በመጪው ገና በዓል ቱሪስቶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ

አዲስ አበባ፡- በላሊበላ በመጪው ገና በዓል የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችን ለመቀበል የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጄ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤በከተማው የገና በዓል ለማክበር ለሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መቀበል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከክልል እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉም ነው ያሉት፡፡

በዓሉን ለማክበር ስምንት ልዩ ልዩ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ምክትል ከንቲባው፤የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የወጣቶች ህብረት በጋራ በመሆን ለበዓሉ ዝግጅት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዓሉ የተቀዛቀዘው የቱሪስት ፍሰትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመጨመር ካለው ፋይዳ ጎን ለጎን ለከተማው ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አቶ ወንድምነው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድምነው ገለጻ፤ አሁን ላይ በከተማው ያለው አንጻራዊ ሰላም መጪው በዓል ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንዲከበር የሚያደርግ ነው፡፡ የዘንድሮ የገና በዓል ሲከበርም በአካባቢው ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በሚያሳደግ መልኩ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

አቶ ወንድምነው፤ ማህበረሰቡ የበዓሉ ባለቤት በመሆኑ በበዓሉ ወቅት የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ከጸጥታ መዋቅሩ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ የተለያዩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ከተደረጉ ዝግጅቶች በተጨማሪ መንገድ፣ ኤሌክትሪካና ውሃ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ችግር እንዳይፈጠር መሰራቱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩ በረራ እንዲያደርግና የበረራ ቁጥር እንዲጨምር ከአየር መንገዱ ጋር ምክክር መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በከተማው ከ45 በላይ ትላልቅ ሆቴሎችና ሌሎች የእንግዳ ማረፊያዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህም ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል፡፡

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በየትኛውም አገልግሎት ዘርፍ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ወንድምነው፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ከዚህ በፊት በነበረው የእንግዳ አቀባበል መልካም ሥርዓት ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You