በክልሉ አራት ሺህ 700 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት እየተሠራ ነው

– ከአዲስ የማሽላ ዝርያ ልማት ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- በሐረሪ ክልል ከአራት ሺህ 700 ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ለማልማት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ በሄክታር ከ42 እስከ 45 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል አዲስ የማሽላ ዝርያ በማልማት 36ሺ ኩንታል መሰብሰቡን ተጠቁሟል፡፡

የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት እና የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በክልሉ የበጋ መስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ዘንድሮም ከአራት ሺህ 700 ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ለማልማት እየተሠራ ይገኛል።

በክልሉ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ የሚመረትበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ የመኸሩን ምርቱን ሰብስቦ በማጠናቀቁ በበጋ መስኖ ለማልማት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኘ ገልጸዋል፡፡

በክልልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ሙሉ ለሙሉ መልማቱን ጠቅሰው፣ ከዚህም ውስጥ 800 ሄክታሩ መሬትም በማሽላ፤ 450 ሄክታሩ በስንዴ በክላስተር እርሻ ኢንሼቲቭ እንዲለማ መደረጉን አስታውቀዋል።

በክልሉ በኩታ ገጠም (በክላስተር) ዘዴ የለማው የማሽላ ዝርያ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ያገኘው መሆኑን አውስተው፤ በምርምር የፈለቀው አዲሱ የማሽላ ዝርያም ምርቱ በሦስት ወር የሚደርስ በመሆኑ ምርቱም ደርሶ ተሰብስቧል ብለዋል።

ወይዘሮ ሮዛ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ማሽላ ከሰባት እስከ ዘጠኝ ወር የሚደርስ ነው። ሲያስገኝ የነበረውም ምርትም በሄክታር 13 ኩንታል ብቻ ነበር። ነገር ግን በምርምር ከተገኘው እና በሦስት ወር የሚደርሰው የማሽላ ምርት ደግሞ በሄክታር ከ42 እስከ 45 ኩንታል ይገኝበታል። ይህም ክልሉ ባለው አነስተኛ መሬት ላይ ዝናብ ሳይጠበቅ በሦስት ወር ለማምረት ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት በፍጥነት የሚደርሰውን ምርት መጠቀም እንደሚገባ ገልጸው፤ በክልሉ ግብርና ቢሮ ድጋፍ የማሽላ ዘሩን በብዛት በማምጣት በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ የማልማት ሥራ የተሠራ መሆኑንና በበጋ መስኖ ልማትም ይኸው ሥራ የሚሠራ እንደሆነም ወይዘሮ  ሮዛ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ በአዲሱ የማሽላ ዝርያ ከለማው 800 ሄክታር መሬት ላይ 36 ሺህ ኩንታል ተሰብስቧል ያሉት ወይዘሮ ሮዛ፤ የማሽላ ዝርያው በተወሰኑ ወረዳዎች አልተዳረሰም። የማሽላው ምርጥ ዘር ወደ ሌሎች ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ለማዳረስም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ምርትን በወቅቱ ከመሰብሰብ አኳያም አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርቱን እንዲሰበስብ ተደርጓል ብለዋል። በተጨማሪም መግዛት ለሚችሉ ወረዳዎች ቴክኖሎጂውን የማስተማር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ይህንን ምርት አርሶ አደሩ ጋር ለማድረስ ከፍተኛ ግዢ አድርጓል ያሉት የግብርና ቢሮ ኃላፊዋ፤ የገዛውን የማሽላ ምርጥ ዘር አንድ ቦታ በማሰባሰብ ላይ ነው፡፡ ይህን ምርጥ ዘርና አዲስ ዝርያ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨትም በሴፍቲኔት እገዛ ውስጥ የቆዩ አንድ ሺህ 200 አርሶ አደሮች በዚህ ዓመት ማብቃት እና ከድጋፉ እንዲወጡ ማድረግ የተቻለ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሐረሪ ክልል ማሽላ በስፋት የሚታወቅ የግብርና ምርት ሲሆን፣ በቆሎ፣ ለውዝ እና ስንዴ በስፋት እንደሚመረት ታውቋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You