የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ከተከሰተ እነሆ ሁለተኛ ወሩን ሊደፍን ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። በነዚህ ጊዜያት ውስጥም የሌለ እስኪመስል ከተገመተባቸው ቀናት ጀምሮ አሁን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋና ጫናውንም እያሳደገ በመሄድ ላይ ነው። መንግሥት የወረርሽኙን ዓለም አቀፍ ባህሪ መሠረት ባደረገ መልኩ በሽታውን ለመከላከል ሰፊ ዝግጅት ቢያደርግምና የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ቢያደርግም ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ከፍተኛ መዘናጋት ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
በአንድ በኩል በበሽታው ዙሪያ የሚተላለፉ የተዛቡ መረጃዎች በማህበረሰቡ ውስጥ በየጊዜው እየፈጠሩት ያለው መዘናጋት፣ ከዚህም በላይ ይዘነው የመጣነው የአኗኗር ባህል ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋነኛው ተግዳሮት ከሆነም ሰንብቷል። ቀናት በተቆጠሩ ቁጥር ደግሞ ሁኔታው ከስጋትነት ተሻግሮ ዋጋ ወደሚያስከፍል የተገለጠ አደጋነት በመሸጋገር ላይ ይገኛል።
የቫይረሱ በሀገር ውስጥ መከሰት ይፋ በተደረገበት ወቅት በማህበረሰቡ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ድንጋጤ፣ ድንጋጤው ፈጥሮት የነበረው መታቀብና መታቀቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የነበረው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ቀናት እየተቆጠሩ ሲመጡ አብዛኛው ሕዝብ በሽታው እስከመኖሩ የረሳው እስኪመስል ድረስ ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ ገብቶ ተስተውሏል።
መዘናጋቱ ሊያስከፍለን ከሚችለው ከፍተኛና ድንገትም ያልተጠበቀ ዋጋ አንጻር ሁኔታውን ቆም ብሎ በሰከነ አእምሮና ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ መመልከት ተገቢና ወቅታዊ ጉዳይ እንደሚሆን ለማሰብ ብዙ የሚከብድ አይሆንም። መዘናጋቶች በዚሁ ከቀጠሉ ልንከፍለው የሚገባ ያልተገባ ዋጋ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አይከብድም።
በአሁኑ ሰዓት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ማሸቀቡ አንድ ነገር ሲሆን ከሁሉም በላይ አስከፊው ግን ቫይረሱ ወደ ማህበረሰቡ በስፋት እየገባ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በየዕለቱ ከሚገለጸው መረጃ ላይ በግልጽ እየታየ ነው። ባለፈው እሁድ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 88 ሰዎች ውስጥ 55ቱ ምንም ዓይነት የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክና ከሌላ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ናቸው። ኮቪድ 19ን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ይፋ በሆነው
መረጃም ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘባቸው 73 ሰዎች መካከል 31ዱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸውና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያልነበራቸው ናቸው። ይህ የሚያሳየን በሽታው ወደ ሕዝቡ በስፋት ተሰራጭቶ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት እየሰራ ያለው መጠነ ሰፊ ሥራ እንዳለ ሆኖ ይህ የመንግሥት ጥረት ግን በራሱ አልፋና ኦሜጋ ሆኖ ችግሩን በራሱ መቀልበስ የሚችል እንዳልሆነ ነው።
የመንግሥት ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ መላው ሕዝብ ከመንግሥትና ከጤና ሚኒስቴር የሚወጡ መመሪያዎችንና ምክሮችን በአግባቡ ማዳመጥ፣ አዳምጦም በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴው ውስጥ በኃላፊነት መንፈስ ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለበት። አሁን ያለነው ሀገርንና ሕዝብን ከከፋ አደጋ መታደግ በሚያስችል ጦርነት ውስጥ ነው። ጦርነቱ የሚካሄደው ደግሞ ከማይታይና ባህሪውን እጅግ ከሚለዋውጥ ጠላት ጋር ነው። ስለሆነም ይህንን ጦርነት በድል መወጣት የምንችለው አሸናፊ በሚያደርገን ዲሲፕሊን ራሳችንን ተገዥ ማድረግ ስንችል ብቻ ነው።
በተለይ አሁን ያለንበት ወቅት ከአደጋው እንደ ሀገር ራሳችንን መታደግ በሚያስችል ልዩ ምዕራፍ ላይ ነን። ይህ ልዩ ምዕራፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ራሳችንን ከበሽታው ወረርሽኝ ለመከላከል የተቀመጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን በከፍተኛ ዲሲፕሊን መተግበር የምንገደድበት ነው።
መንግሥትም ቢሆን ወረርሽኙን ለመከላከል ያስቀመጣቸው ክልከላዎች ተግባራዊ መሆናቸውን በአግባቡ መቆጣጠር፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችን በተቀመጡ አግባቦች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል። ጉዳዩ የሞትና የሕይወት ከመሆኑ አንጻር ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት ሀገርንና ሕዝብን ለማትረፍ በሚያስችል ጠንካራ ዲስፕሊን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል።
ለማንም ግልጽ እንደሆነው አሁን የቫይረሱ አደጋ ከእስትንፋሳችን እየቀረበ የመጣበት ጊዜ ነው። ወረርሽኙን ለመከላከል የምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴም ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል። ከእንግዲህ በጥቂት መዘናጋት ልንከፍለው የምንችለው ዋጋ ለመጪው ትውልድ ጥቁር ታሪክ የመጻፍ ያህል ከባድና በታሪክም ፊት ተወቃሽ የሚያደርግ ነውና የጥንቃቄ እርምጃዎችን በጥብቅ ዲስፕሊን መፈጸም ግድ ይለናል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012