«ዘመን የሰው ልጆች የታሪክ፣ የማንነት፣ የባሕል፣ የሥነ ልቡና እና የህልውና መከተብያ፣ መሳያ፣ መበየኛ፣መንደፍያ እና ማቆያ ትንግርታዊ ሰሌዳ ነው። ይህንን ድንቅ ሸራ በመቁጠር በመቀመር በማስላት እና በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ የሚዘወርበትን ሥርዓት በመዘርጋት የሚጠቀምበት ማኅበረሰብ ደግሞ እርሱ ከዘመን ጋር የማይሄድ ከዘመንም ጋር የማይመጣ በዘመን ገላ ላይ ትናንት በአባቶቹ ዛሬ በራሱ እና ነገም በልጆቹ ህያው የሚሆን ታላቅ ሕዝብ ነው። የሲዳማ ሕዝብ ይህን ታላቅ የሥልጣኔ አበርክቶ አጥሮ፣ ጠብቆ አቆይቶልናል።”ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተናገሩት እንደመግቢያ እንዲሆነኝ ንግግራቸውን ተውሻለሁ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ስሜት ከሚያከብራቸው በዓላት ተወዳጅ ከሆኑት ውስጥ የዘመን መለወጫ በዓል አንዱ ነው። እንደ ዕፅዋት ሁሉ ሰው በመስከረም ላይ በተስፋ ስሜት ይለመልማል። ከዋዜማ ጀምሮ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጐዘጐዛል። አበባ በሥርዓት እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል። በተለይም ልጆች አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ። የሚያበሩት ችቦና የሚያነዱት እሳት በግርማ ምሽት ሲንቀለቀል ውጋገኑ ከአገር አገር ከሰፈር ሰፈር ከቦታ ቦታ… ይታያል።
ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ግን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በተመሳሳይ ወራት እና ስነስርዓት አይደለም የሚከበረው። የተወሰኑ ቦታዎች በተለይም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች አከባበሩ ይለያል። የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸው ከሚለዩባቸው መካከል የሲዳማ ዘመን መለወጫ አንዱ ነው።
«ፊቼ ጫምባላላ» በመባል የሚታወቀው የሲዳማዎች የዘመን ቀመር በከዋክብት ዑደት ላይ የተመሠረተ ነው። ብርሃናቱ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትም የተፈጠሩት ስለ አራት ነገሮች መሆኑንም ኦሪቱ ያብራራል። ለምልክቶችና ለዘመኖች፣ ለዕለታትና ለዓመታት በማለት። ትውፊታዊውና ኦሪታዊው መጽሐፍ ስለ ብርሃናት ተፈጥሮ ይገልጻል። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ በሰማያት ብርሃናት ተደረጉ ይለናል። ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በማታ እንዲገዛ ከዋክብትንም ፈጠረ ሲል ያክልበታል። ምልክቶች ሲል በዓሎቹንና ጾሞችን፤ ዘመኖች ሲል አራቱን ወቅቶች ክረትምና በጋ፣ በልግና ፀደይን፤ ዕለታትና ዓመታት ሲልም እንደየትውፊቱ ያሉትን አቆጣጠሮች ማመልከቱ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን እና ጸሐፍቶች ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ከዘመን ቆጠራ አኳያ በየአካባቢው ባሉ ነገሮች፣ ብሔረሰቦች የየራሳቸው መገለጫ የሆኑ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር አላቸው። ከእነዚህም መካከል የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት የመዘገበው የሲዳማ የዘመን አቆጣጠር ይገኝበታል። እኛም ስለበዓሉ ከመነሻው እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጠቅላላ መረጃ ሊሰጡን የሲዳማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ ጋር ቆይታ አድርገናል።
የፊቼ በዓል በአፈ ታሪክ
አቶ ገነነ አበራ ስለ በዓሉ ከአፈታሪኩ ተነስተው እንደተናገሩት የፊቼ በዓል መጠሪያውን ያገኘው ፊቾ ከምትባል የሲዳማ ሴት ነው። ፊቾ ዕድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ሲደርስ በሲዳማ ብሔር ባህልና ሥርዓት መሠረት ተዳረች።
ይህች ሴት በየዓመቱ ለወላጆቿ፣ ወንድሞቿ፣ ለዘመድ አዝማድና ጎረቤት ቡርሰሜ (ከእንሰት ላይ የሚፋቅ ቆጮ በእሳት ላይ ተነኩሮ እና ቅቤ በብዛት ተጨምሮበት የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ) እና እርጎ በመያዝ በየዓመቱ በሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሚውልበት ዕለት በቋሚነት ትጠይቃቸው ነበር። በዓሉ የሚውለው በተመሳሳይ ቃዋዶ (በሲዳማ ብሔር የቀን አቆጣጠር የሳምንቱ የመጀመርያ ቀን) ሲሆን በአፈ ታሪኩ መሠረት ፊቾ ያመጣችውንም ምግብ በዚሁ ዕለት ምሽት ላይ ዘመድ አዝማድ፣ የአካባቢ ጎረቤትና ቤተሰብ ተሰባስበው ይመገቡት ነበር። አባቷና ታዳሚዎች ዘወትር የፊቾን ደግነትና ያመጣችውን ምግብ በማድነቅ ይመርቋታል። ፊቾ ይህንን በተደጋጋሚ ስትፈጽም ቆይታ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ የአካባቢው ነዋሪዎች ፊቾ በመሞቷ ጥልቅ ኀዘን ተሰማቸው። ከዚህም በላይ የእሷ ድግስ ታዳሚ የነበሩ ሰዎች ይህችን ሩህሩህ ደስታ ፈጣሪ ሴት በዘላቂነት ለማስታወስ ቀደም ሲል እርሷ ምግብ ይዛ የምትመጣበትንና ግብዣው የሚካሄድበትን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ቀን በስሟ ፊቼ ብለው ሰየሙት። የፊቼ በዓል ሁሌም በቃዋዶ ቀን የሚውልበት ምክንያት ቀኑ በብሔሩ የሳምንቱ የመጀመሪያውና ታላቅ ቀን ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ነው።
በበዓሉ ሁሉም ሰው የሚያርፍበት ነው። ከብቱም ሳይቀር እናት ከጥጃዋ የምትውልበት ቀን ነው። የተጣላ ካለም ፍቼ ጨምበላላ ማለትም አዲስ ዓመት ሳይገባ ይቅርታ መጠያየቅ ግዴታው ነው። የተፋቱ ባል እና ሚስት ቢኖሩ እንኳን በዋዜማው ቀን ተጣልታ የወጣችበት ቤት የቀድሞ ባሏ ጋር ሄዳ እርቅ ማድረግ ይገባታል። ይሄ የሚደረገውም በዓሉ የእርቅ የሰላም በዓል ነው ተብሎ ስለሚታሰብ መሆኑን ይናገራሉ።
ማኅበራዊ ክንዋኔዎች
አቶ ገነነ በበዓሉ የሚከወኑ ተግባራትን ሲዘረዝሩ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፊቼ ለሁለት ሳምንታት ያህል በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሥርዓትና ሒደት ያለው ነው። ከእነዚህ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች መካከል የመጀመርያው ላኦ ወይም ምልከታ ነው። የፊቼ በዓል ሁሌም በብሔሩ የሳምንቱ የመጀመርያው ቀን ማለትም በቃዋዶ ቢውልም ቀኑ በየዓመቱ በተመሳሳይ ቀን ስለማይውል መቼ እንደሚውል ተለይቶ የሚታወቀው በባህላዊ ቀን ቆጠራ ስሌትና የሥነ ክዋክብት ምልከታ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሥነ ክዋክብት ምልከታውን የሚያከናውኑት አያንቶ የተሰኙ የሥነ ክዋክብት ጠበብቶች ናቸው። አያንቶዎች ቡሳ የተሰኙ ኅብረ ክዋክብት ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማገናዘብ ማለትም የክዋክብቱ ከጨረቃ የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ሁኔታ በትኩረት በመከታተል በተለይ ከክዋክብቱ መካከል አውራ የሆነችው ኮከብ ከጨረቃ መቅደሟን ሲያረጋግጡ ፊቼ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ባለው የቃዋዶ ዕለት እንደሚውል እንደሚወስኑ አቶ ገነነ ይናገራሉ።
ከዚያም የሥነ ክዋክብት ምልከታውን የሚያከናውኑት አያንቶዎች የፊቼ በዓል የሚውልበትን ቀን ለጎሳ መሪዎች ወይም ገሮ ያሳውቃሉ። አያንቶዎች ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ተመስርተው የጎሳ መሪዎች ከጪሜሳዎች ወይም የበቁ አረጋውያን ጋር ሶንጎ ወይም የአዛውንቶች ስብሰባ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ ቀኑ በአዋጅ ለኅብረተሰቡ እንዲገለጽ ከስምምነት ይደርሳሉ። የጎሳ መሪዎችም በየአካባቢያቸው በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች የበግ ቆዳ ረዥም ዘንግ ላይ ሰቅለው በመያዝ ለኅብረተሰቡ የፊቼ በዓል የሚውልበትን ቀን ያውጃሉ (ላላዋ ያደርጋሉ)። ከላላዋ በኋላ ሳፎቴ ቄጣላ (የመጀመርያው ባህላዊ ጭፈራ) ይቀጥላል።
ዋናው ክብረ በዓል ከመከበሩ አንድ ቀን ቀድሞ ማለትም ከዋዜማ ጀምሮ እንኳን አደረሰህ እንኳን አደረሰሽ መባባል ይጀመራል። በዓሉም ቢሆን መከበር የሚጀመረው ከዋዜማው ቀን ጀምሮ ሲሆን እስከ ሁለት ሳምንትም ይቀጥላል።
በበዓሉ ዕለት እንዲሁም በቀጣይ ቀናት የሚከናወኑ ተግባራትን አቶ ገነነ ሲያስረዱ “ሁሉቃ” በመባል የሚታወቀው ደግሞ ማንኛውም ችግር ይሁን ቅራኔ የሚተውበት እርቅ የሚደረግበት በዳይ እና ተበዳይ በፍቅር በመተቃቀፍ ሰላም የሚያወርዱበት ነው። በአጠቃላይ “ሁሉቃ” ያለፈውን በመተው የወደፊት የማየት ተምሳሌት ነው።
ሌላኛው ክዋኔ ደግሞ ይላሉ አቶ ገነነ በታዋቂው የብሔረሰቡ መለያ በሆነው “ሻፌታ” ዋንጫ መሰል የመመገቢያ ቁስ ዙሪያ ልጅ አዋቂ፤ ሠራተኛ አሠሪ፣ ታላቅ ታናሽ የሚባል ሳይኖር ሁሉም በእኩልነት በመሰብሰብ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ቡርሳሜ የሚቋደሱበት ነው። በማህበረሱቡ በጉጉት የሚጠበቀው ሌላኛው ደግሞ “ጉዱማሌ” ወይም አደባባይ በመውጣት የተለያዩ ባህላዊ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት ነው ይህም ስብስብ ሁሉም በአንድነት የሚገኝበት ማንም የማይከለከልበት ሁሉም በእኩል የሚደሰትበት ክዋኔ ነው።
ፍቼ ጨምበላላ በዘመነ ኮሮና
በዚህ ዘመን የፊቼ ጨንበላላ አከባበር ምን እንደ ሚመስል እንዴት እንደሚከበር ለህዘብ ግንኙነቱ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች ሲያስረዱ በዓሉ በባህሪው የህብረት እና የአደባባይ ባህል እንደሆነ ጠቅሰው የተከሰተው ወረርሽኝ ደግሞ በህብረት ሰብሰብ ማለትን የሚከለክል ነው። የበዓል አከባበሩን በህብረት አሻፈረኝ ተብሎ ቢደረግ ደግሞ ዋነኛ የቫይረሱ የመተላለፊያ መንገድ አካላዊ እርቀትን አለመጠበቅ በመሆኑ ህዝባችንን ለዚህ በሽታ እንደ መጋበዝ ይሆናል።
በተለይ ዘንድሮ ዞኑ ክልል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ከተከበረውም በላይ ሁሉም የሲዳማ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ሊያከብረው ተዘጋጅቶ እንደነበር አቶ ገነነ አውስተው በኮሮና ወረርሽኙ ምክንያት ግን አይደለም በድምቀት ሊከበር ቀድሞ እንደነበረው ማክበር አልተቻለም።
እንደ ህዝብ ግንኙነቱ ገለጻ አያን ቶዎች ወይም አባቶች በወሰኑት መሰረት በአገር ላይ አንድ አደጋ ወይም ወረርሽኝ ሲከሰት በዓሉ ከአደባባይ ወደ ቤት ይመለሳል። ልክ እንደ ዘንድሮ በዓል አከባበር ሁሉ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት አገር ላይ በተከሰተ አደጋ ምክንያት በቤት ውስጥ ፊቼ ጨንበላላን ለማክ በር ማህበረሰቡ ተገዶ እንደነበር ያስታ ውሳሉ።
ዘንድሮም በዓሉ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአደባባይ መከበር አልተ ቻለም። ነገር ግን በዓላዊ ስነስርዓቱ አንዱም ሳይጓደል ማህበረሰቡ በቤቱ እያከበረ ይገኛል። ለዚህም የአባቶችን የመንግሥትንና የጤና ባለሙያ ምክር በመስማት ማህበረሰቡ ቤት በመሆን እያከበረ መሆኑንም ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በየወረዳው እየዞሩ ምልከታ እንዳካሄዱም አቶ ገነነ ገልጸዋል። በዓሉ የአንድ ወይም የሁለት ቀን አለመሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣዮቹ የበዓሉ ቀናቶች ጥንቃቄ መደረጉ እንደሚቀጥል አክለዋል።
ማህበረሰቡ ለአባቶች ሃሳብ እና ስልጣን የሚገዛ መሆኑን አቶ ገነነ ይናገራሉ። ትዕዛዛቸውን አልቀበልም፣ አሻፈረኝ አልታዘዝም ካለ ደግሞ አባቶች ቅጣት ይጥሉበታል። ቅጣቱም ከህብረተሰቡ እስከ መገለል የሚያደርስ ነው። ማንኛውም ህብረተሰብ ፣ ቤተሰብም ሆነ ግለሰብ በማህበር፣በመረዳዳት ውስጥ የኖረ ስለሆነ ከማህበረሰብ መገለል አይፈልግም ፤ስለዚህም ይላሉ አቶ ገነነ የአባቶችን ስልጣን በመጠቀም ወረርሽኙ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዳይስፋፋ እንደ ፊቼ ጨንበላላ ያሉ አካላዊ መቀራረብን ከሚፈጥሩ ማህበራዊ ክዋኔዎች እንዲርቁ በማዘዘም ፣ በማስጠንቀቅም፣በማስተማርም በዓሉ እንዲከበር እየተደረገ ነው።
አቶ ገነነ በመጨረሻም እንዳሉት በሚመጡት ዓመታት ብዙ በዓላትን ለማክበር እንዲህ ያሉ ፈታኝ ጊዜያትን በትዕግስትና የአባቶችን ምክር በመስማት ማለፍ ያስፈልጋል። የሲዳማ ህዝብም ለአባቶች ሃሳብ እና ምክር የሚገዛ ጨዋ ማህበረሰብ በመሆኑም በዓሉን ከአደባባይ ወደ ቤት በመውሰድ ነው ያከበረው።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣የባህልና የሳይንስ ድርጅት(ዩኔስኮ) ፊቼ ጨምበላላን በሰው ልጆች የማይዳሰሱ ወካይ ቅርሶች ውስጥ የመዘገበው በ2008 ዓ.ም ኅዳር ወር ላይ መሆኑ ይታወሳል። ዘመን መለወጫው የጤና ፣የሰላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆን እንመኛለን። ‹‹ አይዴ ጨምበላላ ›› ሰላም!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
አብርሃም ተወልደ