሮባ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን አባል በመሆናቸው በቦታው በክብር ተገኝተው ውድድሩን እንደተመለከቱ ይነገራል። ባርሲሎና ኦሮምፒክ ሲካሄድ አትሌት ንጉሴ ሮባ አሠልጣኝና አማካሪ እንዲሁም የአትሌቲክስ ቡድን መሪ ነበሩ፡፡
አትሌት ንጉሴ ሮባ በአሰልጠኝነት ኢትዮጵያን ባገለገሉበት ዘመን በአጠቃላይ ሦስት ወርቅ፣አንድ ብር እና አምስት ነሐስ ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል። ንጉሴ ሮባ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ፣በዓለም ሀገር አቋራጭ ፣በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድትካፈል ከማድረጋቸውም በላይ ብዙ ሜዳሊያዎችና ዋንጫዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበት የአረንጓዴ ጐርፍ ስም ያጐናፀፉን ጀግናው አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ከሻምበል ማሞ ወልዴ ጀምሮ እስከ እነ ደራርቱ ቱሉ ድረስ ከ80 በላይ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያተረፉትን ወንድና ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሳይቷል።ለእዚህ አስተዋፅኦ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽን፣ከዓለም አቀፍ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣በተለይም ከቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኮሌኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅ የሀገራችን ከፍተኛ የጥቁር ዓባይ ኒሻን ከመሸለማቸውም በላይ ከፍተኛ ምስጋና አግኝተዋል፡፡
ሮተርዳም በተካሄደው ማራቶን ውድድር የመቶ አለቃ በላይነህ ዴንሳሞ 2፡06፡50 ሰዓት በመፈጸም የዓለም ክብረወሰን በሰበረበት ጊዜ አትሌት ንጉሴ ሮባ ከጀርባው ሆኖ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረጋቸው አወዳዳሪ አካል ለሁለቱም ልዩ አውቶሞቢል ሸልሟቸዋል፡፡
እንዲሁም በአትሌቲክስ ስፖርት ባስመዘገቡበት ውጤት በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማህበር “IAAF” የቬትራን የረጅም ጊዜ አገልግሎት ፒንና ዲፕሎማ ተሸልመዋል።
ሆኖም ጀግና ቢሞት ታሪኩ ዘላለማዊ ሆኖ ይቆያል ቢባልም አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ይህንን ሁሉ ውለታ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ቢያበረክቱም ላለፉት 32 ዓመታት ተረስተው ቆይተዋል።ይህ ታሪክ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ባለቤታቸው ወ/ሮ ልዩ ወርቅ መንገሻ ለሥራቸው ልዩ ሐውልት እንዲሆን የአትሌት ንጉሴ ሮባ ሌንጀሶ መታሰቢያ የስፖርት አካዳሚ ፋውንዴሽን ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ወ/ሮ ልዩ ወርቅ መንገሻ ለእዚሁ ሲባል ባለፈው ሳምንት የቀድሞ አትሌቶችና አሰልጣኞች፤ አትሌቶች፣ ደጋፊዎቻቸው ቤተሰቦቻቸውና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወካዮች በተገኙበት ከእዚህ ቀደም በሥራ ላይ በነበሩበት ሰዓት የሚገልጽ ፎቶግራፋቸውን ከጀግኖች አትሌቶች አበበ ቢቂላና ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት በሌላ መስክ ጀግንነት ከፈጸሙ ጀግና አትሌቶች ጎን በኦሮሞ ባሕል ማዕከል ሙዚየም በክብር አስቀምጠዋል።
በአትሌቱ ስም የሚገነባው የስፖርት አካዳሚ በውስጡ የአትሌቲክስ መንደር የስፖርት ማዘውተሪያ ጅምናዚየም የታዳጊ ወጣቶች የስልጠና ማዕከል የመሮጫ ሜዳ፣ የመዋኛ ስፍራ፣ የመዝናኛ ክበብ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የስፖርት አልባሳት መሣሪያዎች የሚሸጡበት ሱቆችን ያካተተ መሆኑን ባለቤታቸው ወ/ሮ ልዩ ወርቅ መንገሻ በወቅቱ ተናግረዋል።
ከእዚህ ውጪ በስማቸው በተለይም በትውልድ መንደራቸው አርሲ አሰላ፣ አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች እንዲሁም በውጪ ሀገር የመታሰቢያ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል። ከእኝህ ታላቅ የኢትዮጵያ አትሌቲክስና አፍሪካ ወጣቶች ባለ ውለታ መንግሥት፣ ድርጅቶች፣ ዲያስፖራ አካላት እገዛ እንደሚያደርጉም ወ/ሮ ልዩ ወርቅ ይገልጻሉ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በእዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሠማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስቶ ለአበርክቷቸው ክብር በሚሰጥበት በእዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ አትሌት ንጉሴ ሮባ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማበብ ላከናወኑት ስኬታማ ጉዞ ምስጋናውን መግለጽ ይወዳል። ሰላም!
ተሾመ ቀዲዳ ከበሪሳ ጋዜጣ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም