የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተቀባይነት ማደጉ የዲፕሎማሲያችን ስኬት ማሳያ ነው!

ኢትዮጵያ ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባሕልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሠረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር ከመቻሏም ባሻገር ከንግሥት ሳባ እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ እምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ሀገር ናት፡፡

በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም ዓለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ሲመሠርቱ ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉዓላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማረጋገጥ የሀገራችን ዲፕሎማሲ ሥራ ማጠንጠኛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥማትን የሉዓላዊነት ፈተናዎች ስታልፍ የቆየች ብትሆንም የባሕር በር ጥያቄን በዘላቂነት መፍታት ግን ሳይቻል ቆይቷል፡፡ በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት ከመደረጉም በላይ ይህ ጥያቄ ዝግ ሆኖ ጥያቄውን ማንሳትም በጠብ አጫሪነት የሚያስፈርጅ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሠራባቸውና ከፍተኛ ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ ሀገር የባሕር በር እንዳይኖራት መደረጉ ትልቅ ስህተት ነው ከሚል መነሻ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የም ታገኝበት አማራጮችን በማፈላለግ ላይ ይገኛል ፡፡

ይህንን ሕጋዊ እና ፍትሃዊ ጥያቄ ለመመለስ ሰላማዊ አማራጭን ብቻ የሚከተለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) በመፈራረም ተዘግቶ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን የባሕር በር ጥያቄ ዳግም ወደ መድረክ አምጥቶታል፡፡ በዚህ ኢትዮጵያውያን ዳግም የመወለድ ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸዋል፡፡

መንግሥት የጀመራቸው ጥረቶች አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው፡፡ ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው፡፡ አሁን ላይ ባለ ግምት የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል፡፡

ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለባሕር በር እጅግ ቅርብ የሆነች ሀገር ናት፡፡ በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር አፈጣጠሯ ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በታሪክ ረገድም በቀይ ባሕር ላይ ለዘመናት ተጠቃሚ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሏት፡፡

እነዚህ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቶች በማንሳት ይህ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ መንግሥት ባደረገው ጥረት እንዲሁም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ የተደረጉ ውጤታማ እና በሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮችም እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ የተለያዩ መሪዎችም በአንደበታቸው መስክረውለታል፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ትክክለኛ እንደሆነ እና ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ፈረንሳይ ባላት አቅም ማድረግ የምትችለውን እንደምታደርግ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ በአንካራ ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ያደራደሩት የቱርኩ መሪ ረሲፕ ጣሂር ኤርዶሃን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

ይህም የባሕር በርን በተመለከተ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የዲፕሎማሲ አካሄድ በቀጣናው ተሰሚነቷን ከማሳደጉም ባሻገር የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ማግኘቱ አይቀሬ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው!

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You