
ድንቁን ፍጡር የሰውን ልጅ ለማንበብ እይታው ያልተንሸዋረረ ምሉዕ መነጽር፣ ዓለምን ማሰሻ፣ ተፈጥሮን መፈተሻ፣ ራስ ማያ መስታወት ነው ጋዜጠኝነት። መጻሕፍትን በሕይወት ለመተርጎም የሚያስችለው ከፀሐፊው ይልቅ ለአንባቢው የመረዳት አቅም ነው፤ እኔም የሰማኋቸውን ጩኸቶች ብሶታቸውን አራግፌ በሰላ ምናብ በጠንካራ ሃሳብ የጨዋታ ብልታቸውን አውጥቼ እንካችሁ ብያለሁና አፈር ስሆን ቅመሱልኝ፤ ካላችሁም ነፍሱን ይማረውና በሰለሞን ተካልኝ ሙዚቃ ተጭነን አብረን እንትመም።
“ቼ ብያለሁ ቼ ቼ፣
ሃሳብ ላይ ወጥቼ።
ሱ ብያለሁ ሱ ሱ፣
ሃሳብ ነው ፈረሱ።”
በረንዳ ሞልተው ጠረጴዛ ከበው በሁለት ስክሪን የኢትዮጵያንና የእንግሊዝን ፕሪሚየር ሊግ እያዩ አንድም ኳሱን በተመለከተ ሁለትም ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳይ አንስተው እንደ ጎመን ወግ ሲቀነጥሱ ጎላ ያለው ድምጻቸው ከጆሮዬ ገብቶ ቀልቤን ገዛውና ከመንገዴ አግልዬ ተቀላቀልኳቸው።
“ያን ጊዜ የጣሊያን ክለቦች መንግሥቱ ወርቁን የእናስፈርምህ ጥያቄ ሲያቀርቡለት እሱ ግን የአባቴ ገዳዮች ናችሁ ብሎ ዝውውሩን ሳይፈጽም ቀረ፤ አስባችሁታል? እሺ ብሎ ቢሆን ኖሮ ለዛሬዎቹ እግር ኳስ ተጫዋቾቻችን መልካም አጋጣሚ ይሆን ነበር” አለ በቁጭት ጸጉሩን ድሬድ የተሠራው ወጣት። “ጣሊያን ቅኝ ብትገዛን ይሻል ነበር፤ ጥሩ ብሔራዊ ቡድን ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት እንኳን ቅኝ ወደገዟቸው ክፍለ ዓለማት እየሄዱ የመጫወት እድል በማግኘታቸው የተሻለ እግር ኳስ እንዲኖራቸው ምክንያት ሆኗቸዋል፤ እኛ ግን በጪስ አልባው ቅኝ ግዛት መቀፍደዳችን ላይቀር በባዶ ሜዳ እየተንቀባረርን ጭልጭል ይል የነበረውን የእግር ኳስ እድገታችንን ሙሉ በሙሉ አዳፈነው” አለ ሌላኛው ወጣት ናኒ የጸጉር ቁርጡን እያፍተለተለ።
ኧረ ለመሆኑ ምን ዓይነት ሀገር እንዳለቻችሁ ታውቁታላችሁ? ስል ጠየኳቸው ድፍርስ ስሜት ውስጥ ሆኜና ሚያዝያ ሃያ ሰባት የተከበረውን የአርበኞቻችንን ቀን አስታውሼ። “አዎ! በጣም እንጂ! ያውም አሳምረን ነዋ የምናውቃት! እኛ ያለችን ሀገርማ በሽተኛው እያለ ጤነኛው እንዲሁም ሽማግሌው እያለ ወጣቱ የሚሞትባት፤ ብሎም እግረ ቀጭኑ እያለ እግረ ወፍራሙ እንቅፋት የሚመታባት ናት” አለ የመጀመሪያው ወጣት በምጸት ሳቅ ታጅቦ።
በመልሱ አኩርፌ ይሁን በሌላ ሰበብ ብቻ ምን እንደሆነ እንጃ ሳላውቀው ተለይቻቸው ራሴን አገኘሁት። ነገር እያንቀራጨሁ ሳዘግም በጎዳናው ግራና ቀኝ የተኮለኮሉት በሸራ የተወጠሩ ቤቶች እስከ መጨረሻው ድረስ የለቀቁት የሙዚቃ ጩኸት የሰውን የጆሮ ታንቡር ይበጥሳል። ሁሉም በሚባል ደረጃ የኛ ሀገር ንግድ ቤቶች ወከባ ከሌለውና ሙዚቃው ካልጮኸ ሥራ የሚሠራ እንደማይመስላቸው ስንቶቻችሁ ታዝባችሁልኝ ይሆን? ደግሞምኮ ገና በጠራራ ፀሐይ አልኮል እየቸበቸቡ የወጣቶቻችንን አዕምሮና የሥራ ሞራል መስለባቸው ነው የሚነደኝ።
በአንድ ወቅት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ቅኝት [ሰርቬይ ኦፍ ኢትዮጵያን ሊትሬቸር] በሚል ኮርስ አማካኝነት ለጉብኝት ትግራይ ክልል በሄድኩበት አጋጣሚ ያየሁት መልካም ነገር ጉድ ትንግርት አስብሎኝ ምን አለ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ቢተገበር? የሚል ቁጭትና መንፈሳዊ ቅናት አሳድሮብኛል፤ ነገሩ እንዲህ ነው። ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል በፊት አልኮል ቤቶች አገልግሎት አይሰጡም፤ ከፍተው የተገኙ እንደሆነ ግን ሕጋዊ ርምጃ ይወሰድባቸዋል። ነዋሪዎችም ቢሆኑ ጫትና ሲጋራ ይዘው የተገኙ እንደሆነ የገንዘብና እስራት ህጋዊ ርምጃ ይወሰድባቸዋል። ታዲያ ይህ መልካም ጎን ያለው ቁጥጥር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ቢተገበር ትውልዱን ከጥፋት አቀብነው ማለት አይደል?
ጉዞዬን ቀጥያለሁ። መንገዱ በሰው ዓይነት ተሞልቶ ያስተዋለ አዲስ አበባ አለመፈንዳቷን ሳያደንቅ የሚያልፍ አይመስለኝም። አንድ ሽማግሌ እጃቸው ላይ ያሉ ርጋፊ ሳንቲሞችን እያንቃጨሉ ሲለምኑ እዝነልቦናዬ አደመጣቸውና ዓይኔ ድምጻቸውን ተከትሎ ሁኔታቸውን አገናዘበ።
“ዋይ ዋይ ሲሉ፣
የረሃብን ጉንፋን ሲስሉ፣
አንጀታቸውን አስረው ሲያለቅሱ አይቼ፣
ምን ላርጋቸው አለፍኳቸው ትቼ።”
በማለት እንደ ጥላሁን ገሰሰ አላለፍኳቸውም፤ ከተነጠፉበት ቆሻሻ ስፍራ አንስቼ በአቅራቢያ ካለው ምግብ ቤት ገብተን መአድ አብረን ተጋራን እንጂ። ውሃ ሲጠጡ እንደነቃ አለት የደረቀ ጉሮሯቸው ‹‹ቺስ›› ይል ነበር፤ ምግብ እንኳን መዋጥ አቅቷቸው ደረታቸውን ደግፈውና አስር ጊዜ እየተመተሙ ያባብሉት ነበር። በዙሪያዎ ጧሪ ቀባሪ የለዎትም አባቴ? አልኳቸው ሆዴ እየተንቦጫቦጨ። በመከራ ጥፍር የምታክል ጉርሻ እያጎረስኩ ካበላኋቸው በኋላ ነፍሳቸው ስትለመልም ጎናቸው ሲጠገን ለጥያቄዬ መልስ ሊሰጡኝ ከንፈራቸውን አላቀቁ።
“ከሰው እህታ ከፈጣሪ ቅርታ ይጠብቅህ ልጄ” ብለው መረቁኝ በስስት እያዩኝ። አሜን አለማለቴን ልብ ሲሉ ታሪክ አስቀደሙና ምርቃታቸውን በውል አስረዱኝ። “አስተምራ፣ ድራና ኩላ ለወግ ማዕረግ ያበቃችው ልጇ በሚስቱ ጥላቻ ተገፋፍቶ እናቱን አልይሽ ይላቸዋል፤ እናትም መሸሻ ቢያጡ እንባቸውን እያዘሩ ገዳም ገቡና ለፈጣሪያቸው አቤት አሉ። ከዓመታት በኋላ ድርቅ ሆነና ልጇና ሚስቱ በረሃብ ተቆሉ፤ እናት ግን የወለደ አንጀታቸው አልችል ቢላቸው አሳቻ ሰዓት ጠብቀው ጨለማን ተገን አድርገው ከፍሬ ግብሩ ስንዴ በነጠላቸው ቋጥረው ቀን እንዲወጡበት ለማንም እንዳይናገር አስጠንቅቀው ሰጡት።
የመከራ ቀናት አልፈው ደህና ጊዜ ስለመጣ ሁኔታቸውን ሊጠይቁ ከልጃቸው ቤት ዘንድ ሲሄዱ አላገኙትምና “ከመጣሁ አይቀር” ብለው ከሚስቱ ጋር ጨዋታ ቢያሰኛቸውም የምራታቸው ፊት ግን አልተፈታም። “ልጄ ሲመጣ እመጣለሁ” ብለው ሊወጡ ሲሰናዱ “ምን አስር ጊዜ ልጄ ልጄ ይላሉ? ለፍሬ ግብር የተሰጠዎትን የገዳሙን ስንዴ ሰርቀው ላበሉት? ቆብ ጭነው ሌብነት?” አለች የንቀት ሳቅ አስከትላ። ሚስጥራቸው ገሃድ እንደወጣ ሲያውቁ መልስ ለመስጠት አልደፈሩምና አንገታቸውን እንደደፉ ሲወጡ ልጃቸው ጋር በመንገድ ተገጣጠሙና ከበቅሎው ሳይወርድ ጫንቃ ሊስም ጎንበስ ሲል “እህ! እህ!” አሉት በመጠየፍ፤ የናቱ እህታ እንደ ጦር የወጋው ልጅም ካጎነበሰበት ቀና አላለም፤ መሬት ተቀብላ ነፍሱን ነጠቀችው።
ሥርዓተ ቀብሩ ሲፈጸም እናት ከማልቀስ ይልቅ “ሰዎችዬ እህታ ሰውን ይገላል?” በማለት ይጠይቁ ነበር፤ እኔም የደረሰብኝ ከዚህ የተለየ አይደለም” አሉ ዓይናቸው እንባ አርግዞ። ‹‹ምን አጋጠመዎት አባቴ?›› አልኳቸው በድጋሚ እድሜ ያቀለመው የሕይወት መጻሕፍቸውን ለማንበብ ጓጉቼ። “ለመስማት እንኳን የሚከብድ ነው ልጄ” አሉ በአዳፋ ጋቢያቸው የፈሰሰ እንባቸውን እየሞዠቁ። ‹‹ግድ የለም ያጫውቱኝ›› ስል አደፋፈርኳቸውና በሰለለ ድምጽ የዘመናቸውን ውጣ ውረድ እየመዘዙ በወግ ሰፌድ አሰጡልኝ።
“በጋ ከክረምት ቀንበሬ የማይፈታ ጎተራዬ የተቀናጣ ነበር፤ ዳሩ ምን ይሆናል! ጉልበቴ ደክሞ ከቤት ስውል በእግሬ የተተካው ልጄ ግፍ ዋለብኝ” አሉ ከጋቢያቸው ጥለት ጋር የሚተፉትን ቃል እየፈተሉ። ከጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ በኋላ ሃሳባቸውን ቀጠሉ። “ሀብት ንብረቴን በስሙ እስኪያደርግ ድረስ እንደ እንቁላል አፈር ዓይንካህ ብሎ ይዞኝ ነበር፤ የልቡ ሲደርስ ግን የሚስቱን ቃል ሰማና የወርቅ ሳጥን አሰርቶ ከሚስቱ ጋር እየተደጋገፉ ከገደል ጫፍ አወጡኝና ሊወረውሩኝ ሲሉ እናገር ዘንድ የመጨረሻ እድል እንዲሰጠኝ ለመንኩት፤ እሽታውን እንዳገኘሁ በቅድሚያ ውድ ዋጋ ያወጣህበትን ሳጥን እንደ ቀላል አትጣለው፤ ሁለተኛ ብታስቀምጠው ላንተም ይጠቅምሃል፤ ምክንያቱም የወለድካቸው ልጆችህ ሲደርሱ አንተንም ይወረውሩበታልና ስለው ጊዜ ደንግጦ እያለቀሰ መለሰኝ። ከዚህ በኋላ አብሪያቸው ለመኖር ሆዴ ሻከረና ለጎዳና በቃሁ” አሉ ጣምራ ጣምራ የሚወርደው እንባቸው ፊታቸውን እያጠበ። የልጃቸውን ግብዝነት የሚስቱን ደባነት የምገልጽበት ቃል ሳጣ ለካስ ሀብታምና ግፈኛ ተረት የለውም ብዬ ተውኩት።
ሂሳብ ከፍዬ ጥቂት የመቶ ብር ኖቶች ካስጨበትኳቸው በኋላ እኛ ካረፍንበት ቀጣይ ቤት ላይ ጩኸት ስለሰማሁ ምንነቱን ለማረጋገጥ ተፈተለኩ። አንዲት ባልቴት እየተብከነከኑ “ልጄን ሊገለው ነው አስጥሉልኝ?” ይላሉ። ከቤት ዘልቄ ሁኔታውን ሳደምጥ ከተቆለፈው ክፍል ውስጥ “እጅህን ዘርጋ” የሚል ድምጽ ሰምቼ ጆሮዬን ብጥልበት “አባዬ የዛሬን ማረኝ፤ ከእንግዲህ አይደገመኝም” ይላል የልጅ ድምጽ። እንዲከፍትልኝ ስማጸነው አባት በጄ ሊል ባለመቻሉ እናትዬዋ ሰብሬ እንድገባ አስገደዱኝና የሳንቃውን መሃል ደረት በርግጫ ሳፈርሰው ከፊቴ ገለል አለ።
እንደገባሁ ባየሁት ነገር ቆሌዬ ተገፎ ፀሐይ እንዳጠወለገው ቅጠል ኩምሽሽ ብዬ ቀረሁ። ገራፊው አባት ሳይሆን ልጅ ነበር። ዳግመኛ ሲጋራ ላያጨስ ምሎ ተገዝቶ ቃሉን የሰጠው ልጁ ተደብቆ ሲያጨስ አገኘውና እያዳፋ አስገብቶ ክፍሉን በመቆለፍ ቀበቶውን ፈትቶ አቀበለው፤ ልጅ ግራ ተጋብቶ ቅጣቱን ሲጠባበቅ አባት ከወገብ በላይ ልብሱን አወለቀና እንዲሰነዝር ልጁን አዘዘው። ልጅ እንባው እንደ ዶፍ እየወረደ ይቅርታ ቢለምነውም አባት ግን “እጅህን ዘርጋ” ይላል በቁጣ። በስንት መከራ ተገለገለና ስለድርጊቱ ሲያስረዳኝ “ልጄን መክሬ መመለስ ካቃተኝ ጥፋተኛው እኔ እንጂ እሱ አይደለምና ሊገርፈኝ ይገባል” አለ አባት የሱም እንባ እንደዥረት እየፈሰሰ።
ይህን ሲል የጠቢቡ ሰለሞን ፍርድ ታወሰኝና ከሃሳቡ መዝገን ከጀለኝ። አባቱን የገደለ ልጅ ይቀርብና ችሎት ሲቆም ሕዝቡ “ይሰቀል፤ ይገደል” በማለት ጮኸ። ልጁ አባቱን ለምን እንደገደለ በተጠየቀ ጊዜ “ሲያሳድገኝ በለው እያለ ነው፤ ሕፃን ሳለሁ እንኳን እኩዮቼ መትተውኝ ሳለቅስ ከአየ አትለውም? ደግሞ እሱ ያሸንፍህ? ይለኝ ነበር፤ በዚህ ሁኔታ ያደኩ ልጅ አንድ ቀን ርቦኝ ብር ሰርቄው ዳቦ ብገዛ ዱላ ጨረሰብኝ፤ እኔም አጸፋውን ስመልስ ነፍሱ አለፈች” ሲል አስረዳ። ጠቢቡ ሰለሞንም “የዘራው መራራ ፍሬ ራሱን አጠፋው” በማለት ፍርዱን ሰጠ።
በዚህ እሳቤ እንሳፈርና የኛ ወላጆችስ በእንዲህ መልኩ አይደል ያሳደጉን? ሙዚቃችንም ቢሆን አባረህ በለው፤ አትልቀቀው፤ አይደል የሚለው? የሚሠሩ ክሊፖችስ ጠመንጃ፣ ገጀራ፣ ቀስት፣ ሳንጃና ጎራዴ አይደል ታጥቀው የሚያሳዩት? ፊልሞቻችንንም ያየን እንደሆነ የሚሳሉት ገጸ ባህሪያት ሲቸገሩ መላ ለመፍጠሩ ሲናደዱ ቶሎ ለመብረዱ መጽሐፍ ሲያነቡ ሳይሆን የሚታየው አልኮል እየገለበጡ ለተጨማሪ ጥፋት ሲነሳሱ ነው።
የሀገሬን የጥበብ ሥራ አኩርፌ እንደ ገደል ዛፍ እየተወዘወዝኩ ሳዘግም ለወጣቱ ስንቅ የሚሆን አንድ አባት ያጫወቱኝ ታሪክ ትዝ አለኝና በብዕር ገመድ አሰርኩት። ሰውዬው ከሚያሳድደው ነብር ለማምለጥ ሲሸሽ ጭው ያለ ገደል ከፊቱ ተደነቀረ፤ “ከመሞት መሰንበት” አለና ከገደሉ ጫፍ የበቀለችውን ሐረግ ይዞ ቁልቁል ሲወርድ አይጦች ሐረጓን ለመቁረጥ በጥርሳቸው ሲገዘግዟት ተመለከተ፤ ተስፋ ባለመቁረጥ የሚይዘው ነገር ሲፈልግ ከገደሉ መሃል ወገብ ላይ የተንዠረገገ የወይን ፍሬ አየና እንደ ምንም እየተንፏቀቀ ተጠግቶ ካስጎመጀው ፍሬ መብላት ቻለ። ለሰውዬው የሚያሳድደው ነብር፣ ሐረጓን ለመበጠስ የሚታገሉ አይጦችም፣ የገደሉ ጥልቀትም ከወይኗ ፍሬ ጋር ለንጽጽር አልቀረቡለትም።
የእኔም ዘመን ወጣት ሆይ ከኋላህ ፈተና ይልቅ ከፊትህ ያለው ስኬትህ ውሃ ያነሳልና ከሰውዬው ታሪክ ለመማር ልቦናህን አስላ የጽሐፌ መልዕክት ነው።
ገፋ ገፋ አድርገህ ውጣው አቀበቱን፣
ልብ ያሰበው ነገር አይገኝ እለቱን።
በሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም