«ሰርቼ አረካሁም፡፡ ለአገሬ ገና ብዙ የማበረክተው እንዳለ አምናለሁ፡፡ ወገኔን በድርጅቴ አማካኝነት ለማገዝ አስባለሁ›› ይላሉ፡፡ ሰዎች በስራቸው ብቻ እንዲያውቋቸው ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ቃለ ምልልስ ስናወራቸው እንኳን «ለመገናኛ ብዙሃን ለማውራት የሚበቃ ሥራ ሰርቻለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ሆኖም ለሌሎች አርአያ ይሆናል ካላችሁ ጥያቄያችሁን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ» በማለት ነበር ፈቃደኝነታቸውን የቸሩን፡፡ የአልሳም ኩባንያ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳቢር አርጋው።
ለተቸገሩ ደራሽነታቸው በዝምድና፤ በሰፈርና በሃይማኖት የተገደበ አይደለም፡፡ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ባይ ናቸው፡፡ ብዙዎችን ከችግራቸው እንዲላቀቁ ያግዛሉ፡፡ የአጎታቸው ድጋፍ እርሳቸውን እንዳቆማቸው ሁሉ ሌሎችም በእርሳቸው ድጋፍ ተለውጠው ማየትን ይሻሉ፡፡ ከትንሽ ሱቅ ተነስተው ዛሬ የግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት በእገዛ መሆኑን ስለሚረዱም «ሰዎችን በዕለታዊ ነገር ከማገዝ ይልቅ ሕይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያመጣ ድጋፍ ማድረግ ይገባል›› አቋማቸው ነው፡፡ ለዚህም የስራ እድል መፍጠርን ያስቀድማሉ፡፡
ስኬትና የህይወት ልምድ እንዴት መጣ? እዚህ ከመድረሳቸው በፊት ያለፉት የህይወት ፈተና ምን ይሆን? የሚለውንና መሰል ተሞክሮዎችን እንዲያካፍሉን ለዛሬ «የሕይወት ገጽታ» አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡
ልጅነት
ተወልደው ያደጉት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በሰደን ሶዶ ወረዳ፤ አሌአበባን በምትባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር፤ ልዩ ስሟ አዳዘር በምትባል መንደር ውስጥ ነው። እትብታቸው በተቀበረበት ስፍራ እስከ 16 ዓመታቸው ኖረዋል። በልጅነታቸው አርሰዋል፤ ኮትኩተው አርመዋል፤ ከብት አግደዋል።
አቶ ሳቢር በልጅነታቸው ከሁሉም ጨዋታ የሚመርጡት በባህሉ ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ‹‹የገና ጨዋታ›› ሲሆን፤ በጨለለቅ ሜዳ ላይ ከክርስትና እምነት ተከታይ ጓደኞቻቸው ጋር ያለ ገደብ መጫወታቸውን መቼም አይረሱትም። በእርግጥ ጨለለቅ ቦታው የቤተክርስቲያን ነው። ግን ክርስቲያን እስላም የሚባል ነገር በአካባቢያቸው ዘንድ ተለይቶ የሚታይ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ባለታሪካችን የልጅነት ትዝታ ዘላለም ከአዕምሯቸው እንዳይጠፋ ታትሟል።
ዛሬ ድረስ የትውልድ መንደራቸውን ለማስታወስ ሲሉ ትልቁንና ብዙ ያለፋቸውን ሕንጻ የልጅነት ትዝታቸው ይሆን ዘንድ ‹‹ጨለለቅ›› ብለው ሰይመውታል። በባህሪያቸው ተጫዋች ናቸው። ከገና ጨዋታ በተጨማሪ ‹‹አስተርዮና አዳብና›› ተብለው የሚከበሩ የሴቶች ጨዋታ መመልከት ያስደስታቸው ነበር። ጊዜው እስኪደርስ በናፍቆት ይጠብቁት እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ለእናታቸው የመጀመሪያም የመጨረሻም በመሆናቸው በእንክብካቤ ያደጉት ባለታሪኩ፤ የግብርናውን ሥራ ከአባታቸው ተረክበው ሲሰሩ ውጤታማ ነበሩ። የያዙትን በውጤት ያጠናቅቃሉ። በተለይም በታዳጊነታቸው ጊዜ በእርሳቸው ደረጃ ይሰራሉ ተብለው የማይታሰቡ ስራዎችን ‹‹እሰራዋለሁ›› ካሉ ቤተሰብ አመኔታ ጥሎባቸው ሥራውን ይሰጧቸው እንደነበር ይናገራሉ። በተፈጥሮ ከባድና አይሞከሩም የሚባሉትን ስራዎች ይመርጡ እንደነበር ያስታውሳሉ። የአቅም ውስንነት እንኳን ቢገጥማቸው የጀመሩትን ከግብ ሳያደርሱት አያቋርጡም። ይህ ደግሞ ለዛሬው ጥንካሬያቸው መሰረት እንደሆናቸው አጫውተውናል።
ቤተሰቡን ከሚያግዙበት ሥራ መካከል እርሻ በጣም ይወዱ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ሳቢር፤ ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ደቦ በባህሉ አጠራር ‹‹ግቦ›› እየተባለ በሚጠራው ላይ ቤተሰቡን ወክለው በመሄድ የሚያስመሰግን ሥራ ይሰሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በአካባቢው ዘንድ በሰው ወዳድነታቸውና በታዛዥነታቸው የሚታወቁት አቶ ሳቢር፤ ያላቸውን ማካፈል ያስደስታቸዋል። ይህ ደግሞ ዛሬ ድረስ በእምነት የተገደበ ድጋፍ እንዳያደርጉ አግዟቸዋል። ያደጉበትን ባህል እንዲያስቀጥሉም ረድቷቸዋል። ያደጉበት ማህበረሰብ የሁሉንም እምነት በእኩል ደረጃ የሚታይበት በመሆኑ እርሳቸውም ከዚህ ትምህርት ወስደዋል። እንደውም ከአስተዳደጋቸው አንጻር እንደክርስቲያኑ ሁሉ ገና ልዩ በዓላቸው እንደነበር ይናገራሉ።
በቤት ውስጥ ብቸኛ ልጅ በመሆናቸው ከብዙ ነገር ራሳቸውን ይቆጥቡ እንደነበር የሚያነሱት እንግዳችን፤ ጥል የሚፈጠርባቸው አካባቢዎች ላይ መገኘት አይወዱም። በዚህም ከማንም ጋር ሳይጋጩ ነው የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት።
ያልተማረ ምስጢር የለውም
‹‹ያልተማረ ሰው ምስጢር የለውም። ያለውን ሁሉ ሰው ያውቅበታል። በራሱ ስኬት ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን መንገድም ይዘጋበታል›› የሚሉት እንግዳችን፤ ያለመማር የተለያዩ እቅዶችን እንደሚያስተጓጉል ይናገራሉ። በዚህ የተነሳ ብዙ ነገሮች አጋጥሟቸዋል።
‹‹አለመማሬ ከዚህ የላቀ ደረጃ ላይ እንዳልደርስ አድርጎኛል። ግን ቅድሚያ ሰርቶ መኖር ስላለብኝ ብቻ ትኩረቴን በሥራዬ ላይ አድርጌ ዓመታትን አለፍኩኝ›› በማለትም፤ በግል ለመማርም ብዙ ጥረት እንዳደረጉ ይገልፃሉ። በተለይ የቋንቋ ትምህርት። ይህም ቢሆን አልተመቻቸላቸውም። ከ25 ዓመታት በላይ የተለያዩ አገራትን ሲጎበኙም የሚንቀሳቀሱት በአስተርጓሚ ነው። ከዚህ ለመውጣት ግን መማር ግዴታ መሆኑን እንደሚያምኑ ያነሳሉ። እንደርሳቸው ገለፃ ‹‹ተስፋ መቁረጥ ባህሪዬ ስላልሆነ አሁንም በስተርጅናም ቢሆን ከቁጭቴ ለመዳን እማራለሁ›› ይላሉ።
ትምህርትና ቋንቋን ሲያነሱ አንድ ነገር ግን አጥብቀው ይናገራሉ። የተማረ ማለት እንግሊዚኛ ብቻ ያወቀ ነው ብሎ መወሰድ እንደሌለበት። ይልቁንም የአገሩን ክብር ላለማስነካትና እንደሌሎች አገሮች ስለአገራቸው ለመኖር ከፈለጉ የአገር ቋንቋን በሚገባ አውቀው ሊኖሩበት ይገባል ይላሉ። ለአብነትም ቱርክንና ቻይናን ያነሳሉ። ማንኛውም ቦታ ሲንቀሳቀሱ ቅድሚያ የሚሰጡት ለአገራቸው ቋንቋ ነው። ስለዚህም ይህንን ማድረግ ይገባል።
ችግር ያልበገረው ነጋዴ
አቶ ሳቢር የጀመሩት ሥራ መሰናክል የበዛበት ቢሆን እንኳን ሳያጠናቅቁ መረታትን አይፈልጉም። በዚህም ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ያውቃሉ። ለዚህ ደግሞ አርኣያቸው አጎታቸው ነበሩ። ስለእርሳቸው ሲያነሱ ‹‹የህይወቴ ቤዛ ነው›› የሚለው ከአንደበታቸው አይጠፋም። የማንም እገዛ ሳይታከልበት ዳገቱን መውጣት ከባድ ነው። በዚህም ለዛሬ ስኬቴ አጎቴ ሐጂ ኢስሃቅ በሽር የማይተካ ሚናን ተጫውቷል። ከዚያ በተጨማሪ የሥራ ባልደረቦቼ እጅግ የማመሰግናቸው ናቸው። ትናንትን ተሻግሬ ዛሬን እንዳየው አድርገውኛል ይላሉ።
በ18 ዓመታቸው አዲስ አበባን ረግጠዋል። በአጎታቸው ቤት ለአንድ ዓመት ያህል በመስራት የንግዱን ዓለም ተቀላቅለዋል። በሱቃቸው በመስራት ልምድ ቀስመዋል። ቆየት ካሉ በኋላ የራስ የሆነ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው በማመን ከአጎታቸው ጋር ተመካከሩ። ደጉና ሰዎችን በአይን አይተው ምን መስራት እንደሚችሉ የሚረዱት አጎታቸውም በራሳቸው ቢሰሩ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ስለተረዱ 10 ሺህ ብር ሰጥተዋቸው በሽርክና እንዲሰሩ ሁኔታዎችን አመቻቹላቸው።
በዚህ ሥራ ላይ አምስት ዓመታትን እንደቆዩ ያጫወቱን ባለታሪኩ፤ በሽርክና ሲሰሩ ከነበሩበት ሱቅ ለቀቁ። በዚህም ብዙ ፈተና ደረሰባቸው። ግን ተስፋ መቁረት በእርሳቸው ዘንድ ቦታ አይሰጠውምና ወደ ሌላ ስራ ገቡ። ይኸውም የለስላሳ መጠጥ ችርቻሮ ንግድ ነበር። አቶ ሳቢር በትዕግስት ፈተና ይታለፋል ብለው ያምናሉ። በዚህም ትንሽ ትልቅ ስራ በማለት ሳያማርጡ መስራት ይወዳሉ። ይህ ደግሞ ላቀዱትና የልጅነት ህልማቸው ለሆነው ባለጸጋነት እንዳበቃቸው ይናገራሉ።
1974 ዓ.ም ለእርሳቸው የስኬት መጀመሪያ ጊዜ እንደነበር የሚያወሱት ባለታሪኩ፤ ከአጎታቸው ዳግም 17 ሺህ ብር የሚገመት የሸቀጥ እቃ ተበድረው አነስተኛ ሱቅ ከፈቱ። ይህ ስራ ደግሞ ለብርቱውና ፈጣኑ አቶ ሳቢር ውጤታማ ያደረጋቸው ነበር። እንዳውም በአንድ ዓመት ውስጥ ብድራቸውን መመለስም አስችሏቸዋል። ከዚያ ንግዱና ተፈላጊነታቸው በመጨመሩ በ1987 ዓ.ም ‹‹ሳም ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር›› በሚል ስያሜ መሰረቱ።
ከጅምላ ንግድ ወደ አስመጪና አከፋፋይ የገቡት እንግዳችን፤ ሌሎች እህት ድርጅቶችንም ማቋቋም የቻሉት ከዚህ በኋላ ነው። በዚህም በ1991 ዓ.ም አልሳምና ሊና የተሰኙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅቶችን መሰረቱ። በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተው ምርቶችን እያመጡም በአገር ውስጥ ማከፋፈሉን ተያያዙት።
ቀጣዩ ጉዟቸው ደግሞ ከውጭ አምራች ድርጅቶች የወኪል አከፋፋይነት ሥራን በመቀበል በአገር ውስጥ የማከፋፈል ሥራ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ቢ 29 ሳሙና፣ ኪዊ የጫማ ቀለም፣ ቢክ እስኪርብቶ፣ ኤፒፒ ጎልደን ፕላስ የፎቶ ኮፒ ወረቀት፣ ኤስ 26 የሕጻናት ወተት፣ የኤቬሬዲና ኢነርጃይዘር ባትሪ ድንጋይ፣የቫይኪንግና የሳኒያ የምግብ ዘይቶችና የቤኮ ቴሌቪዥንና የቤት እቃዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
የኢንዶኖዢያ ኩባንያ ከሆነው ‹‹የፒቲ ሲናር አንጆል›› ጋር ሽርክና በመመስረት ቢ-29 እና ሌሎች የዱቄት ሳሙናዎችን በማምረት በአገር ውስጥ ማከፋፈል የቻሉት አቶ ሳቢር፤ በሥራቸው ውጤታማ የሚያደርጋቸውን አልሳም ጨለለቅ ህንጻን ገንብተዋል። ቀጥለው ደግሞ በሊና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኩል ረጲ ሳሙናና ዲተርጀንት አክሲዮን ማህበርን ከመንግስት በመግዛት ማስተዳደር ጀመሩ።
የቆርቆሮ ማምረቻ ፋብሪካን በማቋቋም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉንም የተቀላቀሉት እንግዳችን፤ በሪል ስቴት ዘርፉም የማይተካ ሚናን እየተጫወቱ ይገኛሉ። በቀጣይም ቢሆን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ህዝባቸውንና አገራቸውን ማሳደግ እንደሚፈልጉ አጫውተውናል። በተለይም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሪልእስቴት፣ በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ዘርፎች የበለጠ መስራትና ትውልድ ተሸጋሪ ስም መትከልም እንደሚፈልጉ አጫውተውናል።
አቶ ሳቢር በሥራ ህይወታቸው ከ150 በላይ የሆኑ ቋሚ ሰራተኞችን ቀጥረው የስራ እድል የፈጠሩ፤ በበርካታ የፕሮጀክት ሥራዎቻቸውም ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ሥራ እንዲያገኙ ያስቻሉ ናቸው። ከዚያም በዘለለ ብዙዎች በኩባንያቸው ሰርተው እንዲለወጡ አግዘዋል። ቤተሰብ መስርተውም የራሳቸውን ድርጅት እንዲያቋቁሙ አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ ያበቃቸው በስራው ልክ ሰው ማግኘት እንዳለበት ስለሚያምኑና ቃላቸውን ስለማያጥፉ ነው።
አቶ ሳቢር ውጤታማ መሆንን በግል ደረጃ የሚያስቡ አይደሉም። በህብረት ማደግ የስኬት ምንጭ እንደሆነ ያምናሉ። በዚህም የሰሩትን በእኩል ደረጃ ተካፍለው ለዛሬ ስኬታቸው እንደበቁ ያስረዳሉ። በስራዎች በርካታ መሰናክሎች ገጥሟቸዋል። ግን መፍትሄው አሁንም መስራት ነው ብለው ያምናሉ። ችግር መምጣቱን ማንም ሰው ሊጠላው አይገባም። በሥራ ህይወት መውደቅና መነሳት ያሉ ናቸው። በዚህም ችግሩ የመጣው ከተኛንበት እንድንነቃ ነው፤ ወቅቱ የጠየቀውን ተዛማች ሥራዎችን እንድንሰራ ያስችለናል፤ የመፍትሔ አካልም ያደርገናል በማለት ያስባሉ።
‹‹ላለመውደቅ ሥራን በአግባቡ መከታተል ያስፈልጋል። የመውደቁን መንስኤ አውቆ የሚነሳበትን ዘዴ መቀየስም ይገባል›› የሚሉት እንግዳችን፤ በዚያ ላይ ንጹህነት ከምንም በላይ አብልጦ መውደድ በአላህ ዘንድ ድጋፍን ይቸራልና መጠቀሙ ተገቢ ነው ይላሉ። በታማኝነት ሥራዎችን ማከናወን፤ የንብረት አስተዳዳሪ እስከሆኑ ድረስ ሥራው ስኬታማ መሆን እስኪችል ድረስ መተኛት አይገባም የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው። ተጨንቆ ተስፋ መቁረጥና ተጨንቆ ችግርን መፍታትን መለየትም ያስፈልጋል የሚል ምክርም ስኬትን ለሚሹ ይለግሳሉ።
ክርስትና በእርሳቸው ዓይን
አቶ ሳቢር ባደጉበት አካባቢ የእስላምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች አብሮ መብላት መለያቸው ነው። ልዩነት ያለው ሥጋ ላይ እንደሆነ ቢታሰብ እንኳን ሥጋ የተበላበት እቃ በአመድ ይታጠባል እንጂ ልዩነት ባለው መልኩ አይሰበክም። በዚያ ላይ አንዱ ቤት ሙስሊም ቀጥሎ ያለው ደግሞ ክርስቲያን በመሆኑ አንዱን ከአንዱ ነጥሎ ለመኖር ያስቸግራል ይላሉ። ጉርብትና ቤተሰባዊነት ነው ተብሎ ስለሚታመንም የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ በእኩል ደረጃ እንደሚደረግም ይገልፃሉ።
‹‹የአብዛኞቻችን ቤተሰቦች በጋብቻም ሆነ በስጋ ከክርስትናው እምነት ተከታዮች ጋር ዝምድና አላቸው›› በማለት፤ ይህ ደግሞ በሁለቱ እምነቶች መካከል የአስተምሮ ልዩነት እንጂ ቤተሰባዊነት እንዳልተገደበ የሚያመላክት መሆኑን ያነሳሉ። ለዚህም ማሳያው የእሳቸው አክስት ክርስቲያን መሆኗና በዓላትን በተለይም ፋሲካን እርሷ ቤት ሄደው እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ።
ሌላው ከክርስቲያኖች ጋር ያላቸውን ቅርበት ያነሱበት ደግሞ በቀያቸው የነበራቸውን የአስተዳደግ ሁኔታ ነው። በበዓለወልድ ዓመታዊ ክብረበዓል ላይ ታቦት ሲወጣ ያለልዩነት ታቦታቱን አጅበው ማስገባታቸው ነው። ጥምቀት ላይም እንዲሁ ማድረጋቸው ሁለቱ እምነቶች ከአስተምህሮ በስተቀር በማህበራዊ መስተጋብር አንድ እንደሆኑ ያሳያል ይላሉ። ‹‹እምነት የግለሰብ ነው። የሚያምንበትን በጥልቀት ማወቅና በዚያም መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ›› በማለትም፤ ይህንን ተከተል ብሎ ማስገደድ እንደማይመቻቸው ያነሳሉ። ለዚህ ደግሞ አስተዳደጋቸው መሰረት ሆኗቸዋል። ዛሬም ለልጆቻቸው እያደረጉ ያለውም ይህንኑ ነው። በእምነታቸው ማሳወቅ ያለባቸውን ፈፅመዋል። ግን ከእሳቸው ውጪ አላሏቸውም። የሰዎችንም እምነት የሚያጎድፍ ነገር ሲናገሩ መስማትም እንዲሁ።
ገጠር ማደግ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነትን መማር ነው ይላሉ እንግዳችን። ባህሉን ፣ አኗኗሩን፤ ልባዊ ፍቅርን ያሳውቃል፤ ያኖራልም። በተለያዩ ፖለቲካዎችና በባዕድ ማንነት ቢፈተኑም መውደቅ እንዳይኖርበትም ያደርጋል። ምክንያቱም ስሜቱ ከአዕምሮ ውስጥ የተተከለ በመሆኑ ለማስወጣት ይከብዳልና ነው። ከስኬት በኋላ ማንን ላግዝ በሚለው ውስጥ ሲመጣም ቤተሰብ ፤ የአካባቢ ማህበረሰብና አገር የሚለው የሚመጣውም በዚህ ማንነት ስለሚታደግ መሆኑን ይገልፃሉ።
በተለያዩ አገራት ስዞር አንድ ነገር አይቻለሁ ይሄውም ሁሉም ሰው አገሩን በጣም ይወዳል። ስለ አገሩ መልካም እንጂ መጥፎ መተንፈስን አይፈልግም። ራሱን ሸጦ አገሩን ማሳደግም ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው። በተለይም በብልጠት ስለአገሩ የሚያደርገው ነገር በጣሙን ያስገርማቸዋል። ምንም የሌለው ሆኖ ሳለ አለኝ ብሎ ያተርፋል። እዚህ ግን ከአገሩ ይልቅ ውጪ ናፋቂ መብዛቱ ያስቆጫቸዋል። መለመን ካለመስራት መቅደሙ ያበሳጫቸዋል። ያለውን ሀብት ተጠቅሞ አገር ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።
ኢድ እንዴት ይለፍ
ሁሉም እምነት መረዳዳትን፤ አንዱ ለአንዱ መኖርንና ካለው ላይ ማካፈልን ያስተምራል። መስጠት ደግሞ አብሮ ይዞት የሚመጣው በረከት ብዙ ነው። እናም ኢድም ማለፍ ያለበት በመስጠትና ብዙ በረከት በማግኘት መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ። በተለይም ነብዩ መሀመድ የሚያስተምረን የጀነት መግቢያችን ልግስናችን መሆኑን ነውና በተለይም በዚህ ጊዜ ይህንን ማድረግ ውዴታ ሳይሆን ግዴታችን ነው ይላሉ። ባለሀብትነት ጸጋ የሚሆነው ገንዘብ ስላለ ሳይሆን ከሰዎች እኩል ሲኖርበት ነው። ተመሳስሎና ከእነርሱ ጋር ተግባብቶ፤ እኩል እንዲያድጉ ሲጣርበት ነው። አለኝ ብሎ መኩራራት ሳይሆን ሌሎችም እንዲኖሩት ማድረግ ነው። ኖረንም አልኖረን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ማደግ ራስን ብቻ ሳይሆን አገርንም ያሳድጋልና ጸጋውን በዚህ እየተረጎሙ ኢድን ማሳለፍ ይገባልም በማለት ወገኖቻቸውን በቅን አባታዊ መንፈስ ይመክራሉ።
‹‹ኢትዮጵያዊነት አንዱ መለያው አብሮ መብላትና መጠጣት ነው። ይህንን ደግሞ ወቅቱ አይፈቅድም›› የሚሉት አቶ ሳቢር፤ በተለይ ኢድ ብቻን ማሳለፍ በጣም ስሜቱን ያጠፋዋል በማለት ቁጭታቸውን ይገልፃሉ። እንደውም በዓሉ በዓል አይመስልም ይላሉ። ግን ከመሞት መሰንበት ያስፈልጋልና ዛሬን መቻል ግድ መሆኑን ይገልፃሉ። ‹‹ገጠር ከአሳደገኝ ማህበረሰብ ጋር ማሳለፍ እፈልግ ነበር›› በማለትም፤ ያንንም ይሄን ናፍቀው ዓመቱን ሙሉ ይጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል። ኮሮና በመምጣቱ የተነሳ ብዙ ነገር አሳጥቷቸዋል። ሆኖም ጊዜውን መምሰል ነገን ለማየት ይጠቅመል ብለው ያምናሉ። ሌሎችም ይህንን ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
‹‹የዘንድሮ ረመዳን አንድ ላይ የሚፈጠርበት አልነበረም። ሆኖም ለሚያልፍ ጊዜ ማለፍ የሌለበትን ሕይወት መገበር አይገባምና አድርጌዋለሁ›› የሚሉት እንግዳችን፤ አሁንም ቢሆን ቢመረንም ኢድን በየቤታችን በማሳለፍ አላህ ለዓመቱ በሰላም እስከሚያደርሰን፤ ጨለማውን እስኪገልጥልን እንጠብቅም ይላሉ። ጾም ጥሩ ነገር እንድንሰራ የሚያደርገን ነው። በዚህም ሰው ከቤቱ ስለማይወጣ ረመዳን ከመድረሱ በፊት ለእስልምናውም ሆነ ለክርስቲያኑ እምነት ተከታዮች ከ350ሺህ ብር በላይ በማውጣት በአካባቢያቸው ላሉ ሰዎች ለግሰዋል። ጊዜው መኖርና አለመኖርን የሚወስን ነውና በቀጣይም ይህንን መሰል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። መቼ እንደምንሞት እንኳን አናውቅምና ልብ እንበለው ይላሉ።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ከሦስት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር፤ በኦሮሚያ ክልል አንድ ሚሊዮን ብር ደግሞ ብቻዬን የሰጠሁት በኮሮና ምክንያት ወገኔ እንዳይቸገር በማሰብ ነው የሚሉት ባለታሪኩ፤ ብዙ የሚያስደስቱን ነገሮች ቢቀሩም መተጋገዛችን ግን ደስታን ይሰጣልና አሁንም እናጠንክረው ሲሉ ይመክራሉ። እስከዛሬ ከሚያወጡት ምጽዋት በላይ አሁን ማድረግ በመቻላቸው በረከት እንዳለበት አምናለሁ ብለውናል። ስለዚህም በቀጣይም ይህንኑ ድጋፋቸውን እንደሚያስቀጥሉ አጫውተውናል።
የኮሮና መምጣት ብዙ ነገሮችን አስተካክሏል። የመጀመሪያው ጥሩ ነገር ማድረግ ምን ያህል እንደሚያስደስት አሳይቷል። ለአገር ሰው መኖርና መርዳት በምን ያህል ሁኔታ አሁን ላይ እንዳለም አመላክቷል። በተጨማሪ በፖለቲካው ውስጥ የነበረንን መከፋፈልና ጽንፍ የወጣ አስተሳሰብን አቁሟልም ይላሉ። ስለአንድነትና ኮሮና ብቻ እንድናስብ፤ ማረን እንድንልና ስለ ስራችንም ቆም ብለን እንድናስታውል አድርጎናል። ይህ ደግሞ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ ምን አይነት ገጽታ እንደሚኖራት ጠቁሟል። ምክንያቱም ወገንተኝነት የሌለበት ድጋፍ በእያንዳንዱ ሰው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳርፏልና ነው።
ኢድን ስናከብርም ሆነ ከኢድ በኋላ ኮሮና እንዲ ወገድ ወደ አላህ መጸለይ አለብን። ጊዜአዊ አድርግልን ልንለውም ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ለማለፍ ይቸግረናል። ስለዚህም መንግስት ቢያንስ በየአካባቢው የሚያግዙበትን መንገድ ቢዘረጋ የተሻለ አማራጭ ይኖራል። በዚህ ደግሞ ኢድን አሁን እያደረግን ያለውን አብዝተን እያደረግን ማሳለፍ አለብንም ይላሉ። ‹‹ሰው ሲኖር ሥራ ይኖራል፤ ቢዝነስም ያድጋል። ከሌለ ግን በማንም ማደግ አይቻልምና ‹‹ለነገ ባለጸጋነታችን ዛሬን ለሰው መስራት ይገባናል›› መልዕክታቸው ነው።
አበርክቶ
መጀመሪያ ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩት በሸጎሌ አካባቢ ነው። እናም በዚያ አካባቢ የለመዱት የገጠሩ ባህል ተግባራዊ እንዲሆን ብዙ ጥረዋል። ለአብነት ምንም ገንዘብ በሌላቸው ጊዜ በቡሄ ጊዜ ሆያ… ሆዬ እየጨፈሩ ሲመጡ በኪሳቸው ያላቸውን ይሰጡ ነበር። እናም የሰፈሩ ልጆች ያንን ልምድ አድርገው በዓመት አይቀሩም። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያላቸውን ድጋፍ ከፍ እያደረጉት እንዲሄዱ አስቻላቸው። ትንሽ ገንዘብ ከመስጠት አልፈው እርድ የሚፈጽሙበት ሁኔታዎችን ፈጥረውላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ወደ ጦር ሃይሎች አካባቢ ሲገቡም ቢሆን ያንን ልምዳቸውን አልተውም። እንደውም ከፍ አድርገውት በአካባቢው የሚገኙ ችግረኞችን ማገዝ ላይ አተኩረዋል። ከአንድ በሬ ጀምረው እስከ አምስት በሬ ድረስ በዓላት በመጡ ቁጥር እያረዱ ቅርጫ እንዲወስዱ አድርገዋል። በሃይማኖታችን ጉርብትና ከሥጋ ዘመድ በላይ ነው። በዚህም ነው ይህንን እንዳደርግ የሆንኩት ይላሉ። ስለዚህም የአገር አበርክቷቸውን የጀመሩት ሰውን በመርዳት ነበር። ከዚያ ከአጎታቸው ልጅ ጋር በመሆን በትውልድ ቀያቸው የተለያዩ ለማህበረሰብ ጥቅም የሚውሉ ተግባራትን አከናውነዋል።
በዋናነት የሚያነሱት ግን ሶስት ነገሮችን ሲሆን፤ የመጀመሪያው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት እንደርሳቸው ያልተማረ እንዳይኖር ለማድረግ በተወለዱበት አካባቢ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ትምህርት ቤት ገንብተው ማስረከባቸውን ነው። መንገድም ቢሆን አሰርተዋል። ድልድዮችንም አሁን ድረስ እያሰሩ ይገኛሉ። በተጨማሪ አንድም ቀን ንጹህ የመጠጥ ውሃ አግኝቶ የማያውቀውን ማህበረሰብ በእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ።
ቤተሰብ
‹‹ቤተሰብን ሳስብ ለምን አመለጡኝ የምላቸው ብዙ ነገሮች ይፈጠሩብኛል። በሥራዬ ምክንያት ቤተሰቤ እንዳይርበውና እንዳይጠማው እጥራለሁ እንጂ ከእኔ ጋር በሚያሳልፈው ነገር ይጠቀማል ብዬ ብዙ አላስብም ነበር›› ይላሉ የዛሬ እንግዳችን። ሆኖም ኮሮና መጥቶ ቤት መዋል ስጀምር በቤት ውስጥ ብዙ ያላየኋቸው ደስታን የሚፈጥሩላቸው ነገሮች እንደነበሩ መታዘባቸውንም ይናገራሉ።
መጀመሪያ አካባቢ እንዲህ ሥራ ሳይበዛባቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲያደርሱ ያገኟቸው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ቀረቤታችን በእጅጉ የተራራቀ ነው። በዚህም እንዳጎደሉባቸው ይሰማቸዋል። ትንሹን ልጃቸውን ግን ከ10ኛ ክፍል በኋላ በደንብ ተከታትለውታል። ኮሮና ደግሞ ይበልጥ አስተ ዋውቆናልም ይላሉ።
ቁጣን ከአባቴ ወርሻለሁ የሚሉት እንግዳችን፤ የማይመስለኝን ነገር ሰዎች ሲያደርጉ ካየሁ ዝም አልልም ይላሉ። በዚህም ልጆችም ሆኑ ሰራተኞች ከስህተታቸው እንዲታረሙ ይገስፃሉ። ቁጣዬ ግን ጊዜያዊ መሆኑም ሁሉም ይረዱኛል ይላሉ። እናም አሁን ላይ ለማህበራዊ ህይወት ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመረዳታቸው ብዙ ነገሮች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በዚህም ቤተሰቤ ተደስቷል ብለውናል።
የስምንት ልጆች አባትና የአስራ አንድ ልጆች አያት የሆኑት አቶ ሳቢር፤ ልጆቻቸው ሁሉም በሚባል ደረጃ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለዋል። ከእርሳቸው የሚለዩት ሁሉም ተምረው በቂ የተባለ እውቀትን ከገበዩ በኋላ በንግድ ዓለም ውስጥ መሰማራታቸው ነው።
መልዕክት
ሰው አላማ ሊኖረው ይገባል ይላሉ አቶ ሳቢር። የሚደርስበትን ማወቅ እንዳለበትም እንደዚሁ። ሰውን አላህ ሲፈጥረው ሁሉን ነገር አመቻችቶለት ነው። እርሱ መስራት የሚችለውንም ነገር አሳይቶታል፤ እድሉንም ቸሮታል። ይህንን አምኖ ደግሞ መስራቱ የሰውዬው ሃላፊነት ነው። ምድር ለቆ እንደሚሄድ ማመን አለበት። ለዚህም የገባው ማስተማር ያልገባው ደግሞ ለመረዳት መሞከር ይኖርበታል የሚል መልክት ያስተላልፋሉ።
‹‹ተርፎት የሚሰጥ ማንም የለም። ስለዚህም ካለው ላይ መስጠትን ልምድ ማድረግ ይገባል›› በማለትም ከዚህ የሚልቀው ደግሞ ሥራን መፍጠር መሆኑን ከልምዳቸው በመነሳት ይመክራሉ። ይህ ሃሳባቸው እውቀትና ገንዘብ የተራራቁ በመሆናቸው ማቀራረብ ይገባል ከሚል ይመነጫል። ከራስ በላይ ለሰው መኖርም ይገባል በማለት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው