
የተባበሩት መንግሥታት የሳይበር ወንጀልን ለመከላከልና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ማፅደቁን አስታወቀ፡፡ ስምምነቱ በተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት መካከል በ20 ዓመታት ውስጥ የተደረገ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የወንጀል መከላከል ስምምነት ነው ተብሏል።
የኢንፎርሜሽን እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ያለአግባብ መጠቀም ለሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ እውቅና የሚሰጠው ይህ ስምምነት፤ መሰል ወንጀሎች በሀገራት፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ኅብረተሰብ ደኅንነት ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተፅዕኖ አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነም ታምኖበታል፡፡
የስምምነት ሰነዱ ከሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና በኦንላይን ከሚደረግ የገንዘብ ዝርፊያና መሰል ወንጀሎች ዓለም እንዲጠበቅ በትኩረት ለመሥራት ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
የሳይበር ወንጀሎች በተጠቂዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በመገንዘብ በተለይ ተጋላጭ ወገኖች ፍትሕ እንዲያገኙ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተመላክቷል። በዚህም በባለድርሻ አካላት መካከል የቴክኒክ ድጋፍ፣ የአቅም ግንባታ እና ትብብር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ ሥምምነቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምሕዳርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን መጠቆማቸውን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ዓለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን ዓላማውም በዓለም አቀፍ ሕግ፣ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዕድገትና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የሀገራትን ትብብር ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም