ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? መቼም አንዱ በዓል አልቆ ሌላው ሲተካ በጣም ያስደስታል። በተለይ የክርስትና እምነት ተከታዮች ልደትን (ገናን) አልፈው አሁን ደግሞ የጥምቀትን በዓል እያከበሩ ይገኛሉ። ጥምቀት ደግሞ ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፈ ባህላዊ ይዘቱ ከእምነቱ ባሻገር ለሌሎች የእምነት ተከታዮችም የሚያካፍለው የተለየ አውዳዊ መለያ አለው።
ብዙ ቱሪስቶች ወደ አገራችን የሚመጡበት፤ ሰዎች በአንድነት የሚሰባሰቡበትና ልጆችም እንደፈለጉ እንዲጫወቱ የሚፈቀድበት የአደባባይ በዓል ነው። ስለዚህ ይህ ዕለት ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ከእምነቱ ውጪ ላሉ ልጆችም ልዩ ቀን ነው። ስለዚህ እናንተም በደስታ እያከበራችሁት እንደሆነ አምናለሁ። ዛሬ ግን ጉዳዬ ይህ አይደለም። ምክንያቱም ባለፈው ሳምንትም ስለ ጥምቀት በዓል አከባበር ጥቂት ነገር ስለፃፍንላችሁ ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ስለ አስገራሚዋ ታዳጊ ልጅ ነው።
ታዳጊዋ ሴኔት ግዛቸው ትባላለች። በሦስት ቋንቋ ረጅም መነባንቦችን በማቅረብ ትታወቃ ለች። ብዙ ጊዜ በኦሮምኛ ቋንቋ የምታቀርባቸው መነባንቦች ሰዎችን በእጅጉ ያስገርማሉ። እንባ አስወጥተው እስከማስለቀስ የሚያደርሱ ግጥሞችን መድረክ ላይ አቅርባለች። ስለ ሰላም ስትናገር ደግሞ በእጅጉ ታላላቆቿ ይደነቁባታል። እንደውም በዚህ ልዩ ተሰጥኦዋ ሰሞኑን ከሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ተገናኝታ ነበር። ልጆች እርሳቸው ምን እንዳሏት ታውቃላችሁ? «ሰላምን በማስተማርና በመስበክ በኩል ትልቅ አቅም አለሽ። ስለዚህም አብረን እየሠራን የአገራችንን ሰላም እናስጠብቅ» ነበር ያሏት። ልጆች የማይጠፋ ብርሃን የሚፈነጥቁና ከልባቸው ንጹህ የሆኑ ናቸው። የሚናገሩት ነገር ተሰሚነቱ ከፍተኛ ነው። ለዚህም ነው የሰላም ሚኒስትሯ አብረን እንሥራ ያሏት።
ሴኔት የተወለደችው ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ጎጆ ቀበሌ 01 ነው። የአራተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ የምትማረውም አለምገና አካባቢ በሚገኘው «ኢንተሌክችዋል እስኩል» በተሰኘ ትምህርት ቤት ነው። በእድሜዋም ቢሆን ከአስር አላለፈችም። ይሁንና በንግግሯ ግን ሰዎችን ሁሉ የመማረክ አቅም አላት። እርሷ መድረክ ላይ ስትወጣ የማያጨበጭብና ከመቀመጫው ቁጭ ብድግ የማይል የለም። በብዙ መድረኮች ላይም የመክፈቻ ንግግር ልክ እንደትልልቆቹ ሁሉ ታደርጋለች። በክብር እንግድነት የምትጋበዝባቸው ቦታዎችም ብዙ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዳማ ላይ የገጠማትን አንድ ነገር አጫውታኛለች።
ነገሩ እንዲህ ነው። በክብር እንግድነት ነበር ቦታው ላይ የተጋበዘችው። ከዚያ የመድረክ አስተዋዋቂው የክብር እንግዳዋ ወደመድረክ መጥተው ንግግር ያደርጋሉ። ቀጥለውም ሌላ እንግዳ ይጋበዛሉ ብሎ መናገር ጀመረ። የክብር እንግዳዋ ሴኔትም መጠራቷን ስታውቅ ተነስታ ወደ መድረኩ አመራች። የመድረኩ መሪ የክብር እንግዳዋን በጭብጨባ ተቀበሉልን ብሎ ነበር ቀደም ሲል። ይሁንና የምትመጣው ልጅ መሆኗን ሲመለከት ግራ ተጋባ። ሌላ ይመጣል በሚልም እርሷን በእጁ ገፋ እያደረገ ያሸሻት ጀመር። ሴኔት ግን ግራ መጋባቱን ተረድታ ኖሮ እጁን አስለቅቃ ወደ ማይኩ አመራች።
ተገቢውን ንግግር በመድረኩ አድርጋ የተጋበዘውን ባለሥልጣን ስም ጠራች። በወቅቱ ሰው ሁሉ ግራ ተጋባ፤ በንግግሯም በእጅጉ ተገረመ። ቃላቶቹ ከታዳጊ አንደበት የሚወጡ አይመስሉም። ከልባቸው እንደሰሟት በዓይናቸው አረጋግጣ ወደ ቦታዋ ስትመለስ ጭብጨባው ቀለጠ። እንደውም ቀጣዩ ተናጋሪ ከእርሷ ንግግር የበለጠ መናገር እንደማይችል በማሰብም ሀሳቤን ገልፃዋለች በሚል ተከትሏት መውረዱን አጫውታኛለች። አያችሁ ልጆች ሴኔት እስከዚህ ድረስ የደረሰ የመናገር ብቃት አላት። ማንንም ሳትፈራ የታዘዘችውን ታደርጋለች። በተለይ የማሳመን ብቃቷን ብዙዎች ያደንቁላታል።
ሴኔት ለምን እንደተባለችም ነግራኛለች። በኦሮምኛ ቋንቋ «መስሎን» የሚል ጥሬ ትርጉም ሲኖረው እርሷ እንዳለችኝ ደግሞ ሴኔት ማለት በአሜሪካ የህግ መወሰኛ አካል ማለት ነው። ስለዚህም ይህንን አብነት በማድረግ እንደወጣላት ነው ያጫወተችኝ። ሴኔት በትምህርቷም ቢሆን በጣም ጎበዝ ተማሪ ናት። የአንደኝነት ደረጃን ለሌሎች አሳልፋ ሰጥታ አታውቅም። ሁልጊዜ አንደኝነቷን አስጠብቃ የምትጓዝ ጎበዝ ተማሪ ነች። ሴኔት የራሷ የሆነ ልዩ ስጦታ ያላት ልጅ ናት። የተሰጣትን ግጥም በመነባንብ መልክ በቃሏ ሸምድዳ ማቅረብ ብቻ አይደለም ችሎታዋ። ግጥም መጻፍም ትችላለች። በተለይም ስለ ሰላም መጻፍ በጣም እንደሚያስደስታት ነግራኛለች።
ሴኔት ትምህርቷን ስትጨርስ ሦስት ነገሮችን መሆን ትፈልጋለች። ለእነዚህም ምርጫዎቿ መሰረታዊ ምክንያቶች አሏት። የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሲሆን፤ አገሯን በሚገባ ማስተዳደርና ዓለም ስለአገሯ ጥሩ ነገር እንዲያወራ ማድረግ ስለምትፈልግ ነው። በተጨማሪም አገሯ ከሌሎች አለማት እኩል በእድገትም ሆነ በፖለቲካው ልቃ ማየት ስለምትሻ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደምትመኝ አጫውታኛለች። ሁለተኛው ደግሞ የዓይን ስፔሻሊስት ዶክተር ነው። በምክንያትነት ያቀረበችልኝ ዓይኗን ከህፃንነቷ ጀምሮ በጣም ስለሚያማት ህፃናትም ሆኑ ወጣቶች እንዲሁም አዋቂዎች በዓይን ህመም እንዳይሰቃዩ ለማድረግ መሆኑን ነግራኛለች። በተለይም ራስ ላይ ያለ በሽታ ጉዳቱ በሚገባ ስለሚታወቅ ስሜቱን በመረዳቷ ነው ይህንን የህክምና መስክ ለማጥናት የፈለገችው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን ያላትን የኪነ ጥበብ ተሰጥኦ ማጎልበትና የተሻለ አርቲስት መሆንንም ትፈልጋለች። ምክንያቱም ልዩ ስጦታን ማዳበር ለሌሎች ስኬቶች አጋዥ መሆኑን ስለተገነዘበች ነው።
ልጆች ልዩ ስጦታቸውም በማንኛውም ጊዜ መጠቀም እንዳለባቸው ያጫወተችኝ ሴኔት፤ ግጥም እየጻፈ ምንም ቃል ሳትዘል በቃሏ ሸምድዳ እንድታቀርብ የሚያግዛት አባቷ እንደሆነ ነግራኛለች። ይሁንና ከዚያ ባለፈ የራሴን ችሎታ ለምን አልጠቀም? በሚል ራሷ መጻፍ እንደጀመረችና ከ20 በላይ ረጃጅም ግጥሞችን ጽፋ እንዳስቀመጠችም ገልጻልኛለች። ስለዚህ ልጆችም ማድረግ ያለባቸው በሰው ላይ ጥገኛ መሆን ሳይሆን፤ የተለያዩ ነገሮችን መሞከር ነው ብላኛለች። ተሰጥኦ የሚወጣው በመሞከር ብቻ ነው። ይህንን አልችለውም ማለት ልዩ ችሎታን ይደብቃል። ስለዚህም ልጆች ሁልጊዜ መሞከር እንዳለባቸው ትመክራለች።
ሴኔት ሁል ጊዜ ስለሰላም መናገር አይሰለቸኝም። ምክንያቱም ሰላም ከሌለ መማር አይኖርም፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስም አይቻልም፤ እንደልብ መጫወትና ማውራትም ይከለከላል። ይህ ደግሞ ጭንቀትን ይፈጥራል። በዚህ ምክንያትም አገር ብቻ ሳትሆን ማህበረሰቡ በሙሉ ችግር ውስጥ ይገባል። ሁልጊዜ ስለሰላም ማውራትና መናገር የምወደው ለዚህ ነው ትላለች። ልጆችም ይህንን ማድረግ እንዳለባቸው ታሳስባለች።
ሴኔት ቃላትን ወይም ግጥሙን በመነባንብ መልክ ከአንደበቷ እያወጣች በመድረክ ላይ ስታቀርብ ዝም ብላ ማነብነብ በሚመስል ድምጸት አይደለም። ለእያንዳንዱ ድምጽ የራሷ የትወና ጥበብን ትጠቀማለች። የፊት ገለጻዋ፣ የእንቅስቃሴዋና የድምጽ አወጣጧ እንደ ሁኔታዎች ይለያያሉ። ሽማግሌ ሲኮን የሽማግሌ ድምጽ፣ ህጻን ሲኮንም እንዲሁ እንደህፃናቱ ድምጿን በማስተካከል ነው መነባንቦቿን የምታቀርበው። አንዳንዴ የተመለከቷት ሰዎች «ይህቺ ትልቅ ተሰጥኦ ያላትና መምህር ነች» ይሏታል። ለምን እንዲህ እያሉ ይጠሩሻል? ስላት ምን እንደመለሰችልኝ ታውቃላችሁ?
«እኔ ምንም አላደረግሁም፤ በዚህ ደረጃ ሰዎችንም አስተምራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ያደረግሁት ሁልጊዜ ችሎታዬን ማውጣት ላይ ማተኮር ነው። አልችልም የሚል ነገር በውስጤ የለም። የማልሞክረውም ነገር አይኖርም። ትምህርቴንም በሚገባ እከታተላለሁ። ከዚያ ባለፈ ደግሞ አነባለሁ። ይህ ደግሞ እኔን ክብርና ሞገስ አላብሶኛል። ለዚህም ነው ብዙ ሰው የወደደኝ ብዬ አምናለሁ» አለችኝ። በጣም ይገርማል አይደል። አያችሁ ልጆች እናንተም ማድረግ ያለባችሁ እንደ ሴኔት ሁሉ በሚገባ ትምህርታችሁን መከታተልና አንባቢ መሆን፤ እንዲሁም ሰዎችን ማክበርና ለታላላቆቻችሁም ሆነ ለታናናሾቻችሁን መታዘዝ ነው። ችሎታችሁንም ለማሳየት መጣር አለባችሁ። ይህንን ካደረጋችሁ አይደለም በአገራችን በዓለም ልትታወቁ ትችላላችሁና የእርሷን አርኣያነት ተከተሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው