በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የብሄራዊ የዳቦ ስንዴ ምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግሉ ከተቋቋሙ መአከላት መካከል በ1987 ዓ.ም የተቋቋመው የቁሉምሳ የግብርና ምርምር ማዕከል አንዱ ነው። ከዚህ ቀደም ማዕከሉ በኢትዮጵያ መንግሥትና በስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (SIDA) የጋራ ስምምነት የተመሰረተ ሲሆን፤ የጭላሎ የገጠር ልማት ድርጅት ውስጥ በዘር ማባዣ ጣቢያነት ያገለግል ነበር።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከአገሪቱ ሥነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ የገበሬውን ሕይወት በማሻሻል በምሥራቅ አፍሪካ የስንዴ ምርምር የልዕቀት ማዕከል ለመሆን እየሠራ ይገኛል። በዚህም ማዕከሉ በመላው አገሪቱ በስፋት በማዳረስ የአርሶ አደሩን ሕይወት የለወጡ የተሻሻሉ የዳቦ ስንዴ፣ የምግብና የቢራ ገብስ፣ የቆላ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ የቻለ ሲሆን በተለይ የአገሪቱ የዳቦ ስንዴ ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ታዲያ በማዕከሉ ለ21 ዓመታት ያገለገሉት አና ለእርሻ ከማይውለው የማዕከሉ 35 ሄክታር የመሬት ይዞታ ውስጥ 25 ሄክታር የሚሆነውን መሬት ለደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በማዋል፣ ጥምር ግብርናን ለማስፋፋት እንዲሁም ከእርሻ ማሳ በመውጣት ከማዕከሉ በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኘው ቁሉምሳ ወንዝ በዝናብና ጎርፍ ኃይል ተጠርጎ የሚገባውን ለም አፈር ለማቀብና መሬቱን በማልማት የሠሩ ቁልምሳ የግብርና ምርምር ማዕከል ከአፈራቸው መካከል አቶ ዘውገ ባህሩ አንዱ ናቸው።
ትውልድና ልጅነት
አቶ ዘውገ ባህሩ ይባላሉ። በቀድሞ አጠራር የአርሲ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ አርሲ ዞን በቀርሳ ከተማ ሙኔሳ ወረዳ በስተደቡብ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጮባ ሚካኤል ተብላ በምትታወቅ ቦታ ላይ የዛሬ 60 ዓመት ነው የተወለዱት። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሰላና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በዲግሪ ፕሮግራም ትምህርታቸውን መከታተል ጀምረው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በተከሰተ የመንግሥት ተቃውሞ እንቅስቃሴ መነሻነት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አለመረጋጋት በመፈጠሩ ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ወደ ሃዋሳ መለስተኛ እርሻ ኮሌጅ በማቅናት በአትክልትና ፍራፍሬ የትምህርት መስክ በዲፕሎም ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል። በኋላም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ በገጠር ልማትና ግብርና ኤክስቴንሽን አግኝተዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የአካባቢ ደን ተከላና የአፈር ጥበቃ ሥራዎችን ለ 21 ዓመታት አከናውነዋል። የችግኝ ተከላው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ባለው ጊዜ ውስጥም ከግማሽ ሚሊየን በላይ ችግኞችን በማፍላት ተከላ አካሂደዋል። ባለሙያው ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ በወቅቱ ምክንያት የሆናቸውን ነገር ሲናገሩ፤ የማዕከሉ ዙሪያው ይዞታ ተዳፋት ድንጋያማና ሸንተራራማ መሬት ሲሆን፣ በበልግና በክረምት ወቅት መሬቱ ሲታረስ አፈሩ ከመላላቱ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ የዝናብ ወቅት ለም አፈር ከማሳ እየተጠረገ ወደ ወንዝና ሸለቆ መወሰዱ ነበር ይላሉ። ታዲያ የእነዚህን መሬቶች ተፈጥሯዊ ይዞታ ለመመለስ የነበራቸው ተነሳሽነት ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
የአካባቢ ደን ተከላና እንክብካቤ
አቶ ዘውገ የልማት ሥራውን ሲጀምሩ ትኩረት ያደረጉት በአገር በቀልና በውጭ አገር ዛፎች ችግኝ ተከላ ላይ ነበር። በአካባቢው ከረጅም ዓመታት በፊት በስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በውጭ አገር ዛፎች ላይ የተወሰነ ጥናት ቢካሄድም በአገር በቀል ዛፎች ላይ ግን የተሠራ ሥራ ባለመኖሩ በዚሁ ዙሪያ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ጠቀሜታ ያላቸው የአገር ውስጥ የዛፍ ዝርያዎች ላይ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
በቁሉምሳ ወንዝ አካባቢ የሚገኘው ድንጋይ ለልማት በሚል በተለያዩ ጊዜያት እየተፈለጠ ይነሳ ስለነበር የአካባቢው መሬት የላላ እንዲሆን አድርጎታል። መሬቱ ተዳፋት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የለማው አፈር የሚያግደው ነገር ባለመኖሩ በጎርፍ ተጠርጎ ይሄዳል። ይህንንም ሁኔታ በመመልከት ድንጋይ የተነሳበት አካባቢ ችግኞችን በመትከል አፈሩን ማዳን እንደሚቻል አቶ ዘውገ ይረዳሉ። በዚህም የቁሉምሳ ወንዝን ተከትለው የነጭ ባህር ዛፍ ችግኞችን በመትከል የዛፍ ተከላን ሀ ብለው ጀመሩ። አሁን በማዕከሉ ይዞታ ነጭ ባህር ዛፍ በ5 ሄክታር መሬት ላይ ተንጣሎ ይታያል።
ለምርምርና ጥናት
የውጭ አገር የዛፍ ዝርያዎችም ከመትከል ባለፈ የአገር ውስጥ ዝርያዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች በማምጣት ተከላ አካሂደዋል። በተለይም በደቡብ ሸለቆ ነጭ ባህር ዛፍ ሊበቅሉ ባልቻሉባቸው ቦታዎች አገር በቀል የሆነውን ሰሳ የተባለ ዝርያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በርካታ ችግኞችን በመትከል ለምርምርና ጥምር ግብርናን ለማስፋት ጠቀሜታ እንዲውሉ ማድረጋቸውን ገልጸውልናል። ባለሞያው ጥምር ግብርናን ሲያስረዱ ጥምር ግብርና (agroforestery) ስንል ዛፍና ሌሎች ሰብሎችን እርስ በርስ በማይጎዳዱበት መንገድ በማጣመር ማልማት ሲሆን፤ ለምሳሌ ቡናን ብንመለከት ከዋንዛ፣ ከኮርችና ሰሳ የዛፍ ዝርያዎች ጋር፣ ቅመማ ቅመም ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ከተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች ጋር በጋራ በማጣመር ይለማሉ በማለት አስረድተውናል።
የባለሞያው የሥራ ውጤት የሆነው የጥምር ግብርና ሥራ የተለያዩ ጥናታዊ ምርምሮች መነሻ መሆንም ችለዋል። የዘር ምንጩ ከምዕራብ ኢትዮጵያ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ሰሳ የተሰኘ አገር በቀል የዛፍ ዝርያ በተለይ በኢትዮጵያ የቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ለቡና ጥላነት የሚያገለግል ሲሆን፤ ለማር እንዲሁም ለማገዶና መሰል አገልግሎቶችም ይውላል።
እንደዛሬው ባህር ዛፍ በአገሪቱ ከመሰራጨቱ በፊት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለከተማ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው የአገራችን ብርቅዬ ዛፍ የሆነው የአበሻ ጽድም በአቶ ዘውገ አይን ውስጥ ገብቷል። ባለሞያ ይህንን ዛፍ ለሙን አፈር ጠብቆ ለማቆየትና እርከን ለመሥራት ተጠቅመውበታል። በጉዟችን መመልከት እንደቻልነው የአበሻ ፅድ በተተከሉባቸው ቦታዎች የሚገኘው መሬት ጥልቀት የሌለውና ተዳፋታማ ከመሆኑ በተጨማሪ የአፈር ክምችት የሌለበት ሲሆን፤ ሁኔታውን ተቋቁሞ ማደጉን መመልከት ችለናል።
በአገራችን ብርቅዬ የሆኑትን የዋንዛና የወይራ ዛፍ ችግኞችን በማፍላትና በሰፊ መሬት ላይ በመትከል በአካባቢው ለሚኖሩ አእዋፋትና እንሰሳት ምግብነትና መኖሪያነት እንዲያገለግሉ ያደረጉ ሲሆን፤ ለንብ መቅሰሚያና ለጣውላ ሥራ የሚውለውን ይህንን ዛፍ ምንም እንኳን እንደ ሰሳ ሁሉ ቆላማ አካባቢ የሚስማማው ቢሆንም በደጋማ አካባቢም በእንክብካቤ ከተያዘ ሊበቅል እንደሚችል ማየት ያስቻለን ነበር።
የአትክልትና ፍራፍሬ የምርምር ሥራዎች እየሰፉ በመምጣታቸው ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ አብዛኛውን ትርፍ ጊዜያቸውን በአትክልትና ፍራፍሬ ምርምር ላይ ማዋል መጀመራቸውን አቶ ዘውገ አጫውተውናል። በአሁኑ ወቅትም በሥራ ሂደቱ በተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች በተለይም አቮካዶና አፕል ላይ ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁን ወቅት በስፋት እየተከናወኑ ላሉት የፍራፍሬ ምርምር ሥራዎች ከረጅም ዓመታት በፊት የተተከሉት የዛፍ ዝርያዎች ከፍተኛ ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል። ሥራው ከፍተኛ የእንጨት ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በሳይንሳዊ አገላለጽ ገረዛ (tinning) በማከናወን እንጨቶቹን ለዚህና ሌሎች አገልግሎቶች በማዋል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የአፈርለምነት ጥበቃና እንክብካቤ
አቶ ዘውገ በአፈር እቀባ ላይ ያነጣጠረና የእንሰሳትና የሰው ንክኪን ለመቆጣጠርና ጥበቃ ለማድረግ ቋሚ አጥር( life fense) ተከላ በኮሽም በቃጫና በቁልቋል ተክሎች ያከናወኑ ሲሆን፤ ተከላው በደቡብ ሸለቆና በሰሜን ቁሉምሳ ወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም በማዕከሉ ቅጠር ግቢ ውስጥ 6 ኪሎ ሜትር የሸፈነ መሆኑን ተዘዋውረን ተመልክተናል። የቃጫ ተክል በዓመት አንድ ጊዜ እንጨት ያበቅላል ያሉት አቶ ዘውገ እንጨቱም ለመኖሪያ አካባቢ አጥር መስሪያነት ፣ለዶሮ እርባታ ቦታ መስሪያንና ለአልጋ ሥራ እንደሚጠቅም ገልጸውልናል። በተመሳሳይም የቁልቋል ተክል በተለያዩ አካባቢዎች ለሰውም ሆነ እንሰሳት ምግብነት የሚያገለግል ተክል ሲሆን፤ አቶ ዘውገም ይህንን ተክል ከኮሽም ጋር በማመሳጠር በደቡብ ሸለቆ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ በመትከል እጅግ ውጤታማ ሥራ መሥራት ችለዋል። በ20 ዘመናዊ ቀፎዎች የጀመሩት የንብ እርባታ ሥራም በማዕከሉ የአቶ ዘውገን ስም የሚያስጠራ ሆኖ አግኝተነዋል።
አቶ ዘውገ በዚህ ብቻ አላበቁም። በገደል ላይ የ2 ኪሎ ሜትር የድንጋይ አጥር በማጠር ለማዕከሉ እንዲሁም ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ ጥቅም የሰጠ የአፈር ጥበቃ ሥራ መሥራታቸውን ተመልክተናል። በዚህም ያለምንም ከልካይ ከእርሻ ማሳዎች ላይ በጎርፍ ታጥቦ ወደ ወንዝ ይገባ የነበረውን ለም አፈር አንቆ በማስቀረት እንዳይሄድ ያግደዋል። ከለም አፈሩ በተጨማሪም በዝናብ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት አፈሩን በመያዝ ወደ ወንዝ ይምዘገዘግ የነበረውን የጎርፍ ውሃ በተወሰነ መልኩ በመገደብ ተረጋግቶ እንዲቆይ ያደርገዋል። ይህም አካባቢው ተፈጥሯዊ ውበቱን የጠበቀ እንዲሆን ያስቻለ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት ለእርሻ የማይውሉ አካባቢዎችን በምን ዓይነት መልኩ በመጠበቅ የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ሳይባክን በቀላሉ መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።
አርአያነትና የማህበረሰብ አሳታፊነት
ይህንን የልማት ሥራም በቅርበት መመልከት እንድንችል ያደረገን በዚሁ ባለሞያ የግል ጥረት የተደለደለ የአንድ ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ መኖሩ መሆኑን መግለጹ ይህ የልማት ሥራ በጣም ጥልቅና ጊዜ የወሰደ እንደነበር በግልጽ ለመመልከት ይረዳናል። በዚህ የልማት ሥራ ውስጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ላለፉት 13 ዓመታት ያለምንም መሰላቸት በአቶ ዘውገ አስተባባሪነት ተሳትፎና ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ዘውገ በኩራት ይናገራሉ። በሌላ በኩል የአካባቢው ገበሬዎችና የከተማ ነዋሪዎች የቡናና የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ የዛፍ ችግኞችን በየመኖሪያ አካባቢዎቻቸው በመትከል የአካባቢያቸውን ተፈጥሯዊ ውበት መጠበቅ የቻሉ ሲሆን፤ ከተክሎቹም ጥቅም መግኘት ችለዋል ብለዋል። ይህም የአካባቢው ማህበረሰብ ሊለሙ አይችሉም ብለው የተዋቸውን መሬቶች መልሶ በምን መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻልም ያስተማረ ነው።
ለውጦች
የደን መበራከትና የአካባቢው መልማት ምን ለውጥ አስከተለ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ዘውገ ምላሽ ሲሰጡ ረጅም ዓመታት የፈጀው የአካባቢ ልማትና የአፈር እቀባ ሥራ አካባቢው አረንጓዴነቱን መልሶ እንዲላበስና ተፈጥሯዊ ይዘቱን ጠብቆ በማቆየት የተሻለና ምርታማ አካባቢ ለመፍጠር አስችሏል። በተጨማሪም እንደ ጅግራ፣ቆቅ፣ የሜዳ ፍየሎች፣ ሚዳቆ፣ ጉሬዛዎች፣ ዱኩላዎች፣ የሜዳ ፍየሎችና የመሳሰሉ የተለያዩ ጠቃሚና ብርቅዬ የዱር እንሰሳት ኑሯቸውን በአካባቢው እንዲያርጉ አስችሏል። ምንም እንኳን የሰብል ምርቶችን በማጥቃት ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙ ቢሆንም ጦጣዎችም የዚህ ደን ልማት ተጠቃሚዎች ሆነዋል ያሉት ባለሞያው እነዚህን የዱር እንሰሳት በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥራቸው እየጨመረ ከመምጣቱ የተነሳ በማዕከሉ ውስጥና አቅራቢያ በቅርብ ርቀት መመልከት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል። በአካባቢው ባደረግነው ጉብኝትም የተወሰኑትን እንሰሳት መመልከት ችለን ነበር።
የወደፊት ራዕይ
ለእርሻ የማይውለውን የአካባቢው የተራቆተ መሬት ሙሉ ለሙሉ በማልማት በደን ተሸፍኖ መመልከት እስካልቻልኩ ድረስ የልማት ሥራዎችን መደገፉን አላቆምም ያሉት አቶ ዘውገ አካባቢውን የሚያለማና የተፈጥሮ ሀብትን በተገቢው መንገድ የሚጠቀም ተተኪ ትውልድ ከማፍራት አንፃር ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል። በሳቸውና መሰሎቻቸው ጥረት በማዕከሉ ለእርሻ የማይውል መሬትን የማልማት ሂደት ቢከናወንም አሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው መሬት ሥራ ይጠይቃል ያሉት ባለሞያው ይህ የሚያመላክተው አሁንም ከዚህ በተሻለ ፍጥነትና ጥረት የማልማት ሥራው መካሄድ እንዳለበት ነው ሲሉ ያክላሉ። የአካባቢውን ተፈጥሮና ለቦታው ተስማሚ የሆኑትን ተክሎች በመለየት የተጠና ልማት ማከናወን ከተቻለ ጥቅም የማይሰጥ መሬት የለም ያሉት አቶ ዘውገ ይህ ካልሆነ ግን ሙሉ ለሙሉ ማልማት ቀርቶ አካባቢው አሁን የደረሰበትን የልማት ውጤት ጠብቆ ማቆየት አስቸጋሪ እንደሚሆን ነግረውናል።
ዕድሜያቸው ለጡረታ መቃረቡን ገልጸን ለዘመናት ከለፉበት ሥራ መገለሉ ስጋት አልፈጠረቦትም የሚል ጥያቄ አስከትለንላቸው ነበር። አቶ ዘውገ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ “የጡረታ መውጣት ስጋቴ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ሥራዬ መልክ ይዞ አካባቢው መልማት ሲጀምር፣ የአካባቢው አፈር ከመሸርሸር መዳኑን ስመለከት፣ ጥረቴ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አርአያ ሆኖ ሌሎችም የኔን መንገድ መከተል ሲጀምሩና ከተለያዩ ከፍተኛና መለስተኛ የትምህርት ተቋማትም ተማሪዎችና መምህራን በተደጋጋሚ በመምጣት ትምህርትና ልምድ ወስደው ሥራ ላይ ማዋል ሲጀምሩ ከምንም በላይ ግን በልማት ዙሪያ የነበረኝ እውቀት ማደጉንና መለወጡን ስመለከት ነበር የጀማመረኝ። ሆኖም የጀመርኩትን የልማት ሥራ አቅሜ በፈቀደ መጠን ማከናወኔን ፈፅሞ አላቆምም ” ነበር ያሉት።
ከአቶ ዘውገ ጋር የነበረንን ቆይታ ከማብቃታችን በፊት አካባቢው ወደፊት ምን መምሰል አለበት ብለው ያስባሉ ብለን ጠይቀናቸው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸውም አካባቢው የአገራችን ብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ እንደመሆኑ መጠን የነሱን ፈለግ በመከተል ለሚመጣው ወጣት ትውልድ ጥሩ የስፖርት መለማመጃ ስፍራ መሆን የሚችል ነው ያሉ ሲሆን፣ ከፍ ሲልም አካባቢው ለአገሪቱ ዋና ከተማ ቅርብ በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ለመጣው የፊልም ኢንዱስትሪ የፕሮዳክሽን ቦታ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል ያላቸውን ምኞት ገልጸውልናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2012
አብርሃም ተወልደ