አገራዊ የትብብር፣ የአንድነት እና የጋራ ጥረቶቻችንን ለማዳከም የሚፈታተኑን ችግሮች በየዘመናቱ አጋጥመውናል። በተለመደው የአርበኝነት ትጋት፣ አንድነትና መስዋዕትነት የመክፈል ታላቅ ተጋድሎ ግን ብዙዎቹን ችግሩ ሳይበረታ ተወጥተ ናቸዋል። ድል ተመተዋል። አገርንም መታደግ የታፈረች፣ የተከበረች፣ ውብና ህብር ኢትዮጵያን እስከአሁን ማቆየት ተችሏል። ይህን ክብር በአባቶቻችን ጥንካሬ መወጣት የቻልን ቢሆንም ቅሉ ከዚሁ ከኛው ጉያ የወጡ ባንዳዎች ዞረው ወገናቸውን መውጋታቸው በጥቁር ታሪክ ላይ መመዝገቡም ከድል ጀርባ ያለ ሌላኛው ጨለማ ጎናችን ነው።
የባንዳዎች ክህደት ታሪክ ዘመናትን ይሻገራል። ምክንያቱ ደግሞ የሚበዘብዙትና ለትውልድ የሚተ ክሉት የሚለመልም ሳይሆን መጥፎ የታሪክ አሻራ በመሆኑ ነው። በተለይ በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት ለህዝብና ለሀገር ታማኝ ያልሆኑ ባንዳዎች መኖራቸውን ስንሰማ ህዝብና መንግሥት ማንን ማመን አለበት የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ያሳ ስባል።
በየዘመናቱ ስለአገር እና ስለሕዝብ የሚያስቡ፤ የትኛውንም ዓይነት ዋጋ ለመክፈል ወደኋላ የማይሉ፤ የቁርጥ ቀን ልጆች ብቅ ብቅ ይላሉ።ታሪካዊ አሻራቸውንም ለትውልድ ትተው ያልፋሉ። በዚህ መልኩ እየተሟገቱ ያለ ድካምና ዕረፍት የሚተጉ እንቁ የአገር ልጆች የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒ የቆሙትን ለዝርፊያ ቀዳዳ ፈላጊ ሙሰኞችን መርገም ስላለብኝ ነው ዛሬ ብዕሬን ያነሳሁት።እነዚህ ሰዎች ጥቅማቸው አገራቸው ነች።በጥቅማቸው አገርና ሕዝብን ሸጠውም ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ቀጥለዋል። ነገም ማስከፈላቸው አይቀሬ ነው።ደማቸው ገንዘብ ነውና።
ዛሬም አገራችን ወቅቱ በፈጠረው ችግር ውስጥ ሆና ይህንን ሃሳብ ባናነሳ ደስ ይል ነበር።ሆኖም የሰውን ልጅ ዋጋ እያስከፈለ ቢሆንም በዚያው ልክ የእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆኑ ፍልፈሎች መጥተውብናልና ዝም ማለቱ ያዳግታል።
ህሊና ያለው ስለ አገሩ ትንሽ የሚያስብ ሰው፤ በአፈፃፀም መመሪያው ከተዘረዘረው ውጪ እንደ አይፎን ስልክና አፕል ላፕቶፖች ሕገ ወጥ ግዥ መፈፀሙ ምን የሚሉት ሃሳብ ነው።ለዚያውም ለአንድ ላፕቶፕ 152 ሺህ ብር እና ለአንድ ሞባይል 94 ሺህ ብር ማውጣት ድሃና ነገ የተሻለ ለመሆን የምትጥርን ሀገር መካድ ይመስለኛል።ከዚያ አልፎ ሲጠቀሙበት የነበረውን ሀብት ለሌላው መጠቀሚያነት እንዲውሉ ለመንግሥት ገቢ አድርጉ ሲባል በፍጹም ፈቃደኛ አልሆኑም።ታዲያ ይህ ጤነኝነት ነው ትላላችሁ።እንደ እኔ እንደኔ ለህዝብ ለመሥራት ሳይሆን ገንዘብና ጥቅም ያናወዛቸው ሰዎች ወደዚያ እንደገቡ ይሰማኛል።
በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት ባላደርግም አንድ ነገር ከጅምሩ የተበላሸ ይመስለኛል።የከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ለማሻሻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት በነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር መ30-899/56 ባወጣው መመሪያ በአንቀጽ 8 ቁጥር 4 ተመላሽ የማይደረግ ሞባይልና ላፕቶፕ ለአንድ ጊዜ ተገዝቶ እንዲሰጥ ሲወስን ዝርዝር መመሪውም አብሮ አለመውጣቱ! አገር ወዳድ ሰው መጀመሪያ ራሱን ለአገሩ መስጠት አለበት።በዚህም በራሳቸው የሚያደርጉበትን መንገድ መቀየስ ይቻል ነበር።ተቋማትን ማራቆት ግን አገርን ከመሸጥ ይተናነሳል ብዬ አላስብም።ተቋማቱ ከሌሉ አገር በማንኛውም መልኩ ልትለወጥ አትችልም።ዛሬም የሆነው ይህ ይመስለኛል።
ይህንን ግዢ ከፈጸሙት መካከል የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አንዱ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ጉዳዩን አስገራሚ ያደርገዋል።ምክንያቱም ብዙዎችን የሚያፈራ፤ በስነምግባር የሚያንፅ ከምረቃ በኋላ አገር ተረካቢ ይሆናሉ የምንላቸውን ዜጎች በአርዓያነት የሚመራ ተቋም ብልሹ አሠራር መከተሉ እጅጉን ያማል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ከዚህ በኋላ ቢያንስ አንሰርቃችሁም” ብለው ለህዝብ ቃል ቢገቡም በእሳቸው የሚመሩ አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ግን ከተፈቀደላቸው ውጪ የላፕቶፕና ሞባይል በተጋነነ ዋጋ በማስገዛት የህዝብና የመንግሥትን ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ለግል ጥቅም እያዋሉ መሆኑ አያጠያይቅም።በእርግጥ ሰው ተቀምሶ አይታወቅ።ሥራው ሲያጋልጠው አውጥቶ መጣል ይቻል ይሆናል እንጂ።
ምንም አፍረት ያልፈጠረባቸው እነዚህ ሰዎች «አዛዥ ታዛዥ የለም» በሚል ህሳቤ የኮሮና በሽታ ከፈጠረው ስጋት በላይ አገራዊ ስጋት በመሆን ከሕግ ውጪ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ጥቅማቸውን ሞሉ።ህዝብ እንዳይራብ በማለት ብዙዎች ያላቸውን እያካፈሉ ባሉበት እነርሱ ግን ተሰብሮ ለሚወድቅና ዘላለም ለማይዙት እቃ ብዙ ህዝብ ዳቦ በልቶ የሚያድርበትን ገንዘብ በዘበዙት።ታዲያ አሁን ምን ሞራል ኖሯቸው ተገዙልን፤ ልዘዛችሁ፤ አድርጉ ወዘተ የሚሉት።ቆይ እስኪ እውነቱን እናውራ ሳይሰጡ መሰጠት አለ እንዴ?
የአገሬ ሰው ‹‹ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል›› ይላል። አሁንስ አመላቸው አለቅም ብሎ ለቸግር ጊዜ ተብሎ ለህዝብ እየተሰበሰበ ያለውን ገንዘብ ቢበሉትስ አገር ምን ይውጣታል።እንጃ አላውቅም መልሱን ለእናንተው ልተወው።እንደ እኔ እነርሱ ስለአገር አፍ ሞልቶ ለማውራት የቱንም ያህል ሞራል የላቸውም።እንዲህ ያለው ኃላፊነት የጎደለው፣ አገራዊ ትብብርና መደጋገፍን የሚያሳንስ የግዢ ስርዓት፤ አገርን እንደ ካሮት ወደታች እንድታድግ የሚያደርግ ነውና መሳሳታችሁን አውቃችሁ ዛሬውኑ ህዝባችሁን በቶሎ ይቅርታ ጠይቁ።የአገርን ዘላቂ ጥቅም ከማሳጣት ያለፈ ርካሽ ሥራችሁ የትም አያደርሳችሁምና መንግሥት ተጠያቂ ሳያደርጋችሁ ራሳችሁን በመጠየቅ ታማኝነታችሁን ማሳየት ይኖርባችኋል የመጨረሻ መልዕክቴ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው