ለልመና የፈሩ እጆች ለሰላምታ ይዘረጉ ዘንድ ይታገዙ

ኢትዮጵያዊነት በጎነት ነው:: ከሙላት ሳይሆን ከጉድለት ለሌላው መድረስ:: ቡና ጠጡ ብሎ መጠራራት፣ ብላ እንጂ እያሉ በአፍ በአፍ ማጉረስ፣ ደግሞም ጉርሻና ፍቅር ሲያስጨንቅ ነው እያሉ ደጋግሞ ማጉረስ እሴታችን የሆነ ሕዝቦች ነን:: የእግዚአብሔር እንግዳ የሚል ብሒልን ተሸክመን ዘር ሳንቆጥር፤ ቀለም ሳንለይ የምናስተናግድ ልዩ ሕዝቦች:: መቼ እንደሚመጣ ለማይታወቅ እንግዳ ሲመጣ የሚስተናገድበት መብያና መጠጫ ለይቶ ማስቀመጥ ወጋችን ነው:: ለጎረቤት ሀዘን ቲቪና ሬድዮ ዘግቶ እኩል ማዘን መለያችን የሆነ ሕዝቦች ነን:: የእንግዳን እግር አጥበን፤ መኝታችንን ለቀን ጭምርም ኖረናል::

በሰፈር መንደሩ የአንዱ እንግዳ የሁሉም እንግዳ ሆኖ ተስተናግዷል:: የሰፈር ልጅ የሁሉ ልጅ ሆኖ አድጓል:: ሁሉም ሕፃናት በሁሉም ሰው እጅ ተንከባክቦ፣ ተቀጥቶና ተገስጾ ለቁምነገር በቅቷል:: እሱም በተራው የሁሉም ልጅነቱን ያስመሰክራል:: ትናንት የሚጣፍጥ ወጥ ያጎረሱትን የሰፈሩ እናቶች እጅ ሲሞላለት የቡና መግዣ ያስጨብጣል:: የትናንቷ ሚጡ እግሯ ስር አስቀምጣ ጸጉሯን የሾረበቻትን መልከ መልካም ወጣት ዛሬ እርጅና ፊቷን ቢሸበሽበውም አትተዋትም:: ዛሬ ሲያልፍላት ኮኮስ መግዛት ያለ ደንብ ነው::

የአንዱ ቤት መሶብ መጉደል ከአንዱ ቤት በመጣ እንጀራ ተሞልቷል:: የተፈጨ እህል ጎረቤት ሁሉ ይቀምሰዋል:: በሰፈሩ በአንዱ ማግኘት ሁሉም ይደሰታል:: ‹‹አንድ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ›› እየተባለ ልጆች አድገዋል:: ካላቸው ማካፈልን እንዲለምዱ ሆነዋል:: አሁን አሁን ትናንትናችን ከትናንት በላይ ሩቅ መስሏል:: ሁሉም በየቤቱ ቤቱን እየዘጋ መቀመጥ ምርጫው እየሆነ ነው:: የጎረቤት ጉድለት መሸፈን ይቅርና የጎረቤት ማንነት መለየት እየከበደ ነው:: በተለይ በመዲናችን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በምዕራባውያኑ የምንሰማው ከሞተ ቀናት በኋላ ቤቱ ሲከፈት አስክሬኑ ተገኘ የሚሉ የእኛ ያል ሆኑ ወጎች ይጎበኙን ጀም ረዋል::

ድሮ በቀኑት ሰፈሮች ግን ጉርብትናው ቀጥሏል:: አሁንም እናቶች ቡና ይጠራራሉ፣ ልጆች ይላካሉ፣ በማህበር፣ በእድር፣ በየሰበቡ መገናኘቱ ቀጥሏል:: ያም ቢሆን ኑሮ ሁሉም በየፊናው ይሮጥ ዘንድ የግድ ብሏል:: ያኔ ጊዜ ይጠፋል፣ ሰው ከጎረቤቱ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ይቀንሳል፣ ያኔ በቡና ቁርስ ምሳቸውን የሸፈኑ ሰዎች ይጎዳሉ:: ‹‹ከዓይን የራቀ ከልብ ይርቃል›› ነውና ቅርባችን ያሉ ሰዎች ጋር ተራርቀን ስልካችን ላይ ላገኘናቸው ሰዎች ልባችንን ከፍተናል::

‹‹ግራ ሲሰጥ ቀኝ አይደል›› የሚለው ቃል መተግበር ያቆመ መስሏል:: አሁን ለቸገረው ስንደርስ ማህበራዊ ሚድያ ላይ መታየት ምርጫችን ሆኗል:: ልባችን እንዲነካ ታሪኩ ቲክቶክ ላይ ይነገረን ባይ ሆነናል:: ለዛም ይመስላል ተቸግረው ያሉ ወገኖች በአቅራቢያቸው እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙና ተጽእኖ ፈጣሪ ያሉትን ሰው ለመፈለግ የተገደዱት:: ቲክቶክ የትናንት ታሪካችን ነው፤ እርስ በእርስ መረዳዳት የቆየ ልማዳችን ነው:: በማህበራዊ ሚድያ መረዳዳቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በሚድያ ያየናቸውን ለመርዳት ስንሽቀዳደም ጎረቤታችንን እየዘነጋን ነው::

ወደ አካባቢያችን ወረድ ስንል፤ ሕይወት ቢከብዳቸውም ለእርዳታ እጅ መዘርጋት ቀርቶ የተዘረጋን እርዳታ ለመቀበልም ከራሳቸው ጋር ግብግብ የሚገጥሙ በርካቶች ናቸው:: ቤታቸው ይልሱት ይቀምሱት ባይኖርም ከሌላቸው ላገባ የሚያዋጡ፤ ሀዘንተኛን የሚያስተዛዝኑ ብዙዎች ናቸው:: በተለይ በቀደምት ሰፈሮች ማህበራዊ መስተጋብሩ የጠበቀ ነውና በበጎም ሆነ በክፉ የሚያዋጡት መዋጮ ከገቢያቸው ግማሹን እየወሰደም ቢሆን በርካቶች አብረው መኖርን መርጠዋል:: የሕይወት ሩጫ ባይሞላላቸውም ያገባ፣ የወለደ፣ የሀዘን፣ የምርቃት (ዘንድሮ ምርቃት ድግሱም ሆነ መዋጮው የመዋዕለ ሕፃናትንም አካቷል) መዋጮዎችን ከአስቤዛቸው ቅድሚያ ሰጥተው እየኖሩ ነው::

ፊታቸው ላይ የሚታየው ገጽታ ኃላፊነቱ ተጭኗቸው እንጂ ሲታዩ የሚመስሉትን ያህል አልኖሩም ይላል:: የለበሱት ልብስ በኤጀንሲ አማካኝነት የጥበቃ ሥራ የሚሰሩ መሆኑን ሳይናገሩ ያሳብቃል:: የእሁድ ገበያን አስታከው ሸራ ወጥረው አትክልት ከሚሸጡት ከአንዱ ወደ አንዱ የሚዘዋወሩ በርካቶች ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ ውክልናን ሊወስዱ የሚችሉ አንድ ወደ ገበያው ጎራ ያሉትን አባት ብቻ እናንሳ:: መግዛት ያሻቸው አንድ ነገር ብቻ ይሆናል:: እርሱም ሽንኩርት ነው:: ነገር ግን አስበው ገበያ የወጡትና የእሳቸው ኪስ አልጣጣም ብሏቸው ሲባዝኑ ይታያሉ::

እንደመፍትሄ የወሰዱት ሃሳብ ለረዥም ጊዜ የሚሆን ሽንኩርት መግዛቱ ቢቀር ግማሽ ኪሎ መግዛትን ነበር:: ሆኖም ግማሽ ኪሎ ለመሸጥ ሻጮቹ ፈቃደኛ አልሆኑም:: ከአንድ ኪሎ በታች አንሸጥም ስለተባሉ ሌሊት ሲጠብቁ ያደሩት አባት ለልጆቻቸውና ለትዳር አጋራቸው ወጥ ማጣፈጫ የሚሆን ሽንኩርት እንደአቅማቸው ለመሸመት ከአንዱ ዳስ ወደአንዱ ዳስ እየተዟዟሩ ይጠይቃሉ:: የሻጮቹ አንጀት ራርቶ እንዳቅማቸው ግማሽ ኪሎ ሊሸጡላቸው አልፈቀዱም:: ለቤታቸው አንድ ኪሎ ሽንኩርት መግዛት ቢከብዳቸውም ከአንድም ሁለት ሥራ የሚሰሩ ጠንካራ አባት ናቸው:: ልጆቻቸው እንዳይራቡ፣ ብሎም የሰው ፊት እንዳያዩ ለሁለት ድርጅት የጥበቃ ሥራ ይሰራሉ:: ከአንዱ መሥሪያ ቤታቸው ሲወጡ በእረፍት ፋንታ ሌላኛው ሥራ ቦታቸው ይገባሉ:: በሳምንት አንድ ቀን እረፍታቸው ነው:: እንዲህም ሰርተው ኑሮው ከብዷቸዋል:: ሆኖም መረዳት ይሉት ነገርን አያስቡም::

ከአቅማቸው በላይ መፍጨርጨርን መርጠዋል:: ለዛም ነው ያን ቀን በሁኔታቸው የተነካ ሌላ ሸማች ከአስቤዛው ቀንሶ የእሳቸውን አንድ ኪሎ ሽንኩርት ቢከፍል ለመቀበል ያመነቱት:: እሳቸው ሲኖሩ መስጠት እንጂ መቀበልን አለመዱም:: ግን ዘመኑ ሲኖር መስጠትን ሲጎል መቀበልን የምንለምድበት ሆኗል:: በተለይ የበዓል ሰሞን ገበያ ሲወጣ ብዙ የለመዱ እናቶች ገበያ መሃል ግራ ተጋብተው መመልከት የተለመደ ነው:: ብዙ አስበው ቢወጡም እጃቸው ላይ ያለውና ፍላጎታቸው አልጣጣም ብሏቸው የቱን ገዝተው የቱን እንደሚቀንሱ ግራ ሲጋቡ ከቻልን አለንላችሁ እንበላቸው::

አብዛኛው ለጋሽ ሰው ስለመርዳት ሲያስብ አልባሳት አዘጋጅቶ፣ ብሩን ዘርዝሮ፣ የተሰናዳ ምግብ ይዞ ስለመውጣት ሲያስብ ምርጫው መንገድ ዳር ለምጽዋት እጃቸውን የዘረጉ፤ ወይም የሃይማኖት ቦታዎች አንጥፈው የተቀመጡትን ነው:: ከላይ እንዳሉት አይነት ባለታሪኮች ግን በርካታ ናቸው:: ምሳ ሳይበሉ ራት ሰዓት ቢደርስም ቸግሮኛል እርዱኝ ማለት አይፈልጉም:: እጃቸውን ለምጽዋት መዘርጋትም በእጅጉ ያሳፍራቸዋል:: ስለሆነም የምትደርሳቸውን አነስተኛ ደመወዝ፣ እንዲሁም የጡረታ ዳረጎት ለማብቃቃት ብቻ ይጥራሉ:: ነገር ግን ኑሯቸው አስር ቀርቶ ዘጠኝም ስምንትም ሆኖ አያውቅም:: ጥረታቸው አይሳካላቸውም:: ገቢያቸውና ወጪያቸው አይመጣጠንላቸውም:: ይሁን እንጂ እጃቸውን የመዘርጋት ወኔ የላቸውም::

ቸግሮኛል እርዱኝ ብሎ በማህበራዊ ሚድያም ሆነ በአካባቢያችን እንደሚጠይቁት አይነትም ለመሆን አዕምሯቸው አይፈቅድላቸውም:: ታዲያ ከዚህ አንጻር ቸግሮኛል እስኪሉ መጠበቅ ይኖርብናል ትላላችሁ? በተደጋጋሚ ቡና ይጠሩ የነበሩ የጎረቤት እናት ቡና ማፍላት ሲቀንሱ ብሎም ሲተው ለምን ማለትስ አይገባንም? አላፊ አግዳሚውን “አፈር ስሆን! ግባና ምሳ ብላ” እያሉ የሚለምኑ እናት “ጎራ በሉ” ማለት ሲያቆሙ ለምን እንደሆነ አናሰላስልም? ይህ የእኛ ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችንም፤ ባህላችንም ነውና ማሰብ ይገባናል::

ገና (ክርስማስ) ለምዕራባዊያን ከሃይማኖታዊ በዓልነቱና በአቅራቢያው አዲስ ዓመቱን ከመቀበላቸው ባለፈ የሥጦታ በዓላቸው ነው:: ለዚህም ለቀናት ያከብሩታል:: ታዲያ ያኔ እንኳን የሚበላና የሚጠጣ ቀርቶ ሥጦታ የሚሰጠኝ የለም የሚል እሳቤ በማንም ላይ እንዲኖር አይፈልጉም:: ሁሉም እንደአቅሙ በቤተሰብ፣ በጓደኝነት፣ በሥራ ቦታ ሥጦታ ይሰጣጣል:: ከዚህ የተረፈውን ጉድለት ለመሙላት ለበዓሉ ሥጦታ መስጠት ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሸፍኑ ይደረጋል:: ይህ መሆኑ ወላጅን ለልጄ ስጦታ መስጠት አልቻልኩም ከሚል የልብ ስብራት ይታደገዋል:: ሕፃናቱንም ሆነ ሌሎችን የሥጦታ ተቀባዮችን ማንም አይፈልገኝም ከሚል ያለመፈለግ ስሜት ውስጥ ከመግባት ይጠብቃቸዋል::

በእነዚህ ድርጅቶች የሚሰጡት ስጦታዎች በአብዛኛው የሚበረከተው በወላጆችና በቅርብ ቤተሰብ ሲሆን፤ ከሥጦታው በላይ አሰጣጡና ሰጪው ትርጉም አለው ተብሎ ይታሰባል:: በተቀባዩ ላይ የተረጂነት ስሜት እንዳይኖርም የሚያደርግ ነው:: ይህ እንዲሆን ባይተርፋቸውም ካላቸው ላይ የሚያካፍሉ በርካቶች ናቸው:: የእነዚህ ሰዎች ክፍያቸው የማያውቁትን አንድ ሰው አለፍ ካለም ቤተሰብን እንዳስደሰቱ ስለሚያውቁ የመንፈስ ደስታ ይሰማቸዋል::

ምዕራባዊያን ‹‹ፔይ ኢት ፎርዋርድ›› የሚሉት ሃሳብ አላቸው:: ጽንሰ ሃሳቡ በጎ ላደረገ ሰው መልሶ ውለታውን ከመክፈል ይልቅ ለሌላ አካል በጎ ነገር ማድረግ ነው:: ይህ መልካምነት የተደረገለትም ሰው በፊናው በጎ ነገር ማድረግ ሲችል እሱም የተደረገለትን በጎነት ለሌላ አካል በማድረግ ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት ይመልሳል:: በእዚህ እሳቤ በጎነት ምድራችንን ይሞላል::

እኛም በዓል መጣ ብለን የሚያስፈልግ የማያስፈልገውን ስንሸምት ቀነስ አድርገን አቅራቢያችንን እናስተውል:: በቀደሙት በዓላት የሰፈሩ አድባር የነበሩት ጋሼ እጃቸው ሲያጥር በጎደለው መሙላት መታደል ነው:: ያኔ ከቀነስነው ትንሽ ብናካፍል በዓሉ የጋራ በዓል ይሆናል:: ሁሉም ጎረቤቱን የቅርቡን ቢያይ ያልተዘረጉት እጆች ሳይዘረጉ ጭብጣቸው ይሞላል:: ታዲያ ስንሰጥ መስጠታችን እንዲታወቅ ድቤ አንምታ:: አንዳንዴ ምነው በቀረብኝ የሚያስብሉ ለጋሾችን ታዝበናል::120 ሚሊዮን መሙላታችን ጥቅም ይኑረው::ምክንያቱም መብዛታችን ለመደጋገፋችን በጎ ተጽዕኖ አለውና::

ልብስ የሸሸገው የጓዳ ጉድለት ሳይሞላ እንዳይቀር አካባቢያችንን እናስተውል:: ቢቻል በየአካባቢያችን ሰብሰብ ብለን ምን እናርግ እንበል:: ለብቻ ከመሮጥ በጋራ መሮጥ ኃይል ይሰጣል:: በዚህም በየአካባቢያቸው በቋሚነት ለአካባቢያቸው ሰዎች ተቆራጭ የሚያደርጉ፣ በዓላትን ጠብቀው የበዓል መዋያ የሚሰጡ፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ የሚያበረክቱ ብዙዎች ነውና ስብስባችንን በዚህ ልክ እናጠንክረው:: ቀን የወጣላቸው ብርቱዎች የወጡበትን አካባቢ ቃኝተው መስራት ለሚችሉት ሥራ ማስጀመሪያ በአይነትም በገንዘብም ድጋፍ ሲያደርጉ ባይበዛም አይተናል:: ይህ ልምምድ ሲዳብር በዓሉ የሁላችንም ይሆናል:: ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነውና ጎረቤት ስለጎረቤቱ ያስብ:: ለልመና ሊዘረጉ ጫፍ የደረሱ እጆች ለሰላምታ ብቻ እንዲዘረጉ እናድርግ:: እኛ ቅርቦቻችንን ካሰብን በልበ ሙሉነት በጎ ኢትዮጵያዊያንን እናፈራለንና ቀደምቱን ባህላችንን፣ ወጋችንን እንጠብቅ፤ እናጠናክረውም!!

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You